Thursday, April 5, 2018

ከቋራ እስከ መቅደላ - የአፄ ቴዎደሮስን ዱካ ተከትለን





ጊዜው ወርሃ መጋቢት 2010 ላይ መሆኑን ትዝ ይሏል።

ከቋራ እስከ መቅደላ የዘለቀውን የአፄ ቴዎድሮስን የህይወት ዘመን እግር በእግር እየተከተልን ለማስታወስ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ አዋጅ አስነገረ። እኔም የጉዞው አካል ለመሆን በመቻሌ ጓዜን ሸክፌ ተነስቻለሁ። ኮስትር የሚባለው መኪና ውስጥ ነኝ።


ጎንደር ጎንደር የቴዎድሮስ አገር
ያንዲት ኢትዮጵያ ዋልታና ማገር
ነፍሱን የሰጣት ለካ ዓለም ንቆ
አገር ሊያቆም ነው ቴዎድሮስ ወድቆ

እያለ የተቀኘላትን የቴዎድሮስ ካሳሁንን ሙዚቃ እያዳመጥኩ ጉዞዬን ወደሰሜን አድርጌያለሁ። መኪናዋ ውስጥ 17 ሰዎች ተሰባስበናል። የአፄ ቴዎድሮስ ህልፈተ ህይወት 150ኛ ዓመት ክብረ በዓል ጋር ተያይዞ ጉብኝቶችን ልናካሂድ ነው።ታሪካዊው ጉብኝት ከካሳንችስ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ እንግዳ ማረፊያ አካባቢ ተጀምሯል። ከአዲስ አበባ እንደወጣን መኪናዋ ውስጥ የነበሩ ከተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን የተውጣጡ ባለሙያዎች የሚያነሷቸው ቀልዶች የረጅሙን መንገድ ጎዞ ከአሰልቺነት አላቀውታል።ሱሉልታን፣ ደርበ ጉራቻን እና ፍቼ ከተሞችን እንዳለፍን የአባይ ወንዝ ድልድይን ለመመልከት መውረዳችን አልቀረም። የጃፓንን ድንቅ ቴክኖሎጂ የታየበትን የአባይ ተንጠልጣይ ድልድይ በአይናችንም እያየን በካሜራም እየቀረጽን ስንጓዝ የበረሃውን ሃሩር ሳናስታውሰው አለፈ።


የሆድ ነገር ሆድ ይቆርጣል ነውና ቢሞረሙረን ጊዜ ምሳችንን ደብረማርቆስ ላይ ካደረግን በኋላ ገስግሰን ባህር ዳር ከተማ ገባን። አዳር በጣና ሐይቅ ዙሪያ በተገነባችው ከተማ ላይ አለፈ። በነጋታው በእንቦጭ አረም ሲመጠጥ የከረመውን የአገሬን ሐይቅን ለማየት ማልጄ ተነስቻለሁ። በውሃው ላይ ተንሳፎ በተሰራው ጣይቱ መዝናኛ ላይ ሆኜ ሳየው የሐይቁ ግርማ ሞገስ አስደምሞኛል። የአባይን ልጅ ውሃ ጠማው ብቻ ሳይሆን የጣናንም ልጅ ውሃ ጠማው የሚያሰኝ ሃብት በጉያችን ይዘን ንጹ የመጠጥ ውሃ የማይደርስባቸው ገጠራማ ቦታዎችን በሃይቁ ዙሪያ መኖራቸውን ሳስብው ግን በቦታው ብዙ ለመቆየት ሞራል አነሰኝ።


የጉዞውን ሁለተኛ ቀን ወደ ጎንደር ነበርና ባህር ዳርን ከጀርባችን ትተን ቋላ ዮሐንስን፣ ጎርጎራን እና ሌሎችንም አካባቢዎች አልፈን አመሻሽ ላይ ከተማዋ ስንገባ በያለንበት ወደ ማረፊያችን ተበታተንን። ከእንቅልፍ መልስ የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ከአስር የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመሆን በአስተባባሪነት ስለሚመራው የጉዞ እቅድ እና አላማ በግቢው ተገኝተን መረጃ ወሰድን። ጎንደር ውብ ናት ብቻ ሳይሆን ውብ ታሪክ አቅፋ ይዛለች። በተለይ ጥንታዊ ሰፈሮቿ መሃል ከተገኙ የኪነህንጻ ውበት ያረፈባቸው ከድንጋይና ኖራ የተገነቡ ሃይማኖታዊ ቦታዎች፣ የነገስታት መኖሪያዎች እና ማረፊያዎችን ይመለከታሉ።




