Friday, December 8, 2017

ሁለት ጊዜ የደረቀው ሃይቅ - ሐሮማያ


ሐይቆች በተለያየ ምክንያት ይደርቃሉ። በኦሮሚያ ክልል የሚገኘው የሐሮማያ ሐይቅ ደግሞ ከሌሎች ውሃ አካላት በተለየ ሁናቴ ሁለት ጊዜ ደርቋል። ለዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው? ሐይቁን መልሶ ለማግኘት ምን ያስፈልጋል


በሐሮማያ ዪኒቨርሲቲ የአግሮኖሚ መምህር ዶክተር የሆኑት አብዱለጢፍ አህመድ ፤ ሐሮማያ ሃይቅ ሰባት ኪሎሜትር የሚሸፍን ርዝመት እና 14 ሜትር ጥልቀት የነበረው ሃይቅ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት ሜዳ ሆኖ ውሃው ሊደርቅ የቻለው በአንድ ጊዜ የመጣ ክስተት አለመሆኑን ይናገራሉ። ከጊዜ ወደ ጊዜ ምህረት የለሽ እና ቁጥር የሌለው የውሃ ብዝበዛ ሲካሄድበት ቆይቶ ከአምስት አመታት በፊት ሃይቁ መድረቁን ይገልጻሉ። በአካባቢው ያሉ አርሶ አደሮች በርካታ ውሃ ከሃይቁ እየተጠቀሙ ውሃው ሲቀንስ እና ሃይቁ በደለል ሲሞላ የእርሻ ቦታቸውን ወደ ሃይቁ እያስጠጉ መሄዳቸውንም ያስረዳሉ። በመቀጠልም የሃይቁን ድንበር ጥሰው ደለሉ ላይ ምርት በመጀመራቸው ውሃ እንዳይተኛ አይነተኛ ምክንያት መሆኑን ይጠቁማሉ።
እንደ መምህር አብለጢፍ ገለጻ፤ በቀጣይ ህብረተሰቡን በማስተባበር እና ስለ ውሃ አጠቃቀም ያላቸውን እውቀት በመጨመር የሚገኘውን ውሃ በቁጠባ እንዲጠቀሙ ማድረግ ይገባል። አርሶአደሮቹም ለእርሻ ስራቸው የጠብታ መስኖ እንዲጠቀሙ ጥብቅ እገዛ ማድረግ ያስፈልጋል። ከዚህ በተጨማሪ አምራቾቹ በእያንዳንዳቸው እርሻ ውስጥ የሚቆፍሩትን የጥልቅ የውሃ ጉድጓድ በማስቀረት በአንድ ጉድጓድ ለጋራ እንዲጠቀሙ በማድረግ የከርሰምድር ውሃውን ብክነት መቀነስ ይገባል። ይህም ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጣው ጎርፍ አሰባስቦ ሃይቁ ቦታ ላይ እንዲቆይ ለማድረግና ተከማችቶ የቆየ የመሬት ውስጥ ውሃ ወደ ላይኛው የመሬት አካል እንዲወጣ ለማድረግ ያግዛል። ይህ ስራ በቀጣዮቹ አመታት በቁጥጥር ከተሰራ ሃይቁ መልሶ የማይመጣበት ምክንያት የለም። የሃይቁን መልሶ መሙላት የሚወስደውን ጊዜ ለመገመት ግን የዝናብ ሁኔታው ወሳኝነት አለው። ድርቅ ተደጋግሞ የሚከሰት ከሆነ የሃይቁ መፈጠር ሊራዘም ይችላል።
የሐሮማያ ተፋሰስ ልማት መልሶ የማልማት ቴክኒክ አስተባባሪ አቶ ተፈሪ ታደሰ እንደሚናገሩት፤ ለሐረማያ ሃይቁ መጥፋት በመንስኤ የሆነው ዋነኛ ምክንያቱ የአካባቢው መሬት መራቆት ነው። በተጨማሪም የመሬት አጠቃቀም ለውጥ ለውሃው መመናን አስተዋጽኦ አድርጓል። ለማሽላ፣ ለጥራጥሬ እህሎች እና ለፍራፍሬ የሚውል የነበረ የአካባቢው መሬት ለጫት ምርት እየዋለ ይገኛል። የምርት አይነቱ በአንደ ጊዜ በመቀየሩም ምክንያት የአፈር እጥበቱ በከፈተኛ ሁኔታ ጨምሯል። በአካባቢው የሚሸረሸረው አፈር ደግሞ በቀጥታ ወደ ሃይቁ በመግባት ከተቀመጠ በኋላ የሃይቁን ውሃ ቦታ ይዟል። በመሆኑም በአሁኑ ወቅተ በቦታው ላይ ደለል እንጂ የውሃ አካል አይገኝም። ከዚህ በተጨማሪ በአካባቢው እየተስፋፋ የመጣው የጫት ተክል ለማደግ በርካታ ውሃ የሚያስፈልገው በመሆኑ የሃይቁን ውሃ በስፋት ጥቅም ላይ እንዲውል በር ከፍቷል። ይህም የሃይቁን ውሃ በማመናመን እንዲደርቅ ምክንያት ሆኗል። 
 
