ባህል
የአንድን ማህበረሰብ የእምነት ፍልስፍና ጥበብ የአስተሳሰብ እሴቶች ያካተተ ነው። ውስብስቡ እሳቤ በቁሳዊ ባህሎቹ እና ልማዶቹ በማህበራዊ
ግንኙነቶቹ እና በተለያዩ ትውፊቶቹ አማካኝነት ተጨባጭ አሰራር ይኖረዋል። በደቡብ ብሔሮችና ብሔረሰቦች ክልል የሚገኘው የጉራጌ
ብሔርም በ13 ወረዳዎች እና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች ማለትም ቡታጅራ እና ወልቂጤ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የማህበረሰቡ አባላትን
ይዟል። የጉራጌ ህዝብ ቆጠራ በብዙዎች ዘንድ አለመግባባትን ይፈጥራል ምክንያቱም አብዛኛዎቹ ተወላጆች በተለያዩ ከተሞች በመሄድ
ኑሯቸውን የሚመሩ በመሆናቸው ህዝቡ በአራቱም አቅጣጫ ተበትኖ ይገኛል። በቀዬአቸው የቆዩ የብሔሩ ተወላጆችም የባህላቸው መገለጫ
የሆኑ የቤት አሰራረሮችን እና የመንደር አመሰራረቶችን እየተከተሉ ለዘመናት ቆይተዋል። ከሁሉም ባለፈ ግን የጉራጌ ህዝበ ራሱን
የሚያስተዳድርባቸው ባህላዊ የፍትህ ስርዓት የሚያከናውኑ ሸነጎዎች ባለቤት ነው።
የጉራጌ ተወላጁ የህግ ባለሙያው አቶ ሰለሞን አሸናፊ እንደሚገልፁት፤
ከጉራጌ ዞን ወረዳዎች መካከል የሰባት ቤቱ የጀካ፣ የመስቃኑ ፈርአገዘኘ፣ የዶቢው ስናኖ እንዲሁም ጎረደና በሚል ስያሜ የሚጠራው
የገደባኖ ጉታዘር ወለኔ እና የሶዶ ጉራጌ ሸነጎዎች በርካታ ጎብኚዎችን ኢትዮጵያ የቆየ የህግ አሰራረ አላት ብለው እንዲያምኑ
ያስገደደ ባህሎች ናቸው። ስዬሜያቸው እንደየወረዳው ቢለያይም ተመሳሳይ የሸነጎ አሰራርን ይከተላሉ። አላማቸውም ተተኪውን ትውልድ
በስነምግባር ከማነጽ ጀምሮ ግጭቶች ዳግም እንዳያገረሹ የማድረቅ አቅም አለው።
የቤተ ጉራጌ ባህላዊ የሸንጎ ስርአት
በ16ኛው መቶ
ክፍለ ዘመን እንደተጀመረ ታሪክ
ያስረዳል የሚሉት አቶ ሰለሞን፤ ማህበረሰቡ በመረዳዳት እና መፈቃቀር ላይ በተመሰረተ አኗኗረ ለረጅም ዘመናት እንዲጓዘ
እንዳገዘው ምስክርነት ይሰጣሉ። በተጨማሪ የሸንጎው አሰራር የአካባቢውን ልማት በማፋጠን
ነዋሪዎችን ለማስተባበር ጥቅም ላይ እንደሚውል ይናገራሉ።
ሸንጎው ችግሮቹ የሚፈቱለት
እና የሚፈርዱለት ዳኛ ወይም የሴራ ዳነ በሚባሉ
አካላት አሉት። በፍትህ አሰጣጣቸውና፣ በአስተዋይነታቸው የተመረጡ ሽማግሌዎች ለቦታው
በእጩነት ይቀርባሉ። በህዝብ ተቀባይነት ያለው እና የፍርድ አሰጣጡም የማያሻማ በሆኑ አካላት ላይ
ጥብቅ ፍተሻ ተደርጎ ለቦታው ሹመት ይሰጣል።
