Thursday, January 13, 2022

ሞገደኛው ጋዜጠኛ መንግስቱ ገዳሙ በአንድ ወቅት ፈረንጅ በ700 ብር ቀጥሮ ካፖርቱን እያሸከመ ፒያሳ ለፒያሳ ያዞር ነበር

ጋዜጠኛና ደራሲ መንግስቱ ገዳሙ በ1920 ዓ/ም በሲዳሞ ክፍለሃገር በቡሬ ገጠራማ መንደር ተወለደ፡፡ እድሜው ለትምህርት እንደደረሰም በተፈሪ መኮነን ትምህርት ቤት ፊደል ቆጠረ ፡፡


ከፍ ሲልም በወታደርነት ለማገልገል ተመዘገበ፡፡በወታደርነት ብዙም ሳይሰራ በፖስታና ቴሌግራም ሚኒስቴር ውስጥ ተቀጠረ፡፡በስራው የተመሰገነና ታታሪ ሰራተኛ በመሆኑ በአጭር ጊዜ ውስጥ እድገት አግኝቶ ወደ ድሬዳዋ ተዘዋወረ፡፡ነገር ግን ደመዎዙ አነስተኛ ስለነበር ስራውን በፈቃዱ ለቀቀ፡፡


ከዚያም በተሻለ ደመወዝ በምድር ባቡር ተቀጠረ፡፡በዚያም አልረካም፡፡ያሰበው ያልተሳካለት መንግስቱ እንደገና በኢትዩጵያ ንግድ ባንክ ውስጥ በመዝገብ ቤት ሹምነት ተቀጠረ፡፡ከትንሽ ጊዜ በኋላም ወደትርጉም ክፍል ተዘዋውሮ መስራት ጀመረ፡፡


መንግስቱ በኢትዩጵያ ንግድ ባንክ ተቀጥሮ በሰራበት ወቅት ሁለት ጊዜ የደመዎዝ ጭማሪ አግኝቷል፡፡ከባንኩ ሃላፊዎች ጋር መግባባት ያልቻለው መንግስቱ በማስታወቂያ ሚኒስቴር በጋዜጠኝነት ተቀጠረ፡፡በወቅቱ በጋዜጣው ላይ ያቀርባቸው በነበሩ ጽሁፎች በብዙዎች ዘንድ እውቅናን አገኘ፡፡

በብእሩ ይደርሳቸው የነበሩ ርእሰ ጉዳዮች የስራ ባልደረቦቹ የማይደፍሯቸው ነበሩ፡፡በነበረው የስነጽሁፍ ችሎታም የተለያዩ መጽሃፍትን ይደርስ ጀመር፡፡በጋዜጠኝነት የጀመረው ጽሁፍ ቀስ በቀስ ወደ ደራሲነቱ እንዲያዘነብል አደረገዉ፡፡


ቤሳ የተባለው የመጀመሪያው ልቦለድ መጽሃፍ በ1949 ዓ/ም ለህትመት በቃ፡፡ከዚህ በመቀጠልም የተለያዩ መጽሃፍትን ለማሳተም ችሏል፡፡


መንግስቱ ጥሩ ጸሃፊ ብቻ ሳይሆን ጥሩ አንባቢም ነበር፡፡በመኖሪያ ቤቱም መጽሃፍት ቤት ነበረው፡፡ በእንግሊዘኛ ቋንቋም መጽሃፍ ለመድረስ ችሏል፡፡ ራሱን በራሱ የፈጠረ ምሁርም ነበር፡፡

ሰዋስው | ሞገደኛው ጋዜጠኛና ደራሲ መንግስቱ ገዳሙ።መንግስቱ ገዳሙ


መንግስቱ በወቅቱ የሚከናወኑ የተደበቁ ነገሮችን ለማውጣት ብእሩ ደፋር ነበረች፡፡በጋዜጣው ላይ ያወጣቸው የነበሩ ጽሁፎች በህዝቡ ዘንድ ይነበቡለት ነበር፡፡ በስነጽሁፍ አለም በቆየባቸው ጥቂት አመታት ውስጥ ከ24 በላይ መጽሃፍትን ጽፏል፡፡ኑሮውን ይደግፍ የነበረውም በእነዚህ መጽሃፍት ሽያጭ ከሚያገኘው ገቢ ነበር፡፡