ከሶስት አመታት በፊት የደረቀው የሃሮማያ ሐይቅ መልሶ ውሃ እንዲይዝ ለማድረግ ፕሮጀክት ተነድፎ ነበር። በሃይቁ አካባቢ የሚገኘው የላይኛው የተፋሰስ ክፍል ላይ የአፈር እና ውሃ እቀባ ስራ ዎች ሲከናወኑ ቆይተዋል። በዚህ ውስጥ አካባቢውን መልሶ የማልማት እና የውሃ ሃብት አጠቃቀም ላይ ውጤታማ ስራዎች በተወሰነ ደረጃ ማከናወን ተችሏል። የመጀመሪያው ሃይቅ በተፈጥሮ የነበረና እና ጥልቀት ያለው ሲሆን ከደረቀ በኋላ መልሶ ለማልማት በተደረገው ጥረት አነስተኛ ውሃ በክረምት ወቅት እንዲይዝ ተደርጎ ነበር። ነገር ግን ያለው የውሃ አጠቃቀም የተዛባ በመሆኑ ለሁለተኛ ጊዜ እንዲደርቅ አስተዋጽኦ አድርጓል። መልሶ ውሃ እንዲይዝ ለሚደረገው ጠረትም ውሃውን ከአቅሙ በላይ የመጠቀም ልምድ ሊስተካከል ይገባል። በመሆኑም ዋነኛው መፍትሄ የአካባቢውን የጫት ምርት በሌሎች ተችሎች በመቀየር የተመጣጠነ የውሃ አጠቃቀም ስርዓት እንዲስፍን ማድረግ ይገባል። በዚህም ከስድስት መቶ ሄክታር በላይ የሆነውን የሃይቁን ይዞታ መልሶ በማልማት ውሃ እንዲዝ ማድረግ ይቻላል። በአግባቡ ከተሰራም በአምስት እስከ አስር አመታት ባሉት ጊዜ ውስጥ ሃይቁን መልሶ ማግኘት የሚቻልበት እድል ሰፊ ነው። በአካባቢው የሚገኘውን ጥንቄ ሃይቅን እንዲሁም ሃረጂቶ የተባሉ አነስተኛ ሃይቆች ተፈጥረዋል።
«ማንኛውም ተክል ውሃ ይፈልጋል ጫት ስለተተከለ ብቻ ከፍተኛ ውሃ ከሃይቁ ላይ ተወስዷል ብሎ መደምደም አይቻልም» የሚሉት ደግሞ በእርሻና ተፈጥሮ ሃብት ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሃብት ልማት አጠቃቀም ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ታደሰ ናቸው። ጫት ከፍተኛ ውሃ ስለሚወስድ ለሃይቁ መድረቅ አስተዋጽኦ አለው ለማለት ጥናት እደሚያስፈልግ ይገልጻሉ። ነገር ግን የሃይቁ ውሃ የሚከማችበት ጉድጓዳማ ስፍራ በተለያዩ ደለሎች እየተሞላ ሲሄድ ውሃው የመያዝ አቅሙ እንደሚቀንስ ይገልጻሉ። ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ከሐይቁ ዙሪያ የሚገኘው የላይኛው ተፋሰስ አካባቢ ለአፈር መከላት የተጋለጠ በመሆኑ እደተከሰተ ያስረዳሉ። በመሆኑም የተፋሰሱን የእጽዋት ሽፋኑን በማሳደግ እና በመንከባከብ በጎርፍ ወቅት አፈር ተሸርሽሮ ወደ ሃይቁ እዳይገባ መጣር ዋነኛ ተግባር መሆን እንደሚገባው ይጠቁማሉ።
እንደ አቶ ተፈራ ገለጻ፤ የአካባቢው ህብረተሰብ የአፈር መሸርሸርን የሚከላከሉ የግብርና ዘዴዎችን እና ቴክኖሊጂዎችን እዲጠቀም ማበረታታት አስፈላጊ ነው። ይህ ከተከናወነ ሃይቁ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጎድጓዳማው አካባቢ በአፈር እየተሞላ ወደ ዝርግ መሬት የሚቀየርበትን ሂደት ያስቀረዋል። ከዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ወደ ሜዳነት የተቀየረው እና ውሃ ለመያዝ አስቸጋሪ የሆነው ደለላላ ቦታ ለማስተካከል በተለያዩ አማራጮች ከሃይቁ ቦታ ላይ ደለሉ ቦታ ዲለቅ ማድረግ ያስፈልጋል። ይህም በዝናብ እና በጎርፍ የሚገኘውን ውሃ እዲጠራቀም ቦታ ይከፍታል።ሁለት ጊዜ የደረቀ ሐይቅ

No comments:

Post a Comment

Featured post

ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጠያቂነትን በማረጋገጥ፣ የሕግ በላይነትን በማስፈን፣ መንግሥትና የስራ አስፈጻሚ አካላቱ በመሉ ለሰብአዊ መብቶች መከበር፣ መጠበቅና መሟላት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያሳዩ ልዩ ትኩረትና ክትትል ይሻል

                    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየደረጃው ያሉ የመንግስት አስፈጻሚ አካላትና ኃላፊዎች ላይ የቅርብ ክትትል በማድረግ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር አስተዋጽኦ ሊያደር...