በኤጀንሲዎች የሠራተኛ ቅጥር ዘመናዊ ጉልበት ብዝበዛ ወይስ?
ቅሬታ
«ለሥራዬ ተገቢውን ክፍያ አላገኝም። ሦስት ቤተሰብ የማስተዳድር ብሆንም ደመወዜ ከቤት ኪራይ ክፍያ እና ከቀለብ አታልፍም» በማለት ደመወዙን እዚህ ግባ የሚባል እንዳይደለ የነገረኝ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጥበቃ ሠራተኛነት ተቀጥሮ የሚያገለግለው (ስሙን በሌላ የተካነው) ወጣት
ሰለሞን አካሉ ነው። ላየን የጥበቃ አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በተሰኘው ሥራና ሠራተኛ አገናኝ
ኤጀንሲ አማካኝነት በዩኒቨርሲቲው መቀጠሩን ነው የሚያስረዳው። ከስድስት ወር በፊት ሥራ በማግኘቱ ደስ ብሎት
ቢቀጠርም በደመወዝ አከፋፈል ስርዓቱ ግን ደስተኛ አለመሆኑን ይናገራል። «ዘመናዊ ጉልበት ብዝበዛ ነው» ሲልም ይገልጻል። ምን ችግር ገጠመህ የሚል ጥያቄ አቀረብኩለት? ፈራ ተባ እያለ ዙሪያ ገባውን ከገላመጠ በኋላ በለሆሳስ «ሥራውን ያስቀጠረኝ ኤጀንሲ ያለአግባብ የእኔን ጨምሮ የሌሎች ጓደኞቼን የጥበቃ ሠራተኞች ደመወዝ እኩል እየተካፈለ ነው። እንዳውም እኛ ታክስና ጡረታ ይቆረጥብናል» አለኝ።
አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለኤጀንሲው በአንድ ሠራተኛ 2400 ብር የሚከፍል ቢሆንም ኤጀንሲው ግማሹን በመጉመድ እንደሚያስቀር ነው የገለጸው። በወር የሚከፈለው ገንዘብ ከተቀጠረበት ዩኒቨርሲቲ የደመወዝ ስኬል እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን እና ጡረታ እና ታክስ ተቆርጦ 1054 ብር ከ50 ሳንቲም እንደሚደርሰው ነው የሚጠቁመው። ይህም የተቀጣሪዎችን ሞራል የሚነካ፣ መብቱንም የሚጋፋ እና ያለአግባብ ለመበልጸግ የሚደረግ ሩጫ መሆኑን ይናገራል።
በመሆኑም ኤጀንሲው በየወሩ ከሠራተኞቹ ላይ ያለአግባብ የሚቀንሰውን ገንዘብ መጠን ዝቅ ሊያደርገው ይገባል። በተጨማሪም የህመም እና የተለያዩ ፍቃዶች በሚያስፈልጉበት ጊዜ ፈቃድ የሚጠየቀው ኤጀንሲው በመሆኑ ተገቢውን መፍትሔ እንደማይሰጥ ይናገራሉ። እንደ ዜጋም መብትና ጥቅማችን የሚከበርበት ህግና መመሪያ ሊኖር ይገባል የሚል እምነት አለው። «እኛ የኤጀንሲ ተቀጣሪዎች ብንሆንም የአገሪቱ ዜጎች በመሆናችን በአገሪቱ የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ መሰረት ተጠቃሚ መሆን ይገባናል። የሠራተኛ ማህበርም ኖሮን በመብትና ጥቅሞቻችን እንዲሁም ግዴታችን ዙሪያ መነጋገርና ማስከበርም ይኖርብናል። ሆኖም ግን እኛ የዚህ መብት ተቋዳሽ አይደለንም» ይላል።
በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ የመንግሥት እና የግል ተቋማት የጥበቃ እና ፅዳት ሠራተኞችን በኤጀንሲ አማካኝነት ቀጥረው የሚያሠሩ በመሆኑ ችግሩ የበርካቶችን በር እያንኳኳ እንደሚገኝ ይናገራል። ይሄ ዘመናዊ ጉልበት ብዝበዛ በመሆኑ ለዚህም ችግር የሚመለከታቸው ተቋማት አስፈላጊውን የመፍትሔ ሃሳብ ቢያዘጋጁ መልካም እንደሆነ ነው የሚጠቁመው።
