Thursday, April 7, 2022

“በህዳሴው ግድብ ኢትዮጵያ ያለፈችባቸው ጫናዎች ለቀጣይ ስራዎች ብርታትን የሚያድሉ ናቸው”

                                                            ረ/ፕሮፌሰር አደም ካሚል  

                                                                         የታሪክ ምሁር

 

ክፍል ሁለት ….

 

አብዛኛዎቹ የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት በተሳሳተ መረጃ አማካኝነት ከግብጽ ጋር መወገናቸውን ቀጥለዋል። 

ከዚህ በኋላም ኢትዮጵያ በድህነቷ ትቀጥል እንጂ ውሃውን አትንካ የሚል አቋማቸውን ይዘው ይቀጥላሉ የሚል እምነት ነው ያለኝ ሲሉም ሃሳባቸውን የኘሚሰነዝሩት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ እነሱ ግን ይህን አቋም ይያዙ እንጂ እውነታውን በግልጽ ሲረዱትና ሃሳባቸው ይቀየር ይሆናል፡፡

እኛ ግን ይህን ሁሉ ጫና ሰባብረን ግንቡን መገንባት ብቻ ሳይሆን ውሃ የማስገባት ሂደቱንም በአግባቡ እያከናወንን ነው ይላሉ። 

ሱዳንም ከግብጽ ጋር ያለባትን የድንበር ችግር ረስታ የምንግዜም ጎረቤቷ ኢትዮጵያ ላይ ጣት መቀሰሯ የግብጽ ጫና ማሳያ ነው።

ሱዳን ግጭት በመቀስቀስ እና ጦሯ የኢትዮጵያን ድንበር እንዲወር ያደረገችበት መንገድ ከግድቡ ጋር የተያያዘ ጫና ለማሳደር ታስቦ የተደረገ ነው ሲሉ የታሪክ ምሁሩ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ያለውን ጫና ያስረዳሉ ሲሉ ያስረዳሉ።


ግብጽ ህዳሴው ግድብ ጉዳይ ኢትዮጵያን ለማንበርከክ ከሱዳን አልፋ ያልተጓዘችበት ሀገር እና የባለስልጣን ቢሮ የለም ማለት እስኪያስችል ብዙ ደክማለች።

በጦር መሳሪያም ጭምር ለማስፈራራት ሞከሩ ግን አልተሳካላቸውም። ከፈረሳይ ሀገር የገዙትን እና ራፋኤል የተሰኘውን ሶስት ሺህ ኪሎሜትር ሊጓዝ የሚችል ፈጣን ጀት በመጠቀም ግድቡን እናፈርሰዋለን እስከማለት ያደረሰ እብሪት ውስጥም ገብታ ነበር ይላሉ።

የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ፊት ቀርበው ኢትዮጵያ ውሃውን ሙሉ ለሙሉ እንደምትገድበው ተናግረውም ያውቃሉ። በወቅቱ ኢትዮጵያ ላይ የነበረው የዓለም አቀፍ ጫና በተለይም ከአሜሪካ ሲደርስ የነበረው ጫና አስቸጋሪ ነበር።

ግብጽ ግድቡን በቦንብ ማጋየት ትችላለች እስኪባል ድረስ ዶናልድ ትራምፕ ያሳዩት ቅሌት ግብጾችን የልብ ልብ ሰጥቷቸው አልፏል። የኋላ ኋላ ግን የአሜሪካም ጫና አልሰራ ማለቱ በገሃድ ታየ። ሁሉ ፉከራ ኢትዮጵያ ግድቡን ከመገንባት የሚያስቆማት እንዳልሆነ ያነሳሉ።    

እንደ ረዳት ፕሮፌሰር አደም ማብራሪያ፤ ወደህዳሴ ግድብ ለመጀመሪያ ጊዜ ውሃ ለማስገባት ዝግጅት በተደረገበት ወቅት ግብጾች የሚይዙት የሚጨብጡትን አጥተው በሃያላን ሀገራት በኩል የበረታ ጫና አሳድረዋል።

አሜሪካም እራሷ ድንበር ተሻጋሪ ወንዝ ላይ ግብድ እንዳልገነባች ሁሉ ለኢትዮጵያ ሲሆን ግን አዲስ አሰራር ለመዘርጋትም ከጅሏት ታይታለች። አምላክ ግን ከኢትዮጵያ ጋር ነበርና በጥቂት ቀን በግድቡ ውሃ የመያዝ የመጀመሪያው ዙር እቅድ በአጭር ቀን ተሳካና ዓለም ጉድ ያሰኘ ስራ ተከናወነ።

ከዚያም በኋላ መለስ ቀለስ እያለች በህዳሴው የሶስትዮሽ ድርድር ላይ የምትሳተፈው ግብጽ በጎን ግን ዲፕሎማሲያዊ ጫናዋን አላቋረጠችም።

በግድቡ ጉዳይ ሴራ ለመጎንጎን የማትሰለቸው ግብጽ ባህር አቋርጣ አሜሪካን አውሮፓን የተለያዩ ሀገራትን ብታዳርስም የፈለገችውን ያክል ውጤት አላገኘችም።

