Saturday, January 27, 2018

የሰሜን ኮሪያ ከደቡብ ኮሪያ ጋር የእንዋሃድ ጥያቄ


 
Two koreans
ሰሜን ኮርያ ሰሞኑን ያልተለመደ አዲስ መልዕክት በብሔራዊ የቴሌቪዥ ጣቢያዋ አማካኝነት አስተላልፋለች። ቀድሞም አንደ አንድ አገር ከነበሩት ደቡብ ኮሪያ ጋር የእንቀላቀል ፍላጎት ጥያቄ ማቅረቧ ግን በርካቶችን ያስገረመ ነበር። ከጣቢያው በወጣው መረጃ መሰረት በአገራቸው እና ከአገራቸው ውጪ የሚገኙ ሁሉም ኮሪያውያን ከሌላ አገራት ድጋፍ ውጩ በሆነ መንገድ አንድነታቸውን ማረጋገጥ እነደሚገባቸው የሚያሳስብ መዕክልት ተላልፏል።
እንደ መረጃው ከሆነ፤ በሁለቱ ኮርያውያን መካከል ነጻ የሆነ በአንድነት ለመመስረት መነሳሳት ያስፈልጋል የሚል ያልተጠበቀ መልዕክት በብሔራዊ ጣቢያው አማካኝነት ተላልፏል። ኮሪያውያን የጦርነት ስጋቶችን ወደ ጎን በመተው ኮሪያ ሰርጥን ሰላማዊ ቀጣና ለማድረግ መነሳሳት እንዳለባቸው አሳስቧል።
የጣቢያው መረጃ የተለቀቀው በአገሪቷ መንግስት እና ፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ ካካሄዱት ውይይት በኋላ እነደነበር እማኞች ይገልጻሉ። ብሔራዊ ጣቢያው የአገራቱ ዜጎችም ገንኙነታቸውን በማጠናከር ከሰሜን ወደ ደቡብ እነዲሁም ከደቡብ ወደ ሰሜን ኮሪያ አገራት ጎዞ ማካሄድን መልመድ እንደሚገባቸው ምክር አዘል መልዕክቱዝን አሰራጭቷል።
በመጨረሻም ያስተላለፈው መረጃ ግን ማስጠንቀቂያ አዘል ቃላትን የያዘ ነበር። በመጨረሻዎቹ አረፍተ ነገሮች ላይ የሁለቱን አገራት ውህደት ሊያደናቅፍ የሚችል ማንኛውንም አይነት ችግር በማጥፋት ፒዮንጊያንግ ቁርጠኛ ስለመሆኗን ነበር ማስጠነቀቂያው የተላለፈው። ይህ የማገባደጃ መልዕክት ግን በብዙዎች ዘንድ በቸልታ አልታለፈም። የፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ፤ የማሳረጊያው መልዕክት የሰሜን ኮርያ መንግስትን እብሪተኝነት መቼም የሚያባራ አለመሆኑን ያሳያል። ምክንያቱም በሁለቱ ኮሪያዎች መካከል ከፍተኛ የፖለቲካ ውጥረት እንዲከሰት ያደረገው የሰሜን ኮሪያ በአካባቢው የምታደርገው ወታደራዊ እንቅስቃሴ መሆኑ ተዘንግቷል። በቃጣናው ላይ የሚደረጉ የኒኩሌር እና የሚሳኤል ሙከራዎች የአካባቢውን ውጥረት አባብሰው አገራቱ መልካም ግንኙነት እንዳያደርጉ እክል መፍጠሩንም በርካቶች ይስማሙበታል።