የጉራጌ ብሔረሰብ ከወረዳ ወረዳ ወይም ከአካባቢ አከባባቢ እንደ ዘዬው
ለዩነት የተለያየ የስም አሰጣጥ ቢኖረውም የሚተዳደሩበት የሸንጎ ደንብና ህግ
ግን መሰረታዊ ለውጥ አይታይበትም። ከሸንጎዎቹ የህግ አፈጻጸም አንፃርም የጉራጌ ባህላዊ የመተዳደሪያ ደንቦች መሆናቸው
ተጠቅሶ በዋናነት ህዝቡ የሚተዳደርባቸው አራት ናቸው።
አንደኛው <<የኧጆካ ቕጫ>>
የተሰኘው የሰባት ቤት ጉራጌ የባህላዊ ሸንጎ መተዳደሪያ ደንብ ሲሆን
ሁለተኛው <<የጎርደና ሴራ>>
የተባለው የክስታኔ እና የወለኔ ቤተ-ጉራጌዎች ባህላዊ የመተዳደሪያ ደንብ
ነው። በሶስተኛነት ደግሞ <<የፈር አገዘኘ ሴራ>> የተባለው
የመስቃን ቤተ-ጉራጌ የባህላዊ ሸንጎ መተዳደሪያ ደንብ ሲሆን
አራተኛው <<የዶቢ ጎጎት ስናኖ ሴራ>>
ማለትም የዶቢ ቤተ-ጉራጌ የባህላዊ ሸንጎ መተዳደሪያ ደንብ ሆኖ
ያገለግላል።
የሸንጎዎቹ
መተዳደሪያ ደንቦች በውስጣቸው የተለያዩ ህጎችን አጭቀው ይዘዋል። የሚሉት ደግሞ የጉራጌ ባህል ልማት ማህበር የባህል ልማት ሃላፊው አቶ መንግስቱ 111 ናቸው። ለአብነት የሰባት ቤት ጉራጌ ባህላዊ ሸንጎን የኧጆካ
ምልከታ ቢደረግ መተዳደሪያ ህጉ በተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች የተዋቀረ ነው። በሸንጎው ንዑስ ክፍል
ውስጥ የጥብ /የጎሳ/
መተዳደሪያ ህግ
ተቀምጧል።
በአንድ ወረዳ ውስጥ በርካታ ጎሳዎች ስለሚኖሩ
የእያንዳንዱ ጎሳ ከሌሎች
ጎሳዎች ጋር ወይም በእራሱ ውስጥ የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመፈታት ይረዳል። በአስተዋይነታቸው በተመሰከረላቸውና በተመረጡ የጎሳው አበቃጥ ወይም
የጎሳ መሪ አማካኝነት የሸንጎ
አፈታት ይካሄድበታል።
የባህላዊ
ሸንጎው በጎሳው አባላት ውስጥ የሚከሰቱ የንብረት ጥፋቶችን፣ የቤት ቃጠሎዎችን፣
የንብረት አለመግባባቶችን እና ከሌላ ጎሳ ጋር የተፈጠሩ ማህበራዊ ችግሮች ከበድ ያሉ የመሬት ይዞታ ክርክሮችን
ለመፈታት ያገለግላል። ከመደበባው የአገሪቷ ህግ ጋር ባልተጣረሰ ሁኔታም ግጭቶችን በመፍታት የባሰ ማህበረሰባዊ ቀውስ
እነዳይከሰት የበኩሉት አበርክቷል። ችግሩን በጋራ በመምከር የሚፈቱበትና አስፈላጊ የእርምት እርምጃ የሚወሰድበት ማህበረሰባዊ ተቋም ሲሆን በመላ የጎሳ አባላት ይሁንታ ያገኘው መሪ የባህላዊ ዳኝነት ስርዓቱን በማስፈፀም አስፈላጊውን እርምጃ