አጼ ቴዎድሮስ /ካሳ ኃይሉ/


ከተማዋ የቱሪስቶች መዳረሻ ከሆኑት አንዱ የአፄ ፋሲልን መዋኛ ግቢ ማለትም የጥምቀተ ባህሩን ነው። ከዲዛይኑ ጀምሮ እስከ ፍሳሽ ማስወገጃው የዘመኑን ስልጣኔ ምጡቅነት አሳይቶኛል። ግቢው ውስጥ መዋኛ ገንዳው መሃል ላይ ባለሁለት ወለል ህንጻ በፋሲል ግንብ ኪነህጻ ተውቦ ቆሟል። በግምት ሰላሳ ሜትር በሰላሳ ሜትር የሚሆነው መዋኛው ሶስት ሜትር የሚሆን ጥልቀት አለው። ግቢው በረጃጅምና እድሜ ጠገብ ዋርካዎች የተሞላ ከመሆኑ የተነሳ ቦታውን ከግዙፍ ጃንጥላዎች የተከበበ አስመስሎታል። በጣም የሚገረመው ግን የመዋኛው የውሃ አወራረድ ንድፍ ነው። በጊዜው ገንዳው ውሃ የሚያገኘው በአቅራቢያው ካለው ወንዝ ሲሆን ውሃውም በግቢው ካለፈ በኋላ ተመልሶ ወደ ወንዙ የሚገባበት የመሬት ውስጥ ማስተንፈሻ ተዘጋጅቶለታል። ይህም ውሃው እንዳይባክን መልሶ ጥቅም ላይ የማዋል ቴክኖሎጂ ቀድሞም የነበረ መሆኑን ያሳያል።



ስለጎንደር ሲነሳ ነዋሪዎቿ ኪነህንጻ ብቻ ሳይሆን ወግ መጠረቅም ያውቁበታል። በቅርቡ በተካሄደው የከተሞች መድረክ ላይ ጎንደር የከተሞች እናት እያሉ ሲያቆላምጧት ነበር። ይህን የሰሙ እንዴት እናት ትባላለች ሌላውስ ብለው ቢጠይቁ የከተማዋ ከንቲባ የነበሩ ሰው ሌላውን ከተማ የከተሞች አያት፣ ቅድመ አያት እና አባት ብሎ መሰም እየቻለ እንዲህ አይነት ወግ መነሳቱ ያስገረማል የሚል አስገራሚ መልስ መስጠታቸውን የጎንደሩ ፋና ኤፍ ኤም ጋዜጠኛ ዋሴ አጫወቶኛል።


ጎንደርን ጎብኝቼ ልጠግባት ባልችልም የዘመኑን ስልጣኔ በየመንገዱ እያስተዋልኩ ወደ አልጋዬ አመራሁ። ወፍ ሲንጫጫ ጉዞ ወደ ቋራ ይደረጋል የሚል ቀጠሮ በመያዙ ከዩኒቨርሲዎች ከተውጣጡ መምህራን ተቀላቅለውን መኪኖች ወደ ቋራ በረሃ አመሩ። በጉዞው ወቅት የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የታሪክና ቅርስ አስተዳደር ተማሪዎች በመካተታቸው የሃገርህን እወቅ ጉዞ መንፈስ ሰፍኗል።


የቋራ በረሃማ አካባቢዎች የአስፓልት መንገድ ባይገነባላቸውም በጥርጊያው መንገድ ላይ ተጓዡን በሰላም አገር እያመላለሱት ይገኛል። ከመንገድ ዳርና ዳር የቆሙት ዛፎች የነጭ እጣን መፍለቂያ መሆናቸውን ለተመለከተ ደግሞ መሬት ለሁሉም እንደየመጠኑ የሚያስፈልገውን ሃብት አድላዋለች ወደሚል ድምዳሜ ላይ ይወስዳል። ከጎንደር 300 ኪሎ ሜትሮችን ተጉዘን ምሽቱን ቆላማው አካባቢ ቋራ እንደደረስን በአማራ፣ በአገው፣ በጉሙዝ እንዲሁም በቅማንት የአጨፋፈር ስልቶች የደመቁ ወጣቶች አቀባበል አደረጉ። ህዝቡ ከጫፍ እስከ ጫፍ ወጥቶ በሆታ እና በጭፈራ እንግዶቹን ተቀበለ። በወጣቶች ጭፈራ ከደመቁ ቦታዎች የሚነሱ ብናኞችን በመኪኖች የፊት መብራት ታጅቦ ለሚመለከት ታዛቢ ከመሬት የሚነሱ የእንፋሎት ትናኞች ወደሰማይ የሚውረገረጉ ይመስለው እንደሁ እንጂ የከተማዋ አቧራ እየጎነ ስለመሆኑ ሊጠራጠረ ይከጅለዋል።


