Thursday, March 2, 2017

 ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ያሰናበተው መመሪያ


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ባንኮች እና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ያላቸውን የአክስዮን መብት ለመቆጣጠር በጥቅምት 22 ቀን 2009 ዓ.ም የማስፈጸሚያ መመሪያ አውጥቷል። መመሪያው የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኢትዮጵያ ውያን በባንኮችና በኢንሹራንስ ኩባንያዎች ያላቸውን አክሲዮን ለኩባንያዎቹ በ60 ቀናት ውስጥ እንዲመለሱ ያስገድዳል። ኩባንያዎቹ ደግሞ ለባለአክስዮኖቹ የድርሻቸውን እንዲከፍሉ ያዛል፡፡ ይህ አሠራር በፋይናንስ ተቋማት አቅም ላይ የሚፈጥረው ተጽእኖ ይኖር ይሆን? ለመፍትሔውስ ምን መደረግ አለበት? ለሚለው ጥያቄ የዘርፉ ባለሙያዎች ሃሳባቸውን ይናገራሉ።
    የአንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ አክሲዮን ማህበር የፋይናንስ መምሪያ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ስለሺ ጥጋቡ፤ ትውልደ ኢትዮጵያውያን በባንኩ ውስጥ ባለአክሲዮን የሆኑት በመጀመሪያ ዜግነታቸው ኢትዮጵያውያን እንደነበሩ ነው የሚናገሩት። ከጊዜ በኋላ ዜግነታቸውን ወደ ሌሎች አገራት በመቀየራቸው ምክንያትም 130 አባላት ከአክሲዮን እንዲወጡ እየተደረገ ነው። ከአጠቃላይ የባንኩ ካፒታል ጋር ሲነፃጸር ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ ያላቸው ድርሻ አንድ ከመቶ እንኳን የማይሞላ በመሆኑ፤ ከአክሲዮን በመውጣታቸው ምክንያት በባንኩ ላይ የሚፈጠር የገንዘብ ቀውስ እንደማይኖር ነው የሚጠቁሙት። በቀጣይም ባንኮች ባስወጧቸው ትውልደ ኢትዮጵያውያን ምትክ ገቢ ለመሰበሰብ እና የፋይናንስ ደረጃውን ለማጠናከር የአክሲዮን ድርሻዎችን ለገበያ ማቅረብ ቀጥተኛው መፍትሔ መሆኑን ነው ያስረዱት።
    የእናት ባንክ አክሲዮን ማህበር የቦርድ ሰብሳቢ ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ፤ የብሔራዊ ባንክን ህግ በአግባቡ ባለመረዳት የተለያዩ ባንኮች ትውልደ ኢትዮጵያንን የአክሲዮናቸው ባለድርሻ አድርገው እንደነበረ ይናገራሉ። እናት ባንክም በቁጥር አነስተኛ የሆኑ እና ዝቅተኛ የካፒታል ምንጩ የነበሩትን የውጭ ዜጎች እያስወጣ እንደሚገኝ ነው የሚጠቁሙት። በዚህም ይዘውት የነበረውን አክሲዮን እንዲያስረክቡ በማድረግ በመልሱ ደግሞ ባንኩ የሚጠበቅበትን ክፍያ እየፈጸመ መሆኑን ያስረዳሉ።
    «ባንኩ የተቀበለውን አክሲዮን ድርሻም በሐራጅ ጨረታ መልሶ ለባለድረሻ ፈላጊዎች እንዲውል ይደረጋል» የሚሉት ወይዘሮ መዓዛ እንደ አንበሳ ባንኩ አቶ ስለሺ ሃሳብ ሁሉ በእርሳቸው ባንክ ላይ ምንም ዓይነት የጎላ የፋይናንስ ተጽእኖ እንደማያስከትል እምነታቸው መሆኑን ነው የሚያስረዱት። በመሆኑም በቀጣይ ሙሉ በሙሉ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ላላቸው ሰዎች ብቻ የባንኩን የካፒታል መጠን እንዲያሳድጉ እና በጋራ ለመሥራት አክሲዮን እንደሚሸጥላቸው ይጠቁማሉ።
    በአፍሪካ ኢንሹራንስ አክሲዮን ማህበር ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ካሳሁን በጋሻው ግን በአንበሳ እና በእናት ባንኮች ሃሳብ አይስማሙም። እርሳቸው እንደሚናገሩት፤ በአሁኑ ወቅት ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ከፋይናንሱ ዘርፍ እንዲወጡ መደረጉ ባንኮች ካፒታላቸውን በማሳደግ ሁለት ቢሊዮን ብር እንዲያደርሱ ከሚጠይቀው አሠራር ጋር የማይጣጣም እና የያዙትንም ካፒታል የሚያመናምን ነው ይላሉ። «ትውልደ ኢትዮጵ ያውያን በተለያዩ ባንኮች ውስጥ እስከ ቦርድ አባልነት በደረሰ ስልጣን ያገለግሉ ነበር። በተለያየ አጋጣጠሚ በአገሪቷ ውስጥ ሀብት አፍርተዋል። በመሆኑም ከሚሰጡት የፋይናንስ እና የእውቀት ጥቅም ጋር ሲነፃፀር ከሌሎች የውጭ አገር ዜጎች በተለየ ለትውልደ ኢትዮጵያውያን በቁጥር የተደገፈ አሠራር ተፈጥሮ በፋይናንስ ዘርፉ እንዲሳተፉ ፍቃድ መሰጠት አለበት» የሚል አቋም አላቸው።