ሁሉ እነዲወሰድ ያዛል። በመሆኑም የጊሳ አባላቱ ፍርዱን ወይም ትዕዛዙን በይሁንታነት አምነው ይቀበላሉ።
በተለያዩ
የሸንጎ ምክር ቤቶች ያልተፈታ ችግረ ያለው አካልም ጉዳዩን ለበላይ የሚያቀርበበት ባህላዊ አሰራር አለው። የጉራጌ ቕጫ ምክር ቤት
በባህላዊው አስተዳደር መሰረት የመጨረሻ አካል ተደረጎ ይወሰዳል። የጉራጌ ቕጫ ምክር ቤት የሁሉም የዳኝነት ስርዓት አካላት አስፈፃሚ የበላይና የመጨረሻ ይግባኝ ሰሚ አካል በመሆኑ
ከተለያዩ የጎሳ እና ብሔረሰብ አካላት የተዋቀረ ነው። ባህላዊ ምክር ቤቱ
በአብዛኛው ጊዜ በተለያዩ ጎሳዎች መካከል የሚነሱ ደም ያፋሰሱ
ግጭቶችን በመፍታት ልምድ አካብቷል። በትርጉም አረዳድ እና በተለያዩ ምክንያቶች የሃሳብ መከፋፈል በምክር ቤቱ ሲያጋጥምም
የቕጫ ምክር ቤት ሰብሳቢው በሚያሰይሟቸው የተከበሩ
ሽማግሌዎች አማካኝነት ውሳኔ
እንዲሰጥ ይደረጋል። የባህላዊ
ምክር ቤቱ ሰብሳቢ የሚሰየመው በጠቅላላ ጉባኤ ወቅት
ሲሆን የስልጣን ዘመኑም የሚቆየው በተሰየመበት ወቅት በዋለው ሸንጎ የተነሱ ጉዳዮች
ተጠናቀው እልባት እስከሚያገኙበት
ጊዜ ድረስ ይሆናል።
በአብዛኛውም የሰብሳቢው የስራ ዘመን ለረዥም አመታት የሚቀጥል በመሆኑ ረጅም
ዘመናትን በቆየ መጠን ጣዕሙ እነደሚጨምር ወይን በልምድ እና በብልሃት እንደሚጨምር ይታመንበታል።
ጉራጌ በባህሉ የደም ብቀላ
/መገዳደል/
የሚያስከትለው ጥፋት አደገኛ መሆኑና ዘርን እንደሚጨርስ ያምናል፡፡ ይጠየፋልም ስለሆነም ግድያ እንዳይፈፀም ከፍተኛ የመከላከል ጥረት ያደርጋል፡፡ ግድያ ከተፈፀመም እንዳይቀጥል
/በትውልድ እንዳይደጋገም/
ደም በቕጫ ስርዓት መሰረት እንዲያልቅ ይደረጋል፡፡ በቕጫ መሰረት እንዲያልቅ ካልተደረገ ግን የሚያስከትለው መዘዝ መጥፎ እንደሚሆን ይታመናል፡፡ ስለሆነም እያንዳንዱ የደም ጉዳይ መንስኤውና አገዳደሉን መሰረት ያደረገ
ካሳ ይከፈላል። በገዳዩና በሟች ዘመዶች መሃል የነበረው መፈላለግና ቁርሾ አብቅቶ ሠላም ወርዶ እንደማንኛውም ሰው ሠላማዊ ህይወት መምራታቸውን ይቀጥላሉ፡፡
በጉራጌዎች ባህላዊ ህግ መሰረት የደም አፋሳሽ
ግጭት አይነቶች በሶስት ደረጃዎች ይከፈላሉ።
አንደዳው ሙራ ደም ወይም የግፍ አገዳደል
ተበሎ የያዛል። በህጉ መሰረት አንድን
ሰው ሆን ብሎ በግፍ የገደለ በሙራ ደም ስርዓት
መሰረት
30 ሺ ብር አሊያም ከዚያ በላይ የደም ካሳ መክፈል
እንደሚገባው የብሔሩ ባህላዊ መቅጫ
ህግ ይደነግጋል።
በሌላ በኩል በስህተት ግድያ ከተፈጸመ መዳራ ይባላል። መዳራ ማለት ባለማወቅ የተፈጸመ እና
