Monday, March 20, 2017

የኢትዮጵያ ሳተላይት የማምጠቅ እቅድ ይሳካ ይሆን?



እንደ ኢትዮጵያ ህዋ ሳይንስ ማህበር መረጃ ከሆነ በህዋ ላይ እየሰሩ የሚገኙ 1400 ሳተላይቶች አሉ። ከዚህ ውስጥ ከ500 በላይ የሚሆኑት የአሜሪካውያን ናቸው። ኢትዮጵያ እስከ አሁን የሌሎቸ አገራት ሳተላይቶችን በኪራይ እየተጠቀመች ትገኛለች። በዚህም የግል ተጠቃሚዎችን ጨምሮ በዓመት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ለኪራይ ታወጣለች።
ይህን ችግር ለማቃለል ኢትዮጵያ ከሶስት እስከ አምስት አመታት ባሉት ጊዜያት ውስጥ ሳተላይት ለማምጠቅ አቅዳለች። በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የሚመራ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተቋቁሟል። የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲም ሰሞኑን በዘርፉ ከተሰማራው የፈረንሳዩ ኩባንያ ዩ ቴል ሳት ጋር የ13 ሚሊየን ዩሮ የማማከር ስምምነት ተፈራርሟል። የኢትዮጵያ ሳተላይት የማምጠቅ ፍላጎት እና ደረጃ ምን ላይ ይገኛል? የሚኖረው ፋይዳስ ከወጭው አንፃር እንዴት ይመዘናል?
የኢትዮጵያ በእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪና ምርምር ማዕከል የመሬት ምልከታ ምርምር ኃላፊ ዶክተር ቱሉ በሻ እንደሚገልፁት፤ የኢትዮጵያ አቅም በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ሳተላይት ለማምጠቅ ያስችላል። የማምጠቂያ ወጪው እና ሳተላይቱ ከሚሰጠው ጥቅም ጋር ሲነጻጸርም የሚገኘው መረጃ አስፈላጊነት እጅጉን ልቆ ይገኛል። በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ፣ የመገናኛ መሳሪያዎችን ጥራት እና ብዛት ከማሻሻል አኳያ እና ለተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች መረጃዎችን ከህዋ ለመሰብሰብ ሳተላይቱ ወሳኝ ድርሻ አለው። በተጨማሪ ኢትዮጵያ በማምጠቋ መረጃውን ከሌሎች አገራት ለማግኘት የምትከፍለውን ከማስቀረት ባሻገር ከሳተላይቱ የሚገኘውን መረጃ ለጎረቤት አገራት በመሸጥም ገቢዋን ለማሳደግ ይረዳታል።
«ለሳተላይቱ ማምጠቂያ የሚሆነውን መሰረተ ልማት የግድ ኢትዮጵያ ላይ መገንባት አያስፈልግም» የሚሉት ዶክተር ቱሉ፤ የመሰረተ ልማቱን ለመገምባት ቢታሰብ ከአገሪቷ አቅም በላይ እንደሚሆን ነው የሚናገሩት። በመሆኑም ከሌሎች አገራት ማስወንጨፊያ ተከራይቶ መላክ አዋጭ መሆኑን ያስረዳሉ። ይሁንና ማምጠቂያውን ገንብቶ ለመጠቀም እና ለማከራየት የረጅም ጊዜ እቅድ ሊያዝ እንደሚገባ ይጠቁማሉ።
የአስትሮ ፊዚክስ ምሁሩ ዶክተር ለገሰ ወትሮ፤ አሁን አይቻልም፤ ማስወንጨፊያውን መከራየት በሚለው ሃሳብም አይስማሙም። በአሁኑ ወቅት አንድ ሳተላይት ለማምጠቅ አንድ ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚፈጅ ይገልፃሉ። «አገሪቷ ያላት የኢኮኖሚ ደረጃ ደግሞ ሳተላይት ማምጠቁም በድህነት ላይ ሌላ ወጪ መጨመር ነው። በቅርብ ዓመታት ውስጥ ይሳካል ብሎ መናገር አይቻልም» ይላሉ። በመሆኑም ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም የአገሪቷ ኢኮኖሚው የበለጠ ማደግ አለበት የሚል እምነት አላቸው። ይህም ጊዜ ወስዶ አስፈላጊውን ግብአት ለማሟላት እንደሚያግዝ ይናገራሉ።
«የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከዳበረ በኋላ የማምጠቂያ ቴክኖሎጂው ለመገንባት ዝግጅት ማድረግ ይገባል። አቅሙ ከተፈጠረና ማስወንጨፊያው ከተገነባ በኋላ የአገሪቷ በምድር ወገብ አካባቢ የሚገኝ በመሆኑ ከመሬት ሽክርክሪት ጋር ተያይዞ አመቺ የሳተላይት ማምጠቂያ አካባቢ ላይ ትገኛለች። በመሆኑም ይህን እድል መጠቀም ይገባል። አገሪቷ ከማስወንጨፊያ ኪራይ የሚያድናት ከመሆኑም በላይ ለሌሎች አገራትም በማከራየት ከፍተኛ ገቢ ታገኛለች። በመሆኑም ማስወንጨፊያውን ከመከራየት ይልቅ ማስወንጨፊያውን በአገር ውስጥ ስለመገንባት መታሰብ አለበት» የሚል አቋም አላቸው።