ከዚያ ስትመለስ ግን ዳግም በዓረብ ሊግን በኩል በመምጣት አዲስ እቅድ ይዛ ብቅ ማለቷ የቅርብ ጊዜ ትዝታ መሆኑን ረዳት ፕሮፌሰሩ አንስተዋል።

ግብጽ የግድቡ ግንባታ እንዳይከናወን ዓለም አቀፍ ጫና ማሳደር አለብኝ በሚል በዓረብ ሊግ በኩል ወደተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት ደብዳቤ እስከመላክ ደርሳለች።

በዚህ መካከል ግን ከጀርባቸው የቱኒዚያንም አጋርነት ጠይቀዋል።  በጸጥታው ምክር ቤት ሱዳንና ግብጽ ከቱኒዜያ ባሻገር አራት የአረብ ሀገራትን ከጀርባቸው አስቀምጠው ነው ውይይቱ ላይ የተሳተፉት። 

የተፈራው ሳይደርስ ጫናው ተቀልብሶ የሶስትዮሽ ድርድር ወደአፍሪካ ህብረት እንዲመለስ ተደረገ።

ዓረብ ሊግ በመጀመሪያ በስሩ ያሉበትን ችግሮች ሳይፈታ ወደህዳሴው ግድብ መምጣቱ በእራሱ አሳዛኝ ነበር።

የየመን፣ የሊባኖስ የሶሪያ ችግሮችን በጉያው ይዞ በአባይ ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለመስጠት መነሳቱ በእራሱ ትክክል አልነበረም። አጀንዳው በግብጽና በሱዳን በኩል የተራመደ ቢሆንም ጫናው ግን ለታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት እርባና ያስገኘ አልሆነም።

የጸጥታው ምክር ቤትም የህዳሴው ሶስትዮሽ ድርድር ወደአፍሪካ ህብረት መመለስ እና መታየት አለበት ማለቱም የአፍሪካ ህብረትን አቅም የሚያሳይ ነው።

አፍሪካውያን አሁን ከእንቅልፋቸው እየነቁ ነው። ኢትዮጵያንም በማየት አብዛኛዎቹ ሀገራት በወንዞቻቸው ላይ ግድብ ለመገንባት እየተነሳሱ ይገኛል። ከዚህ አንጻር የአፍሪካውያን ጥንካሬ እና ህብረት እያደገ ይመጣል ተብሎ ይገመታል። ይህ ለኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ የተገኘ ትልቅ ድል ነው።

እንደ ረዳት ፕሮፌሰር አደም ከሆነ፤ በህዳሴው ግድብ ኢትዮጵያ ያለፈችባቸው ጫናዎች ለቀጣይ ስራዎች ብርታትን የሚያድሉን ናቸው።

ችግር ብልሃትን ያስተምራልና እየተማርንበት ለቀጣዩ ስራ የበለጠ ያነሳሳናል። ኢትዮጵያ በየጊዜው በህዳሴው ግድብ ጉዳይ የሚደርስባትን ጋሬጣ እያነሳች ጉዟን መቀጠሏ የኋላ ኋላ ውጤቱ ያማረ እንዲሆን እያደረገ ነው።

በቅርቡ እንኳን ኢትዮጵያ ውስጥ ምርጫ ሊደረግ ሲል የግብጽ ባለስልጣናት ወደሱዳን ተመላልሰው ነበር። ዋነኛ አላማቸው የሱዳኑ መንግስት ወታደራዊ ክንፍ መሪ አልቡርሃን በኢትዮጵያ ላይ ጥቃት እነዲፈጽምና በጋራ ሀገር ለመበጥበጥ ነበር።

ግብጾች ኢትዮጵያ ምርጫ ልታካሂድ ስትዘጋጅተ ከሶስት ቀን በፊት ዓርብ እለት ጀምሮ በረራቸውን አቋርጠዋል። ይህ ሁሉ በምርጫው ሰበብ ብጥብጥ ይፈጠራል ከሚል የመነጨ ነው።

ኢትዮጵጵያ በምርጫው ጀምሮ ለሳምንት በረብሻና ግጭት ትቀጣጠላለች ብለው ቢያስቡም እንደሰሩት ስላልሆነላቸው ጉዳዩ ከሸፈ። ምን ጊዜም ኢትዮጵያ እንድትዳከም የምትፈልገው ግብጽ የህዳሴው ግድብ ስጋት ሆኖባታል የሚባለውም ለዚህ ነው።

ይሁንና ችግሮቹ ሁለ እንደታሰበው ሊፈጠሩ አልቻሉም፤ የግድቡም ግንባታ በህዝብ ተሳትፎ እንደቀጠለ መሆኑ የኢትዮጵያን ጥንካሬ ያሳያል ሲሉ ይገልጹታል። 

በህዳሴው ግድብ ኢትዮጵያ ላይ የደረሰው ጫና ይህ ብቻም አይደለም። ግብጽ ከሳኡዲው አልጋወራሽ ጋር ከተመካከሩ በኋላ በቀጥታ ህጋዊውንም ሆነ ህጋዊ ፈቃድ የሌላቸውን ዜጎች ማሰርና ማዋከብ ተያይዘዋል።

