Friday, December 8, 2017

የኤሌክትሪክ ፍጆታ ስሌት ልዩነት አለውን?

አቶ መንግስቱ አለሙ በአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ ናቸው። በመኖሪያ ግቢያቸው ውስጥ አንድ አነስተኛ የፍራፍሬ መሸጫ ሱቅ እና አምስት መኖሪያ ቤቶች ይገኛሉ። የፍራፍሬ መሸጫ ሱቋን ገንብተው ካከራዩ አስር ወራት የተቆጠረ ቢሆንም ከሶስት ወራት ወዲህ ግን የኤሌክትሪክ ወጪያቸው እያየለ መምጣቱን ይናገራሉ። በተለይም ከአራት እና አምስት ወራት በፊት ይከፍሉ የነበረው 500 ብር ወርሃዊ የኤሌክትሪክ ፍጆታ ክፍያ በተከታታይ ለሶስት ወራት ከእጥፍ ላይ 1500 ብር የሚጠጋ ገንዘብ አስወጥቷቸዋል። ለንግድ ቤቱ እና ለመኖሪያ ቤቶቹ የሚጠቀሙበት አንድ ቆጣሪ ቢሆንም የክፍያ ጭማሪውን ምክንያቱን ለማወቅ ይጥራሉ። በተከራዮች ከፍተኛ ፍጆታ የተከሰተ መሆኑን ለማጣራትም ሌት ተከን ቢታትሩም ምንም አይነት የአጠቃቀም ለውጥ በተከራዮቻቸው ላይ ሊያገኙ አልቻሉም።
ጉዳዩን ይዘው ወደ ኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ሲዘዋወሩ ግን በግቢያቸው ውስጥ አንድ የንግድ ሱቅ በመኖሩ ምክንያት የኤሌክትሪክ ፍጆታ አቆጣጠሩ ከመደበኛ መኖሪያ ቤት ወደ ንግድ ቤት ታሪፍ መቀየሩ ይነገራቸዋል። ከሶስት ወራት በፊት ጀምሮ በቆጣሪ አነባበብ ላይ የተደረገው የአሰራር ለውጥ በእያንዳዱ የንግድ ቤት ያለው ግለሰብ ላይ የሚደረግ አሰራር መሆኑም ይነገራቸዋል። አቆጣጠሩ የተቀየረውም ቆጣሪ አንባቢዎች ባደረሱት መረጃ መሰረት መሆኑን እና ቀደም ብሎ ንግድ ሱቁ እንደተከፈተ ቢታወቅ ደግሞ የታሪፍ ቅያሪው ከአስር ወራት በፊት መቀየር እንደነበረነት ይነገራቸዋል።
ነገር ግን አቶ መንግስቱ ለአንድ ንግድ ቤት ተብሎ ቀሪዎቹ አምስት መኖሪያ ቤቶች በታሪፍ አሰራሩ ወደ ንግድ ቤት የተጠቃለሉበት ሁኔታ ግርታን ፈጥሮባቸዋል። እንደ እርሳቸው ተመሳሳይ ችግር ያለባቸው የተለያዩ የንግድ ቤት የያዙ መኖሪያ ቤት ባለቤቶችን አነጋግረው ንግድ ቤት ላይ የቆጣሪ አነባበቡ የተለየ ስለሚሆን ከመኖሪያ ቤት ተመሳሳይነት ላለው የኤሌክትሪክ ፍጆታ በመጠን ከፍ ያለ ክፍያ መፈጸም የተለመደ መሆኑ ይነገራቸዋል።
ወይዘሮ እስከዳር አሊ ደግሞ አንድ መኖሪያ ቤት ያላቸው ቢሆንም በግቢያቸው ውስጥ ሁለት ንግድ ቤቶች አከራይተዋል። ንግድ ቤቶቹን ያከራዩት ከሁለት አመታት በፊት ቢሆንም የኤሌክትሪክ ፍጆታቸውን የሚከፍሉት በካርድ በሚሰራ የቆጣሪ መሳሪያ በመሆኑ ተከራዮቻቸው ወጪውን ይሸፍናሉ። በመሆኑም በተከራዮች ለሚሞላው የኤሌክትሪክ ክፍያ መጠን መጨመርና መቀነስ አሳስቧቸው አያውቅም። ነገር ግን ተከራዮቻቸው የፍጆታ ክፍያ መጨመር ላይ ቅሬታ አንስተው ስለማያውቁ በእርሳቸው ስም በተመዘገበው ቆጣሪ ምክንያት አድርገው በኤሌክትሪክ አገልግሎት ጽህፈት ቤት ቀርበው ጥያቄ አቅርበው አያውቁም።
የአቶ መንግስቱን ቅሬታ ሲሰሙ ግን 'አዲስ አሰራር ተዘርግቶ ይሆን' የሚል ሃሳብ ገብቷቸዋል። ተከራዮችም ይህን አይነት ያልተጣራ ወሬ ጆሯቸው ከደረሰ በኋላ ወጪውን ለማካካስ በሚል የሽያጭ እቃዎቻቸው ላይ ጭማሪ ስለማድረጋቸው ማጣራት እስካልተደረገ ድረስ ማንም እርግጠኛ መሆን ይከብደዋል።
