የሰው
ልጅ ከፍጥረታት ሁሉ ብልህ እና አርቆ አሳቢ
ነው። ከጥንት የጋርዮሽ ዘመን ጀምሮ የተለያዩ
ቴክኖሎጂዎችን ሲጠቀም ኖሯል። በቤቱ ውስጥም
እንስሳትን እያላመደ ያቆያል። ነገር ግን
አንድ ለማዳ ሳትሆን በቤቱ ውስጥ የምትራመስ
ጎጆዋን በሰው ጎጆ ቀልሳ የምትኖር እንስሳን
ጨርሶ ማራቅ አልቻለም። ብዙዎች ስሟን እንኳን
ለመጥራትን ሲቀፋቸው ይስተዋላል። አይጥ
በእንግሊዘኛው አጠራር mouse
ወይም rat
አፈጣጠሯ
ከአጥቢ እንስሳት መካከል ትመደባለች። እንዲሁም
በፈጣን እንቅስቃሴዋ እና በማሽተት ችሎታዋ
ከፍተኛነት ትታወቃለች።
የአይጥ
እድሜ 18 ወራት
ሲሆን፤ በርካታዎቹ ግን በተለየዩ አደጋዎች
ምክንያት አንድ አመት ሳይሞላቸው ይሞታሉ።
በአብዛኛው በእንጨት እና ከአፈር በተሰሩ
ቤቶች ውስጥ በቀላሉ ገብታ ለመኖር የሚያስችላል
ጠንካራ ጥርሰንም ታድላለች። አንዳንዴም
በድንጋይ እና በብሎኬት በተሰሩ ቤቶች ውስጥ
ከገባች ዘሮቿን በማብዛት ተደላድላ ለመኖር
አትቸገርም። እናም በኢትዮጵያ ደግሞ አብዛኛው
ቤቶች የተሰሩት ከአፈር እና ከእንጨት በመሆኑ
በእያንዳዱ ጓዳ ውስጥ አለች ቢባል ማጋነን
አይሆንም። አለቃ ገብረሃናም ምግብ በሚበሉበት
ቤት ውስጥ ትንሿ እንስሳን ከእንጀራ ማስቀመጫው
ስፍራ በማየታቸው ከሞሰቡ አይጡ ብለው መቀኘታቸውን
ታሪክ ይነግረናል። ነገሩ ጥንትም ትንሿ እንስሳ
እንደ ድመት ከሰዎች ጋር ተላምዳ ቤት ውስጥ
እንትኖር አይፈቀድላት እንጂ በእያንዳንዱ
ቤት ግን በየስርቻው የመገኘቷን ጉዳይ ያሳያል።
ያለፈቃድ በቤት ውስጥ የመገኘቷ ጉዳይም
ብዙዎችን ሲያንገበግባቸው ይኖራል።
በተለይ
የሰፈራችን እድሜ ጠገብ ልብስ ሰፊ አቶ አክሊሉ
እንስሳዋን ክፉኛ አይወዷትም። በአንድ ወቅት
በቤታቸው ራዲዮናቸውን ከፍተው አረፍ በአሉበት
ያለአንዳች ምክንያት ከዘራቸው ላይ ተጠምጥማ
ስታበቃ ወደ ጉድጓዷ የገባችበት ጊዜ ለእርሳቸው
እንደ ህልም ነው። ከዚያ ጊዜ ወዲህ ላገኙት
ሰው ሁሉ ይቺ ከይሲ ፍጥረት ከዘራዬን አረከሰችው
እያሉ ለለቅሶ እና ለጥየቃ በየሄዱባቸው
በቦታዎች ሁሉ ሲያንቋሽሿት ይውላሉ። አጥይ
ብለው እንኳን ደፍረው መጥራት ስለማይሆንላቸው
«ስሟን
ቄስ ይጥራውና» እያሉ
ነው ወጋቸውን የሚጠርቁት። እናም በየዕለቱ
ወጥመድ ቢያዘጋጁ፤ መርዝ ቢነሰንሱ መንታ
የመሰሉ ዝርያዎቿን ይገድላሉ እንጂ ጭራሽ
ልትጠፋ አልቻለችም። አይጥ አዳኝ የተባሉ
ድመቶችን በቤታቸው ውስጥ ቢያሰማሩም ድመቶቹ
ከመንደሩ በሚቃርሙት ትርፍራፊ ምክንያት
ሆዳቸውን እየነረቱ የቤቱ አሮጌ ሶፋው ላይ
መገላበጡት ተያይዘውታል። በመሆኑም እንስሳዋን
ከቤታቸው ለማጥፋት አዲስ መላ በአዕምሯቸው
እስኪመጣላቸው ድረስ እንደተናደዱ ይኖራሉ።
አንድ
ቀን ታዲያ አዛውንቱ ከስራ ወደ ቤታቸው ገብተው