ወይዘሮ ሰናይት አሸናፊ (ስማቸው በሌላ የተተካ) አጋር የጥበቃ አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በተሰኘ ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ተቋም አማካኝነት በግል ባንክ በጥበቃ ሥራ ላይ ተሰማርተዋል። በአዲስ አበባ መቀመጫቸውን ያደረጉ የአገር ውስጥ ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር ውል በመዋዋል አብዛኛውን የአገሪቱን ጥበቃ ሠራተኞችን በኮንትራት እንደሚያሠሩ ነው የምታስረዳው። በዚህም አንድ ሠራተኛ ስለ ደመወዝ እና የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች በመጀመሪያ የሚነጋገረው ከኤጀንሲው ጋር እንጂ ከቀጣሪው አካል ጋር አለመሆኑን ታስረዳለች። ይህም ኤጀንሲው በሠራተኞች መብት ላይ ሙሉ ኃላፊነት እንዲሰጠው እና የፈለገውን ያህል የደመወዝ መጠን እንዲተምን ዕድል እንደሰጠው ነው የምትገልጸው።
እንደ ወይዘሮ ሰናይት አገላለጽ ከሆነ፤ በተለያዩ ጊዜያት በባንኩ ውስጥ የሚቀጠሩ ጥበቃዎች በኤጀንሲው የአንድ ሺ ብር ደመወዝ ውል ይቀርብላቸዋል። ባንኩ የሚከፍለው ደመወዝ መጠን ከፍተኛ መሆኑን ሲረዱ ለሥራ ያላቸው ተነሳሽነት እጅግ ይቀንሳል። በመሆኑም ኤጀንሲዎች ከሠራተኛው ላይ የሚቀንሱት የኮሚሽን ክፍያ በህግ ላይ ተመስርቶ የተተመነ እና የሠራተኞችን ተጠቃሚነት የማይጎዳ መሆን ነበረበት። አብዛኛውን ጉልበት የሚያወጣው እና ሥራውን የሚያከናውነው ተቀጣሪው ሆኖ ሳለ ኤጀንሲዎች ተጠቃሚ የሆኑበት አሠራር መስተካከል ይገባዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ኤጀንሲዎች በተለያዩ አነስተኛ ምክንያቶች በየወቅቱ ከሠራተኞች ደመወዝ ላይ በቅጣት መልክ ገንዘብ ይቆርጣሉ። ለአብነት በመኪና የሚዞሩ የኤጀንሲ ተቆጣጣሪዎች በምሽት ጥበቃ ሥራ ላይ ለተሰማራ ሰው የመኪና ጥሩንባ (ክላክስ) በማሰማት ሊጣሩ ይሞክራሉ። በዚህ ወቅት ሠራተኛው ካልወጣ እንደተኛ ተቆጥሮ ደመወዝ ይቀነስበታል። ይህንን አሠራር በተለይ መኪና በሚበዛባቸው እና የተለያዩ ድምፆች በሚሰሙባቸው አካባቢዎች ላይ ተግባራዊ ለማድረግ ያስቸግራል። ይህም የሠራተኞችን መብት የሚጋፋ እና ሊስተካከል የሚገባው ነው።
የኤጀንሲዎቹ ምላሽ
የአጋር
የጥበቃ አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የሰው ሀብት ልማት አስተዳደር ኃላፊ የሆኑት ኮሎኔል ከበደ
በጅሮ ከተቀጣሪ ዎቻቸው የሚነሳውን ቅሬታ አይቀበሉም። ማህበሩ ሠራተኞችን በመላ አገሪቱ ከሚገኙ የዲፕሎማቲክ
አካላት፤ ባንኮች እና የግል ተቋማት ጋር በሚደረግ የውል ስምምነት አማካኝነት ከአምስት ሺ በላይ ሠራተኞችን
እንደሚያቀርብ ይገልጻሉ። በዚህም ከተቋማቱ ለእያንዳንዱ ሠራተኛ ከሚከፈል ገንዘብ ለሠራተኛው 80 በመቶውን
እንደሚከፍል ነው የሚናገሩት። ተቀናሽ የሚደረገውን ገንዘብ ማህበሩ የተለያዩ ወጪዎችን ሸፍኖ ለትርፍ እንደሚያውለው
