እ.አ.አ በ2011 በደቡባዊው የቀይ ባይር ክልል በኢትዮ ኤርትራ ድንበር ላይ «ነብሮ» በሚል
ስም የተጠራው እሳተጎሞራ መፈንዳቱ የሚታወስ ነው። በወቅቱ በተከሰተው አደጋ የሰባት ሰዎችን ህይወት አጥፍቶ
አልፏል።
ከዚህም ባለፈ ከእሳተጎሞራው ፍንዳታ ጋር በተያያዘ ከምድር ውስጥ አካል የመነጨው እና ጥንቃቄ
ካልተደረገበት ለመተንፈሻ አካላት በሽታ ሊያጋልጥ የሚችል የተፈጥሮ ጋዞች አየር ላይ ተሰራጭተው እንደነበር የከባቢ
አየር ባለሙያዎች ስጋታቸውን ገልፀው እንደነበር ይታወሳል።
በተፈጠረው ፍንዳታ ለተወሰነ ጊዜ የአካባቢው አየር በጭስ
ተሸፍኖ የቆየ ሲሆን ብናኙም ለሳምንታት አየር ላይ ቆይቶ ነበር። በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ አየር መንገድን
ጨምሮ የበርካታ የምስራቅ አፍሪካ አገራት የአየር በረራዎችን አስተጓጉሏል።
በአሁኑ ወቅት በተለያዩ እሳተጎሞራ ሂደት በሚታይባቸው የአፋር ሦስት ማዕዘን (ደንከል ዲፕረሽን) በሚባለው
አካባቢ ክስተቱ በተጠናከረ መልኩ ዳግም ሊመጣ እንደሚችል ፍንጮች መታየት መጀመራቸውን የሥነ ምድር ባለሙያዎች
ያስረዳሉ። በመሆኑም አስፈላጊው እርምጃ እና ጥንቃቄ ካልተወሰደ አደጋውን መገመት እንደማይቻል ነው ባለሙያዎቹ
የሚጠቁሙት።በመሆኑም የክልሉን እሳተጎሞራ በተመለከተ ስለ ቀጣይ ሥራዎች አስፈላጊነት እየተናገሩ ይገኛል።
የሥነ ምድር ባለሙያው አቶ እንቁ ሙሉጌታ፤ በአፋር ክልል ኤርታአሌ አካባቢ የቀለጠ የድንጋይ ሐይቅ ከ120 ዓመት
ጀምሮ እንደነበረ ነው የሚናገሩት። ቦታውም ለእይታ ክፍት የሆነ ቅልጥአለት በመፍጠር ለጎብኚዎች እና ለተመራማሪዎች
መዳረሻ ሆኖ እንደቆየ ነው የሚያስታውሱት።
ይሁንና ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ
የቅልጥአለቱ መጠን እየጨመረ መምጣቱን በቦታው ተገኝተው መገንዘባቸውን ይገልፃሉ። በዚህም ምክንያት ከመሬት ውስጥ
ያለው እሳተጎመራ ግፊት በመጨመሩ ባለፈው ሳምንት ላይ ለእይታ ክፍት ከነበረበት ቦታ አልፎ በመሬት ገጽ ላይ
ቅልጥአለቱ መፍሰስ መጀመሩን ነው የሚጠቁሙት።
እንደ
አቶ እንቁ ገለጻ ከቀድሞው ክፍት እሳተጎሞራ በተጨማሪም በስተደቡብ አቅጣጫ መሬቱ ተሰንጥቆ አዲስ ቅልጥ አለት
ሃይቅ እየተፈጠረ ይገኛል።
ይህም በኤርታአሌ የምዕተ ዓመት የእሳተጎሞራ ሂደት ውስጥ ታይቶ የማይታወቅ አዲስ ክስተት
ሆኗል። ክስተቱ በአጋጣሚ ያልመጣ እና በርካታ ጊዜያትን የፈጀ ቢሆንም ሊያስከትለው የሚችለው ጉዳት እና ቀጣይ
ደረጃውን ለመገመት የሚያስችል ሰፊ ጥናት አልተደረገም።
ከዚህ ቀደም አካባቢው በተፈጥሮ አደጋ ስጋት የማይዳረግ
ተብሎ ይጠቀስ ነበር። አሁን ላይ የሚታዩ የእሳተጎሞራ ሂደት ለውጦች አማካኝነት የስጋት ቀጣና ሊሆን እንደሚችል
ማሳያ ይሆናል። በመሆኑም የአካባቢው ነዋሪዎች፣ ጎብኚዎች እና ተመራማሪዎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የአደጋ