በዚህች ታሪካዊ ቋራ ላይ ነው ጥር 6 ቀን 1811 ዓ.ም ሻርጌ በተባለ ቦታ አፄ ቴዎድሮስ የተወለዱት። በወቅቱ አገሪቷ በጦረኞች ተከፋፍላ ስለነበር ዘመኑ የመሳፍንታት የበላይነት የነገሰበት ነበር። አባታቸው ደጃዝማች ኃይሉ ወልደጊዮርጊስም የቋራ ገዢ ነበሩ። ቋራ አሁን ላይ ከ30 ዲግሪ ሴለሺየስ በላይ በመሆኗ ትወብቃለች። ማታ ላይ ሙቀቱ ቢቀንስም ለደጋ አካባቢ ነዋሪዎች ግን እስኪላመዱት ወዲያው ወዲያው ውሃ ውሃ ታሰኛለች። በመሆኑም በከተማዋ የሚገኙ መኝታ ቤቶች በአብዛኛው የንፋስ መዘወሪያ /ቬንተሌተር/ የተገጠመላቸው ናቸው።


እኔም ቋራ ላይ ሙቀቱን ለመቆጣጠር እራቁቴን አንሶላ እንደለበስኩ መተኛት የግድ ሆነብኝ። የተወሰኑ ሰዎች ደግሞ ከቤት ውጪ አልጋ አዘጋጅተው ንፋሱን እየሳቡ ማንኮራፋታቸውን ቀጥለዋል። ድንገት አንድ ነገር ትዝ አለኝ። በቋራ ጉዞ ወቅት መኪና ውስጥ እያለን ለሽንት ስንወርድ እባብ እና ጊንጥ ስላሚኖር እያስተዋላችሁ የሚል ማስጠነቀቂያ አዘል መልዕክት ተላልፏል። እናም ከአልጋዬ ወርጄ የማደሪያዬን ዙሪያ ገባውን ከቃኘሁ በኋላ ጫማዬን አንዱን በአንዱ ላይ ደፍቼ አደርኩ። ይህ ማድረጌ ሌሊት ላይ ጊንጡ ገብቶ እንዳያድር ነበር። ጠዋትም ስነሳ ልብሶቼን እና ጫማዬን በደንብ ማራገፉን ማንም አልቀደመኝም።


ቋራ የብዙ እንስሳቶች መኖሪያ ቦታ ናት። በወረዳው ውስጥ ብርቅዬ አዕዋፋትን እና እንስሳትን የያዘውን አልጣሽ ብሔራዊ ፓርክን እናገኘዋለን። አልጣሽ በአፍሪካ ዝርያው እየጠፋ ነው የሚባለው ባለጥቁር ጎፈሬው አንበሳ የያዘ ብሔራዊ ፓርክ ነው። ፓርኩ ከሱዳን ጋር ድንበር የሚጋራ በመሆኑ በርካታ ጊዜያትን በአርብቶ አደሮች አማካኝነት ጥቃት እንደሚደርስበት ሲነገር ቆይቷን አሁን ላይ ግን በተደረገለት እንክብካቤ አደጋ ላይ ወድቋል ከሚል መዝገበ ስሙ ተፍቆ በርካቶች ለመቆብኘት የሚመኙለት ቦታ ሆኗል። የአካባቢው ደካማ መሰረተ ልማትፓርኩን ለመጎብኘተ ለሚፈለጉ የሰማይ ያህል እንዲረቃቸው ያደረጋል።


ቋራን ተሰነባብተን ለመሄድ ሁሉም በየመኪናው ከቷል። ጉዞ ወደ ገንዳ ውሃ ወይም በቀደሞ ስሟ ሸኅዲ ነው። ከዚያም በሳራባት እና አይከል ከተሞች አድርገን ፀሃይ ስትገባ ጎንደር ደረስን። በቀጣዩ ቀን ጉዞ አፄ ቴዎደሮስ የልጅነታቸው ትምህርት የተማሩበት አገር ቸንከር /ቸርገር ተክለሃይማኖት/ ተደረገ። ቸርገር ተክለሃይማኖት የአፄ ቴዎድሮስ የዲቁና የሃይማኖት ትምህርት የጀመረበት ቦታ ነው። ቸርገር ያሉ የሐይማኖት አባቶች እንደሚናገሩት አፄ ቴዎደሮስ በልጅነታቸው ካሳ ኃይሉ በሚባሉበት ወቅት ህጻናትን ሰብስበው በአህያ ላይ ተቀመጠው አጅቡኝ ሆ በሉ እያሉ ያዙ ነበር። ይህም የመሪነት ባህሪ ከልጅነታቸው ጀምሮ የነበረ መሆኑን እንደሚያሳይም ይናገራሉ። ከዚያም ኩራባስ እና ጉራምባ ላይ የነበረውን የአፄ ቴዎድሮስን ጦረኛነት በዘመን ትውስታ ስንጎበኝ አለፋ ጣቁሳ ደልጊ ማርያም ላይ የንጉሱን ዘመድ አዝማዶች ማግኘታችን አልቀረም። የዳሞቱ መስፍን ደጃዝማች ጎሹንም በ1845 ዓ.ም ጉራምባ ላይ ጦርነት ገጥመው ድል አድርገው የንግስና ጉዟቸውን ወደፊት አስቀጥለውበታል። ደልጊ ማርያም ላይ ንጉሱ ያበረከቱት እፀ መስቀል እና ጸሎት የተማሩበት የብራና መጽሃፍ /ዳዊት/ ይገኛል። የታሪክ ማህደሩን ከሃይማኖት አባቶች እና ከባህልና ቱሪዝም ባለሙያዎቸ ከተረዳን በኋላ የንግስና አክሊል ወደ ደፉበት ደረስጌ ማርያም አቀናን።


