“የባለቅኔውን
ሕይወትና ሥራዎች የምንመረምረው ራሳችንን፣
አገራችንን፣ ባህላችንንና ማንነታችንን
ለመመርመር ነው። ባለቅኔው ወደእውነታችን
የሚያደርስ መንገድ እንጂ በራሱ የመጨረሻ
ግብ አይደለም” በሚለው ሃሳብ አቶ ምንዋጋው
ይስማማሉ። በድርሰት ስራዎች ላይ የደራሲውን
ፖለቲካዊ አቋም እናይበታለን፤ ርእዮተ ዓለማዊ
ድምጹን እናደምጥበታለን። የኪነጥበብ ስራዎች
በተለይ ከታላቅ ተመስጦና አንጽሮት የሚወለዱ
ሥነ ጽሑፋዊ ሥራዎች ትንቢታዊነት አያጣቸውም።
ትናንትን ከመጥቀስ፣ ዛሬን ከመቅረጽ አልፈው
ነገን በገሀድ ይተነብያሉ፤ ነገን በገሀድ
ይገልጻሉ።ልቦለድም ይሁን ፍልስፍና የመሰሉ
የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ሁሉ ከማኅበረሰቡ ታሪክ፣
ባህልና ሕይወት ተቀድተው በአዲስ መልክ
ተፈጥረው መልሰው ያንኑ የሚያሳዩን መስታውቶች
ናቸው።
እንደ
አቶ ምንዋጋው ከሆነ፤ ፍቅር እስከመቃብር
የተጻፈበት ጊዜም ሆነ የአሁኑ ዘመን ማሳያ
ይሆናል። ድርሰቱ የሰዎች የተጨናነቀ ማኅበራዊ
ዓለም ማሳያ ነው። ገጸ ባሕርያቱ ከተለያዩ
የሕይወት አቅጣጫዎች የተሳሉ እንደመሆናቸው
በሃያኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የነበረውን
ሰፊ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ይወክላል። ከበርካታ
ገጸ ባሕርያቱ መካከል ባላባቶች (ፊታውራሪ
መሸሻና ፊታውራሪ አሰጌ)፣
የቀሳውስት ቡድን (አባ
ሞገሴና አለቃ ስርግው)፣
ገበሬዎች (ቦጋለ
መብራቱና አበጀ በለው)፣
ባለቅኔዎችና መምህራን (በዛብህና
አለቃ ክንፉ)፣
ባሮች (ሀብትሽና
ልኩራ በሁሉ)፣
ንጉሠ ነገሥቱ (በስም
ያልተጠቀሱ)
ይገኙበታል።
ሐዲስ
እንደሚነግሩን ለመማር ዓይነ ኅሊናን መክፈት
ወሳኝ ነው። ብዙ ጊዜ አካላዊ ዐይኖች ሲዘጉ
የማይታየው ይታያል፡፡ ለሰው ሁለት ዓይነት
ዐይኖች አሉት። አንዱ ዓይነት አካላዊ ሁለተኛው
ዐይነ ኅሊና ናቸው፡፡ ሁለቱ በአንድ ላይ
አያዩም፤ ቢያዩም ደኅና አድርገው አያዩም።
አካላዊ ዐይኖች ማየት የማይችሉትን ለማየት
ዐይነ ኅሊናን መክፈት ያስፈልጋል። ከፍቅር
እስከ መቃብርም እንዲሁ ምን እንማራለን?
