Friday, October 4, 2019

ዋሻ አምባ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳም


ከአዲስ አበባ ወደ ባሕር ዳር የሚወስደውን የአስፋልት መንገድ ይዘው ሲጓዙ ፍቼ፣ ደብረ ጉራቻ፣ጎሀ ጽዮን ከተሞችን አልፈው የዓባይን በረሃ ካጠናቀቁ በኋላ የደጀን ከተማን ያገኛሉ፡፡ ጉዞዎን በመቀጠል ...
የምሥራቅ ጎጃም ዋና ከተማ ደብረ ማርቆስን እንዳለፉ አማኑኤል ከተማ ይደርሳሉ፡፡ የአማኑኤል ከተማ ከአዲስ አበባ 330 . ርቀት ላይ የምትገኝ የማቻክል ወረዳ ዋና ከተማ ናት፡፡ ከአማኑኤል ከተማ ወደ ግራ ታጥፈው በጠጠራማው መንገድ ዐሥር ኪሎ ሜትር ያህል ከተጓዙ በኋላ አማሬ የምትባል አነስተኛ የገጠር መንደር ያገኛሉ፡፡

ትንሽ እንደተጓዙም ግራራም ማርያም ቀበሌ ይደርሳሉ፡፡ በዚህ ቀበሌ ውስጥ በርካታ ተፈጥሮአዊ ጸጋዎች ይገኛሉ፡፡ በደን የተሸፈኑ ተራሮችን በመካከላቸውም ድንቅ ሸለቆ ፈጥሮ የሚያልፈው ‹‹የሸማ ማጠቢያ›› ወንዝ ይገኛል፡፡ ወንዙ ከፀሐይ መግቢያ ወደ ፀሐይ መውጫ ቁልቁል ሲፈስ ላየው ተፈጥሯዊ ውበቱ ይማርካል፡፡ የሸማ ማጠቢያ ወንዝ ከተፈጥሯዊ ውበቱ ባሻገር ለአካባቢው አርሶ አደሮች የፍራፍሬና አትክልት ልማት አስተዋፅኦ እያበረከተ ይገኛል፡፡

ጥቂት እንደተጓዙ ድንገት የሚታይ የቅዱስ ዑራኤል ቤተ ክርስቲያን ይደርሳሉ፡፡ ከቅዱስ ዑራኤል ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን በግራ በኩል ደግሞ የዋሻ አምባ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ገዳምን የእንስሳት ማደሪያ የሆነውን ቆርቆሮ ቤት ያያሉ፡፡ የከብቶችን ቤት ወደ ግራ እየተው ደረጃውን ቁልቁል መንገድ ይዘው ሲጓዙ ቀጭን መንገድ ያገኛሉ፡፡

ከዚያም በቆርቆሮ ክዳን የተሠራውን የተግባር ቤት የገዳሙ ምዕመናን ምግብ የሚዘጋጅበትና የሚታደልበት ቤት ነው፡፡ በዚህ ቤት ውስጥ መቀነታቸውን ታጥቀው፣ ቆባቸውን ደፍተው፣ እንጀራ የሚጋግሩ፣ ወጥ የሚሠሩ፣ ማገዶ የሚያቀርቡ እንስት ባሕታውያን በየዕለቱ በትጋት ሲሠሩ ይመለከታሉ፡፡
 
 እማሆይ ወለተ ማርያም




ከተግባር ቤቱ ወደ ፀሐይ መግቢያ ታጥፈው የአቀበቱን ጉዞ መያያዝ ግድ ይልዎታል፡፡ በዚህ መንገድ ላይ ሲጓዙም በግራ ቀኝ የተለያዩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን ያገኛሉ፡፡ ወደፊት ጥቂት እንደተጓዙም የተለያዩ ምንጮች ከከፍታ ቦታ በስተቀኝ በኩል ሁለት ሰፋፊ ዋሻዎችን ያያሉ፡፡ የመጀመሪያው ዋሻ ወደ ገዳሙ የሚመጡ ጠበልተኞች የሚያርፉበትና ምግባቸውን የሚያበስሉበት ትልቁ ዋሻ ነው፡፡ በዚህ የዋሻ በር የቀኝ ጠርዝ ላይ ከምድር እስከ ዋሻ ጣራ ድረስ በድንጋይ ካብ የተሠራና ጠንካራ የጣውላ መዝጊያ የተገጠመላት ትንሽ ቤት ያያሉ፡፡ ይህች አነስተኛ ቤት የገዳሙ መሥራች ቤት ናት፡፡
የገዳሙ መግቢያ

ትልቁንም ዋሻ በቀኝ በመተው፤ ወደ ግራ ደግሞ ገደላማውን ቦታ እየቃኙ ወደፊት ጥቂት እንደተራመዱ ሁለተኛውን ዋሻ ያገኛሉ፡፡ ይህ ዋሻ ከመጀመሪያው ዋሻ ጋር በተፈጥሮ ግድግዳ ተያይዟል፡፡ በዚህ ዋሻ ፊት ለፊት ደግሞ ከከፍታ ቦታ እየተወረወሩ ወደ ገደሉ የሚወርዱ ሦስት ትንንሽ ጅረቶችን ያገኛሉ፡፡ አንደኛውን ፏፏቴ እልፍ እንዳሉም የዋሻ አምባ አቡነ ተክለሃይማኖት ገዳምን ያገኛሉ፡፡ ይህ ገዳም ሁለት በሮች አሉት፡፡

በመጀመሪያ ከውጪ ወደ ዋናው የሚገባ ሰው ምንም ነገር ማየት አይችልም፡፡ ለዓይን የማይታይበት ድቅድቅ ጨለማ ነው የሚያጋጥመው፡፡ ድቅድቁ ጨለማ ቀስ በቀስ እየተገፈፈና ዓይን ጨለማውን እየተለማመደ ሲሔድ የዋሻውን ምዕራባዊ ዳርቻ ይመለከታሉ፡፡ ዋሻው ከምዕራብ ወይም ከፀሐይ መግቢያ ወደ ምሥራቅ ወይም ፀሐይ መውጫ በቁመት ከፍ እያለ ይሔድና ከበሮቹ ላይ በሚገናኝበት ቦታ ላይ ከሁለት ሜትር ርቀት የበለጠ ቁመት አለው፡፡
ከምስራቅ ወደ ምዕራብ አቅጣጫ ወደ ዋሻ ሲገባ ያለው የጣራ ርዝማኔ እየቀነሰ ይሔድና ከተፈጥሮ የድንጋይ ግድግዳ ጋር ይዋቀራል፡፡ ሰፊው የዋሻ ክፍል የቅዳሴ አገልግሎት የሚሰጥበት ሲሆን በዋሻው የግራ ጠርዝ መጨረሻ ላይ ያለው ደግሞ የተለያዩ ጽላቶች የሚገኙበት ቤተ መቅደስ ነው፡፡ ያላየናቸው ዋሻዎችና ሌሎች ምሥጢራዊ ሀብቶችን ባለቤቱ ያውቀዋል፡፡ ቅዱሳን ያውቁታል፡፡ እማሆይም ሊያውቁት ይችላሉ፡፡

ከዋሻው በር በውጭ የቀኝ አቅጣጫ በአናት በኩል ሁለት ጅረቶች ከከፍታ ቦታ ወደ ታች እየተወረወሩ ፊት ለፊት ካለው ገደል የመዋኛ ገንዳ ከሚመስለው ይቀላቀላሉ፡፡ አንደኛው የአባታችን የአቡነ ተክለሃይማኖት ጠበል ሲሆን፤ ከዚያ እልፍ ብሎ ደግሞ ከአንድ ምሰሶ ሥር የሚፈልቅ የቅዱስ ዑራኤል ጠበል ይገኛል፡፡

ከመጀመሪያው ዋሻ ወደ ገዳሙ ዋሻ ሲኬድ በሁለተኛ መስመር ላይ ከሚገኘው አነስተኛ ምንጭ ሥር አንድ ዛፍ ከዚህ ውሃ እየተመገበ ሥር ሰዶ ድንጋዮችን ሰንጥቆ ገብቶ አድጎ ይታያል፡፡ ይህ እንጨት ከድንጋይ በላይ ያለው አካሉ የመስቀል ቅርፅ ያለው ነው፡፡
የዋሻ አምባ አቡነ ተክለሃይማኖት ገዳም በአማራ ብሔራዊ ክልል በምሥራቅ ጎጃም ዞን ማቻክል ወረዳ ግራራም ቀበሌ የወንዶችና የሴቶች ገዳም ሆኖ በማገልገል ላይ ይገኛል፡፡

ገዳሙ እንዴት ተመሠረተ? በማንስ ተመሠረተ?