ደረስጌ ማርያምን ለማግኘት የሰሜን ተራሮችን ብሔራዊ ፓርክ አቋርጠን ማለፍ ይኖርብናል። ዋልያን እና ሚዷቋን እንዲሁም ጭላዳ ዝንጀሮን በየመንገዳችን እየጎበኘን የቀዝቃዛው አካባቢ ተጽዕኖ ለመቋቋም የመኪናችንን መስኮቶች ጥርቅም አድርገን ዘግተናል። ፓርኩ ከእንስሳቶቹ በተጨማሪ የጅብራ ዛፎቹ የቦታው ማድመቂያ ናቸው። አስቸጋሪውን ጠመዝማዛ መንገድ እንጨረስን ደረስጌ ላይ ደረስን። ደረስጌ ማርያም ደጃች ውቤ እራሳቸውን ለማንገስ አቅደው ያሰሩት ውብ ቤተክርስቲያን ነው። አካባቢው ላይ አሁንም ድረስ ተወዳጁ ሰው ደጃች ውቤ ናቸው።


ነዋሪዎች አፄ ቴዎድሮስ አቡነ ሰላማን ከግብጽ አስመጥተው በአቋራጭ ባይቀደሟቸው የሚመሩት ደጃች ውቤ መሆናቸውን እያስታወሱ በቁጭት ያወራሉ። የደርስጌ ማርያም ቤተክርስቲያን በውስጧ ከደጃች ውቤ እና አፄ ቴዎደሮስ ጋር የተያያዙ በርካታ አስደናቂ ቅርሶችን ይዛለች። የብራና መጽሃፍት፣ የወርቅ ከበሮ እና የወርቅ መስቀሎችን በአይንዎ አየተው ሳይጨርሱ በስዕል ያጌጡ የብር ከበሮ እና መስቀሎችን ፊት ለፊትዎ ማየት ምንኛ አስደሳች ነው። አጼ ቴዎድሮስ ንግስናቸውን ያወጁበት ሰገነት እና18 የፈረስ ጉልበት እንዳለው የሚነገርለት ግዙፍ ደወልም በቦታው ይገኛል። በእንቁ የተጌጡ ካባዎቸ እና የቀንድ ዋንጫዎቸ የንጉሳውያን ቤተሰቦች ዘመንን የሚያስታውሱ የአገሪቷ ውድ የኢትዮጵያ ቅርሶች ናቸው።


ቅርሶቹን ላየም እንዳይዘረፉ በጥብቅ ሚስጥራዊ ስፍራ እንዲቀመጡ መመኘቱ አይቀርም። የደብሩ ቀሳውስት ጠንቃቃ በመሆናቸው ንብረቶቹ እስከአሁን በስድስት ታጣቂዎች እየተጠበቁ እንዲቆዩ ቢያደርጉም ስለቀጣይ ደህንነታቸው ግን አስተማማኝ ጉዳይ አይታይም። እነዚያን የአለም ህዝብ ሊጠብቃቸው የሚገቡ ቅርሶች በደሳሳ የጭቃ ቤት ውስጥ ታጉረዋል።ሁሉም ጎብኚም ሆነ ህብረተሰቡ በአንድነት የተስማማበት ጉዳይ ደረስጌ ዘመናዊ ሙዚየም የሚያስፈልጋት የቅርስ ጓዷ መሆኗን ነው።


