Friday, January 26, 2018

በአንድ ጥይት ሁለት ኢላማ


መፎከር መሸለል ጥንትም ያባቴ ነው
ለፍቶ መከብርን አያቴን ጠይቀው
ያስረዳል ሰርቶ በተግባር እንድታይ
እኔ ግን አቻልኩም ተግባሩ አቃተኝ
ከስራው ይልቅም መቦዘን አማረኝ
ተልፈስፍሶ ቀረ ጉልበቴ በከንቱ
በዚህ መጠጥ ጎድቶት በዚያ ደግሞ ጫቱ
ይህን የተገጠመው ለሰፈራችን አንደኛ ሱሰኛው በቅጽል ስሙ ለድንቢልቢ ነው። ለሱሱ በሚወስደው የጊዜ መጠን መብዛትም ሆነ ካለው ፍላጎት የተነሳ አውራነቱ ማንነቱ ባልታወቀ የመነደሩ ሰው ተሰጥቶታል። እናም ሱሰኛ ነውና እርሱ የሚያስበው ጠዋት ተነስቶ ጠጅ ቤት ያደረ አንቡላ በርካሽ ገንዘብ ለመጠጣት ከዚያም ረፈድ ሲል ቁርስ ቢጤ ቁራሽ ቀማምሶ ዳግም ወደ አረቄው ለመሄድ ነው እንጂ ለስያሜው አይጨነም። ከሰዓት ተበድሮም ሆነ ተለቅቶ ያገኛትን አስር ብር ለጫት መቃሚያ ያውላታል። እሳኑ በአፉ እንደያዘ ደግሞ ወደ ከነ ስፖንጅ መሳይ መያዣዋ ድረስ የምትጨሰውን ሲጃራውን በላይ በላዩ ያክልበታል። የሲጋራ ጢስ ቀለሙን የቀየረው ከንፈሩ በጥቁረቱ በቀን እንድ መቶ እና ሁለት መቶ ኪሎ ሜትሮችን በየቀኑ ከሚጓዙ የከተማዋ ታክሲዎች የጭስ ማውጫ ጋር ሲወዳደር ቢበልጥ እንጂ አያንስም። 
 