አረፍ እንዳሉ ባለቤታቸው ምግብ ለማቅረብ
ሞሰቡን ከፈት ቢያደርጉት አጅሪት ተስፈንጥራ
ወጥታ በአልጋቸው ስርቻ ውስጥ ተደበቀች።
አቶ አክሊሉም የዛን ቀን እህል አልበላም ብለው
እስክ ምሽቱ ሶስት ሰዓት ድረስ ሲገላገሉ
ቆይተው ደረቅ ዳቦ አስገዝተው ተመገቡ። አቶ
አክሊሉ ነገሩ የከነከናቸው እርሳቸው ያልበሉትን
እንጀራ እንዴት አይጧ ቀድማ ትመገበዋለች
የሚለው መበለጥ ነበር። ባለቤታቸው ደግሞ
«የዛሬን
ነው እንዴ አይጧ ሁሌስ ሽር የምትለው ከሞሰቡም
አይደል እንዴ» ብለው
ንዴታቸውን የሚያባብስ ንግግር አከሉላቸው።
«እንዴት
በተከበርኩበት አገር አንዲት መናኛ ጅራታም
እንስሳ ለፍቼ ያገኘሁትን ምግብ ቁጭ ብላ
ትሰለቃለች» በሚል
እልህ እንስሳዋን ለግድያ ሲፈልጓት አደሩ።
ቤቱን አመሰቃቅለው ያገኙት ግን በሶስት ክፍል
ቤታቸው ውስጥ የሚገኙ አስር ጉድጓዶችን ብቻ
ነበር። አስር ጉድጓዶች ስትፈለፍል እኔ የት
ነበርኩ ብለው እራሳቸውን ቢጠይቁም መልስ
አላገኙም። ምክንያቱም አንድም ቀን ከቤታቸው
ውጪ አድረው አያውቁም ነበር። ከተማሰው ቤታቸው
ይልቅ ግን የአባወራነታቸው ቀድሞ የመመገብ
ክብር መደፈሩ አልዋጥ ብሏቸዋል።
አዛውንቱ
ሚስት ከአገቡ ወዲህ ዶሮ ወጥም ይሰራ፣ እንጀራም
ይጋገር ምንአለፋችሁ ማንኛውም ምግብ ከተሰራ
ቀደሞ የሚቀርበው ለእርሳቸው ነበር። አሁን
ግን ስሟን እንኳን በወጉ በማይጠሯን እንስሳ
ተቀድመዋል። ለአቶ አክሊሉ ከአይጧ ጋር የያዙት
እልህ አስጨራሽ ትግል ቀድሞ የመብላት እና
ያለመብላት ነው። በመሆኑም ጉዳዩ ለእርሳቸው
የሞት እና የሽረት ያክል ሆኗል። ነገን አግኝቿት
ልኳን ካሳየኋት በኋላ አባወራነቴን አስከብራለሁ
በሚል ሃሳብ ሌት ተቀን እንስሳዋን የሚያጠፉበት
መንገድ እንዳሰላሰሉ ናቸው። እርሷም ቀድማ
ምግቡን መቀማመሷን አላቆመችም።
እናም
አማካሪም ሆነ ሁነኛ ባለሙያ ሲያፈላልጉ ሰባት
የሰቆቃ አመታትን ያሳለፉት አዛውንት ያለፈው
እሁድ እለት ልባቸው እንደተረጋጋ የሰማ ጎረቤት
ሁሉ ቤታቸውን ከአፍ እስከ ገደፉ አጥለቅልቆት
ሰንብቷል። ላገኙት ሰው ሁሉ ይችን እርኩስ
መና የሚያስቀር ቴክኖሎጂ አጊኝቻለሁ እያሉ
ይናገራሉ። ቀድመው በቤታቸው ለመመገብ
የሚያስችላቸውን እድል የተነፈጉ አባወራዎች
ሁሉ የቴክኖሎጂው ተቋዳሽ ለመሆን ጓጉተዋል።
አቶ አክሊሉ ግን መፍትሄውን በቤታቸው ከሚያስነግሩ
ይልቅ በእድር ጡሩንባ ወይም በራዲዮን ቢያስነግሩ
ነበር አንጀታቸው የሚርሰው።
ነገር
ግን የሰፈሩ ሰው ጉትጎታ ስላላፈናፈናቸው
ይፋ ለማድረግ ከተሰብሳቢው መካከል እንደተወካይ
የሚያገለግሉ አራት ሰዎች መርጠው መደ ቤታቸው
ጓደ ይዘዋቸው ገቡ። ኩራት በተላበሰ አነጋገር
«ይህ
የምትመለከቱት ከብረት የተሰራ መሶብ አንድም
እንስሳ የማያስገባ ከመሆኑም በላይ ቁልፉ
በባለቤቴ እጅ ላይ ብቻ ይገኛል። ሲፈለግ