የሚል
አጠይቆ አቅርበው ኅሊናችንን በመክፈት ስለ
እያንዳንዱ ገጸባህሪ እና መልዕክቶቻቸው
ያስረዱናል።
“ላግባሽ
አሰጌ” (ፊታውራሪ
አሰጌ)
ደራሲው
በፊውታራሪ አሰጌ አሳበው ለዚያን ጊዜዎቹም
ሆነ ለወቅቱ ዋልጌ ባለሥልጣናት ሊነግሩን
የፈለጉት ሥነ ምግባራዊ እሴት ትልቅ ዋጋ
የሚሰጠው ነው። በመጻሕፉ በቅጽል ስማቸው
“ላግባሽ አሰጌ” ስለተባሉት ፊታውራሪ አሰጌ
ሲገልጹ እንዲህ ይሉናል።
“ ላግባሽ
አሰጌ ከማናቸውም የበለጠ ሴትና ዘፈን አጥብቀው
ይወዱ ነበር። ከጀግና ወይም ከሽማግሌ አዝማሪ
የሚያከብሩ፣ ከንጉሥ ቀጠሮ ለሴት ቀጠሮ ቅድሚያ
የሚሰጡ ነበሩ። ቆንጆ ሴት ከመጠን በላይ
ከመውደዳቸው የተነሣ ቆንጆ ሴት ባዩ ጊዜ
አእምሮ የሚሰውር በሽታ እንዳለባቸው ሰዎች
ራሳቸውን መግዛት ያቅታቸው ነበር። ሴት ከመጠን
ያለፈ መውደዳቸውን የሚያውቁ ሰዎቻቸው አንዳንድ
ጥቅም ሲፈልጉ ሴት ይዘው በመቅረብ ወይም ሴት
ለማቅረብ ተስፋ በመስጠት የእሳቸውን ክብርና
ጥቅም የሚጎዳ ወይም ስለአስተዳደርና ስለፍርድ
የነበራቸውን ኃላፊነት የሚጎዳ መሆኑን ለጊዜው
ማየት አይችሉም ነበር።” ተብሎላቸዋል።
ሐዲስ በዚህ በኩል የዘቀጠ ማንነት ለፍርድ
ሰው እና ለአስተዳደርነት እንደማያበቃ በአግባቡ
ነግረውናል።
መንግሥቱ
ፊታውራሪ መሸሻ (የመንግሥታዊ
ሥነ ምግባር ማሳያ)
ፊታውራሪ
መሸሻን ህዝብ ያልወደደው ስራ ለማምም
እንደማይጠቅም የታየበት ገጸ ባህሪ ሆኖ
እናገኘዋለን። “በጎልማሳነትዎ በፈረስ፣
በጉግስ፣ በተኩስ ተወዳዳሪዎችዎን በማሸነፍዎ፣
በጦር ሜዳ ሄደው ጠላቶችዎን ድል መተው በመመለስዎ
ሰዉ ሁሉ ሲያደንቅዎ፣ ሲያከብርዎ፣ ሲፈራዎ
ጊዜ፣ ለምነው ሳይሆን ተለምነው፣ የጠየቁትን
ብቻ ሳይሆን ያልጠየቁትን ጭምር ሲያገኙ ጊዜ
እግዚአብሔር በሰፊ መሬቱ ከእርስዎ በቀር
ሌላ ክብሩንና ጥቅሙን የሚወድ ሰው እንዳልፈጠረ፣
ሰዉ ሁሉ የእርስዎን ፈቃድ ለመፈጸም እንጂ
የራሱ ፈቃድ የሌለው ሆኖ እንደተፈጠረ በሙሉ
ልብዎ አምነው በዚሁ ልመራ ብለው ተነሡ።
በዳኝነት መንበር ቢያስቀምጥዎ በሕግ ፈንታ
ፈቃድዎን ሕግ አድርገው ልፍረድ አሉ። ሀገር
ቢሰጥዎ በሕግ እንዲያስተዳድሩትና እንዲጠብቁት
የተሾሙበትን ሕዝብ እንደቀማኛ ይዘርፉት
ጀመር። እንዲያው በአጭሩ ሕዝብ የጠላው
