Wednesday, August 29, 2018

የማሪዋና መናኸሪያ የሆነው ፍርስራሽ መንደር

አዲስ አበባ ከአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ወይም ከፓርላማ ቁልቁል ወደ ፒያሳ ሲያመሩ እሪ በከንቱ የተሰኘውን ሰፈር ያገኙታል። ከዚያ ከአስፓልት በላይ እና በታች ያሉት መንደሮች፣ ለግንባታ በሚል ሰበብ ከፈረሱ ዓመታት ተቆጥረዋል። አጥራቸው የተከበበው አረንጓዴ እና ቢጫ ቀለማት ባሏቸው ቆርቆሮዎች ነው። ወደ አካባቢው የወሰደኝ ጉዳይ አንድ የመንደሬ ነዋሪ መኸል አዲስ አበባ ላይ እየተሠራ ስላለው ጉድ ካጫወተኝ በኋላ ነው።
የ17 ዓመቱ ወጣት ሶፎንያስ በላይ ሁል ጊዜ ሳገኘው ዓይኑ እንደቀላ ነው። ማታ ማታ ከቤተሰቦቹ ተደብቆ ሲጋራ የማጨስ ልማዱ ሰንበትበት ብሏል። እንደወትሮው ከሥራ ስመለስ መንገድ ላይ ሆኖ ሲያዛጋ አገኘሁት። የማይመለስ አስር ብር እንዳበድረው ጠየቀኝ። ቅድሚያ ግን ምክንያቱን ጠየኩት ሊያጨስበት እንደሆነ ነገረኝ። በእጁ የቀረው የሲጋራ ቁራጭ ሳየው ደግሞ በወረቀት ቢጤ የተጠቀለለ ነበርና ምን እንደሚያጨስ ጠየቅኩት። እየተቅለሰለሰ «ጋንጃ» አለኝ። የምንተፍረቱን የማሪዋናውን ቁራጭ በእጁ አሳየኝ።
የማሪዋና መናኸሪያ የሆነው ፍርስራሽ መንደር
ከአራት ኪሎ እሪ በከንቱ ፍርስራሽ ሰፈሮች እና ቤላ ከሚባል አካባቢ እንደሚገዛ ጠቁሞኝ ብሩን ከእጄ ላይ መንጭቆ ተፈተለከ። ብሩን ከእኔ ባያገኝም ሌሎች ሰዎችን አስቸግሮ አልያም ሰርቆም ቢሆን መጠቀሙ እንደማይቀር
በመረዳቴ አዘንኩለት። ሶፎኒያስ ከዩኒቨርሲቲ ተባሮ ከመጣ ሁለት ዓመታትን አስቆጥሯል። ቤተሰቦቹ በግል ትምህርት ቤት ቢያስገቡትም ለመማር ፍቃደኛ ባለመሆኑ የጤና ችግር አጋጥሞት ሊሆን ይችላል ብለው በህክምና ተቋማትና በፀበል ቦታዎች አመላልሰው ተስፋ በመቁረጣቸው ትተውታል።
ሁልጊዜም ባየሁት ቁጥር አዝንለታለሁ። የጠየቀኝን ሰጥቼ ከማለፍ ውጪ ችግሩን ቀርቤ ለመረዳት ያደረኩት ጥረት አነስተኛ በመሆኑ ዛሬ የነገረኝ መረጃ አስደንግጦኛል። በጆሮዬ የሰማሁትን በዓይኔ ለማረጋገጥ ወደቦታው ለማምራት ለእራሴ ቀጠሮ ያዝኩ። አራት ኪሎ ወረድ ብሎ በሚገኘው እሪ በከንቱ እንደደረስኩ የአደንዛዥ ዕፁን ለመግዛት መፈለጌን ለአካባቢ ወጣቶች ነግሬ ሻጮቹን እንዲያገናኙኝ ጠየኳቸው። ምንም ሳይጠራጠሩ ከአንድ ፍርስራሽ ቤት እንድገባ አመላከቱኝ።
ግቢው ውስጥ ስዘልቅ የሰው ቁመት በሚያክል ሙጃ ሳር እና አልፎ አልፎ በበቀሉ የጉሎ ዛፎች ተሸፍኗል። አካባቢው ለልማት ተብሎ ከፈረሰ ዓመታት በመቆጠራቸው መንግሥት የረሳው ይመስላል። ይሁን እንጅ የቀድሞ ነዋሪዎቹ በላስቲክ እና በሸራ በተሸፈኑ ዳሶች ውስጥ ይኖራሉ። የዛሬ ዓመት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ የነበሩት አቶ አባተ ስጦታው በከተማዋ የታጠሩና ሥራ ያልተሠራባቸውን ቦታዎች እያመላከቱ «ከዛሬ በኋላ ወደ ሥራ እንገባለን» እያሉ ለመገናኛ ብዙኃን እንዳስጎበኙት አስታወስኩ። ግን ከዛሬ በኋላ መቼ ነበር?
