Thursday, March 2, 2017

 የብር ምንዛሪ አቅምና ኢኮኖሚያዊ አንድምታ


የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብት ተወዳዳሪነት ለማጠናከር ይረዳል ያለውን ሃሳብ የዓለም ባንክ አቅርቧል። በዚህም የኢትዮጵያውያን መገበያያ ገንዘብ ብር የመግዛት አቅሙ መቀነስ እንዳለበትና ለዚህም ሥልጣን ያለው ብሔራዊ ባንክ ማስተካከያ ማድረግ እንደሚገ የፈረነጆቹ 2016 አመት ከመጠናቀቁ በፊት ማሳሰቡ የሚታወስ ነው። በዝርዝር ሲያስቀምጠውም በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ እየተደረገ ያለውን የኢትዮጵያ ገንዘብ በዓለም ገበያ በከፍተኛ ብር መመንዘር እንደሚገባው ማለትም በአንድ የአሜሪካን ዶላር አሁን ካለበት(ለህትመት እስከገባንበት ድረስ) ካለው ከ22 ነጥብ 3 ብር በላይ መመንዘር እንደሚገባው ገልጿል። ይህም የአገሪቷን ኢኮኖሚ ለማሳደግ እንደሚረዳ ነው የዓለም ባንክ በሪፖርቱ ያስቀመጠው። የተለያዩ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በጉዳዩ ዙሪያ ምን ይላሉ? 
ባንኩ እ..አ በ2010 ላይ ተመሳሳይ ሃሳብ አቅርቦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም ምክረ ሃሳቡን ተቀብሎ ብር ከዶላር ጋር ያለው የመግዛት አቅም በ17 በመቶ እንዲቀንስ መደረጉ የሚታወስ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢ አቶ ዮሐንስ አያሌው የምንዛሪ ማሻሻያ እንዲደረግ የቀረበው ሃሳብ ሊያመጣው ከሚችለው ጥቅም በላይ ጉዳቱ ሊከፋ እንደሚችል ይናገራሉ። የዓለም ባንክ ሪፖርቱን ባቀረበበት ወቅት ለጋዜጠኞች ገልጸው ነበር። ብሔራዊ ባንክ ከዓለም ባንኩ የቀረበው ሃሳብ ተቀባይነት እንደማይኖረው ያስረዱት ደግሞ ቀደም ባሉ ጊዜያት ተመሳሳይ ዕርምጃ በተወሰደበት ወቅት በአገሪቷ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት መከሰቱን በመጠቆም ነው።
የአፍሪካ አቅም ግንባታ ፋውንዴሽን ዋና ፀሐፊ የኢኮኖሚ ባለሙያው ፕሮፌሰር ኢማኑዌል ናዶዚዬ፣ «የአንድ አገር ገንዘብ የመግዛት አቅም እየቀነሰ መምጣት የአገሪቷ ኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ስለመግባቱ ማሳያ አይደለም» ይላሉ። የበርካታ የአደጉ አገራት መገበያያ ገንዘብ ከአንድ የአሜሪካን ዶላር ጋር ሲነፃፀርም የመግዛት አቅሙ ዝቅተኛ መሆኑን ነው የሚያስረዱት። የኢትዮጵያ የብር አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ቢመጣም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት በአጥጋቢ ሁኔታ እያደገ እንደሚገኝ ይጠቁማሉ። ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ሲነጻጸርም አስተማማኝነቱን በሚያረጋግጥ መልኩ ለአስር ዓመታት የተረጋጋ ዕድገት መታየቱን ነው የጠቀሱት።
እንደ ፕሮፌሰር ኢማኑዌል ገለጻ፤ አገሪቷ የብር መግዛት አቅምን በመቀነሷ ምክንያት ሀብቷን ለውጭ ገበያ በቅናሽ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬን መሰብሰብ ያስችላታል የሚል እምነት አላቸው። ይሁንና «የብር አቅምን በመቀነሱ ምክንያት ተገቢ ጥቅም ማግኘት የሚቻለው ሠፊ ምርት ለዓለም ገበያ በማቅረብ ነው። ይህ ከተደረገ የብር ምንዛሬ መቀነሱ አሳሳቢ አይሆንም» በማለት ነው ሃሳባቸውን ያጠቃለሉት።
የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር አቶ ኃይሌ አደመ እንዳሉት የኢትዮጵያ መንግሥት ፖሊሲ የወጪ ንግድን የሚያበረታታ ነው። ልማትም የውጭ ምንዛሬን በሚያስገኙ ሥራዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባው ስለሚያምን የብር አቅም መቀነስ ወደ ውጭ በሚላኩ ምርቶች ላይ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ያስረዳሉ። የብር የመግዛት አቅም ሲቀንስ አገር ውስጥ ያሉ ምርቶች በዓለም ገበያ ላይ ዋጋቸው እንዲረክስ ያደርጋል። ይህ ደግሞ ላኪዎችን በዋጋ ደረጃ ተመራጭ ስለሚያደርጋቸው የወጪ ንግድን እንደሚያበረታታ ነው የሚጠቁሙት።
ይሁንና ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የላከችው እና የተገኘው የውጭ ምንዛሬ አነስተኛ በመሆኑ የብር የመግዛት አቅምን ሊቀንሰው እንደሚችል ነው የሚገልጹት። ከዚህ በተጨማሪ መንግሥት የብርን መግዛት አቅም በራሱ የሚቀንስ ከሆነ ቅነሳው ከፍተኛ ይሆናል። በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ከወጪ ንግዱ በበለጠ የገቢ ንግድ እንደሆነ ይናገራሉ። በመሆኑም የብርን የመግዛት አቅም አሁን ካለበት በላይ መቀነስ ተገቢ እንደማይሆን ነው የሚጠቁሙት። የብር አቅም ከዚህ በላይ ከቀነሰም ያልተመጣጠነ የንግድ ስርዓት ስለሚፈጠር የአገሪቷን ኢኮኖሚ እንደሚያዳክመው ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።
የኢኮኖሚ ባለሙያው ዶክተር ተኪኤ አለሙ ደግሞ ፤ «የብር የመግዛት አቅም በአንድ ጊዜ እንዲጨምር ወይም እንዲቀንስ ከተደረገ በተለያዩ ዕቃዎች እና ምርቶች ላይ የተጋነነ የዋጋ ለውጥ ያስከትላል» ይላሉ። ይህም በተመሳሳይ ጊዜ አንዱን የንግድ ወገን ድሃ የሚያደርግ ሌላውን ደግሞ ሀብታም የሚያደርግ እንደሚሆንና ፍትሐዊውን የንግድ ስርዓትየሚያዛባ እንደሚሆን ነው የሚያስረዱት። የምርቶችን ዋጋ መልሶ ወደ ነበረበት ለማሸጋገርም እጅግ አዳጋች እንደሚሆን ነው የሚጠቁሙት።
መንግሥት የብር የመግዛት አቅምን በአንድ ጊዜ እንዲቀንስ ካደረገበት እ... 2010 ጀምሮ በየቀኑ የብር የመግዛት አቅም በአንድ ሳንቲም ደረጃ እየቀጠለ እንደሚገኝ ነው የጠቆሙት። «ይህም ጎልቶ የወጣ የዋጋ ግሽበት እንዳይከሰት ረድቷል» ይላሉ ዶክተር ተኪኤ። በመሆኑም እንደእስካሁኑ ብር በጊዜያቶች ሂደት የመግዛት አቅሙ እየቀነሰ ቢሄድ እንደሚሻል ነው የሚጠቁሙት። ይሁንና በቅጽበታዊ ሁኔታ የብር የመግዛት አቅም የሚቀነስ ከሆነ የተጋነነ የዋጋ ግሽበት እንደሚያመጣ ነው ስጋታቸውን የገለጹት።

No comments:

Post a Comment

Featured post

ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጠያቂነትን በማረጋገጥ፣ የሕግ በላይነትን በማስፈን፣ መንግሥትና የስራ አስፈጻሚ አካላቱ በመሉ ለሰብአዊ መብቶች መከበር፣ መጠበቅና መሟላት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያሳዩ ልዩ ትኩረትና ክትትል ይሻል

                    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየደረጃው ያሉ የመንግስት አስፈጻሚ አካላትና ኃላፊዎች ላይ የቅርብ ክትትል በማድረግ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር አስተዋጽኦ ሊያደር...