ልክ
በኦሮሚያ ጃርሱማ እና ገዳ ስርአት፣ በወሎ
አባጋር እና ቅሬ፣ በትግራይ ዕርቂ እንደርታ
እና ቃንጪ፣ በጉራጌ ኪቻ፣ በጋምቤላ አኝዋ
ኦኩድሆ፣ በአፋር ሚዳ እንዲሁም በአማራ
ሽምግልና፣ ደም አዳራቂ፣ ዘመድ ዳኛ፣ አዉጫጭኝ
እና ወፋ የሚባሉ የእርቅ አይነቶች ለመዘናት
ግጭቶችን በማድረቅ ለአርሶአደሩ እፎይታን
ሲሰጡ የቆዩ ባለውለታ ናቸው። በአማራ ክልል
መንዝ ቀያ ገብርኤል ወረዳ ያሉ የተለያዩ
ባህላዊ ስርዓቶችም ግጭትን የሚከላከሉ፣
ከተከሰተ ብኋላ የሚፈቱ እና ከስሩ የሚያደርቁ
በመሆናቸው ኢትዮጵያን ሀገር በቀል የግጭት
አፈታት ስረዓቶች ባለቤት ካደረጓት ባህሎች
መካከል ናቸው።
በወሎ ዩኒቨርሲቲ ፖለቲካል ሳይንስና አለምአቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህሩ
አቶ ጋሻዉ አይፈራም በተለይ በመንዝ የተለያዩ
ቦታወች ማለትም በጃማን፣ በመርሀቤቴን፣
በጅሁር እና የላይኛዉም የመንዝ ክፍል የሚያገናኝ
ታሪካዊ ቦታ በሆነው በዘረት የሀገር በቀል
ግጭት አፈታት ላይ ጥናት አድርገዋል። ቅሬ
፣ የዘመድ ዳኛ፣ ወፋ፣ አውጫጭኝ ወይም አፍርሳታ
የተባሉ የግጭት አፈታት ስረዓቶች በአካባቢው
የተለመዱ መሆናቸው ይገልጻሉ። እያንዳንዳቸውንም
የግጭት ማክሰሚያ ስርዓቶች በተናጠል ያስቃኙናል።
ቅሬ
ዳኝነት
አቶ
ጋሻው እንደሚያስረዱት፤ በአካባቢው የሚገኙ
እያንዳንዱ አጥቢያዎች የየራሳቸው ቅሬ አላቸዉ።
ቅሬ ማለት የየመንደሩ የፍትህ ሸንጎ እንደማለት
ሲሆን በመንደሩ የተከበረ አንድ ሰው ዳኛ
የደርጎ ይሰየማል። ቅሬዉ በሚሰበሰብበት ወር
በገባ በ 12 በመሆኑ
በደል የደረሰበት ሰዉ ጉዳዩን ዳኛው ፊት ቀርቦ
ያስረዳል። የፍትህ ስርዓቱ ማህበረሰቡን
አሳታፊ በመሆኑ ተከሳሽም የቅሬዉ ዳኛ ፊት
ይቀርብና የተሰበሰበዉ ህዝብም ሀሳብ እንዲሰነዝር
ይደረጋል። በመጨረሻም ዳኛው ግራ ቀኙን ካዳመጠ
በኋላ በመንደሩ ህገደንብ መሰረት ብይኑን
ያሳርፋል።
በዚህ
መንገድ የሚፈቱ ችግሮች ጥቃቅን ሲሆኑ የሰው
ህይወት የጠፋበት እና ከባድ ግጭቶት ያሉትን
ለመፍታት አይችሉም። ተበዳይም ፍትሕ በማግኘቱ
ተደስቶ እርሻ ስራውን ያለስጋት ይቀጥላል።
ብዙ ጊዜ ቅጣቱም አንድ እንስራ ጠላ እና ድፎ
ዳቦ ለቀጣዩ ወር ቅሬ ሲሰበሰብ በማምጣት
ባለቅሬዉ እንዲቋደስና ማድረግ ነው። ይህም
አነስተኛ ግጭቶች ወደከፋ ረብሻ እና የሰው
ህይወት መጥፋት እንዳያመሩ ይከላከላል።
የሽምግልና
ውሳኔዎችን ለማስፈጸም ደግሞ የዘመድ ዳኛ
