የዓለም ጤና ድርጅት /WHO/ ኃላፊ ዶክተር የቴዎድሮስ አድሃኖም መድኃኒቶችን ወደትግራይ ክልል እንዳናስገባ የኢትዮጵያ መንግሥት ፈቃድ ከለከለን በሚል ያቀረበው ክስ መሰረተ ቢስ ነው ሲል የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስታወቀ።
ማንም የከለከላቸው የለም ፤ ቀድሞ ፈቃድ እንደተሰጣቸው እየታወቀ መዋሸቱ አግባብ አልነበረም ሲሉ ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ተናግረዋል።
ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ለኢፕድ እንደገለጹት፤ የዓለም ጤና ድርጅት 95 ቶን መድኃኒትና የመድኃኒት ግብአቶች ለትግራይ ክልል ለማቅረብ እንድንችል እ.አ.አ. ከመጋቢት 21 ቀን 2022 አስንቶ እስከ ሚያዚያ 20 ቀን 2022 ድረስ የሰብአዊ ድጋፍ የአየር በረራ ማድረግ እንፈልጋለን፤ ፈቃድ ይሰጠን የሚል ጥያቄ ለኮሚሽኑ በደብዳቤ አቅርቧል።
ጥያቄውም ፈቃድ አግኝቶ በመጪው ሳምንት መጀመር ይችላሉ። ይሁንና ይህ ባለበትና ምንም ክልከላ ባልታየበት ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ወደክስ መግባቱ አግባብ አለመሆኑን ተናግረዋል።
ድርጅቱ እርሱ የጠየቀውን የጊዜ ገደብና ፈቃድ ተከትሎ መድኃኒቶቹን ለማጓጓዝ ቀሪ አምስት ቀናት እያላቸው የኢትዮጵያ መንግሥት ፈቃድ ከልክሎናል ማለታቸው አሳፋሪ ነው ብለዋል። ከዚህ ይልቅ ቀናቸውን ጠብቀው የጠየቁትን ያክል ጭነት ቢያጓጉዙ መልካም ነው ሲሉ ገልጸዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም ከሰሞኑ ለትግራይ 95 ሜትሪክ ቶን መድኃኒት የመድኃኒት ለማቅረብ ፈልገን የኢትዮጵያ መንግስት ፈቃድ ሊሰጥ አልቻለም የሚል ክስ በመገናኛ ብዙሃን በኩል ማውቅረባቸውም ይታወሳል።