እግዚአብሔር የጠላው መሆኑን ማወቅ አቃተዎ።
ስለዚህ ያደንቅዎ፣ ያከብርዎ የነበረው ሰው
ሁሉ ይጠላዎ ጀመር። ሁሉም ሞትዎን ያለዚያም
ሽረትዎን አጥብቆ ፈለገ።” በሚል ሐዲስ
በመጻህፋቸው በገጽ 266
ላይ
በአግባቡ አስተችተዋቸዋል።
የጉድ ማኅበር
ምንነት
አብዛኛውን
ጊዜ በርካቶች የተሳሳቱበት ነገር እንደ
ትክክለኛ ነገር ይቆጠራል ይባላል። ጉዱ ካሳም
ዕውነትን ይዞ ቢጓዝም በዙሪያው ከበውት የሚገኙ
ሰዎች ጋር ለየቅል የሆነ አካሄድ ስላለው
የእርሱ መንገድ የጥፋት ተደርጎ ተቆጠረ።
ባለንበት ዘመንም አገርና ወገን የሚጠቅም
ሃሳብ የሚያነሱ ሰዎች በአብዛኛው ህዝብ
የተሳሳተ አስተሳሰብ ምክንያት እብድ ሊያስብላቸው
ይችላል።
ጉዱ
ካሣ እንደሚነግረን “ጉድ” የሚባለው መጠሪያ
ለእርሱ የተሰጠ አላግባብ ሆኖ እንጂ ደገኛው
ወይም ትክክለኛው ጉድስ የምንኖርበት ማኅበር
ነው። በከበበው ዓለም ውስጥ የግሉን ዓለም
ፈጥሮ በሰው መካከል ብቻውን ሆኖ ይኖር የነበረው
ጉዱ ካሣ የሚኖርበትን (የምንኖርበትን)
ማኅበር
“ዐይን እያለው ፍሬውን ከገለባ ለይቶ ማየት
የማይችል፣ አእምሮ እያለው የሚጠቅመውን
ከሚጎዳው ለይቶ ማስተዋል የማይችል፣ እንደበግ
መንጋ በፊቱ የሚሄደውን ተከትሎ የሚንጋጋ፣
እንደጭነት ከብት የጫኑትን ተሸክሞ የሚጎተት
የጉድ ማኅበር” ይለው ነበር።
የንጉሥ
ግብርንም ሲተች “ከሀብቱ ሀብት ከፍሎ እንደሚገብር
ከሰውነቱ ከፍሎ ለንጉሥ የሚገብረው የመንፈስ
ግብር ነው!”
እያለም
እምቢተኛነት መለመድ እንዳለበት ካሳ ያስተምራል።
ነገር ግን ምንም ቢሆን በግዕዙ እንደሚባለው
‘ብዙኃን ይመውዑ’ ብዙኃን ያሸንፋል ነውና
ብዙኃኑ አሸንፈው ጉዱ የሚለው ቅጥያ የካሣ
ዳምጤ ስም ማዳመቂያ ሆነ።
ጉዱ
ካሳም ይህንንኑ በእራሱ ላይ የደረሰውን ግፍ
ያብራራል። የእኛስ ዘመን ማኅበራዊ ሥሪት
በምን ይለያል?
… ባሪያው
እንዲሸጥ እንዲለወጥ፣ እጀ ሠሪው እንዲናቅ
እንዲጎጠጥ፣ ደሀው በጌታ እንዲገዛ እንዲረገጥ
ተመድቧል። የድሀ ሽማግሌ ‘አንተ’ እየተባለ
እንዲሞት ተደንግጓል። ከንቱ አስቦ ከንቱ
የሚናገር ‘ዘመናይ’ ተብሎ እየተደነቀ ገዥ
እንዲሆን፣ ቁም ነገር አስቦ ቁም ነገር የሚሠራ
የተናቀ ሆኖ ተገዥ እንዲሆን ተመድቧል፡፡
ይገርምሃል!