ያስረዳሉ። ይህም ከሠራተኞች ጋር በሚደረግ የውል ስምምነት መሆኑን ነው የሚናገሩት። በመሆኑም ሠራተኞች የሚያነሱት
የደመወዝ አነሰኝ ቅሬታ ተገቢ ያልሆነና አሠራሩን ያልተከተለ ነው። ወደፊትም የደመወዝ ትመናውን ለማስተካከል እቅድ
እንደሌለም ይናገራሉ። ላየን የጥበቃ አገልግሎት ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አቤል ወርቁ በበኩላቸው እንደሚናገሩት በአገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች እንደየሁኔታው የተለያየ የደመወዝ አከፋፈል ይከተላሉ። ላየን ሠራተኞች ከሚያቀርብላቸው ድርጅቶች ውል ፈፅሞ ከሚቀበለው ገንዘብ ለሠራተኞች ከ60 እስከ 65 በመቶ ይከፍላል። (እርሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ የኤጀንሲው ተቀጣሪዎች 50 በመቶ እንደሚከፈላቸው ነው የተናገሩት) በዚህም በድርጅታቸው አማካኝነት ከአራት ሺ በላይ ሠራተኞች በሥራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ። ከሠራተኞች ደመወዝ ላይ የሚቀነሰው ገንዘብ ለኢንሹራንስ ክፍያ፣ ለቢሮ አስተዳደር ፣ ለደንብልብስ ወጪ እንዲሁም ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል ሲሆን፤ ይህን ታሳቢ ሲደረግ ለሠራተኞች ጥሩ የሚባል ክፍያ ይሰጣል። በኤጀንሲው አማካኝነት ለሚቀጠሩ ሠራተኞች ትንሹ የደመወዝ ክፍያ 900 ብር ሲሆን እንደየደረጃው እያደገ ይሄዳል።
ሌሎች ኤጀንሲዎች በአንፃራዊነት የተሻለ ክፍያ ማለትም 80 በመቶ ለሠራተኛ የሚከፍሉ መኖራቸውን ላነሳንላቸው ጥያቄ እንደገለጹት ይህን ያህል ክፍያ የሚከፍል ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሠራተኛ የሚያስቀጥር ኤጀንሲዎች ይኖራሉ ተብሎ እንደማይገመት ይናገራሉ። «ቢኖርም እንኳን ያሉባቸውን ወጪዎች ሸፍነው ትርፋማ ለመሆን ስለሚከብዳቸው የተሟላ ቢሮ እና ለቀጣሪዎች ንብረት ዋስትና ሽፋን የሌላቸው እንዲሁም ለተቆጣጣሪዎች ክፍያ የማያወጡ ሊሆኑ ይችላሉ» ብለዋል።
እንደ አቶ አቤል አገላለጽ፤ ለሠራተኞች የሥራ ላይ ደህንነት እና ጤንነት የሚሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ አስፈላጊው ስልጠና ይሰጣል። በተጨማሪም ተቆጣጣሪዎች የሠራተኛውን ንቃት ለመፈተሽ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ጥበቃዎች ለሥራ የሚመደቡበት አካባቢ በአብዛኛው ጸጥታ የሰፈነበት በመሆኑ ለሁለቱም አካላት የድምፅ እክል የሚፈጥር ችግር አያጋጥምም። በመሆኑን የንቃት ችግር የታየበት ጥበቃ ፣ የደንብ ልብስ አለባበስ ሥነ-ስርዓት ያልተከተለ ሠራተኛ ለቅጣት ይዳረጋል። ይህም የኤጀንሲው ደንበኛ የሆኑ ተቋማትን ደህንነት ለመጠበቅ እና የተገልጋዩን ፍላጎት ለማርካት ነው። በመሆኑም ሠራተኞች ያለአግባብ ቁጥጥር እንደሚደረግባቸው እና ደመወዝ እንደሚቆ ረጠባቸው የሚያነሱት ሃሳብ ትክክል አይደለም።