... 1948 ሰሜንና ደቡብ ኮሪያ በሚል ሁለት አገሮች ከተፈጠሩ በኋላ ደም አፋሳሽ ጦርነት መካሄዱን ታሪክ ያስረዳናል። 1950 እስከ 1953 የተካሄደው የኮሪያ ጦርነት የሁለቱን መለያየት ይበልጥ እንዲሰፋ ያደረገ ክስተት ሆኖ አልፏል፡፡ በጦርነቱ ላይ ሰሜን ኮሪያ ወረራ ማካሄዷን በመቃወም ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ አገራት ከደቡብ ኮሪያ ጎን ተሰልፈው ውጊያ ማካሄዳቸውም ይታወቃል። በተለይም በጦርነቱ ላይ አሜሪካ እና የቀድሞዋ ሶቪዬብረት ከፍተኛ ፖለቲካዊ ሚና እንደተጫወቱ የአካባቢው ፖለቲካ ምሁራን ይገልጻሉ።
ሰሜንና ደቡብ ኮርያ ለሶስት ዓመታት ባደረጉት ጦርነት ኢኮኖሚያቸው ከፉኛ የተጎዳ ሲሆን፤ አገራቱን ወንድማማች ህዝቦች ያቀያየመ ነበር። ጦርነቱ ከሶስት ሚሊየን በላይ የሰው ህይወት መጥፋቱ፣ በሚሊዮኖች የሚጠጉትን ደግሞ ለአካል ጉዳት እንዲሁም አስር ሚሊኖች ዜጎች ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲለያዩ ምክንያት ሆኗል። በዚህም ምክንያት በአስከፊነቱ በአለም ላይ ከሚጠቀሱ ጦርነቶች መካከል የሚመደብ ነው። በርካቶችን ለሞት እና ለመፈናቀል የዳረገው የኮሪያ ልሳነ ምድር ርነት ከተገባደደ በኋም አገራቱን መልሶ ወደ አንድነት ሊያመጡ የሚችሉ በርካታ ውይይቶች በተለያዩ ጊዜያት ተካሂደዋል። አለም አቀፍ አደራዳሪዎች ጭምር የተካፈሉባቸው የእርስ በእርስ ውይይቶች ተደርገዋል። ነገር ግን ውይይቶቹ መጨረሻቸው ት አልባ በመሆኑ ምክንያት አገራቱን ለማዋሃድ የተደረጉ ሙከራዎች በሙሉ ሊሳኩ አልቻሉም።
ከቅርብ አመታት ወዲህ ደግሞ የሰሜን ኮሪያ የኒኩሌር እና ሚሳኤል መሳሪያዎች ሙከራ አገራቱን ዳግም ወደ ጦርነተ እንዳያመሩ ስጋት የጫረ ጉዳይ ነበር። ሰሜን ኮሪያ ከዚህ ቀደምም በተለያዩ ጊዜያቶች ጎረቤቷን ደቡብ ኮሪያን፣ አሜሪካንን እና የተለያዩ የእስያ አገራትን በፕሬዝዳንቷ ኪም ጁንግ ኡን አማካኝነት ስታስፈራራ አልፎ ተርፎም የኒኩሌር ማብላዋ ውስጥ ያበለጸገችውን መሳሪያ እየሞከረች እራሷን ለጦርነት ስታዘጋጅ መቆየቷ የሚታወስ ነው። የኮሪያውያኑ ልሳነ ምድርም በአለም ሃያላኑ አገራት አሜሪካ፣ ሩሲያ፣ ቻይና እና የተለያዩ የእስያ አገራት የፖለቲካ የበላይነት ለማስጠበቅ በሚደረግ ፉክክር መሃል ገብቶ ቆይቷል። በተለይ በዶናልድ ትራምፕ ፕሬዝዳንትነት የምትመራው አሜሪካ በተለያዩ ጊዜያት የሰሜን ኮሪያን እብሪተኛ መንግስት ለመቅጣት እና እራሷን ከማንኛውም ጥቃት ለመከላከል አስፈላጊውን መታደራዊ ልምምድ እያደረገች መሆኑን ትገልጻለች።
በኮሪያውያኑ ልሣነ ምድር የተደራጀ ወታደራዊ የጦር ሠፈር ያላት አሜሪካ ከወዳጆቿ ከጃፓን እና ደቡብ ኮሪያ ጋር የተቀናጀ የባህር እና የየብስ ወታደራዊ ልምምዶችን ማካሄዷነ ቀጥላለች። በየአመቱም በቀጣናው ከሚገኙ አጋሮቿ ጋር የሁለት ሳምንታት ግፋ ሲልም ለወራት የዘለቀ ወታደራዊ ልምምድ የምታደርገው አሜሪካ ልምምዱ በማንኛውም ጊዜ ሊሰነዘር የሚችል የሰሜን ኮሪያን ጥቃት ለመከላከል እና የአገሯን እንዲሁን የአካባቢውን ደህንነት ለማስጠበቅ አላማ ያደረገ መሆኑንም ትገልጻለች።