ወይዘሮ ድንቃየሁ ከዋሻ አምባ አቡነ ተክለሃይማኖት ገዳም በአጭር ርቀት ላይ በሚገኘውና ቂርቆስ በተባለው የገጠር ቀበሌ ከአርሶ አደር ቤተሰብ ውስጥ ነው የተወለዱት፡፡ ለዘመናዊም ሆነ ለቤተ ክርስቲያን ትምህርት አልታደሉም፡፡ ዕድሜአቸው ለቅመ ሔዋን ሲደርስ ወላጆቻቸው በአካባቢው ባሕልና ወግ መሠረት ዳሩአቸው፡፡ ከዚያም ወይዘሮ ድንቃየሁ ቤት ሠርተው ጎመን ዘርተው የሞቀ ትዳር ባለቤት ሆኑ፡፡ ሁለት ልጆችንም አፈሩ፡፡ በዚህ የትዳር ሕይወታቸው ላይ እያሉ በተደጋጋሚ በሕልም ይታያቸው ነበር፡፡

ወሩን ቀኑንና ዓመተ ምሕረቱን ለይተው በማያውቁት አንድ ሌሊት በርካታ ካህናትና ቀሳውስት በተሰበሰቡበት ቦታ ላይ ይደርሳሉ፡፡ ከእነዚህ ሰዎች መካከል ከፊሎቹ ቀዮች ከፊሎቹ ደግሞ ጥቁሮች ነበሩ፡፡ ወይዘሮ ድንቃየሁ በእነዚህ ሰዎች መካከል ለመቀመጥ ሲሞክሩ አንድ ክንፍ ያለው ቀይ ሰው እጃቸውን ይዞ እየመራ ከዋክብት ወዳሉበት አንድ ቦታ ያደርሳቸዋል፡፡

 ከዚያም ይህ ሰው ከመሬት ወደ ሰማይ የተዘረጋ ቀጭን የብረት መሰላል እያሳየ በዚያ መሰላል ላይ ወደ ላይ እንዲወጡ ይነግራቸዋል፡፡ ወይዘሮ ድንቃየሁ እንደታዘዙት መሰላሉን እየፈሩ እየቸሩ ወደ ላይ መውጣት ይጀምራሉ፡፡ የመሰላሉን ግማሽ ያህል እንደወጡ ወደታች ሲመለከቱ ጥቋቁር ሰዎች ያሉበትን ገደላማ መሬት ያያሉ፡፡ በዚህ ጊዜ በመንታ ሃሳብ ውስጥ ሆነው ቆም ብለው ወደላይ ለመቀጠል እንዳልቻሉ ሲያስቡ ወደታች ለመመለስ በመሬት ላይ ሆነው የሚጠባበቋቸው ጥቋቁር ሰዎች ጉዳት እንደሚያደርሱባቸውና ገደል እንደሚገቡ እየተጨነቁ እያሉ ያው እየመራ ያወጣቸው ሰው ‹‹ቀጥይ አትፍሪ›› በሚል ያበረታታቸዋል፡፡

 ወይዘሮ ድንቃየሁ የጀመሩትን የመሰላል መውጣት ትግል ቀጥለው መጨረሻ ላይ አራት ዙር አጥር የመሰለ ነገር ላይ ያርፋሉ፡፡ በዚያ ቦታ ቤተ መንግሥት አለ፡፡ በእያንዳንዱ አጥር በር ላይ ዘበኞች ቆመዋል፡፡ የመጀመሪያው ዘበኛ ወደ ሁለተኛ የሁለተኛው ወደ ሦስተኛ የሦስተኛው ወደ አራተኛ ዘበኛ በር እየከፈቱላቸው መንገድ እየመሩ ካስተላለፏቸው በኋላ መጀመሪያ መሰላሉን እንዲወጡ ያዘዛቸው ቀይ ሰው ወደ ከበሮ መሰል ቤት ያስገባቸውና ‹‹አይዞሽ አትፍሪ፤ ከእንግዲህ የሚያገኝሽ የለም በቃ›› የሚል ማጽናኛ ቃል ይነግራቸዋል፡፡ ወዲያው ከእንቅልፋቸው ይነቃሉ፡፡ምን ይሆን እያልኩ አደንቃለሁ እፈራም ነበርአሉ እማሆይ፡፡

 ሌላ ጊዜ ደግሞ ትዳራቸውን ትተው ለመውጣት ምክንያት የሆናቸውን ሕልም አዩ ሀገር በእሳት ሲለበለብና ሕዝቡ ሁሉ ከዚህ እሳት ለማምልጥ ሲሮጥ ይመለከታሉ፡፡ እሳቸውም ከእሳቱ ሮጠው አምልጠው ሲሄዱ በተደጋጋሚ ያያሉ፡፡ይህ የእግዚአብሔር ጥሪ ነው፡፡ብለው ሀብት ንብረቴን፤ ልጆቼን ሳይሉ ትዳራቸውን ትተው ወደ ወላጆቻቸው ቤት ይመለሳሉ፡፡ የፈጣሪያቸውን መንገድ መርጠውና ፈቅደው የመንፈሳዊ ሕይወት ጉዞአቸውን ለመጀመር ጎጇቸውን ተሰናበቱ፡፡

 ወይዘሮ ድንቃየሁ ወደ ወላጆቻቸው ቤት እንደተመለሱ ቀን ቀን አብዛኛውን ጊዜአቸውን ወደ ቅዱስ ቂርቆስ ቤተ ክርስቲያን በመሔድ በማስቀደስና ስብከተ ወንጌልን በማዳመጥ ማሳለፍ የዕለት ተዕለት ተግባራቸው አደረጉት፡፡ ድንገት ተነስተው ግን ወደ ሌላ ቦታ ተጓዙ፡፡ ቦታው አሁን ካለበት በግምት 65 ኪሎ ሜትር በላይ በሚርቀውና ‹‹ሰሳ ገዳም›› እየተባለ በሚጠራ ቦታ ነው፡፡ ሰሳ ገዳም ከደረሱ በኋላም ለሰባት ወር በዚያም ተቀመጡ፡፡ ሰሳ ገዳም ከደብረ ማርቆስ ከተማ ወደ ምሥራቅ አቅጣጫ አባ አስራት ገዳም ከሚባለው ጥንታዊ ገዳም አካባቢ የሚገኝ ገዳም ነው፡፡ ከሰባት ወር የገዳም ቆይታቸው በኋላም እንደገና ወደ ወላጆቻቸው ቤት ተመለሱ፡፡