ይህን
የማይረባ ልማድ ይህን በግፍ ላይ የተመሠረተ
ክፉ ልማድ ተመልክተህ ‘እንዲህ ያለ ልማድ
ሊኖር የማይገባው የሚችልም አይደለምና ይልቅ
አወዳደቁ እንዳይከፋ ቀስ ብሎ እንዲለወጥ
ማድረግ ይሻላል’ ብለህ የተናገርህ እንደሆነ
እንደከሀዲ ተቆጥረህ የምትሰቀልበት ገመድ
ይሰናዳልሃል እያለ ያስረዳናል።
ዝም
ብለህ እያዘንህ ተመልካች የሆንህ እንደሆነም
እንዲህ እንደእኔ ‘እብድ፣ ጉድ’ እያሉ
ሰላምህን አሳጥተው ከማኅበር አስወጥተው
በዘመድ መሐል ባዳ ተወልደህ ባደግህበት ሀገር
እንግዳ ሆነህ እንድትኖር ያደርጉሃል። ደግሞኮ
ይህን ሁሉ የሚያደርጉብህ ‘የጌታ ዘር ነን’
የሚሉት ሁሉንም ረግጠው እላይ የተቀመጡት
ብቻ ቢሆኑ ‘ጥቅማቸው እንዳይጎድልባቸው
ነው’ ትላለህ፡፡ ነገር ግን ባሮቹ፣ እጀ
ሠሪዎቹ፣ ድሆቹ ሁሉ፣ ግፍ የሚሠራባቸው ሁሉ
ከግፍ ሠሪዎች ጋር አንድ ላይ ተባብረው ሲፈርዱብህ
ምን ትላለህ?
‘ከልማድ
ጋር የማይስማማ እውነት ሁልጊዜ ሀሰት ነው’
የሚባለውን የማይረባ ተረት አስበህ ዝም ማለት
ብቻ ነው፡፡ እየውልህ!
በጠቅላላው
የዚህ ልማድ እስረኞች ነን፡፡” እያለ ዕውነት
መገለባበጧን እያስረዳ ይቀጥላል።
ቄስ ምሕረቱ፣
ቄስ ሞገሴና አባ ተክለ ሃይማኖት
ቄስ ምሕረቱ
በሐይማኖት ምግባራቸው ትክክለኛ ያልነበሩ
አሳሳች ነበሩ። እንደ አቶ ምንዋጋው ከሆነ፤
“እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ እናንተ የዓለም
ብርሃን ናችሁ” የተባሉ ካህናትና መነኮሳት
ማጣፈጣቸው ቀርቶ ራሳቸው አልጫ ሲሆኑ፣
ብርሃንነታቸውን በጨለማነት ሲተኩ አያድርስ
ነው።
ቄስ ምሕረቱ
ከሰው ሕይወት ይልቅ የገንዘብ ፍቅር እንደሚበልጥባቸው
የአቶ ቦጋለን መሞት ከእመት ውድነሽ ሲሰሙ
የመለሱት መልስ ምስክር ይሆናል።
የአባ
ምሕረቱን የሥነ ምግባር ደረጃ የአባ ቦጋለን
ሬሳ እንዲያመጡ በሚልኳው ሰዎች በኩልም ማየት
ይቻላል። ገብሬ የተባለ አገልጋያቸውን በተላላፊ
በሽታ ነው የሞተ ወደተባለው የቦጋለ መብራቱ
ሬሳ ወዳለበት ቤት ልላከው ወይስ ይቅር እያሉ
ከተወዛገቡ በኋላ “ይሂድ ግዴለም፤ እግዚአብሔር
ለእኔ ካለው ምንም አይሆንም፤ … መቼስ የሰው
መፈረጃ ከመሆን የማይሻል የለም።” እያሉ
ሰው ምን ይለኛል በሚል ስሜት ብቻ መወጠራቸውን
ያሳያል። ይህም ሐዲስ በሐይማኖታዊ ግብራቸው
ሳይሆን በጥቅም የሚመሩ ሰዎች መኖራቸውን
ሲያሳዩን ነው።።
ቄስ
ሞገሴ ደግሞ ዕውቀት አጠር ስለነበሩ ድጋፋቸውም
ሆነ ተቃውሟቸው የእምነቱን ሕግጋት የተከተለ
ሳይሆን የፊታውራሪና የቀራቢዎቻቸው ዓይንና
ግንባር ብቻ ነበር። ለጉዱ ካሣ አንዱ ራስ
ምታትም እነፊታውራሪን ገሥጸው ወደበጎ ከመመለስ
ይልቅ ለግፉ ተግባራት ተባባሪ የሆኑ እነአባ
ሞገሴ መሆናቸው ነው። ጉዱ ካሣ ስለዘመናችን
አባ ሞገሴዎችም እንዲህ የሚለን ይመስላል፡-
“አባ
ሞገሴ እንደምታውቋቸው የራሳቸው ሐሳብ
የሌላቸው፣ የሰውን ሐሳብ ብቻ ከዓይኑና
ከግንባሩ አይተው ለመተርጎም ችሎታ ያላቸው፣
ሆዳቸውን የሞላና በፈለገው መንገድ የሚመራቸው፣
ተግባራቸውን ለሆዳቸው የሸጡ የለወጡ ናቸው፡፡”
እያለ ይወርፋቸዋል።
ከጉሊትና
ከናሞራ ባላገሮች ተልከው የመጡት ሽማግሌ
ሲናገሩም አባ ሞገሴ ፊታውራሪ ሲቆጡ አይተው፣
“ዝም ይበሉ እርስዎ ምን ያሉ የሽማግሌ ባሕሪ
የሌላቸው ናቸው እባካችሁ!
