አማራጭ
አማራጭ
አማራጭ...
በል እንጂ አማራጭ የማይፈልግማ ማን አለ? የምን አማራጭ ነው?
አማራጩማ
ከጫጫታ ርቀህ፣ ከወከባና ከጥድፊያ ኑሮ ወጥተህ፤ በመኪናና ከሞተሮች ጩኸ ት ወዲያ ሆነህ፤ በከብቶች ድምጽ
በለመለመው መስክ ላይ እየተዝናናህ፤ ከጓሮህ እያረስክ ከኬሚካል ነፃ በሆነ ፍራፍሬና ምግብ እየተመገብክ፣ ማራኪ
መልካምድራዊ አቀማመጥ እና ተፈጥሮአዊ ውበቶችን እያደነቅህ ትኖራለህ ወይስ
በመኪና
ጢስ፣ በሰዎች ሁካታና ግርግር በተሞላ መንገድ ላይ እየተጓዝክ፣ ከእንቅልፍህ ስትነሳ የመኪናው ጩኸት፤ ስትተኛ
የሰካራሙን እብደት፣ ስትመገብ የታሸገ የፋብሪካና የኬሚካል ውሁድ ያለበት፤ ስትጠጣ ከፊት ለፊትህ ለካንሰር ያጋልጣል
የሚል ማስታወቂያ በቴሌቪዥንህ ወይም በራዲዮና እየሰማህ መኖር ይሻልሃል?
ምን ያለው ቀልደኛ ነህ እባክህ? መች ጠላሁትና አንተ ምትለኝን የገጠሩን ኑሮ አይደለም? ከተማው
ስቦኝ ነው ከትሜ የቀረሁት። ብፈልግስ እንኳ ስራዬን ጥዬ አልሄድ ወደ ገጠር። ልጆቼም ለምደዋል ከቴክኖሎጂው ጋር
ውለው ማደሩን፤ ለእነሱ ገጠር ማለት እስር ቤት ሆኗል ዘመዴ። እስቲ ማን ይሙት የትኛዋ ልጄ ነች በየቀኑ ከብቶችን
ተንከባክበሽ፤ ወተት እያለብሽ፤ በገጠር እየሰራን እንደግ ብትባል የምትሰማ ትልቋናት? ወይስ ትንሿ? አዬ! እማይሆነውን? ይልቁንስ ባለፈው... ገጠር ዘመዶቼን ልጠይቅ ወደ ይርጋአለም ሄጄ ነበር። እናልህ ቆይታዬ ጥቂት ቀንም ብትሆን አየሩን መለካምድሩን ተፈጥሮውን ባጠቃላይ አድንቄ ነው የመጣሁት። ሁሌም አዲስ ነው የሚሆንብኝ። እነርሱጋ የ50 ዓመቱ የእድሜ ባለጸጋ ውሎው በነፋሻማው መስክ በመሆኑ የ30 ዓመት
ወጣት መስሎ ታየዋለህ። ድሮ ድሮ እኮ ስለገጠሩ አየሩ፤ መለካምድሩ ነበረ ጨዋታው፤ አሁን አሁን ደግሞ በገጠሩ ሁሉ
ሞልቶ እየተባለም አይደል። በገጠር ሀብት እያፈራ ልጁን ዩኒቨርሲቲ ልኮ የሚያስተምረው፤ ትራክተሩን ገዝቶ
የሚያርሰው አርሶ አደር ቤት ይቁጠረው። የተጎዳንማ እኛ ነን እንጂ ከተሜዎች ወይ ከገነዘብ ወይ ከጤናም አልሆንን።
እናስ ምን ሆነህ ነው አንተ ከተማ ለከተማ የምትሯሯጠው? በል ጃል አማራጭህን አይተህ መሄድ ነው እንጂ። አዬ! የኛ ነገር «ከሞኝ ደጅ ሞፈር ይቆረጣል ነው ነገሩ»።
የገጠሩ ወጣት ያን የመሰለ እንቁ መሬት ትቶ በስደት በአረብ አገሮች ህይወቱን ያጣል። ነገር ግን የገጠሩ ወጣት
ትቶት ሄደውን መሬት አጅሬ ፈረንጅ፤ ኢንቨስተር ሆኖ ሰርቶ ያሰራበታል። እናስ ገጠሩስ ያንተው አይደል? ሄደህ ለነፍስም ለስጋም የሚሆን ነገር እማታገኝበት ምነው!?።
እንግዲህ
ገጠር መሄዱን ብፈልግም አልችልም፤ የሚይዙኝ ብዙ ነገሮች አሉ እያልከኝ አይደል። ታዲታ አማራጭ የሌለው ምርጫ