 ወደ ወላጆቻቸው ቤት እንደተመለሱም እንደተለመደው ወደ ቅዱስ ቂርቆስ ቤተ ክርስቲያን እየተመላለሱ ማስቀደስና በዚያው ጸሎት ሲያደርሱ መዋል የዕለት ከዕለት ሕይወታቸው ሆነ፡፡ ይህ በእንዲህ ታላቅ እኅታቸውሰኔ ጎልጎታ መጸሐፍ ገዝተሸ አንብቢብላቸው ስለነበር እንዳለ አንድ ቀን እናታቸው ወደ ከተማ ለገበያ ለመሔድ ሲዘጋጁ መጽሐፍ እንዲገዙላቸው ይጠይቃሉ፡፡ እናትም ‹‹አንቺ አልተማርሽ፤ ፊደል አትለዪ መጽሐፍ ምን ያደርግልሻል?›› ብለው ይመልሱላቸዋል፡፡

ወይዘሮ ድንቃየሁም ግድየለም መጽሐፉን ባየው ብሳለመውስ? የሚል መልስ ይሰጧቸውና እናት ወደ ገበያ ሊወጡ ሲሉ የምትገዢልኝ ደግሞ የሰኔ ጎለጎታ መጽሐፍን ነው ብለዋቸው ይለያያሉ፡፡ እናትም የሰኔ ጎለጎታን መጽሐፍ ከገበያ አጠያይቀውና ገዝተው ያመጡላቸዋል፡፡ መጽሐፉን እየገለጡ ሲመለከቱ ከቆዩ በኋላድንግል ሆይ ምንም እንኳን እንደምኞቴ ጸሎትሽን ማንበብና መድገም ባልችልም ጸሎትሽን እንደጸለይኩ አድርገሽ ቁጠሪልኝ፡፡እያሉ በመማጸን መጽሐፉን ይዘጋሉ፡፡

 ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ተአምር ይከሰታል፡፡ ወይዘሮ ድንቃየሁ እናታቸው የገዙላቸውን የሰኔ ጎልጎታ የቅድሰት ድንግል ማርያም የጸሎት መጽሐፍ እየገለጡ ገጽ በገጽ እያገላበጡ ሲመለከቱ ይቆዩና አጥፈው መማጸናቸውን ይቀጥላሉ፡፡ ወይዘሮ ድንቃየሁ ሳያስቡት የሰኔ ጎልጎታን ከገጽ እስከ ገጽ ማንበብ ጀመሩ፡፡ ይህን የሰሙ እናታቸውምዛሬ ደግሞ ከማን ጋር ታወሪያለሽሲሉ ይጠይቋቸዋል፡፡ 

እዪው መጽሐፉን ማንበብ ቻልኩ እኮ፡፡ ስሚበማለት የንባብ ችሎታቸውን ያሰሟቸዋል፡፡ እናትም በነገሩ ተደንቀው ልጃቸውን ወይዘሮ ድንቃየሁን ወደ ንስሐ አባታቸው ይዘው ይሔዳሉ፡፡ የንስሐ አባታቸውን በቤተ ክርስቲያን ያገኙና የሆነውን ሁሉ ይነግሯቸዋል፡፡ ቄሱ ነገሩን ማመን ቢሳናቸውም የተባለውን ድንቅ ተአምር ለመስማት መርጠው ወይዘሮ ድንቃየሁ መጽሐፉን በንባብ እንዲያሰሟቸው ጠየቋቸው፡፡

 መጽሐፉን ቃል በቃል እያሰሙ ገጾችን እያገላበጡ ድምጻቸውን ከፍ አድርገው አነበቡ፡፡ ቄሱም እየተደነቁና እየተገረሙ ሁሉንም ካዳመጡ በኋላ ‹‹እግዚአብሔር የጀመረልሽን ፀጋ ከዳር ያድርስልሽ፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም አትለይሽ፡፡ ያነበብሽው ጸሎት ድንግል ማርያም በአማልጅነቷ ለአማኞች ያቀረበችው ጸሎት ነው፡፡ 

 በስሟ መጽሐፍ ለጻፉ፣ ቤተ ክርስቲያን ለሠሩ፣ በስሟ ምጽዋት ለመጸወቱ፣ ለቤተ ክርስቲያን ዕጣን፣ ጧፍ ላበረከቱ ምሕረት ጸጋ ይሰጥ ዘንድ ለልጇ ለኢየሱስ ክርስቶስ በመቃብሩ በጎልጎታ ላይ ሆና ያቀረበችለት ልመና ነው፡፡ ልጇም እናቱ የጠየቀችውን ሁሉ ለመፈጸም ቃል ገብቶላታል፡፡ በቃለ መሃላም አረጋግጦላታል፡፡ ይህን ነው አሁን ያነበብሽው፡፡ ጸሎትና ክርስቶስም ለእናቱ የገባውን ቃል ኪዳን ለአንችም ይፈጽምልሽ ዘንድ ጸሎቴ አይለይሽም፡፡ የጀመርሽው መንፈሳዊ ጉዞ በእግዚአብሔር የተፈቀደ በመሆኑ ያለጥርጥር ይሳካል›› ሲሉ አባ ለወይዘሮ ድንቃየሁ ቡራኬ ሰጥተው አሰናበቷቸው፡፡ በሰው ዘንድ የማይቻል በእግዚአብሔር ዘንድ ይቻል የለ፡፡

 ወይዘሮ ድንቃየሁ ሕልም ማየታቸውን አላቋረጡም፡፡ አንድ ቀን አባ ይትባረክ የተባሉ መነኩሴ ከሩቅ ቦታ መጥተው በወላጆቻቸው ቤት የእግዚአብሔር እንግዳ ብለው ይገባሉ፡፡ እማሆይም እራታቸውን አብልተው እግራቸውን አጥበውና ምኞታቸውን አዘጋጅተው እንዲያድሩ ያደርጋሉ፡፡
 የአባ ይትባረክ ወደዚያ አካባቢ መምጣት የተለመደ ነበር፡፡ ከስምንት ዓመት በፊት በወይዘሮ ድንቃየሁ አባት የተጀመረውን የቅዱስ ቂርቆስ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ለማሠራትና ሕዝቡን ለማስተማር ብዙ ጊዜ ተመላልሰዋል፡፡

 ይሁን እንጂ የቤተ ክርስቲያኑ ሥራ ሳይጀመር ይቀራል፡፡ የወይዘሮ ድንቃየሁ ወላጅ አባትና አባ ይትባረክ የተነሱለት ዓላማ ባለመሳካቱ ተስፋ ቆርጠው ጊዜ ይጠብቃሉ፡፡ አባ ይትባረክ በእንግዳነት ባደሩበት ሌሊት ወይዘሮ ድንቃየሁ ሕልም ያያሉ፡፡ ሕልሙ ወይዘሮ ድንቃየሁ ወደ ቅዱስ ቂርቆስ ቤተ ክርስቲያን እየሔዱ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ አዘውትረው የሚሔዱቡት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ ሕንፃ መግቢያ በር ላይ እንደደረሱ ሦስት ሰዎች ቀድመዋቸው በቀጥታ ወደ መቅደስ ይገባሉ፡፡ ከዚያም ወይዘሮ ድንቃየሁ ተከትለው ለመግባት ሲሞክሩ በሩ ላይ ሁለት እርጉዝ ሴቶች ለመውለድ ምጥ ተይዘው ያገኛሉ፡፡

 ሁለቱን ሴቶች ምጥ ተይዛችሁ ለምን እዚህ መጣችሁ? እያሉ በመጠየቅ ላይ እንዳሉ ሴቶቹ ይገላገላሉ፡፡ ወይዘሮ ድንቃየሁ አሁን ተገላግላችኋል፡፡ ምስጋና ለአምላክ ይሁን፡፡ ተነሱና የማርያም መሸኛ እናዘጋጅ ይሏቸዋል፡፡ ሁለቱ አራስ ሴቶች እኛ ማተብ ሳናስር ከዚህ አንወጣም በማለት ለመውጣት ፈቃደኛ አልሆኑም፡:

ወይዘሮ ድንቃየሁ እምቢ ሲሏቸው ከቤተ ክርስቲያኑ ወጥተው ወደ ቤታቸው ለመሔድ ጉዞ ሲጀመሩ አንድ ወጣት ቀይ ግምጃ የለበሰ ወጣት ጠርቶ ያስቆማቸዋል፡፡ ከዚያም ሰውየው ወደ አጠገባቸው ይቀርብናእንኪ ይህን መስቀል ለአባ ይትባረክ ስጫቸው፡፡ይላቸዋል፡፡ ወይዘሮ ድንቃየሁእኔ ቄስ ወይም ዲያቆን አይደለሁም፡፡  

መስቀል እንዴት እይዛለሁ?” በማለት እምቢታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ሰውየው አሁንም ጥያቄውን እየደጋገመ ያስቸግራቸዋል፡፡ ወዲያውአባ ይትባረክን መስቀሉን ይዘህ ቤተ ክርስቲያን ሦስት ጊዜ እየዞርህ ባርከው የታሰበው ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ይሠራል፡፡ የተቀበረውም ይመክናል ብለሽ ንገሪው፡፡ብሎ መልእክቱን እንደነገራቸው ከእንቅልፋቸው ይነቃሉ፡፡

ጥዋት ቀደም ብለው አባ ይትባረክና ወይዘሮ ድንቃየሁ ወደ ቅዱስ ቂርቆስ ቤተ ክርስቲያን ለኪዳን ሲሄዱ ሌሊት ያዩትን ሕልም ለአባ ይትባረክ ይነግሯቸዋል፡፡ አባ ይትባረክ በጥሞና ካዳመጡ በኋላ ትርጉሙን ለወይዘሮ ድንቃየሁ ይነግራሉ፡፡ትርጉሙም የተገላገሉት እኛ የደከምንበት፣ ብዙ ያሰብንበት የዚህ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን ሥራ ከዳር መድረሱን እኛም ከሀሳብ መገላገላችንን የሚያመለክት ነው፡፡ የታሰበው በሕንፃ ቤተ ክርስቲያኑ ሥራ መጀመርና መጠናቀቅም አንቺን አምላክ ምክንያት ያደርጋል፡፡ በአንቺ ቅስቀሳና ማስተባበር የሕዝቡ ልቡና ቀንቶ አሳባችን ይሳካል፡፡በማለት ተረጎሙላቸው፡፡

 በሚቀጥለው የሰንበት ቀን ሕዝቡ በተሰበሰበበት አባ ይትባረክና ወይዘሮ ድንቃየሁ የቤተ ክርስቲያኑ ሕንፃ የሚጀመርበትን ሀሳብ ለቀበሌው ሕዝብ ያቀርባሉ፡፡ ሕዝቡም በአንድ ልብ አስቦ በአንድ መንፈስ ተመካክሮ ለስምንት ዓመት ሲጓተት የቆየው ሥራ እንዲጀመር አስተባባሪ ሽማግሌዎችን ሰይሞ ይለያያል፡፡

 የቤተ ክርስቲያኑ ሕንፃ ሥራ ተጀመረ፡፡ ወይዘሮ ድንቃየሁ የሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑን ሥራ አደራ ከአምላክና ከቀበሌው ሰበካ ጉባኤ ሕዝብ ከተቀበሉ በኋላ እርዳታ ለማሰባሰብ በተለያዩ ከተሞች ጥረታቸውን ቀጠሉ፡፡

የአካባቢው አርሶ አደሮችም በገንዘባቸው፣በጉልበታቸው ሙሉ ትብብር በማድረግ የቅዱስ ቂርቆስ ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ ሥራ በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ተመረቀ፡፡

 የቅዱስ ቂርቆስ ሕንፃ ቤተ ክርስቲያን በአጭር ጊዜ መጠናቀቁን የተመለከተው የጎረቤት ቀበሌ ማለትም የግራራም ማርያም ሕዝብም ለእማሆይ ወለተ ማርያም ጥያቄ አቀረበ፡፡ ቤተ ክርስቲያናችን በዕድሜ ብዛት ማርጀቱንና በአዲስ መልክ መሥራት አስፈላጊ በመሆኑ፤ ለዚህም ሥራ ወይዘሮ ድንቃየሁ እርዳታ እንዲያስተባብሩላቸው ይጠይቃሉ፡፡  

እሳቸውም ሕዝብ በተሰበሰበበት የሕንፃ ቤተ ክርቲያኑን ሥራ ለማስተባበር እርዳታም የሚቻላቸውን ሁሉ ለማፈላለግ ቃል ይገባሉ፡ የአምላክ ፈቃድ ታክሎበት የግራራማ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ሕንፃ በአጭር ጊዜ ተጠናቆ ይመረቃል፡፡

 ወይዘሮ ድንቃየሁ በሕልማቸው ሁልጊዜ የሚያዩት ተራራ፣ደን፣ዋሻ ነበር፡፡ ዋሻው በደን (የወደፊቱ እየታያቸው) የተከበበና አራዊት የሚኖሩበት፣ የተለያዩ ጅረቶች የሚፈሱበት፣ በተራሮች አካባቢ እንደሚገኝም ይታያቸዋል፡፡የት ይሆን?” እያሉ ያስቡ ነበር፡፡ 

 ያዩትን ሕልም መሠረት አድርገው የአካባቢውን ነዋሪዎችንእንዲህ ዓይነት ቦታ አለን? በግራራም ቀበሌ ገበሬ ማኅበር ክልል ውስጥ ይገኝ ይሆንን?” ብለው ጠየቁ፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎችምአዎንብለው ቦታውን ሊያሳይዋቸው ይዘዋቸው ሄዱ፡፡ እግዚአብሔር ቀድሞም ያዘጋጀው ቦታ ስለሆነ ገና ሲያዩት የቦታውን ክብር ተረዱ ሕልማቸውም እውነተኛ ሆነ፡፡

 እማሆይ ወደ ገዳሙ ሲደርሱ የአካባቢው ሰዎችም ወደ ቤታቸው ሄዱ፡፡ ጅብና የነብር መንጋዎች ግን እማሆይን ሳያተናኮሉ ያላምዷቸው ነበር፡፡እማሆይ የአራዊቱ በቦታው መኖር አላስፈራቸውም፡፡ በእምነታቸው ጸንተው በጻድቃን ሰማዕታትና በቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ጥበቃ በጫካ ውስጥ ያሉ አራዊቶች በሙሉ ተገዙላቸው፡፡ የእግዚአብሔር ክብር የሚገለጽበት ቦታ በመሆኑ እግዚአብሔር እማሆይን መንገድ ጠራጊ አደረገ፡፡

 ዋሻዎቹ በጥንት ዘመን ሰዎች ከጦርነት ወረራና ጥቃት ለማምለጥ ይጠለሉበት የነበረ መሆኑን አንዳንድ ካህናት ይጠቁማሉ፡፡ ዋሻው ውስጥ የእህል ማከማቻ ጎተራ የምግብ ማብሰያ ሸክላና ማገዶ እንዲሁም ሌሎች ቁሳቁስ ተገኝተዋል፡፡