አልፎ አልፎ ግን ከደቡብ ኮሪያ እና ሰሜን ኮሪያ ድንበሮች ላይ ለቅኝት በሚል ሰበብ የሚያንዣብቡ የአሜሪካን የጦር ተዋጊ ጄቶች ሰሜን ኮሪያን ከማስቆጣቱም አልፉ የሁለቱ ኮሪያውያኖችን የሻከረ ግንኙነታቸውን ዳግም እንዳያንሰራራ ሲያደርግ የቆየ እንቅስቃሴ ነው። ሰሜን ኮሪያ የአሜሪካ ከደቡብ ኮሪያ ጋር የተያያዘ ወታደራዊ ልምምድ ማከናወኗ ወደለየለት ግጭት ሊያመራ የሚችል በር ከፋች ነው በማለት ማስጠነቀቂያዋን ስትሰጥ ሰንብታለች።
በዚህም ተባለ በዚያ ግን የሁለቱ ኮሪያውያን ወዳጅነት በእራሳቸው መካከል ከተደረገ ጦርነት በተጨማሪ የአለም ኃያላን አገራት በሚያደርጉት ፖለቲካዊ ጨዋታ ምክንያት እየተቀዛቀዘ መሄዱ ገሃድ የወጣ እውነታ ነበር። ከዚህ ሁሉ እሰጥ አገባ በኋላ ሰሜን ኮሪያ የእንዋሃድ መልዕክት ማስተላለፏ ብዙዎችን ያስገረመ ሆኗል። ይህ የእንዋሃድ መዕክት ግን በአጋጣሚ የመጣ እንዳልሆነ የሚከራከሩም አልጠፉም። ከቅርብ ወራት ወዲህ ሰሜን እና ደቡበ ኮሪያ በስፖርቱና በኪነጥበበ መስኮች በጋራ ለመሳተፍ የሚያስችላቸውን ስምምነቶች ሲያደርጉ መቆየታቸውንም የውህደት ጥያቄው ከመሬት የተነሳ ድንገተኛ ጉዳይ አለመሆኑን እንደ ምክንያትነት ይቀርባል።
የተለያዩ የመገናኛ ብዙሃን ሲዘግቡ እንደቆዩትም ሰሜንና ደቡብ ኮርያ ከበርካታ ዓመታት የተዘጋ ግንኙነታቸው በኋላ በኪነጥበቡ መድረክ ላይ ዳግም ለመገናኘት ፍላጎት እንዳላቸው ይፋ አድርገዋል። በቀጣይ ጊዜያት በደቡብ ኮርያዋ ርዕሰ መዲና ሴኡል በሚዘጋጀው የባህል እና የኪነጥበብ ልምድ ልውውጥ የጋራ መድረክም ላይ የሁለቱም አገራት ህዝቦች እንደሚካፈሉም ይጠበቃል። ዝግጅቱም በአገራቱ መካከል መልካም ግንኙነት ለመጀመር በር የሚከፍት ሂደት መሆኑን እየተገለጸ ይገኛል።
በሌላ በኩል የሁለቱ አገራት የስፖርት ውህደት ከወዲሁ አድናቆት እየተቸረው መጥቷል። ሰሜን ኮርያ ቀጣዩ ወር በደቡብ ኮርያዋ ፒዮንግያንግ ለሚካሄደው የክረምት ኦሎምፒክ ውድድር የከፍተኛ ደረጃ ልዑካን ቡድኗን ለመላክ ስምንነት አድርጋለች። የሰሜን እና ደቡብ ኮርያ ኃላፊዎች እና የስፖርት ሰዎች ተገናኝተው ከተነጋገሩ በኋላ ሰሜን ኮርያ የከፍተኛ ልዑካንን ቡድኗን ወደስፍራው ፣ እንደምትልክ በኃላፊዎች በኩል መግለጫ ሰጥታለች። ከዚህ በኋላ በተደረጉ ስምምነቶች ደግሞ በክረምቱ ኦሎምፒክ ከሚላኩ ስፖርተኞች መካከል በጤቶቹ የበረዶ ላይ ገና ጨዋታ ከአገራቱ የተውጣጡ ተጫዋቾች በአንድ ቡድን በጋራ ተወክለው እንደሚጫወቱ ይፋ ሆኗል።