የባለድርሻ አካላት ምላሽ
የቀጣሪዎችንና የተቀጣሪዎችን ቅሬታና ምላሽ ይዘን ያመራነው ወደ ኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ነው። የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በርካታ ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች በአገር ውስጥ እየተንቀሳቀሱ መገኘታቸው በመልካም ጎኑ የሚታይ ቢሆንም አገናኝ ድርጅቶቹ ከእያንዳንዱ ሠራተኛ ደመወዝ አከፋፈል ላይ ያላቸው አሠራር ህጋዊ አካሄድን የተከተለ አለመሆኑን ያምናሉ። አንድን ሠራተኛ ለተለያዩ ተቋማት ካቀረቡ በኋላ የሚቀበሉት ገንዘብ ከፍተኛ ከመሆኑ በተጨማሪ በየወሩ ከሠራተኛው ደመወዝ ላይ የሚቆርጡበት አግባብ ተገቢ አለመሆኑን ይጠቅሳሉ። «ይህም በሰው ጉልበት መነገድ ነው» ብለዋል። በየወሩ እየቆረጡ የሚያስቀሩት ገንዘብ ለሠራተኞች መከፈል የነበረበት ነው።
እንደ አቶ ካሳሁን ገለጻ፤ አገናኝ ድርጅቶቹ ሠራተኞችን ከአሠሪው ድርጅት ጋር በማገናኘ ታቸው ምክንያት ከሠራተኛው ወይም ከቀጣሪው ወገን አንድ ጊዜ የሚከፈል ኮሚሽን መቀበል ነበረባቸው። ይሁንና ዕድሜ ልክ ከሠራተኛው ደመወዝ ላይ እየቀነሱ የሚያስቀሩበት አሠራር ወደፊት በሚኖሩት ጊዜያት መቀየር አለበት። ይህንን ጥያቄ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽም እንዲስተካከል እና የሠራተኞቹ መብት እንዲከበር እየጠየቀ ነው። ይሁንና ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር «ችግሩ ላይ ተጨባጭ ማስረጃ ማግኘት ያስፈልጋል» በሚል ምክንያት ጉዳዩን እያድበሰበሰው ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል።
በተጨማሪም ስለአገናኝ ድርጅቶች የደመወዝ አከፋፈል የሚያስረዳ ተገቢ ህግ የለም በመሆኑም አገናኝ ድርጅቶች ደመወዝ ቀንሰው የመክፈል መብት አልተከለከሉም። በመሆኑም ጉዳዩን ለማስቆም አይቻልም የሚሉ ምክንያቶችን በማቅረብ ሚኒስቴሩ ተገቢውን ቁጥጥር ሊያደርግ አልቻለም። በመሆኑም ችግሩ የሠራተኞችን ገቢ የሚቀንስ በመሆኑ እና እስከ አሁን ድረስ መፍትሔ ያላገኘ በመሆኑ በቀጣይ ለከፍተኛ የመንግሥት አካላት ችግሩን ለማስረዳት ታቅዷል። በዚህም የሠራተኞችን መብት የሚያስከብር መፍትሔ እንደሚገኝ ይጠበቃል።
የአሠሪና ሠራተኛ ህጉ በጉዳዩ ላይ በስፋት የሚያነሳው ሃሳብ ባይኖርም የአገር ውስጥ ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ተቋማትን እና ተቀጣሪ ሠራተኞችን ግንኙነት የተመለከተ ረቂቅ አዋጅ እየተዘጋጀ እንደሚገኝ የጠቆሙት አቶ ካሳሁን፤ በረቂቁ ላይ የአገናኝ ድርጅቶቹን አሠራር የሚደግፍ ሃሳብ መኖሩ በመረጋገጡ አዋጅ ሆኖ ከመውጣቱ በፊት እንዲስተካከል መጠየቃቸውን ገልጸዋል። በቀጣይ በሠራተኞች የደመወዝ ክፍያ ላይ ተገቢው አሠራር እንዲመጣ የህግ ጉዳዩ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ክትትል እንደሚደረግ ነው የሚጠቁሙት።