ከደረስጌ በቀጥታ ወደ ደብረ ታቦር ልውሰዳችሁ። ቦታው በንጉሱ ዘመን ጋፋት የተባለው የመጀመሪያው የአገሪቷ ኢንዱስትሪ መንደር የተገነባበት እንደሆነ ታሪክ ያስረዳናል። ጋፋት የሴባስቶፖል መድፍ እና የዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች መፍለቂያ በመሆኑ ሲታወስ ይኖራል። በወቅቱ ንጉሱ እንግሊዛውያንን ብረት አቅልጠው መሳሪያ እንዲያዘጋጁ ያቋቋሙትና የብረት ማዕድን የሚገኝበት ቦታ ነው። ከዚህ በኋላ አፄ ቴዎደሮስ መድፉን ወደ መቅደላ አምባ ለመውሰድ መንገድ አስጠረገው በሰው ኃይል እያስጎተቱ መንገዳቸውን ተያያዙት። እኛም በአይነ ህሊናችን እያስታወስን ከጎንደር ንፋስ መውጫን እና ጨጨሆን አልፈን በወልዲያ አድርገን ደቡብ ወሎ መቅደላ ገባን። ዘመናዊ የትራንስፖርት አማራጭ በማይታሰብበት ወቅት ይህን ሁሉ ለአገር መሪነት አፄ ቴዎደሮስ መጓዝ መቻላቸው የታሪኩ አስደናቂ አካል ነው።


መቅደላ አምባ ለጦርነት የሚያመች ቦታ በመሆኑ ወራሪውን የአንግሊዝ ጦር ድባቅ ለመምታት የተለያዩ መደፎች ተተክለዋል። እንግሊዝ ቅርሶቹን ዘርፎ ይወደመው መድሃኒያለም ቤተክርስቲያንም የድንጋይ ካብ ፍርስራሽ ብቻ ይታይበታል። ቦታው አሁን ላይ ለቅርሰ የሚሰጠውን ያህል ትኩረት ባያገኝም ታሪክን በኩራት ይናገራል። የንጉሱ ግምጃ ቤት እና መቃብር እና መድፎቹ እንዲሁም የተዋጉባቸው ቦታዎች ዛሬም ለትውልድ የሚያስተላልፉት የአንድነት መልዕክት አለ። ከጎንደር ቋራ እስከ ደልጊ፣ ከማህበረ ስላሴ እስከ ደረስጌ ማርያም፣ ከጎንደር እስከ ጋፋት፣ ከሰሜን ሸዋ አንኮበር እስከ አንጎለላ፣ ከደንቢያ እስከ መቅደላ ወሎ ድረስ የዘለቀው የአፄ ቴዎድሮስ የታሪክ ጉዞ የሚያስረዳን ህልማችን ሰፊ መሆን እንዳለበት በተግባር የሚያስተምር የታሪክ ማህደር ነው። በመሆኑም በሰሜን፣ በደቡብ፣ በምስራቅም በምዕራብም ያለውን የአገራችን ታሪክ ማወቅ፣ መጠበቅና መጠቀም ይገባናል እላለሁ። ቸር እንሰንብት

Wednesday, April 4, 2018

ጉራጌ - ህዝብ የዕርቅ ስርዓትና ባህል


ባህል የአንድን ማህበረሰብ የእምነት ፍልስፍና ጥበብ የአስተሳሰብ እሴቶች ያካተተ ነው። ውስብስቡ እሳቤ በቁሳዊ ባህሎቹ እና ልማዶቹ በማህበራዊ ግንኙነቶቹ እና በተለያዩ ትውፊቶቹ አማካኝነት ተጨባጭ አሰራር ይኖረዋል። በደቡብ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ክልል የሚገኘው የጉራጌ ብሔርም በ13 ወረዳዎች እና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች ማለትም ቡታጅራ እና ወልቂጤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የማህበረሰቡ አባላትን ይዟል። የጉራጌ ህዝብ ቆጠራ በብዙዎች ዘንድ አለመግባባትን ይፈጥራል ምክንያቱም አብዛኛዎቹ ተወላጆች በተለያዩ ከተሞች በመሄድ ኑሯቸውን የሚመሩ በመሆናቸው ህዝቡ በአራቱም አቅጣጫ ተበትኖ ይገኛል። በቀዬአቸው የቆዩ የብሔሩ ተወላጆችም የባህላቸው መገለጫ የሆኑ የቤት አሰራረሮችን እና የመንደር አመሰራረቶችን እየተከተሉ ለዘመናት ቆይተዋል። ከሁሉም ባለፈ ግን የጉራጌ ህዝበ ራሱን የሚያስተዳድርባቸው ባህላዊ የፍትህ ስርዓት የሚያከናውኑ ሸነጎዎች ባለቤት ነው።
        የጉራጌ ተወላጁ የህግ ባለሙያው አቶ ሰለሞን አሸናፊ እንደሚገልፁት፤ ከጉራጌ ዞን ወረዳዎች መካከል የሰባት ቤቱ የጀካ፣ የመስቃኑ ፈርአገዘኘ፣ የዶቢው ስናኖ እንዲሁም ጎረደና በሚል ስያሜ የሚጠራው የገደባኖ ጉታዘር ወለኔ እና የሶዶ ጉራጌ ሸነጎዎች በርካታ ጎብኚዎችን ኢትዮጵያ የቆየ የህግ አሰራረ አላት ብለው እንዲያምኑ ያስገደደ ባህሎች ናቸው። ስዬሜያቸው እንደየወረዳው ቢለያይም ተመሳሳይ የሸነጎ አሰራርን ይከተላሉ። አላማቸውም ተተኪውን ትውልድ በስነምግባር ከማነጽ ጀምሮ ግጭቶች ዳግም እንዳያገረሹ የማድረቅ አቅም አለው።                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                                  
        የቤተ ጉራጌ ባህላዊሸንጎ ስርአት በ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እንደተጀመረ ታሪክ ያስረዳል የሚሉት አቶ ሰለሞን፤ ማህበረሰቡ በመረዳዳት እና መፈቃቀር ላይ በተመሰረተ አኗኗረ ለረጅም ዘመናት እንዲጓዘ እንዳገዘው ምስክርነት ይሰጣሉ። በተጨማሪ የሸንጎው አሰራር የአካባቢውን ልማት በማፋጠን ነዋሪዎችን ለማስተባበር ጥቅም ላይ እንደሚውል ይናገራሉ።
              
