ፈተና የሆኑት ብሔራዊ ፈተናዎች
በኢትዮጵያ በ2008 ዓ.ም የተሰጠውን የ10ኛ እና 12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተናን ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን
በላይ ተማሪዎች እንደወስዱ የሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና የፈተናዎች ኤጀንሲ መረጃ ያመለክታል። በየአመቱም
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ብሔራዊ ፈተናውን እየወሰዱ ይገኛሉ። ይሁንና ብሔራዊ ፈተናዎች ተማሪዎች በፈተና ላይ
ብቻ ትኩረት እንዲያደርጉ እንደሚጋብዝ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ከፊንላንድ ጂቫስኪላ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ፕሮፌሰር ጁውኒ ቫሊጃርቪ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ «የፊንላንድ የትምህርትና የፈጠራ ተሞክሮዎች» በሚል
ርዕስ በተዘጋጀው ውይይት ላይ ተገኝተው እነዳስረዱት ከሆነ በፊንላንድ አገር ብሔራዊ ፈተና የሚባል ነገረ የለም። ብሔራዊ
ፈተና ሲሰጥ ተማሪው ፈተና ላይ ብቻ ያተኩራል በሚል በምርምር እና ውጤታማነት ላይ ያተኮረ ምዘና ይካሄዳል።
በአገሪቷም ለመምህራንና ትምህርት ተቋማት ሙሉ ሃላፊነት በመስጠት የተማሪዎች ዕውቀት እና ክህሎት እድገት ላይ
የበኩላቸውን ጥረት እና ውሳኔ እንዲያስተላልፉ ይደረጋል። ከዚህ በተጨማሪ ብሔራዊ ፈተና በወጪ ረገድ ከፍተኛ ገንዘብ
የሚጠይቅ በመሆኑ አውሮፓዊቷ አገር አትጠቀምበትም።
ከአዲስ
አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ ትምህርት ኮሌጅ ፕሮፌሰር ጥሩሰው ተፈራ ፤ ብሔራዊ ፈተና የሚሰጥበት
ዋነኛው ምክንያት የትምህርቱን ደረጃ ለመፈተሽ ነው ይላሉ። ለአብነት በሁሉም ክልሎች እና ሁለቱ መስተዳደር ከተሞች
ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ስለማግኘታቸው ለማረጋገጥ አገር አቀፍ ፈተና ይካሄዳል። ይህም
ከየአካባቢው የሚወጡ ተማሪዎች የሚመዘኑበት እና በእኩል ደረጃ ውጤታቸውን ለመገምገም የሚያስችል ነው። በተጨማሪም
ሁሉንም በተመጣጠነ ሁኔታ ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት መውሰዳቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል አሰራር ነው። በዚህም
ተማሪው ብሔራዊ ፈተናውን ማለፉ ከተረጋገጠ በዕውቀትም ሆነ በክህሎት እንዲሁም በአመለካከት ረገድ ምን ደረጃ ላይ
ደርሷል? የሚለውን ለመለካት ያግዛል። በመሆኑም የትምህርቱን ጥራት ለማስጠበቅ የሚካሄድ ፈተና አድርጎ መውሰድ ይቻላል ይሉናል።
እንደ
ፕሮፌሰር ጥሩሰው ገለጻ ከሆነ ፤ በኢትዮጵያም ውስጥ አንድ ተማሪ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ሲያጠናቅቅ ማንበብ
መፃፍ፣መግባባት፣ ስነምግባር እና ሁለንተናዊ ስብእና ያለው መሆኑ መረጋገጥ አለበት። በተለይም ከክፍል ክፍል