እዚህ
ጠብ ለመፍጠር የሰይጣን መላክተኛ ሆነው ነው
የመጡት?”
ማለታቸው
የአባ ሞገሴን የወረደ ሥነምግባር ያሳያል።
የሥነ ምግባር ትንተናችንን ሙሉ የሚያደርገው
አባ ሞገሴንና መሰሎቻቸውን ከቤተ ክህነት
አውጥተን ማየት ከቻልን ብቻ መሆኑን ደግሞ
አጥኚው ያስረዳሉ።
አባ
ሞገሴዎች የሌሉበት የማኅበረሰብ ክፍል ካለ
ያ ማኅበረሰብ ከመለካውያን የጸዳ ስለሆነ
ዕድለኛ ነው፡፡“መለካዊ” ማለት በሃይማኖት
ስም የንጉሥን ፈቃድ ብቻ የሚፈጽም እግሩ ቤተ
ክርስቲያን ልቡ ቤተ መንግሥት ያለ ጳጳስ ማለት
ነው። እንደነዚህ አይነት ሰዎች “ድርጓቸውም
ሹመታቸውም ከንጉሡ በመሆኑ ፣ ብዙ ጊዜም
ከነገሥታቱ ጋር ስለሚውሉ ምንም ዓይነት ችግር
ቢያዩ በዝምታ ከማሳለፍ በቀር የሚቃወሙበትና
የሚገሥጹበት አጋጣሚ አልነበረም፡፡” ይላል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ ለሐይማኖታዊ ግብራቸው
በሀቀኝነት የሚቆሙ አይጠፉም። እንደዚህ
አይነት ጊዜ ብዙ ጊዜ አለመግባባትና ችግር
የሚፈጠረው ሹመትና ገንዘብን ንቀው በነበሩ
አባቶች እና ለገንዘብ ሲሉ በመነኮሱትና ክህነት
በተቀበሉት መካከል ነበር።
ስለ
አባ ተክለ ሃይማኖት ደግሞ “እየውልህ!
ቤተ
እግዚአብሔር እንደዚህ ላሉት ሽፍቶች፣ እንደዚህ
ላሉት ዘራፊዎች ዋሻ ሆነች!
እየውልህ!
ካህናታችን
ከሐዋርያታችን የሚበዙት ከአለቆች ጀምሮ
በመነኮሳቱ አልፎ እስከተራ ደብተሮች እስከዲያቆናቱ
ድረስ አንዱ አስማት አድራጊ። አንዱ አስማት
ፈቺ፣ ሌላው ጋኔን ስቦ አምጪ ሌላው አስወጪ፣
አንዱ መቅሰፍት አምጪ ሌላው ምሕረት አሰጪ
ነን እያሉ ውሸታቸውን በየጥምጥማቸው በየቆባቸው
በየደበሏቸው ሸሽገው ሊመሩት ሊያስተምሩት
በተሰጣቸው መንጋ የሚጫወቱ ናቸው!።
ታዲያ ከእነዚህ ጋር ማኅበርተኛ ሆኖ በአንድ
ስመ እግዚአብሔርን መጥራት በተቀደሰ ስሙ
ማፌዝ አይደለም?።
እየውልህ! ይህ
ነው ከምወዳት ቤተ እግዚአብሔር ያራቀኝ!