ከተማውን ገጠር ቀመስ ማድረግ ነው። እንዴት ሳትለኝ እኔው ልንገርህ። ምን ይባላል መሰለህ «አንድ የምትፈልገው ነገር ወደ አንተ የማይመጣ ከሆነ አንተ ራስህ ወደ እርሱ ሂድ» ይባላል። የወደድከውን ከተማ የምትኖርበትን ቀዬ በአትክልቶችና የልምላሜ ምልክት በሆኑ ተከሎች በማስዋብ ንጹህ አየር መማግ አንደኛው የመልካም ገጠራማ አካባቢ ንጹህ አየርን ለመሳብ የሚያስችል አይነተኛ ዘዴ«ሞደ ፌክ» ነው። ስለዚህ ከኬሚካልና ከአላስፈላጊ ንጥረ ነገሮች የጸዱ የጓሮ አትክልቶችን በቤትም ሆነ በጓሮ አካባቢ መትከልና መጠቀም ያስፈልጋል። ይህ ጤንነትን ብቻ ሳይሆን መንፈስንም የሚያድስ ስራ ይሆናል።
እንኳን
ለአትክልትና ቆሞ ለመቆዘሚያም የሚሆን ጓሮም የለኝ፤ እንዲያው የጋራ መኖሪያ ቤት ላይ ነዋሪ ነኝ የምትል ከሆነ
ደግሞ። ጓሮም የጋራ አለው እልሃለው። ብትችል ብትችል በረንዳህ ላይ በጥሩ ሁኔታ በተዘጋጁ እቃዎች አትክልቶችን
መትከል ከዚያም ውጤቱን በትንሹም ቢሆን ማየት ትችል የለ።
በሁለተኛ
ደረጃ ላይ እንደ ስሙ ቆሻሻ የሆነውን የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት ፈር ማስያዝ ነው። በየአካባቢው ያለው አፍንጫ
የሚሰነፍጥ መጥፎ ጠረን በአብዛኛው ከየቤቱ በሚወጣ ተረፈ ምግብም በለው ሌላ በየቦታው ይዝረከረክና ለሳይነስ ብሎም
ለጉንፋን በሽታ የሚያጋልጠው እሱ ነው። በተለይ ከበዓል ሰሞን በኋላ በኛ ከተሜዎች መንደር አለማለፍ ነው የሚሻለው።
እኔማ በሰማይ በርሬ ቤቴ ብገባ እመርጥ ነበር? ዳሩ «አልበር እንዳሞራ» ሆነብኝ እንጂ። ታዲታ ልክ እንደ ቀን ተቀን የምግብ አወሳሰዳችን ጥንቃቄ ያለው የቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት በየሰፈሩ ማስፈን ሳያስፈልግ አይቀርም።
ከቅርብ
ዓመታት ወዲህ ቆሻሻ የሚያነሱ ወጣቶች ስራ ፈጣሪ ሆነው ቢንቀሳቀሱም መቼም የውሃ መውረጃ ትቦውን ነገር አንተም
ታውቀዋለህ ውስጡን ለቄስ ነው። መቼም እነዛ የረጋ ቆሻሻ ውሃ የያዙ የመንደር ውሃ መፍሰሻ ቦዮች ላይ አዳልጦት
የገባ ሰው «ተንቀሳቃሽ ከሰል» መሰሎ መውጣቱ አይቀሬ ነው። ምክንያቱም ውሃው ወደ ጥቁርነት ተቀይሮ የለ!? እፍ... ያንገሸግሻል ሽታውማ። እንዲያ ነው ነገሩ፤ ገጠር ዝም ብሎም አይገኝም። እንደገጠሩ ከተማውም መስተካከል አለበት ተፈጥሮን በልኳ ለማግኘት።
ሌላው
እንግዲህ የገጠሩን ሰላማዊ መንደር በእውንህ ለማግኘት ብሎም በአካባቢ ያሉ ጫጫታዎችንና ሁካታዎችን ላለመስማትና
ከእነርሱም ለመራቅ የግድ ጥብቅ ደን ውስጥ መግባት አይጠበቅብህም እንዲያው ህጉን ጠበቅ ስርአቱን ጠንከር እንዲል
በማድረግ በየመንገዱ ይሄ ካሴት ወጥቷል እያሉ ከሚለፍፉት ባለመኪኖች ጭምር አደብ እንዲይዙ መጣር ነው። እናም ነገሩ
እስከ ቤት ድረስ ይዘልቃል ። ታዲያ በውጭ የሚያልፍ ብቻም አይደል ጸጥታ ማስከበሩ። እናስ ከዚያ በኋላ ከስራ
ሲመለሱም ሆነ ወደ ሥራ ሲሄዱ ለአይን ማራኪ አካባቢ ማየት መቻል ከተሜን ከነ ሙሉ ትጥቁ ገጠር ቀመስ አደረገው
ማለት አይደል። ይሄ ነው እንግዲህ አማራጭ የሌለው ምርጫ ከተሜ።