ጊዜ ጥንቃቄ መመሪያ ሊሰጥ እንደሚገባ ነው የሚናገሩት።
«ሊፈጠር የሚችለውን ጉዳት ለመከላከልም ሰዎች ከአካባቢው እስከ 150 ኪሎሜትር ርቀው መገኘት አለባቸው» የሚሉት
የስነምድር ባለሙያው፤ በተለይ የሰው ህይወት እንዳይጠፋ ግንዛቤ ማስፋት እንደሚያስፈልግ ነው የሚገልፁት።
በተለይም
በአፋር ክልል ከእሳተጎሞራው አቅራቢያ ላሉ አፍዴራ፣ ኩርሶዋድ እና በዙሪያቸው ያሉ 20 እና 30 አባወራዎች የሚገኙባቸው ቦታዎች ላይ መንግሥት እና የዘርፉ ባለሙያዎች አስፈላጊው የአደጋ ጊዜ ጥንቃቄ እርምጃ እንዲወሰድ ግፊት ማድረግ እንዳለባቸው ያሳስባሉ።
የጂኦኬሚስትሪ
ባለሙያው አቶ ዳዊት አለሙ በበኩላቸው፤ በኤርታአሌ አዲስ ቅልጥአለት ከመሬት በመውጣቱ በአካባቢው ላይ ጭስ እና
የተለያዩ ጋዞች እንደሚፈጠሩ ይገልፃሉ። በዚህም በዙሪያቸው የሚገኙ ሰዎች ላይ የመተንፈሻ አካላት በሽታ ሊያስከትል
እንደሚችል ነው ስጋታቸውን የሚጠቁመት። በተለይም ሰልፈርዳይ ኦክሳይድ የተባለው ጋዝ ለጤና አደገኛ መሆኑንም
ያስረዳሉ። በመሆኑም የጤና ባለሙያዎች በአካባቢው ላይ ክትትላቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ነው የሚያሳስቡት።
«ከጥንቃቄው
ጎን ለጎን በእሳተጎሞራው ላይ የሚካሄዱ ጥናቶችን በጊዜው ማከናወን ካልተቻለ የሚደርሰውን ጥፋት መገመት
እንደማይቻል የሚናገሩት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የምድር ሳይንስ ክፍል መምህሩ ፕሮፌሰር ገዛኸን ይርጉ
ናቸው።
ከሳተላይት በተገኘ መረጃ የኤርታአሌ እሳተ ጎመራ ሐይቅ ሞልቶ በመፍሰስ እስከ አሁን ድረስ በመሬት ላይ
አምስት ኪሎ ሜትር መጓዙን ይጠቁማሉ። ይህም ማንም ሳያውቀው የተከሰተ በመሆኑ አደጋ ሊያስከትል የሚችልበት ዕድል
ሰፊ እንደነበር ነው የሚናገሩት። በቦታው ላይ ግንባታዎች የማይካሄዱ በመሆኑ እና ሰዎች በብዛት ባለመኖራቸው አደጋ
አልደረሰም።
«ይሁንና በርካታ የአፋር አካባቢዎች ከእሳተጎሞራ ጋር የተያያዘ ያልተጠበቀ ክስተት እንደሚኖር ይገመታል» የሚሉት
ፕሮፌሰር ገዛኸን በዚህ ምክንያት የሚደርሰውን ጉዳት ለመመዘን ብሎም ለመከላከል ሰፊ ጥናቶች መካሄድ እንዳለባቸው
ነው የሚናገሩት።
በአሁኑ ወቅት ጉዳዩን በተመለከተ ተከታታይ ሪፖርቶችን ለመመልከት እና የናሙና ምርምር ለማካሄድ
በቦታው መገኘት እንደሚጠበቅ ይጠቁማሉ። ይሁንና ለተሽከርካሪ በማይመቸው ክስተት ለመገኘት ሄሊኮፕተር ለመጠቀም
እንኳን ዕድሉ እንዳልተገኘ ነው የሚያስረዱት።
በመሆኑም በቀጣይ ጊዜያት በእሳተጎሞራው አማካኝነት የሚደርሱ ጉዳቶችን
ለመለየት ጥልቅ ጥናት መደረግ ይኖርበታል። ለዚህም አስፈላጊው የግብዓት አቅርቦት መመቻቸት እንዳለበት ይናገራሉ።
ጥናቱ በወቅቱ እና በአግባቡ ካልተከናወነ ግን የችግሩን ስፋት ማወቅ ስለማይቻል አገሪቷ ላይ የሚደርሰው ጉዳቱ
ሊያይል እንደሚችል ነው ስጋታቸውን የጠቆሙት።

No comments:
Post a Comment