 ከዋሻው አናት በላይ ከረጅም ርቀት እየተወረወሩ ቁልቁል የሚፈሱት ጅረቶች መውረጃ መንገዳቸውን ስተው ወደ ዋሻው ውስጥ በመፍሰሳቸው ዋሻው በደለል ተሞልቷል፡፡ ዋሻውን ከደለል አጽድቶ ቅርጽ እንዲይዝ የእማሆይ ቀጣዩ ተግባር ነበር፡፡ ለዚህ ሥራ የአካባቢውን ሕዝብ በማስተባበር ደለሉ ተጠረገ፡፡ እማሆይም መኖሪያቸውን ከአራዊት ጋር አደረጉ፡፡

 እማሆይ ወለተ ማርያም ደለል ጠርገው መኖሪያ ባደረጉት ዋሻ ውስጥ ቀድመው ይኖሩ የነበሩ የተለያዩ የዱር አራዊት ማታ ከጫካ ሲመለሱ፣ ጥዋት ወደ መዋያቸው ሲሰማሩ በእማሆይ ላይ ምንም ጥቃት አላደረሱም፡፡ በድምፁ የረበሸ፣ ፀጥታ የነፈገ አውሬ ሳይኖር እማሆይና አራዊቱ ዓይን ለዓይን እየተያዩ ለሁለት ዓመታት በሠላም አብረው ቆዩ፡፡

 ከሁለት ዓመታት የጋራ ኑሮ በኋላ አራዊቱ ዋሻውን ለእማሆይ የብቸኝነት መኖሪያ ለቅቀውላቸው ወደ ሌላ አካባቢ በእግዚአብሔር ፈቃድ ተሰደዱ፡፡እንዲህ አሉ እማሆይአንድ ቀን ጅቦቹና ነብሮቹ ተሰበሰቡ የዛን ቀን ልዩ ነገር አየሁ፤ መሬቱን ጫሩ፣ጮኹ፣አለቀሱ፡፡ ጩኸታቸው እንደዛ ቀን አስፈርቶኝ አያውቅም፡፡ ወዲያው ገዳሙን ለቀው ሄዱ፡፡ ያኔ ፈራሁ አለቀስኩ፡፡ 

 ጓደኞቼ ነበሩና ሲለዩኝ አዘንኩ፡፡እማሆይ በዚህን ጊዜ ነው የበለጠ የተጨነቁት፡፡ የአራዊቱ መውጣትና መግባት መቆም ለእማሆይ አሳሳቢ ፈተና ነበር፡፡ አራዊቱ ጥዋትና ማታ ሲወጡና ሲገቡ ለእማሆይ እንደ ቅርብ ዘመዶቻቸው ፍቅር አሳድረዋል፡፡ በዓይን በመተያየት ተላምደዋል፡፡ ባለመጣላታቸውና ጉዳት ለማድረስ ባለመሞከራቸው አራዊቱ ለእማሆይ ታላቅ ባለውለታዎች ሆነዋል፡፡ ኀጥዕ ማንም ሳያሳድደው ይሸሻል፡፡ ጻድቅ ግን እንደ አንበሳ ያለፍርሃት ይኖራል፡፡ እንዳለ መጽሐፈ ምሳሌ፡፡

 እማሆይ ወለተ ማርያም ለሁለት ዓመታት በዋሻው ውስጥ ከቆዩ በኋላ በወቅቱ ወደ ነበሩት ወደ ምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዘካርያስ እርዳታ ጠየቁ፡፡ ለሊቀ ጳጳሱ ስለ ዋሻው ምንነትና የወደፊት መንፈሳዊ ፀጋ አስረዱ፡፡ በመጨረሻም ሊቀ ጳጳሱ ዋሻውን እንደሚያዩላቸው ቃል ገቡላቸው፡፡ በቃላቸው መሠረትም ወደ አካባቢው ተጉዘው ዋሻውንና አካባቢውን ከተመለከቱ በኋላይህማ ገዳመ ቆሮንቶስ ነው፡፡ብለው እማሆይ ምን እንደሚፈልጉ ጠየቁ፡፡ እማሆይ ወለተ ማርያምምየእግዚአብሔር መልካም ፈቃዱ ቢሆን እኔ የምመኘው የአባታችንን የአቡነ ተክለ ሃይማኖትንና የቅዱስ ዑራኤልን ጽላት ቢገባልንና ቢገደምአሉ፡፡

 የምሥራቅ ጎጃም ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዘካርያስ መልካም ፈቃዳቸው ሆኖ ግንቦት 22 ቀን 1987 . የተጠየቁትን ጽላቶች ይዘው ወደስፍራ በመሄድ ጽላቶቹን አስገብተው ገዳም መሆኑን አበሠሩ፡፡ በአካባቢው ሕዝብ ዘንድ ታላቅ በዓል ተደረገ፡፡ በዕለቱ የቅዱስ ዑራኤልና የአባታችን የአቡነ ተክለ ሃይማኖት ፀበሎች ተባርከው ለሕዝቡ አገልግሎት መስጠት ጀመሩ ፡፡ 

 እማሆይ ገዳሙን አስፍተው፤ሥርዐተ ገዳሙን አጠናክረው በልማት መስክ ተሰማርተው ሳለየቅዱስ ዑራኤልን ቤተክርስቲያን ብንሠራብለው አሰቡ፡፡ የመንፈስ ልጆቻቸውን አማከሩ፡፡ በገዳሙ የተፈወሱ ወንድሞች ዲዛይኑን ሠርተው በማስረከባቸውና ገንዘብ በማሰባሰባቸው እማሆይም አዲስ አበባ ድረስ በመሄድ ለህንጻው የሚሆን የግንባታ ዕቃ በማሰባሰብ በአጭር ጊዜ ቤተክርስቲያኑ ተሠርቶ አለቀ፡፡

 ቤተክርስቲያኑን ድንገት ለሚያየው እጅግ ያማረ ሆኖ ደኑን ከጀርባው አድርጎ የበቀለ የሚመስል እጅግ የሚማርክና መንፈስን የሚያድስ ነው ፡፡ በዚያ ቦታ ያንን የመሰለ ቤተክርስቲያን መሠራቱ በእናቶቸ አስተባባሪነት፡፡ ያውም ፊደል ባልቆጠረ፡፡ እኔ ባየሁት ሁሉ ነፍሴ ረክታለች፡፡ ተስፋዬም ለምልሟል፡፡ደግ ሰው! የሃይማኖት ሰው! ታታሪ ሰው! እግዚአብሔር አላሳጣንምና፡፡ ገዳሙን ያስፋልን ሺህ እልፍ ያድርግልን፡፡

 እማሆይ የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበራት ቅንጅት ድርጅት ተምሳሌት ዕጹብ ድንቅ ኢትዮጵያውያን ሴቶች በሚለው መጽሐፍ ላይ በደን ልማት፣ በባዮ ጋዝና በትጋታቸው ከታዋቂ ኢትዮጵያውያን ሴቶች ጋራ ሥራቸውን አቀርቧል፡፡

ተጻፈ ታኅሣሥ 8 ቀን 2007 ዓ.ም.
በመ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ



Friday, September 21, 2018

'Spiders from Mars' spotted

 

  • Scientists found the features using the Hirise imaging camera aboard Nasa's Mars Reconnaissance Orbiter
  • The arachnid-like troughs are a type of land erosion where networks of cracks form in the Martian soil 
  • They occur at the planet’s South Pole and form when carbon dioxide turns to ice during the Martian winter
  • There are thousands of them in Nasa's image according to a citizen scientist group that helped uncover them  
  • David Bowie was right ! ' Spiders from Mars ' spotted in stunning Nasa photograph of araneiform troughs that eerily resemble the eight-legged bugs on the surface of the red planet.