መንደሩ ለልማት ተብሎ የፈረሰ ስለመሆኑ የሚያሳብቁ የአፈር ቤት ፍርስራሾች እና አሮጌ የእንጨት በሮች እዚህም እዚያም ይታያሉ። ህፃናት ሳይቀሩ ከላስቲክ ዳሶቻቸው እየወጡ ውር ውር ይላሉ። ቦታው ተዳፋት ሲሆን፤ ለጎርፍ የተጋለጠ ከመሆኑም በላይ ከአጠገቡ ቆሻሻ የሚደፋበት ወንዝ አለ። ከመንደሩ ጀርባ ደግሞ የአራት ኪሎ ባሻ ወልዴ ችሎት የጋራ መኖሪያ ቤቶችና የተለያዩ ህንጻ ግንባታዎች ይካሄዳሉ። አለፍ ብሎም የአካባቢው ፖሊስ ጣቢያም ይገኛል።
ድንገት ከፊት ለፊቴ የሚመጣውን ወጣት ሠላምታ ሰጥቼ በተጠቃሚዎች አጠራር «ጋንጃ ፈልጌ ነበር» አልኩት። ጊዜ ሳያባክን «ባለስንት» የሚል አስደንጭ ጥያቄ አቀረበልኝ። «ባለ ሰላሳ፣ ባለስልሳና ባለ መቶ አለ፤ የትኛው ይሁን» እያለ የዋጋ ተመኖቹን አሳወቀኝ።
ወጣት አሸናፊ አለሙ (ስሙን እንደቀየረው ነግሮኛል) እሪ በከንቱ አካባቢ ማሪዋና ከሚያከፋፍሉ ወጣቶች መካከል ታዋቂው ነው። እርሱ እንደሚለው፤ በአካባቢው ለልማት ትነሳላችሁ ተብለው ቤት ያልተሰጣቸውና የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸው በርካታ ሰዎች ይኖራሉ። ያንን የኢኮኖሚ ቀዳዳ ለመሸፈን ደግሞ ማሪዋና መሸጥ እንደ አማራጭ አድርገውታል። በአካባቢው 125 የሚደርሱ የላስቲክ መጠለያዎች ይገኛሉ። በእያንዳንዱ ውስጥ ደግሞ አስርም አስራ አምስትም ሰው ታጭቆ ይኖርባቸዋል። የጎዳና ተዳዳሪዎችም የእራሳቸውን ዳስ ሠርተው እንደሚያድሩበት አብራራልኝ። በመሆኑም የኢኮኖሚ ምንጭ የሌለው ማህበረሰብ በሕግ የተከለከለውን የአደንዛዥ ዕፅ ንግድ ውስጥ ተሰማርቶ መገኘቱ የእራሱን ህይወት ከማዳን ጋር ሊያያዝ ይችላል? እራሴ ለራሴ ያቀረብኩት ጥያቄ ነበር።
በቀን ውስጥ ከ100 በላይ ወጣቶች ዕፁን ለመግዛት እንደሚመጡ የሚናገረው ወጣቱ፤ አብዛኛዎቹ ሴቶች መሆናቸውን ይገልፃል። ዕድሜያቸው ከ14 እስከ52 የሚደርሱ ሰዎችም ዕፁን እንደሚጠቀሙ አጫውቶኛል። የዕፁ ዘር ከሌላ ቦታ በማምጣት ሲዘራ ከሳር ጋር ተቀላቅሎ እንደሚበቅል እና ቅጠሉ ደርቆ ለወጣቶቹ ይሸጥላቸዋል። የማሪዋና አቅርቦቱ ከፈላጊው ጋር ሊጣጣም ባለመቻሉ እጥረት የሚከሰትበት ጊዜ እንዳለም ይጠቁማል። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እና ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ ወጣቶች በወረቀት የተጠቀለለውን ደረቅ ዕፅ እየወሰዱ በሲጋራ መልክ ያጨሱታል። ዕፁ ሲጨስ የሚከረፋ ጠረን ቢኖረውም በፊልም እንዳዩት ለመሆን ብለው አደንዛዥ ዕፁን የሚወስዱ በርካታ መሆናቸውን ይገልፃል።