ይሰየማል። የዘመድ ዳኛ ሁለት አይነት ሲሆን
አንደኛዉ የነገር አባት የሚባል ነዉ። የነገር
አባት ማለት አንድ ግጭት ከተፈጠረ በኋላ
በሽማግሌ የተወሰነን ዉሳኔ የሚይዝ እና ወደፊት
እንዳይጣሉ የተጣለባቸዉን ገደብ እንዳይተላለፉ
የሚቆጣጠር ነው። በግጭቱ ለተሳሰፉ ሁለቱም
ወገኖች እንደ ቅርብ ዘመድ በመሆን የተጣለባቸውን
ኃላፊነት ሁሉ ያስፈጽማል። ተከሳሽ የተወሰነበትን
ቀላል ቅጣት አልቀበልም ካለ ግን ከቅሬዉ ብሎም
ከአጥቢያዉ እስከ መዉጣት የሚያደርስ ዉሳኔ
ይወሰንበታል።
የዘመድ
ዳኛ
የመጀመሪያው
የዘመድ ዳኛ የፍትህ አስፈጻሚ ቢሆንም ሁለተኛዉ
ዘመድ ዳኛ በአይነቱ የተለየ ነው። የአንድ
የዘር ግንድ አካል የሆኑ ዘመዳሞችን የሚዳኙበት
ስርዓት ነዉ። የተቋቋመዉ ሰዉ በትምህርት
እና በስራ ከቦታ ቦታ ሲዘዋወር አዉቆም ሆነ
ሳያዉቅ ከዘመድ አዝማድ ጋር ጋብቻ እየመሰረተ
በመሆኑ ይሄ ደግሞ ከታወቀ በኋላ ፍታ አትፍታ
የሚል ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀዉስ ስለሚፈጥር
ችግሩን ቀድሞ ለመከላከል የታሰበ ነዉ። በመሆኑ
የዘረት፣ የሾላ፣ የጎየት፣የጎሽ፣የሻህ ዝርያ
እየተባለ የዘመድ ዳኞች ተቋቁመው ተመሳሳይ
ችግሮች ወደግጭት እንዳመሩ ይከላከላሉ።
በየወሩ በቤተክርስቲያን ማርገጃ ተሰብስበዉ
ልጅህ ልጅሽ የት ነዉ የት ናት በማለት ይመካከራሉ።
ይህም በአካባቢዉ ያለዉል ለዝምድና የሚሰጠዉን
ትኩረት ከትውልድ ወደ ትዉልድ እንዲተላለፍ
ለማድረግ ነዉ። ዝምድናን አፍርሶ ማግባት
ግጭትን ብቻ ሳይሆን መገለልን፣ መረገምን፣
ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀዉስ ስለሚፈጥር ይህ
መቋቋሙ ግጭቱን ቀድሞ ለማኮላሸት ይጠቅማል።
ወፋ
ወፋ ሌላኛዉ
የግጭት መፍቻ ስርዓት ነዉ። ወፋ ከጥንቆላ
ጋር የተያያዘ ሲሆን በኢትዮጵያ በተለያዩ
አካባቢዎች የተለያዩ ወፋዎች ሲኖሩ ለአብነት
በዘረት እና አካባቢዉ ያሉ ወፋ ነገሰ ፣ ወፋ
ዘነበ ክምር ድንጋይ እንዲሁም አንባት ይባላሉ።
እነዚህ ወፋዎች በመንፈስ እንደሚፈርዱ ቅሬታ
አቅራቢዎች ያምናሉ። ወፋ አጋፋሪ ሲኖረዉ
አጋፋሪዉ ሰዎችን ሲመጡ መቀበል፣ መመዝገብ፣
የጉባኤ ቀንና ሰአቱን ማሳወቅ፣ ፍርድ የሚሹ
ወደ ወፋዉ እንዲገቡ ማድረግ ሀላፊነቶቹ ናቸዉ።
ለፍርድ የመጡ ደጅ ጠኚዎች ደግሞ የታዘዙትን
በመፈጸም የፍርድ ሂደታቸዉን ይከታተላሉ።
ለወፋ
የሚቀርቡት ሁሉንም አይነት የሲቪል እና