     
  • Troughs across the surface of the red planet (pictured) eerily resemble the eight-legged bugs, stunning Nasa satellite images have revealed. Dubbed araneiforms for their arachnid-like appearance, they are a type of land erosion where networks of cracks form on Martian soil, completely different to anything on Earth

It turns out the 'Spiders from Mars' are not only the name of David Bowie's band in the well-known concept album from 1972, but are real-life geological features etched across the surface of the red planet. 
Troughs across the surface of Mars that eerily resemble the eight-legged bugs have been captured in a stunning Nasa satellite photograph.
Dubbed araneiforms for their arachnid-like appearance, they are a type of land erosion where networks of cracks form on Martian soil, completely different to anything seen on Earth. 
Scientists from the University of Arizona located the strange features using the Hirise (High Resolution Imaging Experiment) camera aboard Nasa's Mars Reconnaissance Orbiter (MRO).
Volunteers working on behalf of Planet Four – an online project hosted by Zooniverse, the world’s largest and most popular people-powered research platform – helped to make the discovery. 
Planet Four trawls through images of the southern polar region of Mars in an effort to uncover formations called fans and blotches.
These could point to signs of water on the surface of the red planet, one of the main goals of the MRO.
Their efforts assist the team behind the orbiter in directing their search to specific locations, where they can then capture more detailed images. 
'As part of the Planet Four citizen science effort, volunteers searched Context Camera images for possible new locations on Mars with “spiders,” or features with radial troughs from which fans emanate in the springtime,' a spokesman for the group said.
'We planned this HiRISE image over one such location, to verify that they are spiders. There are thousands of them in this image.'