ጉዳዩ ይመለከተዋል የተባለው የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአገር ውስጥ ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎችን ቁጥጥር እና ፍቃድ የሚሰጡት የክልል እና የከተማ አስተዳደር ቢሮዎች ናቸው በሚል ለጥያቄዎቻችን ምላሽ አልሰጡም።
በዚህም መሠረት ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የአገር ውስጥ ሥራ ስምሪት ንዑስ የሥራ ሂደት መሪ አቶ አህመድ ኢርጎ ነው። አቶ አህመድ እንደሚናገሩት፤ በከተማዋ ውስጥ 263 ፍቃድ አውጥተው የሚንቀሳቀሱ የአገር ውስጥ ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ይገኛሉ። እነዚህም በሥራቸውም 11 ሺ ሠራተኞችን በተለያዩ ተቋማት አሰማርተዋል። ኤጀንሲዎቹ ሁለት ዓይነት ሲሆኑ አንደኛው ሠራተኛ በመመልመል ከአሠሪዎች ጋር አገናኝተው ሥራቸውን በኮሚሽን የሚጨርሱ ኤጀንሲዎች ሲሆኑ፤ ሁለተኛዎቹ ደግሞ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመደራደር የጥበቃ፣ የፅዳት እና የመሳሰሉትን ሥራዎች በኮንትራት በመያዝ ሠራተኛ ቀጥረው የሚያሠሩ ናቸው።
ሁለተኛዎቹ ኤጀንሲዎች ቀጥታ የሥራ ውል ከአሠሪ ተቋማት ጋር በመፈጸም ክፍያ የሚቀበሉ ሲሆን፤ ለተሰጣቸው ሥራ በራሳቸው ሠራተኞችን በመቅጠር ያሠራሉ። በዚህ ጊዜ ሠራተኞቹን በቀጥታ የሚያዘው ኤጀንሲው የሚሆንበትን ዕድል ይፈጥራል። የደመወዝ አከፋፈሉም ሠራተኛው ከሥራ አገናኙ ድርጅት ጋር በተፈራረመው ውል መሠረት የሚፈጸም ሲሆን፤ የክፍያውን መጠን የሚወስን ህግ ባለመኖሩ ኤጀንሲዎቹ እና ሠራተኞቹ በተስማሙበት የገንዘብ መጠን መሠረት ደመወዝ ይከፈላል።
በተጨማሪም ኤጀንሲዎቹ ሥራ ለመሥራት ኮንትራት ከፈጸሙለት ተቋም ጋር ውላቸው እስኪቋረጥ ወይም በሥራቸው የቀጠሩት ሠራተኛ በስራ ላይ እስከሚገኝ ድረስ የደመወዝ ነክ ጉዳዮችን በፈጸሙት ውል መሠረት ሊፈጽሙ ይችላሉ። በዚህ መሠረት አገናኝ ድርጅቶች (ኤጀንሲዎች) የተለያየ የደመወዝ አከፋፈል ስርዓት የሚከተሉ ሲሆን፤ ቢሮው ኤጀንሲዎቹ የተተመነ አከፋፈል እንዲከተሉ ሊያስገድድ አይችልም። ይህም የነፃ ገበያ መርህን የተከተለ የውድድር አሠራር ነው።
ይሁንና ሠራተኛው ከተዋዋለው ውጪ ደመወዙን ቀንሰው የሚሰጡ ኤጀንሲዎች እንዳሉ ጥቆማ ሲደርስ ቢሮው በሥራና ሠራተኛ ማገናኘት አገልግሎትት አዋጅ ቁጥር 632/2001 በተሰጠው ስልጣን መሠረት በፍጥነት ዕርምጃ እንደሚወስድ ነው የሚጠቁሙት። ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በዚህ መንገድ ጥፋት ፈጽሞ የተቀጣ አገናኝ ድርጅት እንደሌለም ይገልጻሉ። ከኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ስለቀረበው የአገናኝ ተቋማቱን አሠራር ስለሚመለከተው አዲስ ረቂቅ አዋጅ በተመለከተ ምንም መረጃ እንደሌላቸውና እንደማያውቁት ተናግረዋል።