    እንደ አቶ ካሳሁን ገለጻ፤ የትውልደ ኢትዮጵ ያውያኑን መውጣት ተከትሎ የየፋይናንስ ተቋማት ካፒታል አቅም መመናመኑን ለመቀነስ ተቋማቱ በመጣመር ወይም አንዱ አንዱን በመጠቅለል አቅማቸውን ማጠናከር እንደሚያገባቸው ሃሳቦች ይቀርባሉ። ይሁንና ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የፋይናስ ተቋማት ቢዝነስን ብቻ ሳይሆን ብሔርን፤ ፖለቲካን እና «የዘርፉ ባለሙያ ነን» የሚል አጀንዳን መሠረት አድረገው የተቋቋሙ በመሆናቸው አንዱን ከአንዱ ለማዋሃድ አስቸጋሪ እንደሚሆን ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።
    በመሆኑም በቀጣይ የፋይናንስ ዘርፉን ለማጠናከር የዲያስፖራው የአክሲዮን ድርሻ በህግ ሊደገፍ ይገባል። በሥራ ላይ ሲሰማሩም ተጽእኖ ፈጣሪ እንዳይሆኑ በጥናት ላይ ተመስርቶ የአክሲዮን ድርሻቸውን ከአጠቃላይ ካፒታሉ ጋር ያለውን ንጽጽር በመቶኛ መገደብ ይቻላል። ለዚህም ደግሞ አስፈላጊው የቁጥጥር እና የአሠራር መመሪያ ማዘጋጀት ያስፈልጋል።
    የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር ተኪኤ ዓለሙ፤ ብሔራዊ ባንክም ሆነ የአገሪቷ ህገመንግሥት የውጭ አገር ዜግነት ያላቸው ግለሰቦች በባንክ ሥራ ላይ መሰማራት እንደሌለባቸው በግልጽ ማስቀመጡን ይጠቁማሉ። ይሁንና የግል ፋይናንስ ተቋማት ትውልደ ኢትዮጵያውያንን በአክሲዮን ድርሻቸው ላይ አሳትፈው መገኘታቸው ቀድሞውንም ትክክለኛ አካሄድ እንዳልነበረ ነው የሚናገሩት። በአሁኑ ወቅት ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ከአክሲዮን ድርሻቸው ሲያስወጡ የፋይናንስ አቅማቸው እና አሠራራቸው ደካማ እንደሚሆን የሚያነሱት ሃሳብ ትክክለኛ እንዳልሆነ ነው የሚናገሩት። በአገሪቷ ውስጥ ያሉት ባንኮች በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ በመስማማት ጥምረት ፈጥረው ሊሠሩ እና ካፒታላቸውን ማሳደግ ሲችሉ የሚገጥማቸውን የፋይናንስ መዳከም ለመከላከል እንደሚችሉም ነው የሚያስረዱት።
    «በተለያዩ የአደጉ አገራት የሚገኙ ባንኮች ሦስት እና አራት ብቻ ሲሆኑ አቅማቸውም ከፍተኛ ነው» የሚሉት ዶክተር ተኪኤ፤ በኢትዮጵያ ግን ከ20 በላይ ባንኮች እና የፋይናንስ ተቋማት እንደሚገኙ ነው የጠቆሙት። ይህም የተበጣጠሰ የካፒታል አቅም እና ያልተዋቀረ አሠራር እንዲኖር ማድረጉን ያስረዳሉ። በመሆኑም በየቦታው ባንክ ከፍቶ ከመንቀሳቀስ ይልቅ ተቋማቱን በማቀናጀት የተደራጁ እና ከፍተኛ አቅም ያላቸው ሁለት እና ሦስት ባንኮችን መመስረት እንደሚያስፈልግ ነው የሚመክሩት። ብሔራዊ ባንክም በየወቅቱ የፋይናንስ ተቋማቱ ካፒታል እንዲያድግ የሚጠቁመውም በሌላ አነጋገር ተዋሐዱ እያላቸው መሆኑን መገንዘብ እንደሚቻል ነው የሚናገሩት።
    እንደ ዶክተር ተኪኤ ገለጻ፤ በትውልደ ኢትዮጵያውያኑ መውጣት የሚደርሰውን የካፒታል መቀዛቀዝ ባንኮቹ ውህደት በመፈጸም ሊከላከሉት ይገባል። በዚህም ሊያጋጥም የሚችለውን የፋይናንስ እና የከፍተኛ ባለሙያ እጥረት መቅረፍ ይቻላል።

No comments:

Post a Comment

Featured post

ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጠያቂነትን በማረጋገጥ፣ የሕግ በላይነትን በማስፈን፣ መንግሥትና የስራ አስፈጻሚ አካላቱ በመሉ ለሰብአዊ መብቶች መከበር፣ መጠበቅና መሟላት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያሳዩ ልዩ ትኩረትና ክትትል ይሻል

                    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየደረጃው ያሉ የመንግስት አስፈጻሚ አካላትና ኃላፊዎች ላይ የቅርብ ክትትል በማድረግ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር አስተዋጽኦ ሊያደር...