source www.dailymail.co.uk/

Wednesday, August 29, 2018

የማሪዋና መናኸሪያ የሆነው ፍርስራሽ መንደር

አዲስ አበባ ከአራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ወይም ከፓርላማ ቁልቁል ወደ ፒያሳ ሲያመሩ እሪ በከንቱ የተሰኘውን ሰፈር ያገኙታል። ከዚያ ከአስፓልት በላይ እና በታች ያሉት መንደሮች፣ ለግንባታ በሚል ሰበብ ከፈረሱ ዓመታት ተቆጥረዋል። አጥራቸው የተከበበው አረንጓዴ እና ቢጫ ቀለማት ባሏቸው ቆርቆሮዎች ነው። ወደ አካባቢው የወሰደኝ ጉዳይ አንድ የመንደሬ ነዋሪ መኸል አዲስ አበባ ላይ እየተሠራ ስላለው ጉድ ካጫወተኝ በኋላ ነው።
የ17 ዓመቱ ወጣት ሶፎንያስ በላይ ሁል ጊዜ ሳገኘው ዓይኑ እንደቀላ ነው። ማታ ማታ ከቤተሰቦቹ ተደብቆ ሲጋራ የማጨስ ልማዱ ሰንበትበት ብሏል። እንደወትሮው ከሥራ ስመለስ መንገድ ላይ ሆኖ ሲያዛጋ አገኘሁት። የማይመለስ አስር ብር እንዳበድረው ጠየቀኝ። ቅድሚያ ግን ምክንያቱን ጠየኩት ሊያጨስበት እንደሆነ ነገረኝ። በእጁ የቀረው የሲጋራ ቁራጭ ሳየው ደግሞ በወረቀት ቢጤ የተጠቀለለ ነበርና ምን እንደሚያጨስ ጠየቅኩት። እየተቅለሰለሰ «ጋንጃ» አለኝ። የምንተፍረቱን የማሪዋናውን ቁራጭ በእጁ አሳየኝ።
የማሪዋና መናኸሪያ የሆነው ፍርስራሽ መንደር
ከአራት ኪሎ እሪ በከንቱ ፍርስራሽ ሰፈሮች እና ቤላ ከሚባል አካባቢ እንደሚገዛ ጠቁሞኝ ብሩን ከእጄ ላይ መንጭቆ ተፈተለከ። ብሩን ከእኔ ባያገኝም ሌሎች ሰዎችን አስቸግሮ አልያም ሰርቆም ቢሆን መጠቀሙ እንደማይቀር
በመረዳቴ አዘንኩለት። ሶፎኒያስ ከዩኒቨርሲቲ ተባሮ ከመጣ ሁለት ዓመታትን አስቆጥሯል። ቤተሰቦቹ በግል ትምህርት ቤት ቢያስገቡትም ለመማር ፍቃደኛ ባለመሆኑ የጤና ችግር አጋጥሞት ሊሆን ይችላል ብለው በህክምና ተቋማትና በፀበል ቦታዎች አመላልሰው ተስፋ በመቁረጣቸው ትተውታል።
ሁልጊዜም ባየሁት ቁጥር አዝንለታለሁ። የጠየቀኝን ሰጥቼ ከማለፍ ውጪ ችግሩን ቀርቤ ለመረዳት ያደረኩት ጥረት አነስተኛ በመሆኑ ዛሬ የነገረኝ መረጃ አስደንግጦኛል። በጆሮዬ የሰማሁትን በዓይኔ ለማረጋገጥ ወደቦታው ለማምራት ለእራሴ ቀጠሮ ያዝኩ። አራት ኪሎ ወረድ ብሎ በሚገኘው እሪ በከንቱ እንደደረስኩ የአደንዛዥ ዕፁን ለመግዛት መፈለጌን ለአካባቢ ወጣቶች ነግሬ ሻጮቹን እንዲያገናኙኝ ጠየኳቸው። ምንም ሳይጠራጠሩ ከአንድ ፍርስራሽ ቤት እንድገባ አመላከቱኝ።
ግቢው ውስጥ ስዘልቅ የሰው ቁመት በሚያክል ሙጃ ሳር እና አልፎ አልፎ በበቀሉ የጉሎ ዛፎች ተሸፍኗል። አካባቢው ለልማት ተብሎ ከፈረሰ ዓመታት በመቆጠራቸው መንግሥት የረሳው ይመስላል። ይሁን እንጅ የቀድሞ ነዋሪዎቹ በላስቲክ እና በሸራ በተሸፈኑ ዳሶች ውስጥ ይኖራሉ። የዛሬ ዓመት የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ የነበሩት አቶ አባተ ስጦታው በከተማዋ የታጠሩና ሥራ ያልተሠራባቸውን ቦታዎች እያመላከቱ «ከዛሬ በኋላ ወደ ሥራ እንገባለን» እያሉ ለመገናኛ ብዙኃን እንዳስጎበኙት አስታወስኩ። ግን ከዛሬ በኋላ መቼ ነበር?
መንደሩ ለልማት ተብሎ የፈረሰ ስለመሆኑ የሚያሳብቁ የአፈር ቤት ፍርስራሾች እና አሮጌ የእንጨት በሮች እዚህም እዚያም ይታያሉ። ህፃናት ሳይቀሩ ከላስቲክ ዳሶቻቸው እየወጡ ውር ውር ይላሉ። ቦታው ተዳፋት ሲሆን፤ ለጎርፍ የተጋለጠ ከመሆኑም በላይ ከአጠገቡ ቆሻሻ የሚደፋበት ወንዝ አለ። ከመንደሩ ጀርባ ደግሞ የአራት ኪሎ ባሻ ወልዴ ችሎት የጋራ መኖሪያ ቤቶችና የተለያዩ ህንጻ ግንባታዎች ይካሄዳሉ። አለፍ ብሎም የአካባቢው ፖሊስ ጣቢያም ይገኛል።
ድንገት ከፊት ለፊቴ የሚመጣውን ወጣት ሠላምታ ሰጥቼ በተጠቃሚዎች አጠራር «ጋንጃ ፈልጌ ነበር» አልኩት። ጊዜ ሳያባክን «ባለስንት» የሚል አስደንጭ ጥያቄ አቀረበልኝ። «ባለ ሰላሳ፣ ባለስልሳና ባለ መቶ አለ፤ የትኛው ይሁን» እያለ የዋጋ ተመኖቹን አሳወቀኝ።
ወጣት አሸናፊ አለሙ (ስሙን እንደቀየረው ነግሮኛል) እሪ በከንቱ አካባቢ ማሪዋና ከሚያከፋፍሉ ወጣቶች መካከል ታዋቂው ነው። እርሱ እንደሚለው፤ በአካባቢው ለልማት ትነሳላችሁ ተብለው ቤት ያልተሰጣቸውና የኢኮኖሚ ችግር ያለባቸው በርካታ ሰዎች ይኖራሉ። ያንን የኢኮኖሚ ቀዳዳ ለመሸፈን ደግሞ ማሪዋና መሸጥ እንደ አማራጭ አድርገውታል። በአካባቢው 125 የሚደርሱ የላስቲክ መጠለያዎች ይገኛሉ። በእያንዳንዱ ውስጥ ደግሞ አስርም አስራ አምስትም ሰው ታጭቆ ይኖርባቸዋል። የጎዳና ተዳዳሪዎችም የእራሳቸውን ዳስ ሠርተው እንደሚያድሩበት አብራራልኝ። በመሆኑም የኢኮኖሚ ምንጭ የሌለው ማህበረሰብ በሕግ የተከለከለውን የአደንዛዥ ዕፅ ንግድ ውስጥ ተሰማርቶ መገኘቱ የእራሱን ህይወት ከማዳን ጋር ሊያያዝ ይችላል? እራሴ ለራሴ ያቀረብኩት ጥያቄ ነበር።
በቀን ውስጥ ከ100 በላይ ወጣቶች ዕፁን ለመግዛት እንደሚመጡ የሚናገረው ወጣቱ፤ አብዛኛዎቹ ሴቶች መሆናቸውን ይገልፃል። ዕድሜያቸው ከ14 እስከ52 የሚደርሱ ሰዎችም ዕፁን እንደሚጠቀሙ አጫውቶኛል። የዕፁ ዘር ከሌላ ቦታ በማምጣት ሲዘራ ከሳር ጋር ተቀላቅሎ እንደሚበቅል እና ቅጠሉ ደርቆ ለወጣቶቹ ይሸጥላቸዋል። የማሪዋና አቅርቦቱ ከፈላጊው ጋር ሊጣጣም ባለመቻሉ እጥረት የሚከሰትበት ጊዜ እንዳለም ይጠቁማል። የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እና ከተለያዩ አካባቢዎች የሚመጡ ወጣቶች በወረቀት የተጠቀለለውን ደረቅ ዕፅ እየወሰዱ በሲጋራ መልክ ያጨሱታል። ዕፁ ሲጨስ የሚከረፋ ጠረን ቢኖረውም በፊልም እንዳዩት ለመሆን ብለው አደንዛዥ ዕፁን የሚወስዱ በርካታ መሆናቸውን ይገልፃል።
የአካባቢው ነዋሪ የሆነው አቶ ሰለሞን አበበ በበኩሉ፤ በየቀኑ ታዳጊና ወጣት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንደሚመጡ ታዝቧል። የዕፁን ንግድ ለማስቆምና የወጣቶችን ህይወት መታደግ ካስፈለገ ጠንከር ያለ እርምጃ በመውሰድ ከምንጩ ማድረቅ እንደሚያስፈልግ ይናገራል። በመላ አገሪቷ የሚከፋፈለው የማሪዋና ዘር ከኦሮሚያ ክልል ሻሸመኔ ከተማ የሚመጣ ነው። ሻሸመኔ ውስጥ ጃማይካዎች ማሪዋና ማብቀልና መጠቀም እንደ ባህል የተለመደ በመሆኑ በአካባቢው በብዛት ዘሩ ይመረታል። የተመረተው ዘርም በሕገ ወጥ መንገድ እየተጓጓዘና የፍተሻ ኬላዎችን እያለፈ ወደ ተለያዩ ከተሞች ይዛመታል። መንግሥት በዚህ ንግድ ውስጥ የተሰማሩ ሰዎችን ተከታትሎ መፍትሔ መስጠት ካልተቻለ እያንዳንዱ ቦታ ያለውን የዕፅ ተጠቃሚ እያሳደዱ መያዝ ዘለቄታዊ መፍትሄ አያመጣም ይላል።
የስነ አዕምሮ ህክምና ባለሙያው ዶክተር ታደሰ በዳሳ እንደሚናገሩት፤ በጥናት እንደተረጋገጠው ወደ ሱስ ከሚገቡ የሁለተኛ ደረጃ እና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች መካከል አንድ ሦስተኛው በሱስ ውስጥ የሚቆዩ ናቸው። ሌሎቹ ግን ጥቂት ከሞከሩት በኋላ ጉዳቱን ተረድተው ይተውታል። ሱሱ ውስጥ የሚቀሩት መቋቋም እስኪያቅታቸው ድረስ የጤና ችግር ቀስ በቀስ ስለሚያጋጥማቸው በባለሙያ የተደገፈ የአዕምሮ ህክምና ያስፈልጋቸዋል።
የማሪዋና ተጠቃሚዎች ላይ በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት ዓይናቸው የመቅላት ምልክት እና ልብሳቸው ላይ መጥፎ ጠረን የሚፈጠር ሲሆን፤ ይህን ምልክት እና ተያያዥ የባህሪ ለውጥ የሚያስተውሉ ወላጆች ችግሩን ቀድመው ለመከላከል መንቃት ይኖርባቸዋል ይላሉ። ወጣቶቹ ወደ ችግሩ ሙሉ በሙሉ እንዳይገቡ ወላጆች የመከላከል ኃላፊነት እንዳለባቸውም ያሳስባሉ።
እንደ ዶክተር ታደሰ ማብራሪያ፤ በወጣቶቹ ላይ የሚደርሰው ችግር ወደ ማህበራዊ ቀውስ እንዳያመራ ከወላጆች ባለፈ መንግሥት፣ ፖሊስና የተለያዩ የሕግ አካላት፣ መገናኛ ብዙኃን እንዲሁም የሃይማኖት ተቋማት የማይቋረጥ የመከላከል ሥራ መሥራት አለባቸው። በተለይ የማህበራዊ ሚዲያ አክቲቪስቶች የችግሩን ግዝፈት ተመልክተው ሃሳብ ሊያፈልቁ እና ወጣቱን ሊያስተምሩት ይገባል ይላሉ።
ከዓመታት በፊት «የአገሪቱ ታላቁ አደባባይ የማሪዋና ቅጠል መብቀያ ሆኗል» በሚል ርዕስ የመስቀል አደባባይ ላይ በርካታ ወጣቶች ዕፁን እያበቀሉ ይሸጡና ይጠቀሙ እንደነበር መዘገቡ ይታወሳል።

Saturday, August 4, 2018

ባዮቴክኖሎጂ እና ኢትዮጵያ



ዮቴክኖሎጂ እና ኢትዮጵያ

ትነት ተስፋማርያም
በኢትዮጵያ ያለው የባዮቴክኖሎጂ አጠቃቀም ዕድሜ አጭር ጊዜ ያስቆጠረ ነው። በተለይ በአፋር ክልል ባለው የግብርና ምርምር አማካኝነት የጥጥ ባዮቴክኖሎጂ ምርት ሙከራ በጥሩ ሁኔታ እይተካሄደ እደሚገኝ የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር በተለያዩ ጊዜያት ገልጾታል።

