Thursday, March 2, 2017

ለወጣት ጥፋተኝነት መበራከት ተጠያቂው ማን ነው?



ወይዘሮ አመለወርቅ አበጋዝ በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ የ13 እና የ15 ዓመት ልጆች አሏቸው። ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያስተውሉት የልጆቻቸው ዕድገት ቢያስደስታቸውም አንድ ያስጨነቃቸው ጉዳይ ግን አለ። ይኸውም ለቤተሰብ አለመታዘዝ፣ ከማህበረሰቡ ሞራል ውጪ የሆኑ ድርጊቶችን ማከናወን እንዲሁም፣ ለጥፋት መጋበዝ አሳስቧቸዋል። ምክንያቱም በልጆቻቸው ባህሪ ላይ እንዳይከሰት ጥረት ቢያደርጉም የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው የሚያመላክተው ጉዳይ ግን ከዚህ የተለየ እየሆነባቸው ይገኛል።
በተለይም ከትምህርት ቤት ይልቅ አልባሌ ቦታ ውለው እንደሚመጡ ተገንዝበዋል። በዚህም በለጋ ዕድሜያቸው ጥፋት አጥፍተው እስር ቤት እንዳይገቡ የሚል ሃሳብ ገብቷቸዋል። በዋነኛነት ደግሞ ትልቁ ልጃቸው ከአንድም ሁለት ጊዜ በመኖሪያቸው አካባቢ በተነሳ መጠነኛ ጸብ ላይ ተሳታፊ መሆኑን በማረጋገጣቸው የልጆቹን ጸባይ የበለጠ ወደ ጥፋተኝነት እንዳይሄድ ምን ማድረግ አለብኝ? የሚለው የሚያሳስባቸው ጉዳይ ከሆነ ሰነባብቷል።
ለመሆኑ ልጆች በለጋ ዕድሜያቸው ወደ ጥፋት የሚከቱ ጉዳዮች እና ወጣት ጥፋተኝነትን ለመከላከል የሚያስችሉ ጉዳዮች ምንድን ናቸው? የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የህጻናት ጉዳይ ዳኛ የሆኑት አቶ ልዑለስላሴ ሊበን እንደሚገልፁት፤ የኢትዮጵያ የወንጀል ህግ ከ18 ዓመት በታች ያሉ ህፃናትን ለወንጀል ፍትህ አስተዳደር ሂደት ሲባል ለሦስት ምድብ ይከፍላቸዋል፡፡ በመጀመሪያ ከ9 ዓመት ዕድሜ በታች ያሉ ህፃናትን የወንጀል ኃላፊነት የሌለባቸው በመሆኑ ቤተሰቦቻቸው ወይም ሌሎች የቅርብ አካላት ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርጉላቸው እንደሚገባ ያትታል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ከዘጠኝ እስከ 15 ዓመት የዕድሜ ክልል ያሉ ህፃናት በወንጀል ውስጥ ተካፋይ ሆነው በተገኙ ጊዜ እንደወጣት አጥፊ ተቆጥረው በወንጀል ተጠያቂ እንደሚሆኑም ተደንግጓል። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ከ15 እስከ 18 ዓመት የዕድሜ ክልል ያሉ የወንጀል ኃላፊነት ያለባቸው ሲሆኑ እንደ አዋቂ ተቆጥረው በመደበኛው ፍርድ ቤት ጉዳያቸው ይዳኛል።
ከዘጠኝ ዓመት እስከ 15 ዓመት ከሆናቸው ልጆች መካከል በልደታ፣ በቦሌ፣ በጨርቆስ እና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች ላይ በዓመት እስከ 450 የሚደርሱ የወጣት ጥፋተኝነት ጉዳዮች እንደሚታዩ የሚጠቁሙት አቶ ልዑለስላሴ፤ ጉዳዩ በአገር ደረጃ ሲታይ ከፍተኛ ቁጥር እንደሚይዝ ነው የሚያስረዱት። የወንጀል ሂደት ከአዋቂዎች በተለየ ሁኔታ ጥፋቱን ሳያውቁ ወንጀለኛ የሚሆኑበትን መንገድ በመገንዘብ እና በቀላሉ ከወንጀል ሊርቁ የሚችሉበት የዕድሜ እርከን ላይ የሚገኙ በመሆኑ ቀጪ ከመሆን ይልቅ ትምህርትንና ማረምን መሠረት ያደረገ መሆኑን ይጠቁማሉ።
እንደ ህግ ባለሙያው ማብራሪያ ወጣት ጥፋተኝነት የሚከሰተው ከኢኮኖሚ ችግር የተነሳ ገንዘብ በአቋራጭ ለማግኘት ከመፈለግ እንዲሁም በማህበራዊ ጉዳይ ላይ የቤተሰብ መፍረስ ሲያጋጥም እንዲሁም ከገጠር ወደ ከተማ በሚደረግ ፍልሰት ነው። በአጠቃላይ ምክንያቶቹ ሲታዩ ልጆች አሳዳጊ ወይም ተቆጣጣሪ አካል በሚያጡበት ወቅት ችግሩ ይከሰታል። በመሆኑም ልጆች በሚኖሩበት ማህበረሰብ ውስጥ ተገቢውን ክትትል እና ድጋፍ የሚሰጥ አሳዳጊ ያስፈልጋቸዋል። ወጣት ጥፋተኝነትን ለመከላከል ደግሞ ከህጉ ይልቅ የአገሪቷ ማህበራዊ ጉዳይ ጠንካራ ሊሆን ይገባል። በዚህም አሳዳጊዎች ወይም መንግሥት ለልጆች አስፈላጊው ትምህርት እና መሰረታዊ ፍላጎቶች እንዲሟሉ ክትትል የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው። ይህ ካልሆነ ግን ጥሩ ሥነ ምግባር የላቸውም በሚባሉ ጓደኞቻቸው ጭምር እየተገፉ ጥፋት የሚፈጽሙ ወጣቶች ይበራከታሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር ዶክተር ሰጣርገው ቀናው ደግሞ፤ እንደድሮው ዘመን የወጣቶችን ባህሪ መቅረጽ የሚችሉት ትምህርት ቤቶች እና ቤተሰብ ብቻ አለመሆናቸውን ይጠቁማሉ። ኢንተርኔት እና መገናኛ ብዙኃን በወጣቶች ባህሪ ላይ ተጽዕኖ ማሳደር የሚችሉበት ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ነው የሚናገሩት። በተለይም ማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ የሚታዩ ከማህበረሰቡ ልማድ የወጡ ድርጊቶችን የያዙ መረጃዎች ሲቀረቡ ይስተዋላል። በተጨማሪም «በተለያዩ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ላይ በየዕለቱ በስፋት የሚተላለፉ ፕሮግራሞች የህብረተሰቡን ባህል እና የአኗኗር ዘይቤ ያላማከሉ በመሆናቸው ለወጣቶች ባህሪ መበላሸት ዋነኛ ምክንያት ናቸው» ይላሉ።
«መገናኛ ብዙሃን ለትውልድ የሚጠቅሙ መረጃዎችን በማስተላለፍ ለወጣቶች እንዲሁም ለአገሪቷ አጠቃላይ ህዝብ ከማይጠቅም ዘገባ መውጣት አለባቸው» የሚሉት ዶክተር ሰጣርገው፤ በዚህም ለ20 እና 30 ዓመታት በኋላ ለሚፈጠሩ ትውልዶች መሰረት የሚጥሉ አዝናኝ እና አስተማሪ መረጃዎችን በጥንቃቄ በማስተላለፍ ወጣት ጥፋተኝነትን መቀነስ ተገቢ መሆኑን ነው የሚያስረዱት። በሌላ በኩል «አንዳንድ ጥሩ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች ላይ ልጆች የቤተሰቡ አስተዳዳሪ እስኪመስሉ ድረስ ስልጣን ይሰጣቸዋል» ይላሉ።
ይህ አግባብ ካለመሆኑ የተነሳ ልቅ ነጻነት የተሰጣቸው ልጆች በአብዛኛው በወጣትነት ዕድሜያቸው ለጥፋት እንደሚጋበዙ ነው የሚናገሩት። በመሆኑም ወላጆች ለልጆቻቸው የሚያስፈልጋቸውን መምረጥ እንጂ ልጆች የጠየቁትን ሁሉ እንዲያደርጉ ልቅ ነፃነትን መስጠት የለባቸውም የሚል መከራከሪያ ያነሳሉ። ከዚህ ውስጥ ቤተሰብ ልጆች የሚጠቀሟቸውን የመገናኛ ብዙሃን ዝግጅቶች መምረጥ አንዱ ተግባር መሆኑንም ይጠቁማሉ።
የህግ ባለሙያውን እና የፍልስፍና መምህሩን ሃሳብ የሚጋሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ ልቦና መምህር ሆኑት ዶክተር ሙላት አስናቀ ናቸው፡፡ እንደ እርሳቸው ገለጻ የችግሩ መንስኤና መፍትሄዎች ላይ መመካከር ተገቢ እና በቀጣይ መፍትሄ ለማበጀት ይረዳል፡፡ በፍርድ ቤቶች የሚስተዋለው ህጻናት በፍርድ ሂደት የሥነልቦና ጫና እንዳይደርስባቸው የሚደረጉ ልዩ እንክብካቤዎች ማለትም ቤታቸው ያሉ እንዲመስላቸው የፍትህ መከታተያ ክፍሉ መዘጋጀቱ መልካም ከሚባሉ አሰራሮች ውስጥ ይመደባል፡፡ ነገር ግን ወጣት ጥፋተኞች መልሰው ወደ ወንጀል እንዳይገቡ መከላከል የሚቻልበት የእርምት አሰራሩ ጉድለት አለው፡፡ በተለይም በክልሎች ወጣት ጥፋተኞችን ከአዋቂ ጥፋተኞች ነጥሎ የእርምት ትምህርት ለመስጠት የሚረዱ ማዕከላት አልተገነቡም፡፡ በመሆኑም ጥፋተኞቹ በቀላሉ ከችግሩ እንዲወጡ ለመከላከል የማረሚያ ማዕከላቱ ግንባታ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም፡፡

No comments:

Post a Comment

Featured post

ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጠያቂነትን በማረጋገጥ፣ የሕግ በላይነትን በማስፈን፣ መንግሥትና የስራ አስፈጻሚ አካላቱ በመሉ ለሰብአዊ መብቶች መከበር፣ መጠበቅና መሟላት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያሳዩ ልዩ ትኩረትና ክትትል ይሻል

                    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየደረጃው ያሉ የመንግስት አስፈጻሚ አካላትና ኃላፊዎች ላይ የቅርብ ክትትል በማድረግ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር አስተዋጽኦ ሊያደር...