በሰፈሩ መስቀለኛ መንገድ ላይ አንዲት ለሁለት ሰው በምትነሳ ጥቁር ድንጋር ላይ መቀጥ ለእርሱ ስራም ነው መዝናኛም ነው። ምክንያቱም አላፊ አግዳሚውን በተለይም ለሰፈሩ አዲስ የሆኑ ሰዎችን ለሻይ እና ለዳቦ በሚል ገንዘብ ይለምንበታል። በሌላ በኩል ሆዱ ሲሞላ ደግሞ አላፊ አግዳሚ ኮረዶችን በነገር በመጎንተል ልቡን ያስደስትባታል። ዛሬም እንደ ትላንቱ አምናም እንደ ካቻምናው ከነበረው የሱስ የህይወት ዑደት ጋር የተመሳሰለ ጊዜን ያሳልፋል። ታዲያ የሰፈሩ ድንጋይ ላይ ለስድስት አመታት መቀመጡን ያስተዋሉት እናቱ ወየዘሮ አዛለች በሰላሳ አመትህ የድንጋይ አሟቂ ሁነህ ቀረህ እያሉ ቤታቸው ውስጥ በገባ በወጣ ቁጥር ይነዘንዙታል።
አንዳንድ የሰፈረ አሽሟጣጮች ደግሞ ይች ጥቁር ድንጋር ያለ ነገር አይቀመጥባትም ምንአልባት አንስተን ብንቆፍራት የከበረ እንቁ እና አልማዝ ተቀብሮባት ይሆናል እያሉ ይዘብታሉ። የቀድሞ ወዳጆቹ ግን ይሻለው ይሆን ብለው የሰፈር ጎረቤቶቹን አስተባብረው ከአዕምሮ ሃኪም ቤትንም ሆነ ጠበል ቢወስዱት አምልጦ እየመጣ ያች የለመዳት ድንጋይ ላይ ጎብ ብሎ ይጠብቃቸዋል። እንደውም አንድ ጊዜ በእድሜ ጠና ያሉ የሃይማኖት አባት አግኝተውት «ተው ልጄ በዚህ እጅህ ሲጋራ እና ጫት ልትይዝበት አይገባም» ብለው ቢገዝቱት እሱ ለጄ ለማን ይበገራል አንድ ሰሞን በቀኝ እጅህ ሲጋራ አትያዝ ተብዬ ነው ብሎ በግራ እጁ እየለኮሰ ያንበለብለው ጀምሮ ነበር።
አሁን አሁንማ እዚያ ድንቢልቢ የሚቀመጠበት ቦታ ጋር ስትደርስ ታጠፍ እየተባለ የሰፈር መጠቆሚያ ሆኖ አርፎታል። ነገሩ ያሳሰባቸው እናቱ ግን የአባቱ ጠንካራ ሰራተኛነት ወደ እርሱ እንዴት እንዳልተወረሰ ግራ ገብቷቸው ጣት ማታ እንተብሰለሰሉ ናቸው። አባቱ በመንደራቸው አሉ የተባሉ የማር ነጋዴ ሲሆኑ ልጃቸው ደግሞ በሰፈሩ አለ የተባለ አዲስ ጠጅ ቀማሽ ሆኖ ቀርቷል። አያቱ እንዲሁ ጠንካራ ገበሬ ናቸው። ወይፈኖቻቸውን ከጠመዱ እህል ውሃ ሳይቀምሱ ቀምበር ታዘቀዝቃለች የሚባልላቸው ነበሩ። ታዲያ የልጅ ልጃቸው ደግሞ ጀምበር በቅጡ ሳትወጣ ከቤቱ እንደወጣ ከአረቄ እስከ ሲጋራ ያሉትን አዳርሶ ማታ ላይ እየተንጎማለለ ለመኝታ ብቻ ቤቱ ይደርሳል። እናቱ እውነት ልጄ ስወልድ ተቀይሮ የሆን ወይስ ምን ነክቶት ነው ይህን ያህል የዘሮቹን ያህል ታታሪ ያልሆነው ብለው ይብሰለሰላሉ።
ወትሮም ለትምህርት ግድ የሌለው ወጣት ስምንተኛን እንዳገባደደ ነበር ስራ መጀመር አለብኝ ብሎ የከባድ መኪና ረዳት የሆነው። በወቅቱ አስርም አምስትም ብር ለቤት ስለሚወረውር እናቱም ብትማር ይሻላል የሚለውን ምክራቸውን ከጊዜ ወደ ጊዜ ለዘብ እያደረጉ መጥተው ጭራሹንም ረሱት። እናም ወጣቱ በስራ ላይ የለመደው አጓጉል ሱስ ከስራም አሰናብቶት ሰፈር እንዲውል ዳርጎታል። ሆነም ቀረ ስራው ይቀራል እንጂ ሱሱ አይቀርም ያለ ይመስል ግን አጓጉል ተግባሩን ለአንድ ቀን አቋርጦት አያውቅም።
ነገ ግን እናቱ ወይዘሮ አዛለች ለእርሱ አዲስ ወደሆነ አንድ ቦታ ወስደው ታታሪነትን ሊያስተምሩት ቆርጠው እቅድ እያወጡ ናቸው። «በሌሊት አውቶቢስ ተራ ተገኝተን የጅሩን አቀበት የሚያስወጣን መኪና እንይዛለን። ከዚያም የዘመጆችህን ጥማድ በሬ ተውሼ አርባ ክንድ መሬት እሰጠዋለሁ እናም ከመንደሩ ውልፍት እንዳይል በዘመዶቼ አስጠብቀዋለሁ። እኔ አዲሳባ መጥቼ በስልክ አዋዋሉን እየተረዳሁ እራሱን እንዲችል ማድረግ አለብኝ» አሉ ለእራሳቸው። በረጅሙ ከተፈሱ በኋላ በሚስጥር የያዙትን እቅድ ለማስፈጸም በጠዋት ዘመድ ጥየቃ ወደ ገጠር እንደሚሄዱ ለልጃቸው ነግረውት አብሯቸው አውቶቢስ ተራ እንዲሄድ ነግረውት ወደ አልጋቸው አመሩ።
ነገ ለእርሳቸው የተስፋ ቀን ነች። በሰፈሩ የቡና ማጣጫ ያደረጋቸውን ሱሰኛ ልጃቸውን ገጠር ወስደው በግብርና ስራ ጊዜውን አሳልፎ እንዲመለስ ወጥነውለታል። እናም እንቅልፍ እንኳን ሳይወስዳቸው ቢያድርም ልጃቸውን አንጠልጥለው በነጋታው ጅሩ ገቡ። ጉዳዩን ለዘመዶቻቸው አሰረድተው የለጃቸው ጉዳይ አደራ ሰጥተው ሰነባብ ተው ወደ አዲስ አበባ ተመለሱ።
እዛ ድንጋይ ማሞቅ የለ ወይ ሲጋራ ማጤስ የለም የአገሩ ሰው ጠዋት ተነስቶ ወደ ስራ ይሄዳል። እናም ምንም አማራጭ የሌለው ወመኔ ልጃቸው የታቀደለትን ሲረዳ ወመውጫ መግቢያ እንደሌለው በመረዳቱ ከዘመዶቹ ጋር ጠዋት ተነስቶ ወደ ስራ መሄዱን ተለማመደው። ቀናት ቀናትን እየወለዱ በሁለት ሳምንቱ ጠንካራ ገበሬ መሆን እነደሚችል ማሳየት ጀመረ። ወይዘሮ አዛሉም ጉዳዩን በስልክ እየተረዱ የልጃቸው መለወጥ ገርሟቸዋል። ሁለት ወራትን ካሳለፈ በኋላ ወደ መኖሪያው አምጠተው ቀን እየሰራ ማታ ትምህርቱን እንደሚያስቀጥሉት ለእራሳቸው ቃል ገቡ።
አሁን ልጃቸው እየተለወጠ ነው። ይህን ለውጥ ያዩ ሰዎችም ምክር ቢጤ ይጠይቋቸዋል። እናም እርደ እርሳቸው ሱሰኛ ልጅ ላላቸው የሌላ መንደር ሰዎች የስነልቦና አማካሪነት ሆነው አረፉት። አማካሪነቱም የገንዘብም ሆነ የአይነት ስጦታ ይዞላቸው ይጎርፈ በመምጣቱ ደግሞ ደስተኛ ሆነዋል። በአንድ ጥይት ሁለት ኢላማ መምታት ይሉሃል ይሄ ነው።

No comments:

Post a Comment

Featured post

ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጠያቂነትን በማረጋገጥ፣ የሕግ በላይነትን በማስፈን፣ መንግሥትና የስራ አስፈጻሚ አካላቱ በመሉ ለሰብአዊ መብቶች መከበር፣ መጠበቅና መሟላት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያሳዩ ልዩ ትኩረትና ክትትል ይሻል

                    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየደረጃው ያሉ የመንግስት አስፈጻሚ አካላትና ኃላፊዎች ላይ የቅርብ ክትትል በማድረግ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር አስተዋጽኦ ሊያደር...