 
በተለያዩ ቴክኖሎጂዎች ላይ እንደታየው ባዮቴክኖሎጂ ብዙ ባህላዊ, ኢኮኖሚያዊ፣ አካባቢያዊ፣ ስነምግባር፣ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ ስጋቶችን እያጋጠሙት ይገኛል። ከባዮቴክኖሎጂ ጋር የተያያዙ ክርክሮችን ከሌሎች ቴክኖሎጂዎች ጋር ሲነፃፀር እጅግ በጣም ከፍተኛ ሆነው እናገኛቸዋለን። በተለይ አንዳንድ ሰዎቸ በባዮቴክኖሎጂ አማካኝነት የተመረቱ ምግቦችን የሚጠቀም ትውልድ ጆሮው ትላልቅ አስተሳሰቡ ዘገምተኛ ይሆናል የሚሉ እና የተለየያዩ ማስፈራሪያዎች የሚሰነዝሩበት ወቅት አለ። ባዮቴክኖሎጂ ተጠቅሞ የተመረተ የግብርና ምርት ዘርን በማኮላሸት ለመሃንነት ያጋልጣል፣ የባዮቴክኖሎጂ አሰራር የተከተለ ምግቦችን የተመገበ ትውልድ ለተለያዩ የጤና እክሎች ስለሚዳረግ ለአውሮፓውያኑ የህክምና ወጪ መዳረጉ አይቀርም የሚል መላ ምት የሚስነዝሩ አካላት አሉ። ይሁን እንጂ ሁሉም ባዮቴክኖሎጂዎች በአጠቃላይ ጎጂ ናቸው ተብሎ መገመት የለበትም. ለአብነት በአውሮፓ ውስጥ የሕክምና እና የፋርማሲው ባዮቴክኖሎጂዎች ውጤቶች ተቀባይነታቸው ከፍተኛ ቢሆንም የምግብ እና የእርሻ ባዮቴክኖሎጂዎች በጣም ጥብቅ ቁጥጥር ይደረግባቸዋል።
የግብርና ምርትና ምርታማነት ከባዮቴክኖሎጂ ውጪ በሆኑ መደበኛ ዘዴዎች መጠቀም የተለመደ ቢሆንም ባዮቴክኖሎጂም ተጠቅመው ከፍተኛ ምርት የሚያመርቱ ሰዎች ላይ የሚደርሰው ስነልቦናዊ ጫና ለቴክኖሎጂው እድገት እንቅፋት እንዳይሆን ያሰጋል። ምክንያቱም በባዮቴክኖሎጂ ተጠቅሞ የተመረተ ቲማቲም ላይ የሚደረገው ቁጥጥር ከፍተኛ ከሆነ እና ገበያተኛውም ምርቶቹ በጤናችን ላይ ችግር ያመጣል ብሎ ካሰበ አምራቹ በመደበኛው የእርሻ ቴክኖሎጂ ተጠቅሞ ወደማምረት ሊመለስ እንደሚችል የእንግሊዙ ኤቲ የተሰኘ የምርምር ጥናት ቡድን መረጃ አውጥቷ። 
  ዘመናዊ የግብርና ባዮቴክኖሎጂ ዘዴዎች እምብዛም ዋጋ አለማግኘታቸው አሳሳቢ ቢሆንም ቅሉ በሌላ በኩል የሕክምና እና የፋርማሲ እንዲሁም የፋብሪካ ግብአት የሚመረትባቸው ባዮቴክኖሎጂዎች ካላቸው በአነስተኛ ቦታ ሰፊ ምርት የማስገኘት ጥቅም ጋር ተያይዞ ተመራጭነታቸው እያደገ ይገኛል። ህንድ እና ቻይና ብቻ ካላቸው የጥጥ ማምረቻ ቦታዎች በባዮቴክኖሎጂ በመታገዝ እጥፍ ማምረት እንደቻሉ እና ከፋብሪካ ግብዓቶቻቸው አልፈው ወደውጭ ንግድ መላክ መቻላቸው ተጠቃሽ ይሆናል።
ወደ ኢትዮጵያ ስንመለስ ቅድሚያ ትኩረት የሚደረገውው የምግብ ዋስትና እና ራስን መቻል ላይ ነው። የግብርና ባዮቴክኖሎጂ ሳይንስ ደግሞ በአነስተኛ ቦታ ሰፊ ምርት ለማምረት የሚያስችል እድል የሚሰጥ አሰራር አለው። ምንም እንኳን የባዮቴክኖሎጂ ዘር ማለትም በላብራቶሪ የበለጸገ እና ከመደበኛው ዘር የተሻለ ምርት የሚሰጥ ለማድረግ በሚሊዮኖች አንዳንዴም በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ያስፈልጋል። ከዚህ በፊት ግን ህብረተሰቡ ስለባዮቴክኖሎጂ ያለውን አመለካከት ማቃናት እንደሚያስፈልግ ይታመናል።
ለዚህ ስራ ደግሞ የባዮቴክኖሎጂ ትምህርት ማስፋፋት አስፈላጊ ነው። በተለይ በከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ስለባዮቴክኖሎጂ ጥቅም እና አስፈላጊነት የሚያስረዱ በምስል እና በጽሁፍ የታገዙ ትምህርቶች ለወጣቶች ማዳረስ ይገባል። ትምህርቱም ወደባለሙያዎች እና ወጣቶቹ እየሰረጸ ሲሄድ የቴክኖሎጂው አስፈላጊነት በእራሱ ጊዜ ከህዝብ ጥያቄ አማካኝነት ሊመጣ የሚችልበት እድል ይኖራል። በሌላ በኩል አምራቹን ወይም አርሶአደሩን ባሳተፈ መልኩ ስለባዮቴክኖሎጂ ምርቶች ጥቅም የሚያስረዳ አንድ ኮሜቴ በመንግስት ደረጃ በማዋቀር ግንዛቤውን ማሳደግ ያስፈልጋል። አልፎ ተርፎም ከባዮቴክኖሎጂው ዘርፍ ጥሩ ተጠቃሚነት ያላቸውን አገራት ተሞክሮ ለአምራቹ በተለይም ለግብርና ኢንቨስተሮች በማሳየት በሰፋፊ እርሻዎች ላይ ተግባራዊ እንዲሆን መጣር ያስፈልጋል። ይህ ሲሆን በአንድ ሄክታር ላይ ይገኝ የነበረውን ምርት በእጥፍ እና ከዚያም በላይ በማሳደግ የኢትዮጵያን የምግብ ፍላጎት ማሟላት የሚያስችል ስራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማከናወን ይቻላል። በዚህ ስራ ውስጥ ደግሞ ባለሥልጣኖች፣ የቴክኖሎጂ ተቋማት፣ የግብርና አካላት እና ሌሎችም ማህበራዊ ሃላፊነት ያለባቸው ተቋማት ሊሳተፉበት የሚገባ ጉዳይ ነው።
ይህን አሰራር መተግበር ከተቻለ እና ዘርፉን በመንግስት እና በግል ኢንቨስተሮች መደገፍ ከተቻለ የባዮቴክኖሎጂ ምርቶችን ለኢትዮጵያውያን ብሎም ለምስራቅ አፍሪካ አገራት ማቅረብ የማይቻልበት ምንም ምክንያት አይኖርም።

Featured post

ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጠያቂነትን በማረጋገጥ፣ የሕግ በላይነትን በማስፈን፣ መንግሥትና የስራ አስፈጻሚ አካላቱ በመሉ ለሰብአዊ መብቶች መከበር፣ መጠበቅና መሟላት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያሳዩ ልዩ ትኩረትና ክትትል ይሻል

                    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየደረጃው ያሉ የመንግስት አስፈጻሚ አካላትና ኃላፊዎች ላይ የቅርብ ክትትል በማድረግ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር አስተዋጽኦ ሊያደር...