ክሪሚናል ጉዳይ ያዩ ክሶች ሲሆን በተለይ
ጭለማን ተገን ተደርጎ የተሰራ ድርጊት ማለትም
ስርቆት፣ ነፍስ መግደል በብዛት ይቀርቡበታል።
ለአብነት ያህል ያደራ ገንዘብ፣ የቤተሰብ
ጉዳይ፣ ሽርክና፣የነጋዴ ጉዳይ ፣ የምርት
ጉዳይ፣ ግድያ ፣ቅሚያ ወይም ዝርፊያ፣ የቤት
እና ክምር ቃጠሎ ጉዳዮች በብዛት ወደ ወፋው
ያመራሉ። የፍርድ ሂደቱም በጉባኤ የሚከወን
ሲሆን የራሱ የተመደበለት ሰአትና ቦታ አለ።
የተፈረደላቸዉም ሰዎች ሰዉ ጥሩ ከተባሉ መጥሪያ
ይዘዉ ሄደዉ ይጠራሉ።
ሰዉየዉ
ካልመጣ ጧፍ አስረዉ ይሄዳሉ። ጧፍ ሲታሰርም
ተከሳሽ ላይ ችግረ ይመጣል ተብሎ ይታሰባለ።
የጧፍ አሳሪዉ ቤተሰብ
እርቅ እሰኪወርድ
ከጠላቱ ቤተሰብ ጋር
አብሮ መዋል፣ ማደር፣ መብላት አይችልም።
ምክንያቱም ጧፍ
ያሰረ ከተከሳሽ ጋር ከበላ መአት ይወርድበታል
ተብሎ ይታሰባል። ነገር ግን የተከሰሰው
ሰው ጧፉን ሄደህ
አስፈታ ሲባል
ወፋው ጋር ሄዶ
ጥፋቱን ካመነ እርቅ
ይወርዳል። በሌላ
በኩል ሁለት ሰዎች ያልተግባቡበት ጉዳይ ካለ
እና ወደ ግጭት እንዳያመራ ከታሰበ ወፋው ጋር
ተያይዘው እንዲሄዱ ይደረጋል። በዚህ ወቅት
ሁለቱን
ሰዎች እንደ ቋረኛ
አስተሳስረዉ
ይልኳቸዋል። ወፋዉ
ከፈረደላቸዉ በኋላ
ከደጅ ተኚዎች ሽማግሌ መርጣችሁ ታዩ ካለ
እንደተባለዉ በአጋፋሪዉ እገዛ ተሸማግለው
ወደየቤታቸው ያመራሉ። የወፋ
ጥንካራ ጎን ወጪ
ቀናሽ መሆኑ ነው።
ለወፋዉ የሚከፈለዉ ክፍያ አናሳ ሲሆን ባለ
ጉዳዩ በእግር ወይም በትራንስፖርት ለሚመጣበት
ብቻ ነዉ ገንዘብ የሚያወጣዉ።
አውጫጭኝ
ወይም አፍርሳታ
ተበዳይ
ማን በደደል እንደፈጸመበት በውል በማያውቅበት
ወቅት አንዱ ጎረቤቱ ላይ ያለአግባብ ጣቱን
ሊቀስር ይችላል። ለአብነት አንድ አርሶአደር
ከማሳው አምሽቶ ወደቤቱ በሚመጣበት ወቅት
ለአይን ያዝ በሚያደርግ አካባቢ ሲደርስ
ወንበዴዎች የያዘውን ንብረት ዘርፈውት ቢሰወሩ
ማን እንዳጠቃው አያውቅም። በዚህም ምክንያት
እገሌ ነው የዘረፈኝ ወይም ያዘረፈኝ እያለ
ከብዙ ጎረቤቶቹ ጋር ግጭት ውስጥ ይገባል።
በዚህ ጊዜ አውጫጭኝ ይጠራና የቀዬው ህዝብ
በሙሉ አንድ ጥላማ ስፍራ ላይ እንዲሰበሰብ
ደረጋል። አውጫጭኝ ወይም አፍርሳታ አሁን
አሁን እየቀረ የመጣ የግጭት አፈታት መፍቻ
ስርዓት ቢሆንም በመንዝ አንዳንድ አካባቢዎች
ደግሞ ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል።
ለአፍርሳታ
የተሰበሰበው ነዋሪ ማን ያውቃል ስለጉዳዩ?
