Thursday, April 28, 2022

ጥብቅ ዕርምጃ የሚሻው - ከሐይማኖት ተቋምት እስከ መንግሥት ጓዳ የዘለቀውን ሙስና

 

ሙስና ለዕድገታቸው ጠንቅ ሆኖባቸዋል ከሚባሉ አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷና ዋነኛዋ አገር ናት። በየወረዳው፣ በፍርድቤቶችና፣ በትላልቅ ባለስልጣናት ጭምር ሙስና መቀበል ልክ ዕንደመብት የሚታይበት ጊዜ ላይ ነን። ደርሰናል።

Corruption Free India — A Far Cry | by Editor @ The Dialogue | The Dialogue  | Medium    

 

 

 

 

 

 

 

 

ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተሰኘው ዓለም አቀፍ ተቋም በሙስና መስፋፋት ረገድ ከዜጎችና ከባለሙያዎች በሚሰበሰብ መረጃና ግምታዊ አሰራር  በየዓመቱ በሚያወጣው ሪፖርት እ.አ.አ. በ2020 ለኢትዮጵያ ከ100 ነጥብ 39 ሰጥቷታል። ይህም  ኢትዮጵያን ሙስና ዕጅግ ተስፋፍቶባቸዋል ከሚባሉ አገራት ተርታ ያሰልፋታል። 

የማኀበራዊና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ጥናትና የማማከር አገልግሎት የሚሰጠው ፍሮንቲየርአይ ተቋም የኢትዮጵያ ኃላፊ የሆኑት ዶክተር በላይነህ ተቋማቸው እ.አ.አ. በ2021 ሙስና ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ጉዳት በተመለከተ ጥናት መስራቱን ገልጸው፤ በጥናቱ ውጤት መሰረት ሙስና ኢትዮጵያ ውስጥ የገነገነ አገራዊ ችግር ሆኖ መቀጠሉን ይገልጻሉ።

ሌብነትን መከላከል የሚገባቸው ተቋማት ጭምር የለየለት ዘረፋ ውስጥ መግባታቸውን መግባታቸውን በመጠቆም፤ በተለይም የሐይማኖት ተቋማት፣ የጉምሩክና ቀረጥ ተቀባይ ተቋማት፣ የመሬት አስተዳደር እንዲሁም ከፌዴራል አንስቶ እስከ ወረዳ ደረጃ ያሉ ፍርድ ቤቶች ላይ ሙስና በመስፋፋቱ ዜጎች ምሬት ውስጥ መሆናቸውን ይገልጻሉ።

ሙስና በድብቅ የሚከናወን በመሆኑ የሚጠፋውን ገንዘብ በትክክል ማወቅ ባይቻልም፤ የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ በየዓመቱ በሙስና ከተገኘው ገንዘብ 30 ቢሊዮኑ ወደውጪ እንደሚወጣ  ይፋ አድርጓል። ይሁንና ቁጥሩ ከዚህም በላይ ሊወጣ የሚችልበትም ሁኔታ አለ ይላሉ።

ምክንያቱም ሙስና በየትኛውም ስፍራ እየተለመደ የመጣ በመሆኑ እንደአገር ከዚህም በላይ መጠን ያለው ገንዘብ ሊወጣ ይችላልና፤ ሕዝብ እየተበዘበዘ ስለመሆኑ ማወቅ አያዳግትም ሲሉ ሃሳባቸውን አጠናክረዋል።  

በጥቁር ገበያ የዶላር ምንዛሬ ጋር የተዛመዱ፣ ከአስመጪና ላኪነት ጋር በተያያዘ እንዲሁም በየመንግሥት ተቋማት ጉዳይ ለማስፈጸም በሚል የሚፈጸሙ የሙስና ወንጀሎች እንዳሉ መንግሥትም ሕዝብም ያውቃል። ዋናው ጉዳይ ግን ከወሬ በዘለለ ቁርጠኛ ዕርምጃ መውሰድ ነው። አስፈላጊውን የሕግ ቅጣት እየሰጡ አስተማሪ ውሳኔ መስጠት ይጠበቃል። ለዚህም የመንግሥት ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው ይላሉ።

