Tuesday, November 14, 2017

የደጃች ኩምሳ ሞረዳ ቤተመንግስት

 

ነቀምቴ በኦሮሚያ ክልል በምስራቅ ወለጋ ዞን ውስጥ ትገኛለች። እንደ አካባቢው አባቶች የስሟ ትርጓሜ «የታጨች» እንደማለት ነው። በከተማዋ ከሚገኙ መስህቦች ውስጥ ደግሞ ባለ ግርማ ሞገሱ እና ሁለት ነጥብ አምስት ሄክታር ላይ ያረፈው የንጉስ ደጃዝማች ኩምሳ ሞረዳ ቤተመንግስት ዋነኛው ነው። ንጉሱ የነቀምቴ ከተማ መስራች እንደሆኑ የሚታመን ሲሆን ከ1881ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 1916 ዓ.ም. ድረስ የቀድሞ ወለጋ ጠቅላይ ግዛትን ያስተዳድሩ የነበሩ ንጉሥ ናቸው። ንጉሱ ቤተመንግስታቸውንም ያስገነቡት በ1981 ዓ.ም ነበር።
    የኩምሳ ሞረዳ ቤተመንግስት የኦሮሞ አምስት ገዳዎችን ለመወከል ታስቦ አምስት በሮች አሉት።  ከአምስቱ በሮች በየትኛው መግባት ይፈልጉ ይሆን?። 
    አንደኛው በር የንጉሱ እና ቤተሰባቸው መግቢያ ሲሆን ሁለተኛው በር ደግሞ የሰራተኞች መግቢያ ነበር። ሶስተኛው በር የቤት እንስሳት ከመስክ ወደ ግቢው ከግቢው ወደ ውጪ የሚመላለሱበት ሲሆን፤ አራተኛው በር ደግሞ ለግቢው ሰራተኞች መተላለፊያነት ብቻ ያገለግላል። አምስተኛው በር የእንግዶች በመሆኑ ለአገሩና ለቤተመንግስቱ አዲስ ከሆኑ በወቅቱ ሊጠቀሙ የሚችሉት በዚሁ መግቢያ እንደሆነ ያስቡ።
    ቤተ-መንግስቱን አስር ህንጻዎችን በሁለት ግቢዎች አጠቃሎ ይዟል። ግንባታው በኢትዮጵያውያን ሰራተኞችና በግሪካውያን አማካሪዎች የተከናወነ መሆኑን ታሪክ ያስረዳናል። ሁሉም ህንጻዎች በእንጨት፣ በኖራ ድንጋይና አፈር ብቻ የተዋቀሩ ናቸው።   
    በመጀመሪያ የንጉሱን ማረፊያ ክፍሎችን ቃኘት ቢያደርጉ በጣውላ ምንጣፍ የተሰሩ እና የእሳት ማሞቂያ የተሰራላቸው የእንግዳ ቤት፣ የመኝታ ክፍሎችና የምግብ ማቅረቢያ ክፍሎችን በአማረ የስነህንጻ ጥበብ ተውበው ይመለከታሉ። በመስኮቶቹ አሽንቀጥረው ቢመለከቱ ደግሞ ለንጉሱ ባህሉን የጠበቀ ምግብ የሚዘጋጅበት ማዕድ ቤትና የፈረንጅ እንግዶች እንዳይቸገሩ በማሰብ የተዘጋጀውን የውጭ አገር ምግብ ማሰናጃ ቤቶችን ያገኛሉ። ለንግድ እና ለተለያዩ ጉዳዮች የንጉሱን ደጅ የሚረግጡ የውጭ አገር ዜጎች በምግብ ችግር እንዳያጋጥማቸው ታስቦ የተገነባው ማዕድ ማዘጋጃ የአገሪቷን እንግዳ ተቀባይነት አጉልቶ የሚያሳይ ነው።     