ሰው
የሚለው ሌላ ነው፡፡ ነገር ግን እውነቱ ይህ
ነው፡፡” እያለ በመጻህፉ ገጽ 428
ላይ
ያስቀምጣቸዋል።
ስለእኝህ
አስመሳይ ሰው ወይም አባ ተክለ ሃይማኖት
የቀረበው ምጸታዊ ገለጻ ቤተ እግዚአብሔርን
ተጠግተው በሚያረክሱት የካህናት አባላት ላይ
ያነጣጠረ ጠንካራ ሂስ ነው። ጉዱ ካሣ ስለብዙኀኑ
ካህናት ምግባረ ብልሹነት ለበዛብህ ሲነግረው
የነበረውን በተግባር የሚያሳይ ነው። ሰብለ
የአባ ተክለ ሃይማኖትን የመነኩሴ ደበሎና
ቆብ መግፈፍ በአንድ በኩል ትእምርታዊ ሆኖ
እናገኘዋለን። አባ ተክለ ሃይማኖት የማይገባቸውን
ሃይማኖታዊ ክብር በአስመሳይነት ስለተጎናጸፉ
ያን በመግፈፍ እውነተኛ ማንነታቸውን የማጋለጥ
ሚና ሲኖረው፣ ያ የተጨማለቁበት ትውኪያ ደግሞ
የኃጢአታቸውን፣ የርኩሰታቸውን፣ የዝቅጠታቸውን
መጠን ማሳያ ነው።
እንደ
አቶ ምንዋጋው ከሆነ፤ ይህን የአባ ተክለ
ሃይማኖትን “ቤተ እግዚአብሔርን ተጠግተው
በሚያረክሱት የካህናት አባላት” ማሳያ ብቻ
አድርጎ ማቆም አያስፈልግም። ይልቁንም
እርሳቸውን “ቤተ መንግሥትን ተጠግተው”
ያልተገባ ሥራ በሚሠሩ የካቢኔ አባላትም መመሰል
ይቻላል። ይህ የዘመናችን መንፈስ መገለጫ
ስለሆነ ደግሞ ዘረኝነት፣ ጉቦኝነት፣ ፣
ሴሰኝነትና ዕብሪት አድርገን ልንተረጉመው
እንችላለን።
አበጀ በለውና
ነጋዴው ዓሊ ጅብሪ
አበጀ በለው
በፊታውራሪና በሹማምንታቸው የሚፈጸመው ግፍ
ሲበዛ ተመልክቶ ለብዙኀኑ መብት መጠበቅ ሲል
የሸፈተ ገበሬ ነው። ሊዘርፉ የሄዱትን ፊታውራሪ
ከማረካቸው በኋላ የሚናገራቸው ነገርም ይህን
ዓላማውን ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል። እርሳቸው
ተማርከውም እንኳ ባልተረታ መንፈሳቸው አበጀ
በለውን “ሕዝቡን ያሳመጽህ ሽፍታ ነህ” ቢሉትም
አበጀ ግን ሲመልስላቸው ዕውነቱን ያግታቸው
ነበር።
“ሥልጣንን
በዙሪያቸው አጥረው በሥልጣን ውስጥ ተሸሽገው
ድሀ የሚዘርፉትን፣ ድሀ የሚቀሙትን፣ በራሳቸው
ወንጀል ድሀ አስረው የሚገድሉትን ግፈኞች
ሽፍቶች እቃወም ነበር እንጂ ሽፍታ አልነበርሁም።
እቤቴ ተቀምጨ ባለሥልጣኖች የሚሠሩትን ግፍ
በሕግ ለመቃወም ስላልቻልሁ ቤቴን ትቼ መሰደዴ
ሽፍታ አያሰኘኝም። አብረውኝ ሰባት ዓመት
በዱር በገደሉ የተንከራተቱት ብዙዎች ስለሆኑ
አንዱን በአጋጣሚ አግኝተው ቢጠይቁት እንኳን
የሰው የከብት ደም ሲፈስ ማየት የማልወድ
መሆኔን ይነግርዎታል። ደም ሲፈስ ከማየቱም
ደግሞ የድሀ ሕይወትና ንብረት እንዲጠበቅበት