ሸንጎው ችግሮቹ የሚፈቱለት እና የሚፈርዱለት ዳኛ ወይም የሴራ ዳነ በሚባሉ አካላት አሉት። በፍትህ አሰጣጣቸውና፣ በአስተዋይነታቸው የተመረጡ ሽማግሌዎች ለቦታው በእጩነት ይቀርባሉ። በህዝብ ተቀባይነት ያለው እና የፍርድ አሰጣጡም የማያሻማ በሆኑ አካላት ላይ ጥብቅ ፍተሻ ተደርጎ ለቦታው ሹመት ይሰጣል።
 የጉራጌ ብሔረሰብ ከወረዳ ወረዳ ወይም ከአካባቢ አከባባቢ እንደ ዘዬው ለዩነት የተለያየ የስም አሰጣጥ ቢኖረውም የሚተዳደሩበት የሸንጎ ደንብና ህግ ግን መሰረታዊ ለውጥ አይታይበትም። ከሸንጎዎቹ የህግ አፈጻጸም አንፃርም የጉራጌ ባህላዊ የመተዳደሪያ ደንቦች መሆናቸው ተጠቅሶ በዋናነት ህዝቡ የሚተዳደርባቸው አራት ናቸው።
  አንደኛው <<የኧጆካ ቕጫ>> የተሰኘው የሰባት ቤት ጉራጌ የባህላዊ ሸንጎ መተዳደሪያ ደንብ ሲሆን ሁለተኛው <<የጎርደና ሴራ>> የተባለው የክስታኔ እና የወለኔ ቤተ-ጉራጌዎች ባህላዊ የመተዳደሪያ ደንብ ነው። በሶስተኛነት ደግሞ <<የፈር አገዘኘ ሴራ>> የተባለው የመስቃን ቤተ-ጉራጌ የባህላዊ ሸንጎ መተዳደሪያ ደንብ ሲሆን አራተኛው <<የዶቢ ጎጎት ስናኖ ሴራ>> ማለትም የዶቢ ቤተ-ጉራጌ የባህላዊ ሸንጎ መተዳደሪያ ደንብ ሆኖ ያገለግላል።
የሸንጎዎቹ መተዳደሪያ ደንቦች በውስጣቸው የተለያዩ ህጎችን አጭቀው ይዘዋል። የሚሉት ደግሞ የጉራጌ ባህል ልማት ማህበር የባህል ልማት ሃላፊው አቶ መንግስቱ  111 ናቸው። ለአብነት የሰባት ቤት ጉራጌ ባህላዊ ሸንጎን የኧጆካ ምልከታ ቢደረግ መተዳደሪያ ህጉ በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተዋቀረ ነው። በሸንጎው ንዑስ ክፍል ውስጥ የጥብ /የጎሳ/ መተዳደሪያ ህግ ተቀምጧል።  
   በአንድ ወረዳ ውስጥ በርካታ ጎሳዎች ስለሚኖሩ የእያንዳንዱ ጎሳ  ከሌሎች ጎሳዎች ጋር ወይም በእራሱ ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፈታት ይረዳል። በአስተዋይነታቸው በተመሰከረላቸውና በተመረጡ የጎሳው አበቃጥ ወይም የጎሳ መሪ አማካኝነት የሸንጎ አፈታት ይካሄድበታል።
የባህላዊ ሸንጎው በጎሳው አባላት ውስጥ የሚከሰቱ የንብረት ጥፋቶችን፣ የቤት ቃጠሎዎችን፣ የንብረት አለመግባባቶችን እና ከሌላ ጎሳ ጋር የተፈጠሩ ማህበራዊ ችግሮች ከበድ ያሉ የመሬት ይዞታ ክርክሮችን ለመፈታት ያገለግላል። ከመደበባው የአገሪቷ ህግ ጋር ባልተጣረሰ ሁኔታም ግጭቶችን በመፍታት የባሰ ማህበረሰባዊ ቀውስ እነዳይከሰት የበኩሉት አበርክቷል። ችግሩን በጋራ በመምከር የሚፈቱበትና አስፈላጊ የእርምት እርምጃ የሚወሰድበት ማህበረሰባዊ ተቋም ሲሆን በመላ የጎሳ አባላት ይሁንታ ያገኘው መሪ የባህላዊ ዳኝነት ስርዓቱን በማስፈፀም አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ እነዲወሰድ ያዛል። በመሆኑም የጊሳ አባላቱ ፍርዱን ወይም ትዕዛዙን በይሁንታነት አምነው ይቀበላሉ።
 