ከዚህ በተጨማሪም በኦሎምፒኩ የመክፈቻ ስነስርዓት ወቅት አገራቱ በአንድ ሰንደቅ አላማ ስር እራሳቸውን በማስተዋወቅ በህዝብ ፊት እንደሚተዋወቁ ቃል ተገብቷል። ውድድሩም ከሁለት ሳምንታት በኃላ እ... የካቲት ዘጠኝ ቀን 2018 የሚጀመር በመሆኑ በርካቶች የአገራቱን የአንድነት ትዕይንት ለመመልከት ጓጉተዋል። ከስፖርትና ከኪነጥበድ ውህደቶቹ በተጨማሪ የሰሜን ኮሪያ የአንድነት ጥያቄ መቅረቡ አገራቱ በጋራ ለመንቀሳቀስ እድል እንዳላቸው አመላካች ነው የሚል ተስፋን ኮሪያዎች እንዲሰንኩ ምክንያት ሆኗል።
ጥቂት የማይባሉ የደቡብ ኮሪያ ዜጎች ግን የሰሜን ኮርያው ፕሬዝዳንት እብሪተኛነት እና በየጊዜው የሚወረወሩ የጦርነት ቃላት ግንኙነቱ ወደ ውህደት እንዳያመራ እክል የሚፈጥር ነው የሚል ፈጥሮባቸዋል። የዘርፉ ፖለቲካ ተንታኞች እንደሚሉት ደግሞ ከበርካታ አመታት ጦርነት እና የፖለቲካ ፍጥጫ በኋላ ለውህደት ጅማሮ የሚፈጥሩ ጉዳዮች መከሰታቸው አገራቱን ወደ አንድነት የማያመራ ቢሆን እንኳን በመካከላቸው መልካም ግንኙነት እንዲኖር እድል የሚፈጥር አጋጣሚ ይፈጥራል።

Friday, January 26, 2018

በአንድ ጥይት ሁለት ኢላማ


መፎከር መሸለል ጥንትም ያባቴ ነው
ለፍቶ መከብርን አያቴን ጠይቀው
ያስረዳል ሰርቶ በተግባር እንድታይ
እኔ ግን አቻልኩም ተግባሩ አቃተኝ
ከስራው ይልቅም መቦዘን አማረኝ
ተልፈስፍሶ ቀረ ጉልበቴ በከንቱ
በዚህ መጠጥ ጎድቶት በዚያ ደግሞ ጫቱ
ይህን የተገጠመው ለሰፈራችን አንደኛ ሱሰኛው በቅጽል ስሙ ለድንቢልቢ ነው። ለሱሱ በሚወስደው የጊዜ መጠን መብዛትም ሆነ ካለው ፍላጎት የተነሳ አውራነቱ ማንነቱ ባልታወቀ የመነደሩ ሰው ተሰጥቶታል። እናም ሱሰኛ ነውና እርሱ የሚያስበው ጠዋት ተነስቶ ጠጅ ቤት ያደረ አንቡላ በርካሽ ገንዘብ ለመጠጣት ከዚያም ረፈድ ሲል ቁርስ ቢጤ ቁራሽ ቀማምሶ ዳግም ወደ አረቄው ለመሄድ ነው እንጂ ለስያሜው አይጨነም። ከሰዓት ተበድሮም ሆነ ተለቅቶ ያገኛትን አስር ብር ለጫት መቃሚያ ያውላታል። እሳኑ በአፉ እንደያዘ ደግሞ ወደ ከነ ስፖንጅ መሳይ መያዣዋ ድረስ የምትጨሰውን ሲጃራውን በላይ በላዩ ያክልበታል። የሲጋራ ጢስ ቀለሙን የቀየረው ከንፈሩ በጥቁረቱ በቀን እንድ መቶ እና ሁለት መቶ ኪሎ ሜትሮችን በየቀኑ ከሚጓዙ የከተማዋ ታክሲዎች የጭስ ማውጫ ጋር ሲወዳደር ቢበልጥ እንጂ አያንስም። 
 
በሰፈሩ መስቀለኛ መንገድ ላይ አንዲት ለሁለት ሰው በምትነሳ ጥቁር ድንጋር ላይ መቀጥ ለእርሱ ስራም ነው መዝናኛም ነው። ምክንያቱም አላፊ አግዳሚውን በተለይም ለሰፈሩ አዲስ የሆኑ ሰዎችን ለሻይ እና ለዳቦ በሚል ገንዘብ ይለምንበታል። በሌላ በኩል ሆዱ ሲሞላ ደግሞ አላፊ አግዳሚ ኮረዶችን በነገር በመጎንተል ልቡን ያስደስትባታል። ዛሬም እንደ ትላንቱ አምናም እንደ ካቻምናው ከነበረው የሱስ የህይወት ዑደት ጋር የተመሳሰለ ጊዜን ያሳልፋል። ታዲያ የሰፈሩ ድንጋይ ላይ ለስድስት አመታት መቀመጡን ያስተዋሉት እናቱ ወየዘሮ አዛለች በሰላሳ አመትህ የድንጋይ አሟቂ ሁነህ ቀረህ እያሉ ቤታቸው ውስጥ በገባ በወጣ ቁጥር ይነዘንዙታል።