ገዳይ እና ሟች የከረረ ፀብ እንደሌላቸው የሚያሳይ የክስ አይነት ነው። በመዳራ መሰረት ጥፋተኛ
15 ሺ ብር የደም ካሳ በመክፈል
ከሟቸ ቤተሰቦች ጋር እርቅ ያወርዳል። ሶስተታው ደግሞ የመዳራ መዳራ ወይም በፍፁም ስህተት የተፈፀመ ግድያ
የሚባለው ወነጀል ነው። በፍፁም አለማወቅ የተፈጸመ ወንጀል በመሆኑም ቅጣቱ ይቀልለታል። ደም ማፍሰሱ በፍፁም ስህተት የተፈፀመ
ከሆነ ተጣርቶ ጥፋተኛው
ሰባት ሺ አምስተ መቶ ብር እንዲቀፍል ይታዘዛል።ከዚህ በኋላ ደም መላሽ ወይም በቀላ የሚባል ጉዳይ አይነሳም በአንድነት ህይወት
ተቀጥላለች።
በክስታኔና የወለኔ ቤተ-ጉራጌዎች ባህላዊ ሸንጎ (የጎርደና ሴራ)
መሰረት ደግሞ
በወማኖ
/ጉታቻ ሴራ/ በተባለው
ህግ መሰረት አንድ ሰው የግድያ ወንጀል ከፈጸመ ላልተወሰነ ጊዜ አካባቢውን ለቆ ይሰደዳል፣ ቤተሰቡም ይበተናል። ምክንያቱም በአካባቢው ከቆየና ቤተሰቡም ካልተበተነ ተጨማሪ
ደግ አፋሳሽ የጨተገባር ሊፈጸም ይችላል ከሚል እሳቤ ነው። ከጥቂት ዓመታት የስደት ኑሮ በኋላ የሚታወቁ ሽማግሌዎች ካህናትና ዲያቆናት ጋር በመሆን ሰባት ልጃገረዶችና ጎረምሶች በማስከተል የቤተክርስቲያን መረዋ እየተደወለ ቃጭል እየተቃጨለ ወደ ሟች ቤተ ዘመዶች
ይኬዳል። ከተደጋጋሚ ልመና በኋላ ለእርቁ የእሺታ መልሳቸውን ሲሰጥ
የእርቅ ስነስርአት ለማከናወን
የሁለቱን ወገን ስምምነት ያገሹ የአገር ሽማግሌዎች ይሰየማሉ።
የአገሬው ሸንጎ ግድያው ሳይታሰብ የተፈጠረ መሆኑን አሊያም በቂም በቀል መሆን አለመሆኑን አጣርቶ በገዳይ ወገን የሚከፈል የደም ካሳ በመወሰን የእርቅ ስርዓት ይፈጸማል።
የእርቅ ስነ-ስርዓት ከተከናወነ በኋላ ሁለቱ ወገኖች ፍፁም ቂም እንዳይዙ ጉዳ ባህል
መፈፀም የተለመደ ሲሆን በጉዳው ስነ-ስርዓት ላይ ጥቁር ፍየል ታርዶ ከሁለቱም ወገኖች አንዳንድ ሰዎች ተመርጠው አውራ ጣቶቻቸው በፍየሉ አንጀት ታስሮ ይቋጠራል። ይህም ጉዳ የተያያዙ ሰዎች የጠላትንት ስሜትን አስወግደው በመሃላቸው ሰላም ያሰፍናል ተብሎ ስለሚታመን ነው።
በመሆኑም ከዚያች ቀን በኋላ እንደ ጠላት እና ደመኛ መተያየት ያበቃለታል። የቤተጉራጌ የሸንጎ ባህል እና ግጭት
አፈታት ተዝቆ የማያልቅ ሃብት ያለው በመሆኑ ከብሔሩ አልፎ ለአገር የሚተርፍ መልካም ስርዓትን ማስተላለፍ የሚያስችል አቅም
አለው። በመሆኑም በሸንጎው ስርዓት ላይ ሰፊ ጠናት እና ምርምር ማድረግ ከታሪክ ተመራማሪዎች ይጠበቃል።
No comments:
Post a Comment