በኩልፍ ይከፈታል ሳይፈለግ ደግሞ ይዘጋል።
በመሆኑም ያች እርኩስ እንስሳ ከእኔ የተረፈውን
ወዳድቆ ታገኝ የሆን እንጂ ቀድሞ የመብላቷ
ጉዳይ አበቃለት» ብለው
በክብ ቅርጽ የተሰራውን መሶብ እንደተዘጋ
አሳዩ። አራቱ አባወራዎች አዲሱን ግኝት
በአድናቆት ከተመለከቱ በኋላ ሳሎን ለተሰበሰበው
ሰው ለማስረዳት በሽግድምድሞሽ እርምጃ ቀኝ
ኋላቸውን ያዙ። ለተብሳቢውም አዲሱ ግኝት
በሰበዝ ከሚሰራው መሶብ ይልቅ የተሻለና አይጥም
ሆነ በረሮ ሊያሳልፍ እንደማይችል አጠናክረው
የአይን እማኝነታቸውን በየተራ አቀነባብረው
አሰሙ።
![]() |
| አባ አክሊሉ እና ቀድሜ እንድበላ |
ከወደ
መስኮቱ ስር የተሰበቡት ወይዛዝርቶች ግን
አዲሱ ግኝት ላይ ፊታቸውን እነደማዞር አደረጉበት።
የብረት ሞሰቡ ሙቀት ሲነካው እንጀራውን
በፍጥነት የማሻገት እድሉ ሰፊ ስለሚሆን ምግቡን
በየቀኑ ማሞቅ እነደሚኖርባቸውና ለተጨማሪ
ስራ እንደሚዳርጋቸው ቅሬታ በማንሳት ማጉረምረም
ጀመሩ። አቶ አክሊሉ በዚህ ጊዜ ግኝታቸው
እንዳይዋደቅባቸው በመስጋት በፍጥነት ተነስተው
በከፍተኛ ድምጽ ምግቡ እንዳይበላሽ ካስፈለገ
ወደ ፊት የብረቱ መሶብ ማቀዝቀዣ ያለው እንዲሆን
ከባለሙያዎች ጋር መነጋገር እንደሚቻል ተናገሩ።
ለአሁኑ ግን ለአንገብጋቢው ችግሩ መፍትሄ
መገኘቱን በማብሰር ጉዳዩን በአጭሩ ደመደሙት።
መሶቡንም «ቀድሜ
እንድበላ» የሚል
ስም ካወጡለት በኋላ ሁሉም በየቤቱ ቢጠቀምበት
አይነተኛ ዘዴ መሆኑን በመንደሩ ነዋሪ ፊት
ማስታወቂያ ሰሩለት።
«ቀድሜ
እንድበላ» የተሰኘው
መሶብ በአቶ አክሊሉ ቤት ግልጋሎት ላይ እየዋለ
ቢሆንም በተቀሩት የመንደሩ ሰዎች ቤት ግን
ጥቅም ላይ ለማዋል የአዛውንቱ ባለቤት ተሞክሮ
መረጋገጥ ስለነበረበት ጥቂት ቀናት ለመጠበቅ
የግድ ሆኖ ነበር። የአቶ አክሊሉ ባለቤት ግን
ሩህሩህ እና አይጥም እንስሳ ነው ምን በልቶ
ያድራል የሚል አስተሳሰብ የያዙ በመሆናቸው
የቀድሜ እንድበላን ጥቅም በሙሉ ልባቸው ወደ
መንደሩ ለማስተላለፍ አልቻሉም። ደግሞም ሁል
ጊዜ መሶብ እየቆለፉ እና እየከፈቱ ምግብ
ማውጣት እና ማስገባት አሰልቺ መሆኑን በመረዳታቸው
እስከዛሬ የኖርኩበት ነው ያገኘሁትን በመሶብ
አስቀምጬ ብበላ ይሻለኛል የሚል ሃሳብ
እንዳደረባቸው መገመት አያስቸግርም። እናም
የአዲሱ ግኝት ጥቅም በወይዘሮዋ ማረጋገጫ
ማጣት እና በአንዳንድ ቸልተኛ አባወራዎች
ቀድሞ የመብላት ፍላጎት ማነስ ምክንያት
ሳይስፋፋ ቀረ። አቶ አክሊሉ ግን ባለቤታቸው
ላይ ባሳደሩት ጫና ምክንያት ከሚጠሏት እንስሳ
በፊት በቤታቸው ቀድሞ የመብላትን ደስታ በየቀኑ
ማጣጣማቸውን ቀጥለዋል። እውነት ግን እንደ
አዛውንቱ ከእኛ የተረፈውን መብላት ሲገባት
ከእርሷ የተረፈውን መብላታችን የሚያስቆጨን
ስንቶቻችን እንሆን።