ሳኡዲ አራቢያም የግብጽን አጀንዳ ለማስፈጸም ስትል ኢትዮጵያውያን ላይ የምታሳድረው ግፍ ሀገራችን ላይ ጫና ለማሳደር መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል ሲሉ የታሪክ ምሁሩ ደባውን ይገልጹታል።

አሁን ላይ ከሳኡዲ አራቢያ በባዶ እግራቸው ወደሀገራቸው እንዲመለሱ የሚደረጉት ኢትዮጵያውያን እና በአረቡ ዓለም በረሃው ላይ የሚወድቁ ዜጎች ለዚህ ችግር የተጋለጡት ኢትዮጵያው ውስጥ ድህነት በመኖሩ ነው።

ከድህነት እንውጣ ብለን ፕሮጀክት ስንጀምር ደግሞ በድህነታችህ መሙቱ እንጂ ውሃውን አትጠቀሙም የሚል ሃሳብ ካመጡ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው።

ገንዘቡን አዋጥቶ ቁርስና ምሳውን ትቶ ቦንድ በመግዛት ግድቡን እያሰራ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ ሁሉ በግንባታው ውጤት ላይ የእራሱ አሻራ አለው።

ይሄ ግድብ ደግሞ የዐብይ አህመድ ወይም የደመቀ መኮንን ሳይሆን የኢትዮጵያ ህዝብ ግድብ ነውና ሁሉም ውጤቱን ይጠባበቀዋል ይላሉ።

ከብዙ ጫናዎች በኳላ አሁን ላይ የግድቡ ውሃ የመያዝ አቅም ከፍ ብሏል። ከዚህ በኋላ ምንም ቢያደርጉ መዘዙ ለእነሱም እንደሚተርፍ ሱዳንና ግብጽም ያውቁታል። ምክንያቱም ግድቡ ከባህር ወለል በላይ 500 ሜትር አልፏል ሱዳን በበኩሏ የምትገኘው ከባህር ወለል 320 ሜትር ላይ ነው።

ግብጽ በበኩላ ከባህር ወለል 220 ሜትር ከፍታ ላይ ነው ይምትገኘው። ስለዚህ የህዳሴው ግድብ አንድ አደጋ ቢደርስበት ሀገራቱን በጎርፍ ሊያጥለቀልቅ እንደሚችል ባለሙያዎቹ ይረዳሉ።

ግንባታውም በጥሩ ፍጥነት ከቀጠለ ውሃውንም አምላክ ይሞላዋልና ከዚህ በኋላ ግብጽና ሱዳን የሚደሳድሩት ሃይል እንደማይኖራቸው ረዳት ፕሮፌሰር አደም ያስረዳሉ።

ግብጾች ኢትዮጵያውያን እርስ በእርስ ከተጋጩ 920 ሰራዊት አለንና እናዘምታለን የሚል ፉከራ ሲያሰሙ ቆይተዋል። አሁን የግድቡ ግንባታ በእራሱ ችግር ቢፈጥሩበት የሚያጠፋቸው በመሆኑ ሊገቡብን የሚችሉበት ቀዳዳ በግጭቶቻችን መካከል ቤንዚን ማቀጣጠል ብቻ መሆኑን ማወቅ ያስፈልጋል።

ግብጾች ኢትዮጵያን ለማፈራረስ የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለ ማወቅ ደግሞ አለብን። በመሆኑም ከውጭ ሃይሎች ጋር ተባብሮ ሀገርን መክዳት የኋላ ኋላ ጉዳቱ ለእሳት ጫሪውም የሚተርፍ መዘዝ አለውና  አንድነታችንን ስልማጠናከር ልናስብ ይገባል የሚለው ደግሞ የታሪክ ምሁሩ ምክር ነው።

ከሀገር ውስጥ አንድነትን የማጠናከር ስራ ባለፈ በአፍሪካ እና አጎራባች ሀገራት እንዲሁም በባህር ማዶ በዳሴው ግድብ ዙሪያ ጠንካራ ዲፕሎማሲ ያስፈልጋል። የአፍሪካውያንን በጋራ የመጠቀም ባህል የሚያጎለብቱ እና ሀገራዊ አንድነትን የሚያጎለብቱ ስራዎች ላይ ማተኮር ተገቢ ነው።

No comments:

Post a Comment

Featured post

ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጠያቂነትን በማረጋገጥ፣ የሕግ በላይነትን በማስፈን፣ መንግሥትና የስራ አስፈጻሚ አካላቱ በመሉ ለሰብአዊ መብቶች መከበር፣ መጠበቅና መሟላት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያሳዩ ልዩ ትኩረትና ክትትል ይሻል

                    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየደረጃው ያሉ የመንግስት አስፈጻሚ አካላትና ኃላፊዎች ላይ የቅርብ ክትትል በማድረግ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር አስተዋጽኦ ሊያደር...