በተለያዩ የሸንጎ ምክር ቤቶች ያልተፈታ ችግረ ያለው አካልም ጉዳዩን ለበላይ የሚያቀርበበት ባህላዊ አሰራር አለው። የጉራጌ ቕጫ ምክር ቤት በባህላዊው አስተዳደር መሰረት የመጨረሻ አካል ተደረጎ ይወሰዳል። የጉራጌ ቕጫ ምክር ቤት የሁሉም የዳኝነት ስርዓት አካላት አስፈፃሚ የበላይና የመጨረሻ ይግባኝ ሰሚ አካል በመሆኑ ከተለያዩ የጎሳ እና ብሔረሰብ አካላት የተዋቀረ ነው። ባህላዊ ምክር ቤቱ በአብዛኛው ጊዜ በተለያዩ ጎሳዎች መካከል የሚነሱ ደም ያፋሰሱ ግጭቶችን በመፍታት ልምድ አካብቷል። በትርጉም አረዳድ እና በተለያዩ ምክንያቶች የሃሳብ መከፋፈል በምክር ቤቱ ሲያጋጥምም
የቕጫ ምክር ቤት ሰብሳቢው በሚያሰይሟቸው የተከበሩ ሽማግሌዎች አማካኝነት ውሳኔ እንዲሰጥ ይደረጋል። የባህላዊ ምክር ቤቱ ሰብሳቢ የሚሰየመው በጠቅላላ ጉባኤ ወቅት ሲሆን የስልጣን ዘመኑም የሚቆየው በተሰየመበት ወቅት በዋለው ሸንጎ የተነሱ ጉዳዮች
 