የአሰራር ሁኔታውን ለማጣራት ወደ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የኮሚዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ገብረእግዚያብሄር ታፈረ ደወልን። እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ በአገሪቷ ውስጥ ምንም አይነት የኤሌክትሪክ ፍጆታ ክፍያ ጭማሪ የለም። የሚቀየር የክፍያ አገልግሎት አሰራር ቢኖር እንኳን በመንግስት ደረጃ ፍቃድ ተደርጎበትና ለህብረተሰቡ በይፋ ተገልጾ እንጂ በድብብቆሽ የሚከናወን ጉዳይ አይኖርም። በኢትዮጵያ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ክፍያ ዝቅተኛ በሚባል ዋጋ እየቀረበ ይገኛል። ደንበኞቹ የሚያነሱት ጉዳይ ከአጠቃቀም ለውጥ ጋር የተያያዘ ስለመሆኑ እና ከቆጣሪ ብልሽት ጋር ተያይዞ የተከሰተ ስለመሆኑ በቅድሚያ ማጣራት ያስፈልጋል። ነገር ግን በመኖሪያ ቤቱ ግቢ ውስጥ የንግድ ቤት ያለው ሰው በጋራ ለሚጠቀምበት ቆጣሪ እዲከፍል የሚጠየቀው የአገልግሎት ክፍያ ለመኖሪያ ቤት ከሚጠየቀው ጋር ሲነጻጸር ልዩነት አለው።
ለቤት አገልግሎት የሚጠቀሙት ላይ እስከ 50 ኪሎ ዋት ኤሌክትሪክ ፍጆታ ድረስ ሲገለገሉ በኪሎ ዋት 0 ነጥብ 273 ሳንቲም እንደሚጠየቅ ይጠቁማሉ። ከ50 ኪሎ ዋት በላይ ሲጨምር ግን የክፍያ ስሌቱ የመጨመር አዝማሚያ /progressive/ ባህሪ እንዳለው ያስረዳሉ። የንግድ ቤቶች ላይ ደግሞ እስከ 50 ኪሎ ዋት ኤሌክትሪክ ፍጆታ ድረስ ሲገለገሉ 0 ነጥብ 6088 ሳንቲም እንዲከፍሉ ይደረጋል። ፍጆታው በንግድ ቤቶች ላይ ከ50 ኪሎ ዋት ሲበልጥ ግን የክፍያ ስሌቱ አጨማመር አነስተኛ /semi progressive/ እየሆነ እንደሚሄድ ይገልፃሉ
እንደ አቶ ገብረእግዚአብሔር ማብራሪያ፤ የመኖሪያ ቤታቸው ውስጥ በሚገኝ የንግድ ቤት ምክንያት የኤሌክትሪክ ክፍያ ስሌቱ ጨምሯለ የሚል ቅሬታ ያላቸው ሰዎች ከዚህ ቀደም ሲሰራበት የቆየ ስሌት በመሆኑ ምንም የተፈጠረ አዲስ አሰራር አለመሆኑን ማወቅ ይገባቸዋል። ለቤት አገልገሎት ሲሰራበት የነበረው የግለሰቦች ቆጣሪ የንግድ ቤት በመክፈታቸው ምክንያት ወደ ንግድ እንዲዞር ይደረጋል። ነገር ግን ለንግድ ቤቱ እና ለመኖሪያ ቤታቸው ባስገጠሙት አንድ ቆጣሪ ምክንያት ሁሉም ክፍያ በንግድ ቤት የቆጣሪ ስሌት ተጠቃሎብኛል የሚል ቅሬታ ያላቸው ሰዎች በህጋዊ መንገድ የተለያየዩ ቆጣሪዎችን በማስገጠም መጠቀም ይኖርባቸዋል። ለንግድ ቤቱ እና ለመኖሪያ ቤታቸው የተለያየ ቆጣሪ ከፋፍለው የሚጠቀሙ ከሆነም የመኖሪያ ቤቶቹን ኤሌክትሪክ ክፍያ በአነስተኛ ታሪፍ ሊጠቀሙ ይችላሉ።

No comments:

Post a Comment

Featured post

ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጠያቂነትን በማረጋገጥ፣ የሕግ በላይነትን በማስፈን፣ መንግሥትና የስራ አስፈጻሚ አካላቱ በመሉ ለሰብአዊ መብቶች መከበር፣ መጠበቅና መሟላት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያሳዩ ልዩ ትኩረትና ክትትል ይሻል

                    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየደረጃው ያሉ የመንግስት አስፈጻሚ አካላትና ኃላፊዎች ላይ የቅርብ ክትትል በማድረግ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር አስተዋጽኦ ሊያደር...