የግብርና ምርቶችን በአነስተኛ ዋጋ ለተጠቃሚዎች ለማቅረብ የሚረዱ ሱፐርማርኬቶችን በ350 ሚሊዮን ብር ሊገነባ መሆኑን ሚድሮክ ኢንቨስትመንት ግሩፕ አስታወቀ።
የሚድሮክ ኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ግሩፕ ኃላፊ አቶ ጀማል አህመድ እንደገለጹት፤ የግብርና ውጤቶችን በቅናሽ ዋጋ ለህብረተሰቡ የሚቀርቡ ሱፐርማርኬቶች በ350 ሚሊዮን ብር ወጪ ለመገንባት እቅድ ተይዟል። የገበያ ሰንሰለቱን በማሳጠር የሚሰሩ ሱፐርማርኬቶችን በማጠናከር ሸማቹ ህብረተሰብ በቅናሽ ዋና የአርሶአደሩን ምርቶች እንዲያገኝ ይደረጋል።
እንደ አቶ ጀማል ገለጻ፤ ተቋሙ በስሩ ባሉት 10 የኩዊንስ ሱፐርማርኬት አና አዲስ ሆም ዴፖ ቅርንጫፎች አማካኝነት የመጀመሪያ ደረጃ የግብርና ውጤቶችን እና የተለያዩ ምርቶችን ለህብረተሰቡ በቅናሽ ዋጋ ለማቅረብ እየሰራ ይገኛል። የሱፐርማርኬት ዘርፉን በማስፋት የህብረተሰቡን የምግብ አቅርቦት ለማስፋት የሚያስችል ጥናት እየተካሄደ ይገኛል። በአዲስ አበባ አገልግሎት እየሰጡ በሚገኙ የኩዊንስ ሱፐርማርኬቶች ላይ የማስፋፊያ ስራ የሚከናወን ሲሆን፤ በተለያዩ የምግብ ምርቶች የታየው የሸማቾችን ፍላጎት ለማሟላትም በሚቀጥሉት ሶስት ወራት ተጨማሪ ሱፐርማርኬቶች ይሰራሉ። በቀጣይ ሁለት ዓመታት ውስጥ 13 ትላልቅ የሱፐርማርኬት አገልግሎት መስጫ ፋሲሊቲዎች ይገነባሉ።
ከመንግስት ጋር በተቀናጀ አሰራር የግብርና ውጤቶችን ለተጠቃሚዎቸ በስፋት እንዲቀርቡ ይደረጋል ያሉት አቶ ጀማል፤ የምርት ሽያጩንም አሰራር በቴከኖሎጂ የታገዘ በማድረግ የገንዘብ ኖት ንክኪን በሚቀንሱ አሰራሮች አስተማማኝ ግብይት ለማከናወን የሚያስችል ትግበራ መጀመሩን ተናግረዋል። እንደ እርሳቸ፤ ለዚህ አሰራር ከዳሽን ባንክ ጋር በመተባባር የግዥ ስጦታ ካርድ ተዘጋጅቷል። ካርዱ በየጊዜው የሚሞላ የገንዘብ መጠን የሚኖረው ሲሆን ሸማቾች በተፈቀዱ ሱፐርማርኬቶች በኩል ያለጥሬ ገንዘብ እንዲገበያዩ ይረዳል። በካርዱ ላይ የተጫነው ገነዘብ ሲያልቅ በማንኛውም የዳሽን ባንክ ቅርንጫፍ በማስሞላት ለተጨማሪ አገልግሎት ማዋል የሚያስችል አሰራርን ይዟል።
የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱልፈታህ የሱፍ እንደገለጹት ደግሞ፤ በአቅርቦት እና ፍላጎት አለመጣጣም ምክንያት የሚመጣ ችግርን ለመቅረፍ የሱፐርኬቶች ድርሻ ከፍተኛ ነው። ከተማ አስተዳደሩ የግብርና እና የተለያዩ ምርቶችን ለህብረተሰቡ ከሚያቀርቡ የሱፐርማርኬት ዘርፍ ላይ ከተሰማሩ ባለሃብቶች ጋር በጋራ ለመስራት ፍላጎት አለው። የከተማው ነዋሪ የግብርና ውጤቶችን በቅናሽ ዋጋ እና በአፋጣኝ እንዲያገኝ የከተማ አስተዳደሩ በዘርፉ መዋዕለ ነዋያቸውን ለሚያፈሱ የግል ባለሃብቶች ምቹ የአሰራር ሁኔታዎችን አዘጋጅቷል።
እንደ አቶ አብዱልፈታህ ገለጻ፤ በዝቅተኛው የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኘው የህብረተሰብ ክፍል የምግብ እና ሸቀጣሸቀጥ አቅርቦትን ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት ውጤታማ ለመሆን በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራርን መከተል ይገባል። በዚህ ረገድ የዲጂታል ካርዶችን ጥቅም ላይ በማዋል እና ከጥሬ ገንዘብ ንክኪ የሆኑ አሰራሮችን በመከተል ረገድ የተጀመሩ መልካም ተሞክሮዎችን ማስፋት ያስፈልጋል። ከተማ አስተዳደሩም የንግድ ዘርፉን የማዘመን ተግባሩን አጠናክሮ ይቀጥላል።በጌትነት ተስፋማርያም
No comments:
Post a Comment