በሙስና ሰዎችን ተጠያቁ ማድረግ ሲጀመርና አንዱን ሲነካ በጥቅም የተሳሰሩ ሰዎች ስላሉ ሌላውንም ሰው ሊነካ ይችላል ያሉት ዶክተር በላይነህ፤ ለዚህም አሰራሮችን ግልጽ ማድረግና ሌብነቱም ሲገኝ ሁሉንም ተጠያቂ በማድረግ ዘላቂ መፍትሄን ማምጣት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ በሙስና የሚጠየቁ ሰዎች ከመንግሥት የፖለቲካ አካሄድ አፈንግጠዋል የሚባሉ ሰዎች ናቸው፤ ይሁንና ዘርፈውም ከመንግሥት ጋር የሆኑ ሰዎች በብዛት ተጠያቂ አይደረጉም የሚሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብቶች ጥናት ማዕከል መምህሩ ዶክተር አብዱለጢፍ ከድር ናቸው።

እንደ ዶክተር አብዱለጢፍ ገለጻ፤ ሙስና የሚገባውን ደረጃ ትኩረት ስላልተሰጠው፤ ዘርፈ ብዙ ውጥንቅጦችን በአገር ላይ እያስከተለ ነው። ከዚህ ቀደምም ያለው ሆነ የቀጠለው ፖለቲካዊ ስርዓት በሙስናና ጥቅም ትስስር ላይ የተመሰረተ ነው። አገርን አገለግላለሁ በሚል ዘለቅ ያለ ዓላማ ይዞ ሳይሆን እበላለሁ በሚል መንፈስ ነው ሰዎች ሹመቶችን የሚቀበሉት።

ስለሆነም ይህን ስር የሰደደ አስተሳሰብ እንዲወገድ ጥረት ማድረግ፤ እንዲሁም ችግር ሲገኝ አስተማሪ ዕርምጃ መውሰድ ከሕግ አስፈጻሚዎች አካላት ይጠበቃል። ይህ ሲባል ግን ሕግ አስፈጻሚውም በዕራሱ ሙሰኛ በመሆኑ ዕርምጃው መጀመር ያለበት ዕዚያው አስፈጻሚዎቹ ጋር ነው ብለዋል።

ምክንያቱም ሙስና የኢኮኖሚ ችግር ብቻ ሳይሆን የማኀበረስብም ሆነ የአገር አብሮ የመቀጠል ትልቁ ፈተና ነው። ስለዚህ ሙስናን ወይም ሌብነትን መቀነስ ካስፈለገ ከመንግሥት ጋር የተጠጉትንም ጭምር ተጠያቂ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ ይሞግታሉ።

ስለዚህም ካንጀት ካለቀሱ ዕንባ አይገድም እንደሚባለው ሁሉም የሽግ አስፈጻሚዎች በሃቀኝነት ከሰሩ ውስብስብ የሆነውን የሙስና ወንጀል እንዲቀንስ ማድረግ ይችላሉ።   መረጃ ላይ መሰረት ያደረገ አሰራርን በመከተልና የፖለቲካ ወገንተኝነትን ባራቀ መንፈስ በመቆጣጠር ዋነኛ ሙሰኞችን ማደን እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ።

ዶክተር አብዱለጢፍ እንዳስታወቁት፤ አስተማሪ የሕግ እርምጃ በመውሰድ ከዚህ ችግር አገር እንድትድን  ማድረግ ያስፈልጋል። በዚህ ሂደት ህብረተሰቡም ሆነ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ሙስናን በማጋለጥ ረገድ ዋነኛ የመረጃ ምንጭ መሆን አለባቸው።

No comments:

Post a Comment

Featured post

ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጠያቂነትን በማረጋገጥ፣ የሕግ በላይነትን በማስፈን፣ መንግሥትና የስራ አስፈጻሚ አካላቱ በመሉ ለሰብአዊ መብቶች መከበር፣ መጠበቅና መሟላት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያሳዩ ልዩ ትኩረትና ክትትል ይሻል

                    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየደረጃው ያሉ የመንግስት አስፈጻሚ አካላትና ኃላፊዎች ላይ የቅርብ ክትትል በማድረግ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር አስተዋጽኦ ሊያደር...