 ተጠናቀው እልባት እስከሚያገኙበት ጊዜ ድረስ ይሆናል። በአብዛኛውም የሰብሳቢው የስራ ዘመን ለረዥም አመታት የሚቀጥል በመሆኑ ረጅም ዘመናትን በቆየ መጠን ጣዕሙ እነደሚጨምር ወይን በልምድ እና በብልሃት እንደሚጨምር ይታመንበታል።  
  ጉራጌ በባህሉ የደም ብቀላ /መገዳደል/ የሚያስከትለው ጥፋት አደገኛ መሆኑና ዘርን እንደሚጨርስ ያምናል፡፡ ይጠየፋልም ስለሆነም ግድያ እንዳይፈፀም ከፍተኛ የመከላከል ጥረት ያደርጋል፡፡ ግድያ ከተፈፀመም እንዳይቀጥል /በትውልድ  እንዳይደጋገም/ ደም በቕጫ ስርዓት መሰረት እንዲያልቅ ይደረጋል፡፡ በቕጫ መሰረት እንዲያልቅ ካልተደረገ ግን የሚያስከትለው መዘዝ መጥፎ እንደሚሆን ይታመናል፡፡ ስለሆነም እያንዳንዱ የደም ጉዳይ መንስኤውና አገዳደሉን መሰረት ያደረገ ካሳ ይከፈላል። በገዳዩና በሟች ዘመዶች መሃል የነበረው መፈላለግና ቁርሾ አብቅቶ ሠላም ወርዶ እንደማንኛውም ሰው ሠላማዊ ህይወት መምራታቸውን ይቀጥላሉ፡፡
        በጉራጌዎች ባህላዊ ህግ መሰረት የደም አፋሳሽ ግጭት አይነቶች በሶስት ደረጃዎች ይከፈላሉ። አንደዳው  ሙራ ደም ወይም የግፍ አገዳደል ተበሎ የያዛል።  በህጉ መሰረት አንድን ሰው ሆን ብሎ በግፍ የገደለ በሙራ ደም ስርዓት መሰረት 30 ሺ ብር አሊያም ከዚያ በላይ የደም ካሳ መክፈል እንደሚገባው የብሔሩ ባህላዊ መቅጫ ህግ ይደነግጋል። በሌላ በኩል በስህተት ግድያ ከተፈጸመ መዳራ ይባላል። መዳራ ማለት ባለማወቅ የተፈጸመ እና ገዳይ እና ሟች የከረረ ፀብ እንደሌላቸው የሚያሳይ የክስ አይነት ነው። በመዳራ መሰረት ጥፋተኛ 15 ሺ ብር የደም ካሳ በመክፈል ከሟቸ ቤተሰቦች ጋር እርቅ ያወርዳል። ሶስተታው ደግሞ የመዳራ መዳራ ወይም በፍፁም ስህተት የተፈፀመ ግድያ የሚባለው ወነጀል ነው። በፍፁም አለማወቅ የተፈጸመ ወንጀል በመሆኑም ቅጣቱ ይቀልለታል። ደም ማፍሰሱ በፍፁም ስህተት የተፈፀመ ከሆነ ተጣርቶ ጥፋተኛው ሰባት ሺ አምስተ መቶ ብር እንዲቀፍል ይታዘዛል።ከዚህ በኋላ ደም መላሽ ወይም በቀላ የሚባል ጉዳይ አይነሳም በአንድነት ህይወት ተቀጥላለች።
        ክስታኔና የወለኔ ቤተ-ጉራጌዎች ባህላዊ ሸንጎ (የጎርደና ሴራ) መሰረት ደግሞ
በወማኖ /ጉታቻ ሴራ/ በተባለው ህግ መሰረት አንድ ሰው የግድያ ወንጀል ከፈጸመ ላልተወሰነ ጊዜ አካባቢውን ለቆ ይሰደዳል፣ ቤተሰቡም ይበተናል። ምክንያቱም በአካባቢው ከቆየና ቤተሰቡም ካልተበተነ ተጨማሪ ደግ አፋሳሽ የጨተገባር ሊፈጸም ይችላል ከሚል እሳቤ ነው። ከጥቂት ዓመታት የስደት ኑሮ በኋላ የሚታወቁ ሽማግሌዎች ካህናትና ዲያቆናት ጋር በመሆን ሰባት ልጃገረዶችና ጎረምሶች በማስከተል የቤተክርስቲያን መረዋ እየተደወለ ቃጭል እየተቃጨለ ወደ ሟች ቤተ ዘመዶች ይኬዳል። ከተደጋጋሚ ልመና በኋላ ለእርቁ የእሺታ መልሳቸውን ሲሰጥ የእርቅ ስነስርአት ለማከናወን የሁለቱን ወገን ስምምነት ያገሹ የአገር ሽማግሌዎች ይሰየማሉ።
        የአገሬው ሸንጎ ግድያው ሳይታሰብ የተፈጠረ መሆኑን አሊያም በቂም በቀል መሆን አለመሆኑን አጣርቶ በገዳይ ወገን የሚከፈል የደም ካሳ በመወሰን የእርቅ ስርዓት ይፈጸማል።
        የእርቅ ስነ-ስርዓት ከተከናወነ በኋላ ሁለቱ ወገኖች ፍፁም ቂም እንዳይዙ ጉዳ ባህል መፈፀም የተለመደ ሲሆን በጉዳው ስነ-ስርዓት ላይ ጥቁር ፍየል ታርዶ ከሁለቱም ወገኖች አንዳንድ ሰዎች ተመርጠው አውራ ጣቶቻቸው በፍየሉ አንጀት ታስሮ ይቋጠራል። ይህም ጉዳ የተያያዙ ሰዎች የጠላትንት ስሜትን አስወግደው በመሃላቸው ሰላም ያሰፍናል ተብሎ ስለሚታመን ነው። በመሆኑም ከዚያች ቀን በኋላ እንደ ጠላት እና ደመኛ መተያየት ያበቃለታል። የቤተጉራጌ የሸንጎ ባህል እና ግጭት አፈታት ተዝቆ የማያልቅ ሃብት ያለው በመሆኑ ከብሔሩ አልፎ ለአገር የሚተርፍ መልካም ስርዓትን ማስተላለፍ የሚያስችል አቅም አለው። በመሆኑም በሸንጎው ስርዓት ላይ ሰፊ ጠናት እና ምርምር ማድረግ ከታሪክ ተመራማሪዎች ይጠበቃል።

Featured post

ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጠያቂነትን በማረጋገጥ፣ የሕግ በላይነትን በማስፈን፣ መንግሥትና የስራ አስፈጻሚ አካላቱ በመሉ ለሰብአዊ መብቶች መከበር፣ መጠበቅና መሟላት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያሳዩ ልዩ ትኩረትና ክትትል ይሻል

                    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየደረጃው ያሉ የመንግስት አስፈጻሚ አካላትና ኃላፊዎች ላይ የቅርብ ክትትል በማድረግ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር አስተዋጽኦ ሊያደር...