የተሠራው ሕግና የተሰጠው ሥልጣን ተጣሞና
ተቆልምሞ ለድሀ ሕይወት ማጥፊያ፣ ለንብረት
መዝረፊያ፣ ለአመጽ መፈጸሚያ ሲሆን ማየት
ከሁሉ የበለጠ ያስጠላኛል፤ በጣም ያነገፈግፈኛል፡፡”
እያለ የልቡን ይነግራቸዋል። ይህም በገሃዱ
አለም የሚታዩ ለህዝብ ሲሉ የሚታገሉ ሰዎችን
ያስታውሰናል።
ነጋዴው
ዓሊ ጅብሪል በበኩሉ የንግድ ሥነ ምግባር
የሌለውና ለህዝቡ ሲሉ በሚታገሉ ግለሰቦች
ጋር አንድ አገር ላይ የሚኖር አስከፊ ሰው
ነው። “የገበያ ሽብር ለሌባ ይበጃል” እንደሚባለው
ሁሉ የንግድ ሥነ ምግባር ሲጠፋ ነጋዴዎች ሁሉ
ሕጋውያን ቀማኞች ይሆናሉ። በዛብህ አዲስ
አበባ ወደጉለሌ ሲሄድ ሁለት የጎጃም ነጋዴዎች
ሲነጋገሩ ያደመጣቸውን እናንሳ “አሁንኮ
ዐሊ ጅብሪ ቆዳችንን መዝንልንና ዋጋ እንነጋገር
ብንለው አንድ ጊዜ ‘ሚዛኑ ተሰብሯል፤’ አንድ
ጊዜ ‘መዛኙ ታሟል’ እያለ ዛሬ ነገ የሚለን
ፋሲካ እስኪደርስለት ነው፡፡” አለ አንዱ
ነጋዴ። “ፋሲካ ሚዛን ይሆናል ወይስ መዛኝ?”
አለ
ሁለተኛው፡፡ “የለም ‘ዛሬ ነገ እያልሁ ፋሲጋ
እስኪለግት ካቆየኋቸው ለማጫረት ጊዜ ያጥራቸውና
በርካሽ ዋጋ ጥለውልኝ ይሄዳሉ’ ብሎ ነው
እንጂ።” እያሉ ስለ ዓሊ መጥፎ ስነምግባር
አውርተዋል። ይህም ዝም ብሎ ከመጻህፉ ውስጥ
የተገኘ አይደለም እነደውም የዘመናችንን
የዘመናችንን የንግድ መንፈስ የሚወክል
ይመስላል።
የቦጋለ
መብራቱን ቻይነት
ቦጋለ ትዕግስተኛና
ቻይ በመሆኑ ደግሞ ለትዳሩ መቆም አቅም ሰጠው።
ችግር ሳይሸነፉለት ሲለምዱት ከእርሱ ጋር
እየታገሉ እየወደቁ እየተነሡ ሲኖሩ ጥሩ ነው።
ከችግር ጋር ሲታገል የኖረ ቆዳው ይወፍራል፤
ጅማቱ ይጠነክራል፤ ጡንቻው ይደነድናል፤
የተጣለበትን ሸክም ሁሉ መሸከም ይችላል፤
የገጠመውን ሁሉ ያሸንፋል። ስለዚህ እድሜ
ላሳዳጊያቸው፣ እድሜ ለአስተማሪያቸው፣ እድሜ
ለችግር፣ ቦጋለ መብራቱን ቆዳቸውን አወፍሮ፣
ጅማታቸውን አጠንክሮ ትግል እያስተማረ
አደንድኗቸዋል። ስድብና ቁጣ፣ የንቀትና
የግልምጫ ውሽንፍር እንዳይገባቸው አድርጎ
ሁሉን እንዳመሉ እንዲችሉ አድርጎ ላነፃቸው
ለቀረጻቸው እድሜ ለችግር አቶ ቦጋለ ሁሉንም
ቻይ ነበሩ። ይህ
የአቶ ቦጋለ መቻል ትዕግሥታቸውና መሸነፍን
እንደውርደት አለመቁጠራቸው ከእመት ውድነሽ
ይቅር ባይነት ጋር የተቆጡበትንና ምርር ብለው
ያለቀሱበትን ቶሎ የሚረሱ ከመሆናቸው ጋር
አንድ ላይ ሆኖ ጠቅሟቸዋል። ይህም ጊዜ ባለፈ
መጠን ባልና ሚስት እንዲቻቻሉ፣ ባሕርይ
ለባሕርይ እንዲተዋወቁ፣ ለፍሬ እንዲበቁ
‘ማን አለው?