አንዳንድ የሰፈረ አሽሟጣጮች ደግሞ ይች ጥቁር ድንጋር ያለ ነገር አይቀመጥባትም ምንአልባት አንስተን ብንቆፍራት የከበረ እንቁ እና አልማዝ ተቀብሮባት ይሆናል እያሉ ይዘብታሉ። የቀድሞ ወዳጆቹ ግን ይሻለው ይሆን ብለው የሰፈር ጎረቤቶቹን አስተባብረው ከአዕምሮ ሃኪም ቤትንም ሆነ ጠበል ቢወስዱት አምልጦ እየመጣ ያች የለመዳት ድንጋይ ላይ ጎብ ብሎ ይጠብቃቸዋል። እንደውም አንድ ጊዜ በእድሜ ጠና ያሉ የሃይማኖት አባት አግኝተውት «ተው ልጄ በዚህ እጅህ ሲጋራ እና ጫት ልትይዝበት አይገባም» ብለው ቢገዝቱት እሱ ለጄ ለማን ይበገራል አንድ ሰሞን በቀኝ እጅህ ሲጋራ አትያዝ ተብዬ ነው ብሎ በግራ እጁ እየለኮሰ ያንበለብለው ጀምሮ ነበር።
አሁን አሁንማ እዚያ ድንቢልቢ የሚቀመጠበት ቦታ ጋር ስትደርስ ታጠፍ እየተባለ የሰፈር መጠቆሚያ ሆኖ አርፎታል። ነገሩ ያሳሰባቸው እናቱ ግን የአባቱ ጠንካራ ሰራተኛነት ወደ እርሱ እንዴት እንዳልተወረሰ ግራ ገብቷቸው ጣት ማታ እንተብሰለሰሉ ናቸው። አባቱ በመንደራቸው አሉ የተባሉ የማር ነጋዴ ሲሆኑ ልጃቸው ደግሞ በሰፈሩ አለ የተባለ አዲስ ጠጅ ቀማሽ ሆኖ ቀርቷል። አያቱ እንዲሁ ጠንካራ ገበሬ ናቸው። ወይፈኖቻቸውን ከጠመዱ እህል ውሃ ሳይቀምሱ ቀምበር ታዘቀዝቃለች የሚባልላቸው ነበሩ። ታዲያ የልጅ ልጃቸው ደግሞ ጀምበር በቅጡ ሳትወጣ ከቤቱ እንደወጣ ከአረቄ እስከ ሲጋራ ያሉትን አዳርሶ ማታ ላይ እየተንጎማለለ ለመኝታ ብቻ ቤቱ ይደርሳል። እናቱ እውነት ልጄ ስወልድ ተቀይሮ የሆን ወይስ ምን ነክቶት ነው ይህን ያህል የዘሮቹን ያህል ታታሪ ያልሆነው ብለው ይብሰለሰላሉ።
ወትሮም ለትምህርት ግድ የሌለው ወጣት ስምንተኛን እንዳገባደደ ነበር ስራ መጀመር አለብኝ ብሎ የከባድ መኪና ረዳት የሆነው። በወቅቱ አስርም አምስትም ብር ለቤት ስለሚወረውር እናቱም ብትማር ይሻላል የሚለውን ምክራቸውን ከጊዜ ወደ ጊዜ ለዘብ እያደረጉ መጥተው ጭራሹንም ረሱት። እናም ወጣቱ በስራ ላይ የለመደው አጓጉል ሱስ ከስራም አሰናብቶት ሰፈር እንዲውል ዳርጎታል። ሆነም ቀረ ስራው ይቀራል እንጂ ሱሱ አይቀርም ያለ ይመስል ግን አጓጉል ተግባሩን ለአንድ ቀን አቋርጦት አያውቅም።
