Tuesday, April 25, 2017

አበበች ጎበና


ድካም ድካም ያላቸው «ዘመን ተሻጋሪዋ እናት»
 
Abebech Gobena <<Africa's Mother Theresa>>
ሴትየዋ ጠንካራ ናቸው። ውልደታቸው በ1938.ም ነው። በተለይም «እማማ» እያሉ የሚጠሯቸው ልጆች የእናትነት ፍቅርን ከእርሳቸው ያለስስት እንዳገኙ ይመሰክራሉ። ወይዘሮ አበበች ጎበና በ1972 .ም ሃይማቶታዊ በዓል ለማክበር ለንግሥ ወደ ግሸን ማርያም በሄዱበት ወቅት በኢትዮጵያ በነበረው ድርቅ ምክንያት ከሞት አፋፍ የነበሩ ሁለት ህፃናት ያገኛሉ። አላስችል ያላቻው ወይዘሮ ታዲያ ህጻናቱን ወደ ወደ ቤታቸው ይዘው በመመጣት የህጻናት ማሳደጊያ ስራቸውን «» ብለው ይጀምራሉ። ለ39 አመታትም በሺዎች የሚቆጠሩ ወላድ አልባ ህጻናትን ሳይታክቱ ለዘመናት አሳድገዋል።
በዚህም የክብር ዶክተር ማዕረግ የተሰጣቸው ወይዘሮ አበበች ጎበና በህጻናት ላይ በሚሰሩት በጎ ተግባር «አፍሪካዊቷ ማዘር ቴሬሳ» በሚል ውብ ስም የሚጠሯቸውም አሉ። አሁን ግን ያ ጠንካራ ጉልበት ደክሟል፤ ጤናቸውም አስጊ ደረጃ ላይ ይገኛል። በመኖሪያቸው አካባቢያቸው ጉዳዬ ብሎ የሄደ ሰው ወይዘሮ አበበች የቀድሞውን ጊዜ እንኳን በቅጡ ማስታወስ ተስኗቸው ውል የሌለው ንግግር ሲያደርጉ ሊያደምጥ ይችላል።
ህይወታቸውንም በእራሳቸው እገዛ ብቻ መመራት የማይቸሉበት ደረጃ ላይ ናቸው። በመሆኑም ዘወትር አልጋቸው ላይ ጋደም እንዳሉ ነው። እርጅናውም ተጫጭኗቸዋል። ምግብ እና መጠጥ እንዲሁም አስፈላጊውን እንክብካቤ የምታደርግ ሞግዚት ከአጠገባቸው አትጠፋም። የጤናቸውንም ሁናቴ በየጊዜው የሚከታተል የህክምና ባለሙያዎች ተመድቦላቸዋል። ይሁንና ጤናቸው ባልታወቀ ሁኔታ ታውኮ አልጋ ላይ መዋል ከጀመሩ አመት ከአመት በላይ መቆጠሩን በአካባቢው ያሉ ነዋሪዎች ይገልፃሉ። ህጻናት ማሳደጊያውን መምራት የማይችሉበት ደረጃ ላይ ናቸው።
የአበበች ጎበና ህጻናት እንክብካቤና ልማት ማህበር ምክትል ዋና ዳይሬክተር እና የወይዘሮ አበበች የስጋ ዘመድ የሆኑት አቶ እሸቱ አረዶ እንደሚናገሩት፤ ህጻናት ማሳደጊያውን የመሰረቱት የወይዘሮ አበበች የጤና መታወክ ቢገጥማቸውም ድርጅቱ በቦርድ የሚመራ በመሆኑ ስራው እንደቀጠለ ይገኛል። ቦርዱ አምስት አባላት ያሉት ሲሆን የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተርም በአሁኑ ወቅት ወይዘሮ አበበች ጎበና ናቸው። መስራቿ ጤናቸው ታውኮ አስተዳዳሪ ተደርገው የተቀመጡትም ከሞራል ጋር በተያያዘ መንገድ ሲሆን በተጨማሪም ጤናቸው በጊዜ ሂደት ይሻሻላል ከሚል ግምት የመነጨ ነው። ይሁንና በቦርዱ ውክልና መሰረት ማንኛውንም ስራ እየመሩ ያሉት አቶ እሸቱ ናቸው።
«ወይዘሮ አበበች ከሰባት አመታት በፊት ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር» የሚሉት አቶ እሸቱ፤ በጊዜውም 'እኔ ስሞት ድርጅቱን መንግስት ይረከበው' የሚል ኑዛዜ ማቅረባቸውንም ይናገራሉ። ይሁንና ይህ ኑዛዜ በህግ ደረጃ እንደማይደገፍ ይገልፃሉ። ይህን የተናዘዙትም ድርጅቱ በግለሰብ እጅ ገብቶ አሰራሩ እንዳይበላሽ እና ገንዘብ እንዳይባክን ከሚል ስጋት የመነጨ እንደሚሆን ግምታቸውን ያስቀምጣሉ። የኢፌዲሪ የበጎ አድራጎት ድርጅቶችና ማህበራት ኤጀንሲ ህግ ግን ማንኛውም ተተኪ እስከመጣ ድረስ ስራው እንዲቀጥ ማድረግ እንደሚችል ይጠቁማሉ።
የህጻናት ማሳደጊያው የአስተዳደር መምሪያ ኃላፊ አቶ ቸሩ በቀለ በበኩላቸው እንደሚገልፁት፤ በፍቼ፣ ጉደር ፣ ቡራዩ እና በአዲስ አበባ ላይ ባሉ ቅርንጫፎችም ከ250 በላይ ሰራተኞች ተቀጥረው ለማህበረሰቡ ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል። በህጻናት ማሳደጊያ ማዕከል ውስጥ ሰላሳ አራት ህጻናቶች ይገኛሉ። በማህበረሰቡ ውስጥ ድጋፍ የሚደረገላቸው በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች ይገኛሉ። በተለይ ሴቶቹ የተለያዩ የሙያ ስልጠና በመስጠት ወደ ሰራ እንዲሰማሩ ይደረጋል። ብድር እና ቁጠባ ላይ ድጋፍ የሚያገኙ ሴቶች አሉ።
«በማዕከሉ ስለሚያድጉ አዲስ ህጻናትን ላይ ትኩረት አይደረግም» የሚሉት አቶ ቸሩ፤ ይለቁንም በማህበረሰቡ ውስጥ ሆነው ድጋፍ የሚያሻቸው ህጻናት ላይ ትኩረት እንደሚደረግ ይገልፃሉ። ይህም የሚሆነው ህጻናትን በማዕከል ውስጥ ከማሳደግ ይልቅ ከማህበረሰቡ ጋር ቀላቅሎ ማሳደገ በስነልቦና እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ አዋጭ መሆኑ በመታመኑ መሆኑን ያስረዳሉ። በመሆኑም በቀጣይ ጊዜያት አስገዳጅ ሁኔታ ካልተፈጠረ በቀር ህጻናትን በማዕከሉ ውስጥ ለማሳደግ እንደማይሞከር ይናገራሉ።

No comments:

Post a Comment

Featured post

ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጠያቂነትን በማረጋገጥ፣ የሕግ በላይነትን በማስፈን፣ መንግሥትና የስራ አስፈጻሚ አካላቱ በመሉ ለሰብአዊ መብቶች መከበር፣ መጠበቅና መሟላት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያሳዩ ልዩ ትኩረትና ክትትል ይሻል

                    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየደረጃው ያሉ የመንግስት አስፈጻሚ አካላትና ኃላፊዎች ላይ የቅርብ ክትትል በማድረግ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር አስተዋጽኦ ሊያደር...