    ከቤቶቹ ፊት ለፊቱ ደግሞ ሰፊ አዳራሽ ያገኛሉ። ወደ አዳራሹ ሲገቡ እነደ ኪስ የተሰሩ ሶስት በሮች ያላቸው ክፍሎች ይገኛሉ። አነስተኛ ክፍሎቹ ወደ ታዳሚው የሚዳረሱትን ምግብና መጠጥ  የሚቀመጥባቸው ቦታዎች ሲሆኑ፤ ለእያንዳንዱ ክፍል አንድ አንድ አሳላፊ ተመድቦላቸው ንጉሱ ግብር ያበሉበታል።
    ከዋናው ሳሎኑ አለፍ እንዳሉ ደግሞ ሌላ ውብ የንህጻ ዲዛይን ያረፈበት የፍርድ ችሎት ያገኛሉ። ችሎቱ በክብ ቅርጽ የተሰራ ህንጻ ነው። ባለ አንድ ወለል ከፍታም አለው። የላይኛው ወለል አንድ መግቢያ እና ሶስት ከበር የማይተናነሱ መስኮቶች ተዘጋጅታውለታል። ንጉስ ኩምሳ ብቻቸውን ተቀምጠው ፍርድ የሚሰጡበት ቦታ ነው። ከእርሳቸው በትክክል ወደታች ያለው ክፍል ደግሞ የተከሳሾች ዶሴ የሚደራጅበት ሚስጥራዊ ክፍል ሲሆን የሚከፈተውም ሆነ የሚዘጋው ንጉሱ ለዳኝነት በሚቀርቡባቸው ጊዜያት ብቻ ነበር።
    በምዕራብ አቅጣጫ በሚገኘው የፍርድ መስጫው የታችኛው ወለል ረቡዕ ዕለት ብቻ የፍትሐብሔር ተከሳሾች ቆመው ጉዳያቸውን ይከታተሉበታል። በተቃራኒው አቅጣጫ ደግሞ አርብ ዕለት የወንጀል ፍርድ የሚሰጣቸው ተከሳሾች በቦታው እንዲቀርቡ ይደረጋል። በወቅቱም ነጻ መውጣት እና አለመውጣታቸው እስኪታወቅ ድረስ ከሳሽ የተከሳሽን ቀለብ እና የተለያዩ ወጪዎች ችሎ የፍርድ ሂደቱን እንዲከታተሉ ይደረጋል። ፍርድ የተጣለባቸው ተከሳሾችን ለማጎር በግቢው ውስጥ የተገነባ ድቅድቅ ጨለማ የዋጠው እስር ቤት አለ። ጨለማ ቤቱ በጾታ የተከፋፈለ ነው። በአብዛኛው ጊዜ በጨለማ ክፍሉ የሚታሰሩ ሴቶች ንጉሱን በዘፈን እና በወሬ የሚያናድዱ እንደነበር የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ። 
    ሌላኛው ክፍል የስጦታ እቃዎች በክብር የሚቀመጡበት ቦታ ነው። የተለያዩ መጎናጸፊያዎች እንዲሁም የጦር መሳሪያዎች ተሽቆጥቁጠው ይቀመጣሉ። በአሁኑ ወቅት ግን አብዛኛዎቹ የንጉሱ ንብረቶች የነቀምቴ ከተማ ሙዚየም ውስጥ ለጎብኚዎች ክፍት ሆነው ይገኛሉ።
    በሌላ በኩል ንጉሱ ዘመናዊ ትምህርት ካላቸው ፍቅር የተነሳ ለልጆቻቸው መማሪያ ክፍሎችን አዘጋጅተዋል። የውጭ አገር ዜጎች ተቀጥረው የቤተሰብ አባላቱን ያስተምሩ ነበር። ንጉሱ የኋላ ኋላ ስማቸውን ወደ ደጃዝማች ገብረእግዚአብሔር ማስቀየራቸውን እና የክርስትና እምነት ተከታይ መሆናቸውን የታሪክ ድርሳናችው ያስረዳናል።
    በግቢው ውስጥ አስደናቂ ታሪክ የሚማሩባቸው ክፍሎች ደግሞ ንጉሱ ለአንደኛ እና ሁለተኛ ሚስቶቻቸው ያስገነቧቸው ክፍሎች ናቸው። የመጀመሪያዋ ሚስታቸው ክፍል ከአንድ ወጥ እንጨት የተሰራ በግምት ስምንት ሜትር የሚደርስ ቁመት ያለው ምሰሶ ከመሃል ቤቱ ላይ ተተክሏል። የሁለተኛዋ ሚስታቸው ቤት ግን ምሰሶ የሚባል ነገር የለውም። ወንድ ልጅ ለአንድ ሴት ብቻ ባል መሆን እንደሚችልና ከአንድ በላይ ለሆነ ቤተሰብ ምሰሶ መሆን እንደማይችል ለማሳየት ታስቦ የተደረገ መሆኑን ታሪክ አዋቂዎች ያስረዳሉ።     ምሰሶውም የኦሮሞን ገዳዎች በዕድሜ በየስምንት አመት እንደሚለያዩ ለትውልጾ ቀርጾ ለማስተላለፍ ስምንት ጠርዞችን እንዲይዝ ተደርጎ ተቀርጿል። ይህን ቤተመንግስት ከጅማው አባጅፋር ጋር የሚያመሳስለው ቅርጽ አለው። ቤተመንግስቱን በመጎብኘት ታሪክዎን የበለጠ ይወቁ!!!

No comments:

Post a Comment

Featured post

ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጠያቂነትን በማረጋገጥ፣ የሕግ በላይነትን በማስፈን፣ መንግሥትና የስራ አስፈጻሚ አካላቱ በመሉ ለሰብአዊ መብቶች መከበር፣ መጠበቅና መሟላት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያሳዩ ልዩ ትኩረትና ክትትል ይሻል

                    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየደረጃው ያሉ የመንግስት አስፈጻሚ አካላትና ኃላፊዎች ላይ የቅርብ ክትትል በማድረግ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር አስተዋጽኦ ሊያደር...