ማን
አላት?’ እየተባባሉ
እንዲተሳሰቡ አድርጎ ትዳራቸውን አጸናላቸው።
በዚህ ገጸባህሪም ውስጥ በትዳር እና በማህበረሰብ
ውስጥ የትዕግስትንና የጽናትን ተምሳሌትነት
መማር እነደሚቻል አጥኚው ያስረዳሉ።
የቀኛዝማች
አካሉ <<ጽርየት>>
(ለሌሎች
ክብር መኖር)
ቀኛዝማች
አካሉ ፊታውራሪ መሸሻን በጣም ይወዷቸዋል።
ትውልዳቸውም እኩል ነው። ፊታውራሪ መሸሻና
የፊታውራሪ አሰጌ ግጭት በሆነ ጊዜ ደግሞ
ቀኛዝማች የራሳቸውን ክብር ረስተው የፊታውራሪ
አገልጋያቸው ለመሆን የቆረጡ ሰው መሆናቸው
በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ባይሆን ኖሮ የመሰንበቻው
ሁኔታቸው የፊታውራሪ አሰጌ ወገን አስመስሎ
ባስጠረጠራቸው ነበር። በወሬው ሁሉ የፊታውራሪ
መሸሻ ጀግንነትና የፊታውራሪ አሰጌ ፈሪነት
ሲነሣ ጥርሳቸው ሌሎችን ለመምሰል ያክል ቢስቅም
ግንባራቸው ሲቋጠር ወይም አንዳንድ ምክንያት
ፈጥረው ከዘመድ መሐል ተነሥተው ሲወጡ ወይም
ሌሎቹ የሚያደርጉትን ሁሉ በማድረግና ባለማድረግ
መሐከል መቁረጥ አቅቷቸው ሲያመነቱ ይታዩ
ነበር።
ምክንያቱ
ሌሎቹ የማያውቁትን የፊታውራሪ አሰጌ ፈሪ
አለመሆን እርሳቸው ያውቁ
ስለነበረ ነው።
ነገር ግን ተነስተው ዘራፍ አላሉም።
ይህም ለሌሎች
ክብር መኖር የመሰለ
ህይወትን ያሳየናል። አቶ
ምንዋጋው ሲያጠቃልሉም በአጠቃላይ
ፍቅር እስከመቃብር ላይ ያሉ ገጸባህሪያትን
ብንመለከት የአሁኑ ዘመንም የማህበረሰቡ
ነጸብራቅ ሆነው እናገኛቸዋለን። የሐዲስን
ማኅበራዊ ሂስ በታላላቆቹ ገጸባህሪያት ብቻ
ሳይሆን በታናናሾቹም ላይ የሚያሳይ በመሆኑ
ለዘመናት ቢነገርለት
የማይሰለች ልብወለድ ነው። በመሆኑም
ሐዲስ በስራቸው ለማህበረሰቡ መስታወት ሆነዋል።
No comments:
Post a Comment