የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ዛሬ ባወጣው መግለጫ በኦሮሚያ፡ ከሕግ አግባብ ውጪ በእስር ላይ የሚገኙ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አባላት በአፋጣኝ ከእስር ሊለቀቁ ይገባል፤ ሌሎች የቅድመ-ክስ ታሳሪዎችም ተዓማኒ ክስ ካልቀረበባቸው በአፋጣኝ ከእስር ሊለቀቁ ይገባል ብሏል
የተራዘመ ቅድመ-ክስ እስር (prolonged pre-trial detention) ሰዎች በፍትሕ አስተዳደር ላይ ያላቸውን እምነት ያጠፋል ሲል አሳስቧል።
ኢሰመኮ በተለያዩ ፖሊስ መምሪያዎች በእስር ላይ ያሉ የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) አባሎች የእስር ሁኔታን በተመለከተ ለረጅም ጊዜ ሲያደርገው ከነበረው ክትትል በተጨማሪ ከፓርቲው እና ከእስረኞች ቤተሰቦች በቀረቡ አቤቱታዎች መነሻነት ከመጋቢት 1 እስከ 10 ቀን 2014 ዓ.ም. በቡራዩ ከተማ፣ በገላን ከተማ እና በሰበታ ፖሊስ መምሪያዎች በአካል በመገኘት ክትትል ማድረጉን ገልጿል።
በዚህም እስረኞችን፣ የፖሊስ መምሪያ ኃላፊዎችን፣ የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽንን እና የኦሮሚያ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ተወካዮችን በማነጋገር ምርመራ ማድረጉን አስታውቋል።
በተጨማሪም በተለያዩ ጊዜያት እስረኞቹን በሚመለከት በፍርድ ቤት እና በዐቃቤ ሕግ የተሰጡ ውሳኔዎችን እና ትዕዛዞችን እንዲሁም የሕክምና ሰነዶችን መመልከቱን አሳውቋል።
በቡራዩ ፖሊስ መምሪያ በእስር ላይ የነበሩ አቶ ሚካኤል ጎበና፣ አቶ ኬኔሳ አያና፣ ዶ/ር ገዳ ወልጅራ፣ አቶ ዳዊት አብደታ፣ አቶ ለሚ ቤኛ፣ አቶ ገዳ ገቢሳ የተባሉ የፓርቲው አመራር መሆናቸውን የገለጹ ስድስት እስረኞችን ኮሚሽኑ አነጋግሯል። በተጨማሪም ኮሎኔል ገመቹ አያና በፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ማዕከል፣ እንዲሁም አቶ አብዲ ረጋሳ ገላን ከተማ በሚገኘው የኦሮሚያ ክልል ልዩ ፖሊስ ካምፕ ውስጥ በእስር ላይ የሚገኙ መሆኑን ከቤተሰብ እና ከጠበቆቻቸው መረዳት መቻሉን ጠቁሟል።
በተመሳሳይ አቶ በቴ ኡርጌሳ በእስር ላይ እያሉ ባጋጠማቸው ሕመም ምክንያት በፖሊስ ዋስትና ተፈቅዶላቸው በአንድ የሕክምና ተቋም ሕክምና ላይ የነበሩ መሆኑን ኮሚሽኑ መመልከቱን ይፋ አድርጓል፡፡
በዚህ ምርመራ መሰረት፣ ፍርድ ቤት በዋስትና እንዲለቀቁ የፈቀደላቸው፣ የክስ መዝገቦቻቸው ተዘግተው በፍርድ ቤት ውሳኔ በነፃ የተሰናበቱ፣ ምንም አይነት ክስ ያልተመሰረተባቸው እና ዐቃቤ ሕግ ክስ የማይመሰርትባቸው መሆኑን በማረጋገጥ የምርመራ መዝገባቸው የተዘጋ፤ ሆኖም ከወራት እስከ 2 ዓመት ለሚሆን ጊዜ በተለያዩ ቦታዎች እየተዘዋወሩ ከሕግ አግባብ ውጪ በእስር ላይ የሚገኙና የተወሰኑትም በእስሩ ሂደት በተፈጸመ ተገቢ ያልሆነ አያያዝ እና ድብደባ ለተለያዩ የአካል ጉዳቶችና የጤና እክል የተጋለጡ እስረኞች መሆናቸውን ኢሰመኮ መረዳቱን ገልጿል።
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ “የኦነግ ፓርቲ አመራሮች ለተራዘመ ጊዜ ከሕግ አግባብ ውጭ ታስረው የሚገኙ በመሆኑ በአፋጣኝ ከእስር ሊለቀቁ እና ለደረሰባችው ጉዳት ሊካሱ የሚገባ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም “የፍርድ ቤትና የዐቃቤ ሕግ ውሳኔዎች በተደጋጋሚ እየተጣሰ እስረኞቹ ከሕግ ውጪ ለተራዘመ እስር መዳረጋቸው ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም ስለሆነ የኦሮሚያ ክልል መንግሥት አፋጣኝ ማጣራት አካሂዶ ተገቢውን እርምጃ ሊወሰድበት ይገባል” ብለዋል፡፡
የኢሰመኮ የሲቪል፣ ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ መብቶች ኮሚሽነር ዶ/ር አብዲ ጂብሪል በበኩላቸው “በተለይም ታሳሪዎቹ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች በመሆናቸው በሕዝባዊ አገልግሎት ስራቸው ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት እንዳይጋለጡ ጥበቃ ሊደረግ ሲገባ፤ በተግባር የተገላቢጦሽ መሆኑ አሳዛኝ መሆኑን አስታውሰው ጉዳዩ አፋጣኝ እልባት ያስፈልገዋል” ሲሉ አሳስበዋል።