የአካባቢው ነዋሪ የሆነው አቶ ሰለሞን አበበ በበኩሉ፤ በየቀኑ ታዳጊና ወጣት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንደሚመጡ ታዝቧል። የዕፁን ንግድ ለማስቆምና የወጣቶችን ህይወት መታደግ ካስፈለገ ጠንከር ያለ እርምጃ በመውሰድ ከምንጩ ማድረቅ እንደሚያስፈልግ ይናገራል። በመላ አገሪቷ የሚከፋፈለው የማሪዋና ዘር ከኦሮሚያ ክልል ሻሸመኔ ከተማ የሚመጣ ነው። ሻሸመኔ ውስጥ ጃማይካዎች ማሪዋና ማብቀልና መጠቀም እንደ ባህል የተለመደ በመሆኑ በአካባቢው በብዛት ዘሩ ይመረታል። የተመረተው ዘርም በሕገ ወጥ መንገድ እየተጓጓዘና የፍተሻ ኬላዎችን እያለፈ ወደ ተለያዩ ከተሞች ይዛመታል። መንግሥት በዚህ ንግድ ውስጥ የተሰማሩ ሰዎችን ተከታትሎ መፍትሔ መስጠት ካልተቻለ እያንዳንዱ ቦታ ያለውን የዕፅ ተጠቃሚ እያሳደዱ መያዝ ዘለቄታዊ መፍትሄ አያመጣም ይላል።
የስነ አዕምሮ ህክምና ባለሙያው ዶክተር ታደሰ በዳሳ እንደሚናገሩት፤ በጥናት እንደተረጋገጠው ወደ ሱስ ከሚገቡ የሁለተኛ ደረጃ እና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል አንድ ሦስተኛው በሱስ ውስጥ የሚቆዩ ናቸው። ሌሎቹ ግን ጥቂት ከሞከሩት በኋላ ጉዳቱን ተረድተው ይተውታል። ሱሱ ውስጥ የሚቀሩት መቋቋም እስኪያቅታቸው ድረስ የጤና ችግር ቀስ በቀስ ስለሚያጋጥማቸው በባለሙያ የተደገፈ የአዕምሮ ህክምና ያስፈልጋቸዋል።
የማሪዋና ተጠቃሚዎች ላይ በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ዓይናቸው የመቅላት ምልክት እና ልብሳቸው ላይ መጥፎ ጠረን የሚፈጠር ሲሆን፤ ይህን ምልክት እና ተያያዥ የባህሪ ለውጥ የሚያስተውሉ ወላጆች ችግሩን ቀድመው ለመከላከል መንቃት ይኖርባቸዋል ይላሉ። ወጣቶቹ ወደ ችግሩ ሙሉ በሙሉ እንዳይገቡ ወላጆች የመከላከል ኃላፊነት እንዳለባቸውም ያሳስባሉ።
እንደ ዶክተር ታደሰ ማብራሪያ፤ በወጣቶቹ ላይ የሚደርሰው ችግር ወደ ማህበራዊ ቀውስ እንዳያመራ ከወላጆች ባለፈ መንግሥት፣ ፖሊስና የተለያዩ የሕግ አካላት፣ መገናኛ ብዙኃን እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማት የማይቋረጥ የመከላከል ሥራ መሥራት አለባቸው። በተለይ የማህበራዊ ሚዲያ አክቲቪስቶች የችግሩን ግዝፈት ተመልክተው ሃሳብ ሊያፈልቁ እና ወጣቱን ሊያስተምሩት ይገባል ይላሉ።
ከዓመታት በፊት «የአገሪቱ ታላቁ አደባባይ የማሪዋና ቅጠል መብቀያ ሆኗል» በሚል ርዕስ የመስቀል አደባባይ ላይ በርካታ ወጣቶች ዕፁን እያበቀሉ ይሸጡና ይጠቀሙ እንደነበር መዘገቡ ይታወሳል።