ሲዘዋወሩ ማለፋቸውንና ብቁ መሆናቸውን የሚያረጋግጠው መምህሩ ነው። ይህም በመሆኑ አስተማሪም ብቁ ተማሪ እንዲኖረው
ጥረት ያደርጋል። በቀጣይም ከመነሻው ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ ተጠብቆ መሄድ ያለበት አሰራር መሆን
ይገባዋል። ተማሪው ትምህርቱን መማሩን ማረጋገጥ የሚቻለው በክፍል ውስጥ ነው። ይሁንና በርካታ ተማሪዎች ሳይማሩ
በኩረጃ ብቻ ፈተናዎችን ያልፋሉ። በተለይ የግል ትምህርት ተቋማት ከብሔራዊ ፈተናዎች ጋር ተያይዞ ተማሪዎች ለፈተና
ብቻ እንዲዘጋጁ ማድረጋቸው አግባብ አይደለም። ይህም ተማሪዎቹ ከፈተና በኋላ ዕውቀቱን እንዲረሱ የሚገፋፋ ይሆናል።
በመሆኑም ውጤታማ የትምህርት አካሄድ የተከተለ ነው ለማለት እንደሚከብድ ይናገራሉ።
«በየትምህርት ቤቱ ያሉ መምህራን እና ርዕሰ መምህራን ሃላፊነታቸውን በሚገባ መወጣት ይኖርባቸዋል» የሚሉት ፕሮፌሰር ጥሩሰው፤ ብሔራዊ ፈተናን በኢትዮጵያ ማስቀረት የሚቻለው ሙሉ በሙሉ ሃላፊነቱን መሸከም የሚችል መምህርና ርዕሰ-መምህር
ማዘጋጀት ሲቻል መሆኑን ነው የሚያስረዱት። እዚህ ላይ የመምህራን ብቻ ሳይሆን የወላጆችም ሃላፊነት መታከል
እንዳለበት ይጠቁማሉ። ይህም ተማሪዎች በውስጣዊ የትምህርት ፍላጎት እንዲማሩ እንጂ ለፈተና ብቻ እንዳይዘጋጁ
እንደሚረዳ ይናገራሉ። ይሁንና አሁን በአገሪቷ የሚታየው ተማሪዎችን ለፈተና ብቻ እንዲዘጋጁ የማድረግ አሰራር ሲሆን፤
በዚህ ጉዳይ ከፍተኛ የለውጥ እርምጃ የሚያስፈልገው የመምህራን ምልመላ እና ስልጠና ላይ መሆኑን ይገልፃሉ።
ዋነኛው
የትምህርት አነቃናቂው ሞተር መምህራን በመሆናቸው ለአሰራሩ ዝግጁ እንዲሆኑ በቂ ዝግጅት ያስፈልጋል። በዚህም
ትምህርት ቤቶች አስፈላጊውን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ያግዛል። በርካታ የግል ትምህርት ተቋማት ፈተና ላይ
ያልተመረኮዘ የትምህርት አሰራርን እንዲከተሉ ማድረግ ይገባል። ይህ እስካልተከናወነ ድረስ ተማሪዎች ለዕውቀት እና
ክህሎት ሳይሆን ብሔራዊ ፈተና ላይ ብቻ ያተኩራሉ የሚል ሃሳብ ይሰነዝራሉ።
የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ «የኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓት የሚያተኩረው ዕውቀት እና ክህሎት የማሻሻል ተግባር ላይ ነው። በመሆኑም ፈተና ላይ ትኩረት አድርጎ ውጤት የሚለካው ተማሪዎችን መለየት ስለሚያስፈልግ ብቻ ነው። ስለዚህ 10ኛ እና 12ኛ
ክፍሎች ላይ ብሔራዊ ፈተና እየተሰጠ የሚገኘው በዚሁ አሰራር መሰረት ነው። በመሆኑም በቀጣይ ብሔራዊ ፈተናዎችን
ለማንሳት የሚያስችል ምንም አይነት ስራና አዲስ እቅድ አይኖርም። ሆኖም በትምህርት ዘርፉ ላይ ተማሪዎች አቅማቸውን
ለማጎልበት እንዲችሉ የግል ጥረት እንዲያደርጉ ይጠበቃል። ይህም ብሔራዊ ፈተናን ብቻ ሳይሆን እውቀት እና ክህሎትን
በበቂ ሁኔታ ይዘው አገራቸውን እንዲያገለግሉ ይረዳቸዋል» በማለት ነው ሃሳቡን ውድቅ ያደረጉት።

No comments:
Post a Comment