መጽሃፍቱ ውስጥ ያሉ ገጸባህርያት ከህይዎቱ ጋር ቁርኝት ያላቸው ናቸው ይባል ነበር፡፡
የመንግስቱ ገዳሙ ህይዎት በአብዛኛው ውጣ ውረድ የበዛበት ነበር፡፡ የሚሰራቸው ነገሮች የሚያስቁም የሚያስደምሙም ነበሩ፡፡ 

መንግስቱ አንድ ጊዜ ፈረንጅ የአበሻ አሽከር አይሆንም የሚለውን አመለካከት ለመቀየር አንድ ፈረንጅን በሰባት መቶ ብር ደመዎዝ ቀጥሮ ካፖርት እያሸከመ ፒያሳ ለፒያሳ ያዞር ነበር፡፡በአንድ ወቅት ደግሞ ለስራ ጉዳይ አስመራ ይላካል ፤በዚህ ጊዜ በከተማዋ ስላሉ እስር ቤቶች ጽሁፍ ለማቅረብ ይፈልጋል ፡፡ነገር ግን ባለስልጣኖቹ ወደ እስር ቤቱ እንዳይገባ ከለከሉት፡፡


በዚህ የተናደደው ሞገደኛው ጋዜጠኛ መንግስቱ ምሽት ላይ አንድ መላ ይገለጽለታል፡፡ መላውም ወንጀል ሰርቶ ወደ እስር ቤት መግባት ነበር፡፡ይህንን ለማድረግ መጠጥ ቤት ገብቶ ጠርሙሶችን ሰባበረ፡፡በዚህ ጊዜ ግርግር ይፈጠራና በፖሊስ ተወስዶ ይታሰራል፡፡ከሶስት ቀናት እስር በኋላ በዋስ ተለቆ ተመለሰ፡፡ 


እንደተመለሰም ስለአስመራ ማረሚያ ቤቶች በርከት ያሉ መጣጥፎችን በመጻፍ ለማጋለጥ ቻለ፡፡አዲስ አበባ ላይም የተለያዩ ፖሊስ ጣቢያዎችንና ማረሚያ ቤቶችን ለመመልከት ያመቸው ዘንድ ችግር በመፍጠር ፖሊስ ጣቢያዎችንና ማረሚያ ቤቶችን በእስረኝነት ጐብኝቷል፡፡


መንግስቱ ገዳሙ የተለያዩ ስራወችን ለመስራት በመሞከሩ ስሙ በጊዜው በነበረው ትውልድ እንደጉደኛ ይጠቀስ ነበር፡፡መንግስቱ ገዳሙ በአለም የሚታወቁ ሰዎችን በሚመዘግበው የሁ ኢዝ ሁ ባህረ መዝገብ ወስጥ ስሙ ሰፍሯል፡፡ጋዜጠኛና ደራሲ መንግስቱ ገዳሙ በተወለደ በ48 አመቱ በሞት ተይቷል፡፡የቀብር ስርዓቱም ሃምሌ 20 ቀን 1968 ዓ/ም ተፈጽሟል፡፡ 


ምንጭ ከወልደማርያም «ያልተዘመረላቸው» መጽሃፍ

Featured post

ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጠያቂነትን በማረጋገጥ፣ የሕግ በላይነትን በማስፈን፣ መንግሥትና የስራ አስፈጻሚ አካላቱ በመሉ ለሰብአዊ መብቶች መከበር፣ መጠበቅና መሟላት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያሳዩ ልዩ ትኩረትና ክትትል ይሻል

                    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየደረጃው ያሉ የመንግስት አስፈጻሚ አካላትና ኃላፊዎች ላይ የቅርብ ክትትል በማድረግ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር አስተዋጽኦ ሊያደር...