Saturday, August 4, 2018

ባዮቴክኖሎጂ እና ኢትዮጵያ



ዮቴክኖሎጂ እና ኢትዮጵያ

ትነት ተስፋማርያም
በኢትዮጵያ ያለው የባዮቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዕድሜ አጭር ጊዜ ያስቆጠረ ነው። በተለይ በአፋር ክልል ባለው የግብርና ምርምር አማካኝነት የጥጥ ባዮቴክኖሎጂ ምርት ሙከራ በጥሩ ሁኔታ እይተካሄደ እደሚገኝ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር በተለያዩ ጊዜያት ገልጾታል።

 
በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ላይ እንደታየው ባዮቴክኖሎጂ ብዙ ባህላዊ, ኢኮኖሚያዊ፣ አካባቢያዊ፣ ስነምግባር፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ስጋቶችን እያጋጠሙት ይገኛል። ከባዮቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ ክርክሮችን ከሌሎች ቴክኖሎጂዎች ጋር ሲነፃፀር እጅግ በጣም ከፍተኛ ሆነው እናገኛቸዋለን። በተለይ አንዳንድ ሰዎቸ በባዮቴክኖሎጂ አማካኝነት የተመረቱ ምግቦችን የሚጠቀም ትውልድ ጆሮው ትላልቅ አስተሳሰቡ ዘገምተኛ ይሆናል የሚሉ እና የተለየያዩ ማስፈራሪያዎች የሚሰነዝሩበት ወቅት አለ። ባዮቴክኖሎጂ ተጠቅሞ የተመረተ የግብርና ምርት ዘርን በማኮላሸት ለመሃንነት ያጋልጣል፣ የባዮቴክኖሎጂ አሰራር የተከተለ ምግቦችን የተመገበ ትውልድ ለተለያዩ የጤና እክሎች ስለሚዳረግ ለአውሮፓውያኑ የህክምና ወጪ መዳረጉ አይቀርም የሚል መላ ምት የሚስነዝሩ አካላት አሉ። ይሁን እንጂ ሁሉም ባዮቴክኖሎጂዎች በአጠቃላይ ጎጂ ናቸው ተብሎ መገመት የለበትም. ለአብነት በአውሮፓ ውስጥ የሕክምና እና የፋርማሲው ባዮቴክኖሎጂዎች ውጤቶች ተቀባይነታቸው ከፍተኛ ቢሆንም የምግብ እና የእርሻ ባዮቴክኖሎጂዎች በጣም ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል።
የግብርና ምርትና ምርታማነት ከባዮቴክኖሎጂ ውጪ በሆኑ መደበኛ ዘዴዎች መጠቀም የተለመደ ቢሆንም ባዮቴክኖሎጂም ተጠቅመው ከፍተኛ ምርት የሚያመርቱ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ስነልቦናዊ ጫና ለቴክኖሎጂው እድገት እንቅፋት እንዳይሆን ያሰጋል። ምክንያቱም በባዮቴክኖሎጂ ተጠቅሞ የተመረተ ቲማቲም ላይ የሚደረገው ቁጥጥር ከፍተኛ ከሆነ እና ገበያተኛውም ምርቶቹ በጤናችን ላይ ችግር ያመጣል ብሎ ካሰበ አምራቹ በመደበኛው የእርሻ ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ወደማምረት ሊመለስ እንደሚችል የእንግሊዙ ኤቲ የተሰኘ የምርምር ጥናት ቡድን መረጃ አውጥቷ። 
  ዘመናዊ የግብርና ባዮቴክኖሎጂ ዘዴዎች እምብዛም ዋጋ አለማግኘታቸው አሳሳቢ ቢሆንም ቅሉ በሌላ በኩል የሕክምና እና የፋርማሲ እንዲሁም የፋብሪካ ግብአት የሚመረትባቸው ባዮቴክኖሎጂዎች ካላቸው በአነስተኛ ቦታ ሰፊ ምርት የማስገኘት ጥቅም ጋር ተያይዞ ተመራጭነታቸው እያደገ ይገኛል። ህንድ እና ቻይና ብቻ ካላቸው የጥጥ ማምረቻ ቦታዎች በባዮቴክኖሎጂ በመታገዝ እጥፍ ማምረት እንደቻሉ እና ከፋብሪካ ግብዓቶቻቸው አልፈው ወደውጭ ንግድ መላክ መቻላቸው ተጠቃሽ ይሆናል።