ነገ ግን እናቱ ወይዘሮ አዛለች ለእርሱ አዲስ ወደሆነ አንድ ቦታ ወስደው ታታሪነትን ሊያስተምሩት ቆርጠው እቅድ እያወጡ ናቸው። «በሌሊት አውቶቢስ ተራ ተገኝተን የጅሩን አቀበት የሚያስወጣን መኪና እንይዛለን። ከዚያም የዘመጆችህን ጥማድ በሬ ተውሼ አርባ ክንድ መሬት እሰጠዋለሁ እናም ከመንደሩ ውልፍት እንዳይል በዘመዶቼ አስጠብቀዋለሁ። እኔ አዲሳባ መጥቼ በስልክ አዋዋሉን እየተረዳሁ እራሱን እንዲችል ማድረግ አለብኝ» አሉ ለእራሳቸው። በረጅሙ ከተፈሱ በኋላ በሚስጥር የያዙትን እቅድ ለማስፈጸም በጠዋት ዘመድ ጥየቃ ወደ ገጠር እንደሚሄዱ ለልጃቸው ነግረውት አብሯቸው አውቶቢስ ተራ እንዲሄድ ነግረውት ወደ አልጋቸው አመሩ።
ነገ ለእርሳቸው የተስፋ ቀን ነች። በሰፈሩ የቡና ማጣጫ ያደረጋቸውን ሱሰኛ ልጃቸውን ገጠር ወስደው በግብርና ስራ ጊዜውን አሳልፎ እንዲመለስ ወጥነውለታል። እናም እንቅልፍ እንኳን ሳይወስዳቸው ቢያድርም ልጃቸውን አንጠልጥለው በነጋታው ጅሩ ገቡ። ጉዳዩን ለዘመዶቻቸው አሰረድተው የለጃቸው ጉዳይ አደራ ሰጥተው ሰነባብ ተው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ።
እዛ ድንጋይ ማሞቅ የለ ወይ ሲጋራ ማጤስ የለም የአገሩ ሰው ጠዋት ተነስቶ ወደ ስራ ይሄዳል። እናም ምንም አማራጭ የሌለው ወመኔ ልጃቸው የታቀደለትን ሲረዳ ወመውጫ መግቢያ እንደሌለው በመረዳቱ ከዘመዶቹ ጋር ጠዋት ተነስቶ ወደ ስራ መሄዱን ተለማመደው። ቀናት ቀናትን እየወለዱ በሁለት ሳምንቱ ጠንካራ ገበሬ መሆን እነደሚችል ማሳየት ጀመረ። ወይዘሮ አዛሉም ጉዳዩን በስልክ እየተረዱ የልጃቸው መለወጥ ገርሟቸዋል። ሁለት ወራትን ካሳለፈ በኋላ ወደ መኖሪያው አምጠተው ቀን እየሰራ ማታ ትምህርቱን እንደሚያስቀጥሉት ለእራሳቸው ቃል ገቡ።
አሁን ልጃቸው እየተለወጠ ነው። ይህን ለውጥ ያዩ ሰዎችም ምክር ቢጤ ይጠይቋቸዋል። እናም እርደ እርሳቸው ሱሰኛ ልጅ ላላቸው የሌላ መንደር ሰዎች የስነልቦና አማካሪነት ሆነው አረፉት። አማካሪነቱም የገንዘብም ሆነ የአይነት ስጦታ ይዞላቸው ይጎርፈ በመምጣቱ ደግሞ ደስተኛ ሆነዋል። በአንድ ጥይት ሁለት ኢላማ መምታት ይሉሃል ይሄ ነው።

Featured post

ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጠያቂነትን በማረጋገጥ፣ የሕግ በላይነትን በማስፈን፣ መንግሥትና የስራ አስፈጻሚ አካላቱ በመሉ ለሰብአዊ መብቶች መከበር፣ መጠበቅና መሟላት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያሳዩ ልዩ ትኩረትና ክትትል ይሻል

                    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየደረጃው ያሉ የመንግስት አስፈጻሚ አካላትና ኃላፊዎች ላይ የቅርብ ክትትል በማድረግ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር አስተዋጽኦ ሊያደር...