እያለ
ሲወያይ ከቆየ በኋላ ወንጀሉ ሲፈጸም እማኝ
የነበረ ወይም ዘራፊዎቹ እነማን እንደሆኑ
መረጃው ያለው ሰው ተመርጦ በህዝብ ፊት እንዲቆም
ይደረጋል። በወቅቱም ዳኝነት ሊሰጥ የሚችል
ሰው ይሰየምና ጉዳዩን ከእማኞች እንዲሰማ
ይደረጋል። የዳኛው ስራ ሽምግልና ሲሆን
“ነገርን ከስሩ ውሃን ከጥሩ” እንዲሉ እዉነትን
የመፈለጊያ ጥያቄ ከተሰብሳቢዎች ዘንድ
ይቀበላሉ። ተበዳይም በጭለማ የተፈጸመበትን
በደል በማስረዳት ወንጀለኞቹ እንዲጠየቁለት
አቤቱታውን ያሰማል። እማኞኙም እነማን ዘረፋውን
እንፈጸሙ በማጋለጥ ለዳኛው ያስረዳል። በዚህ
ወቅት ተጠርጣሪዎቹ በቦታው ከተገኙ ተነስተው
ስለጉዳዩ እንዲያስረዱ ይጠየቃሉ። ነገር ግን
በቦታው ከሌሉ በሌላ ቀን እንዲመጡ ትዕዛዝ
ተጥቶ ተሰብሳቢው ይበተናል። በድጋሚ
በሚጠራ ጉባኤ ላይም ተጠርጣሪዎች ቀርበው
የእውነት ውሸት ምስክራቸውን እንዲሰጡ
ይደረጋል። ዳኛውም ጉዳዩን ካዳመጠ በኋላ
ፍርድ በመስጠት ግጭቱ እንዲበርድ ያደርጋል።
ካስፈለገም ሁለቱም ወገኖች እንዲስማሙ በዳይ
ላይ የካሳ ክፍያ ይጣልና ቤተሰቡም እርቀ ሰላም
እንዲያወርድ አብሮ ማዕድ የመቁረስበትን ቀነ
ቀጠሮ ያደርጋል። ተበዳይ የሚፈልገዉ ነገር
እዉነት ብቻ ነዉ ይህንንም አቆምኩት፣ ገተርኩት፣
ረታሁት አሳመንኩት በሚል ይገልጽበታል።
የሚፈለገዉ የሞራል አሸናፊነት ብቻ ነዉ።
ከዚህ በኋላ ከሳሽም ዘራፊዎችም እርቅ በመፈፀም
ኑሯቸውን ይቀጥላሉ።
አቶ
ጋሻው እንደሚሉት፤ ሀገር በቀሎቹ የግጭት
አፈታት ዘዴዎች ግጭትን ከስሩ መፍታትና
ከማድረቅ ባለፈ በየአካባቢው የሚከናወኑ
በመሆኑ ለአርሶአደሩ ጊዜ፣ ገንዘብ እና ጉልበት
ቆጣቢ ናቸው። በተፈረደበት ሰው ላይ ቀላል
የሆነ ቅጣት ስለሚጣል ህብረተሰቡን ለኢኮኖሚ
ቀዉስ አይዳረጉም። በግጭት አፈታቶቹ ላይ
ዋናው የሚፈለገው የሞራል አሸናፊነት በመሆኑ
ይቅር ባይነት እና አብሮነት እንደገና ከመገንባት
አኳያ ከመደበኛዉ የፍትህ ስርአት ይሻላሉ።
በመሆኑም ከመደበኛው የፍትህ ስርዓት ጋር
እያጣጠሙ እንዲቀጥሉ ማድረግ ይገባል።
መልካም ነዉ ግን እኔ አምቦ ዩኒቨርሲቲ ከለቀቅሁ ቆየት ብያለሁ። ወሎ ዩኒቨርሲቲ ፖለቲካል ሳይንስና አለምአቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል በሚለዉ ቢስተካከል። በተረፈ ጥሩ ነዉ።
ReplyDeleteበጣም አመሰግናለሁ። መልካም ጽሁፎችህን ያብዛልን
Delete