ወደ ኢትዮጵያ ስንመለስ ቅድሚያ ትኩረት የሚደረገውው የምግብ ዋስትና እና ራስን መቻል ላይ ነው። የግብርና ባዮቴክኖሎጂ ሳይንስ ደግሞ በአነስተኛ ቦታ ሰፊ ምርት ለማምረት የሚያስችል እድል የሚሰጥ አሰራር አለው። ምንም እንኳን የባዮቴክኖሎጂ ዘር ማለትም በላብራቶሪ የበለጸገ እና ከመደበኛው ዘር የተሻለ ምርት የሚሰጥ ለማድረግ በሚሊዮኖች አንዳንዴም በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ያስፈልጋል። ከዚህ በፊት ግን ህብረተሰቡ ስለባዮቴክኖሎጂ ያለውን አመለካከት ማቃናት እንደሚያስፈልግ ይታመናል።
ለዚህ ስራ ደግሞ የባዮቴክኖሎጂ ትምህርት ማስፋፋት አስፈላጊ ነው። በተለይ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ስለባዮቴክኖሎጂ ጥቅም እና አስፈላጊነት የሚያስረዱ በምስል እና በጽሁፍ የታገዙ ትምህርቶች ለወጣቶች ማዳረስ ይገባል። ትምህርቱም ወደባለሙያዎች እና ወጣቶቹ እየሰረጸ ሲሄድ የቴክኖሎጂው አስፈላጊነት በእራሱ ጊዜ ከህዝብ ጥያቄ አማካኝነት ሊመጣ የሚችልበት እድል ይኖራል። በሌላ በኩል አምራቹን ወይም አርሶአደሩን ባሳተፈ መልኩ ስለባዮቴክኖሎጂ ምርቶች ጥቅም የሚያስረዳ አንድ ኮሜቴ በመንግስት ደረጃ በማዋቀር ግንዛቤውን ማሳደግ ያስፈልጋል። አልፎ ተርፎም ከባዮቴክኖሎጂው ዘርፍ ጥሩ ተጠቃሚነት ያላቸውን አገራት ተሞክሮ ለአምራቹ በተለይም ለግብርና ኢንቨስተሮች በማሳየት በሰፋፊ እርሻዎች ላይ ተግባራዊ እንዲሆን መጣር ያስፈልጋል። ይህ ሲሆን በአንድ ሄክታር ላይ ይገኝ የነበረውን ምርት በእጥፍ እና ከዚያም በላይ በማሳደግ የኢትዮጵያን የምግብ ፍላጎት ማሟላት የሚያስችል ስራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማከናወን ይቻላል። በዚህ ስራ ውስጥ ደግሞ ባለሥልጣኖች፣ የቴክኖሎጂ ተቋማት፣ የግብርና አካላት እና ሌሎችም ማህበራዊ ሃላፊነት ያለባቸው ተቋማት ሊሳተፉበት የሚገባ ጉዳይ ነው።
ይህን አሰራር መተግበር ከተቻለ እና ዘርፉን በመንግስት እና በግል ኢንቨስተሮች መደገፍ ከተቻለ የባዮቴክኖሎጂ ምርቶችን ለኢትዮጵያውያን ብሎም ለምስራቅ አፍሪካ አገራት ማቅረብ የማይቻልበት ምንም ምክንያት አይኖርም።

Featured post

ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጠያቂነትን በማረጋገጥ፣ የሕግ በላይነትን በማስፈን፣ መንግሥትና የስራ አስፈጻሚ አካላቱ በመሉ ለሰብአዊ መብቶች መከበር፣ መጠበቅና መሟላት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያሳዩ ልዩ ትኩረትና ክትትል ይሻል

                    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየደረጃው ያሉ የመንግስት አስፈጻሚ አካላትና ኃላፊዎች ላይ የቅርብ ክትትል በማድረግ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር አስተዋጽኦ ሊያደር...