እንደ አቶ አህመድ ገለጻ ከሆነ፤ በቀጣይ በሚኖሩ ጊዜያት የሠራተኞችን ጥቅም የበለጠ ለማስከበር እንዲቻል አንገናኝ ድርጅቶች በድርድር የደመወዝ አከፋፈል ስርዓታቸውን ከፍ እንዲያደርጉ ጥረት ይደረጋል። በመሆኑም የአመለካከት ችግር ያለባቸውን ተቋሟት በመለየት ጥሩ ክፍያ ይፈጽማሉ ከሚባሉ እና የሠራተኞችን ጥቅም ያስከብራሉ ከሚባሉ አገናኝ ድርጅቶች ትምህርት እንዲወስዱ ማድረግ ያስፈልጋል። በዚህም ኤጀንሲዎቹ የሚያገኙት ገቢ እና የሠራተኞቹ ደመወዝ ተመጣጣኝነት የለውም የሚለውን ቅሬታ መቀነስ ይቻላል ብለዋል።
የህግ አስተያየት
«በደመወዝ አከፋፈሉ እንዲሁም በሥራ ግንኙነቱ ላይ የሠራተኞቹ እና የአገናኝ ድርጅቶቹ ውል ስምምነት ወሳኝነት አለው» የሚሉት ደግሞ የህግ ባለሙያው አቶ ብርሃኑ አሰፋ ናቸው። እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ አንዳንድ አገናኝ ኤጀንሲዎች ሠራተኛ ካገናኙ በኋላ ከቀጣሪው ተቋም ጋር ምንም ዓይነት ግዴታዎችን ሳይዋዋሉ አንድ ጊዜ ብቻ የኮሚሽን ክፍያቸውን ተቀብለው ይሰናበታሉ። ይሁንና አንዳንዶቹ ያገናኟቸው ሠራተኞች ሥራቸውን እስከሚያጠናቅቁበት ጊዜ ድረስ ለሚፈጽሙት ጥፋት እንዲሁም በቀጣሪያቸው ላይ ለሚያደርሱት ኪሳራ ዋስትና ይገባሉ።
በዚህ ወቅት ከሠራተኛው ደመወዝ ላይ በየወሩ ተቀናሽ በማድረግ ገንዘብ ሊቆርጡ የሚችሉበት አሠራር ይፈጠራል። በመሆኑም እያንዳንዱ ሠራተኛ ከአገናኙ ጋር ውል በሚፈጽምበት ወቅት ስምምነቱን መረዳት አለበት። ይሁንና ጉዳዩ በአገር ደረጃ በህግ የተደገፈ መመሪያ ወይም አዋጅ ቢዘጋጅለት የደመወዝ አከፋፈሉ እና ሌሎች የሥራ ግንኙነቶቹ ላይ ወጥ አሠራር ለመዘርጋት ያስችላል የሚል ሙያዊ አስተያየት አላቸው ።
በአጠቃላይ በአገር ውስጥ ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ድርጅቶች፣ በሠራተኞች እንዲሁም የቀጣሪዎች ግንኙነት ዋነኛ ዓላማው ኢንዱስ ትሪያዊ ሰላምን በማምጣት ብቁ ሥራ ለመሥራት ነው። ይሁንና በሠራተኛ አገናኝ ድርጅቶች እና በአሠሪዎች መካከል ያለውን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ለሁለቱ ወገኖች ስምምነት ብቻ መተው ሠራተኛውን በአንጻራዊነት የኢኮኖሚ አቅሙ ጠንካራ ለሆኑ ድርጅቶች ጥቃት ሊያጋልጠው የሚችል ጉዳይ ሆኖ እናገኘዋለን።
በመሆኑም መንግሥት እንደ ሦስተኛ ወገን ሆኖ በግንኙነቱ ውስጥ እየገባ የሠራተኛውን መብትና ጥቅም ማስከበር ፤ ከአሠሪው የሚደርሱ ጥቃቶች ለመከላከልም ወጥ የሆነ ህግና መመሪያ እንዲኖር ማድረግ ይገባል። ይሄ ሲሆን ነው ዜጋው መብትና ጥቅሙ ተከብሮ ግዴታውን በአግባቡ መወጣት የሚችለው። በህግና ደንብ ያልተገዛ የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት አሁን እንደሚባለው «ከዘመናዊ ጉልበት ብዝበዛ » የተለየ አይሆንም።

No comments:
Post a Comment