«ለዘርፉ ከኮሚዩኒኬሽን ጋር የተያያዘ በርካታ ስራ ቢያስፈልግም በኢትዮጵያ የተጠናከረ የቴክኖሎጂ አቅም ስለመኖሩ እርግጠኛ መሆን አይቻልም» የሚሉት ዶክተር ለገሰ፤ ለዚህም ደግሞ የአገር ውስጥ የተማሪዎችን እና ምሁራንን የቴክኖሎጂ አቅም ደረጃን ከፍ ማድረግ መቅደም አንደሚገባው ይናገራሉ። «በተለይም አሁን ያለው የህዋ ተመራማሪዎች የቴክኖሊጂ አቅም አገሪቱ በሙሉ እምነት ሳተላይት ለማምጠቅ የሚያስችል አይደለም። በዚህም ምክንያት የውጭ ባለሙያዎች ተቀጥረው እስካልተሳተፉ ድረስ ከሶስት እስከ አምስት ዓመታት ድረስ ሳተላይት ወደ ህዋ ለማምጠቅ አይቻልም። በመሆኑም በዩኒቨርሲቲዎች በኩል ዕውቀት እና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ይገባል» የሚል ጠንካራ አቋም ይዘዋል። በተጨማሪም ከሳተላይቱ የሚገኘውን መረጃ በሳይንሳዊ መንገድ በአግባቡ ስለመጠቀም ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል። ይህ ካልሆነ ግን ከሳተላይት የሚገኘው መረጃ ከተለያዩ ሚዲያዎች ከሚገኘው ቁምነገር የተለየ ጥቅም ሊያገስገኝ እንደማይችል ነው የሚገልፁት።
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አብነት እዝራ በበኩላቸው፤ የተለያዩ የሳተላይት አይነቶች ቢኖሩም በአሁኑ ወቅት በአትዮጵያ ቅድሚያ የተሰጠው የመሬት ምልከታ/Earth Observation/ ሳተላይት ሲሆን ለመገናኛ መሳሪያነትም ያገለግላል። ይህም በህዋ ላይ እስከ 15 ዓመት የቆይታ እድሜ ይኖረዋል። አሁን ባለው እቅድ መሳሪያው በውጭ ሰዎች የሚዘጋጅ እና በአገር ውስጥ የሚገጣጠም በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በቂ የዕውቀት ሽግግር እንዲያገኙ ማድረግ ይገባል። በቀጣይ ሳተላይቱን ለመቆጣጠር እና ለማምጠቅ የቴክኖሎጂ ተላምዶ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ነው የሚናገሩት። ናይጄሪያ የመጀመሪያውን ሳተላይቷን ስታመጥቅ የውጭ አገር ባለሙያዎችን ተጠቅማ ቢሆንም ከአራት ዓመታት በኋላ ስራውን ሙሉ በሙሉ በአገሯ ሰዎች መቆጣጠር ችላለችና ከዚህ ልምድ መውሰድ ይቻላል።
በመሆኑም አሁን ባለው የአገሪቷ ኢኮኖሚያዊ እና የዘርፉ ቴክኖሎጂ ደረጃ ሳተላይት ለማምጠቅ ረጅም ዓመታት ይፈጃል የሚለውን በዶክተር ለገሰ ሃሳብ አይስማሙም። በዋጋ ደረጃ አሁን አገሪቷ የሳተላይት አገልግሎት ለማግኘት በየዓመቱ የሚወጣው ወጪ ቢደመር ሳተላይት ለማምጠቅ በቂ መሆኑን ነው የሚናገሩት። የወጪው ጉዳይ እንደማያሳስብ ይገልፃሉ።
«ሳተላይት ስለተገኘ ብቻ ሁሉም አገራት ያስተኩሳሉ ማለት አይደለም» የሚሉት አቶ አብነት፤ 65 አገራት ሳተላይት ቢያመጥቁም በዓለም ላይ የእራሳቸው ማስወንጨፊያ ያላቸው 12 አገራት ብቻ መሆናቸውን ነው የሚጠቁሙት። በአፍሪካ ውስጥ ሳተላይት ተወንጭፎ እንደማያውቅ እና ኢትዮጵያም የሌሎች አገራት ማስወንጨፊያ መጠቀሟ ተገቢ መሆኑን ነው የጠቆሙት።
«ጉዳዩን ለማሳካት ቁርጠኛ በመሆን የዘርፉ ፖሊሲ እና ስትራቴጂ በፍጥነት መዘጋጀት አለበት» የሚሉት አቶ አብነት፤ ይህም ስራውን በትክክለኛው መንገድ ለመምራት እና ብቁ ባለሙያዎችን በብዛት ለማፍራት አይነተኛ ሚና ይኖረዋል። ይህ ከተሳካ የአሜሪካ የህዋና የጠፈር ምርምር ማዕከል (ናሳ) የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን ጭምር በማስመጣት አገሪቷን በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ የእራሷ ሳተላይት ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል የሚል እምነት አላቸው።

 

No comments:

Post a Comment

Featured post

ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጠያቂነትን በማረጋገጥ፣ የሕግ በላይነትን በማስፈን፣ መንግሥትና የስራ አስፈጻሚ አካላቱ በመሉ ለሰብአዊ መብቶች መከበር፣ መጠበቅና መሟላት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያሳዩ ልዩ ትኩረትና ክትትል ይሻል

                    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየደረጃው ያሉ የመንግስት አስፈጻሚ አካላትና ኃላፊዎች ላይ የቅርብ ክትትል በማድረግ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር አስተዋጽኦ ሊያደር...