Friday, May 5, 2017

ከድጡ ወደ ማጡ የሆነው የትምህርት ጥራት

ከድጡ ወደ ማጡ የሆነው የትምህርት ጥራት 

በኢትዮጵያ በግሉም ሆነ በመንግስት የትምህርት ተቋማት የተማረ የሰው ኃይል ለማፍራት ጥረት እየተደረገ ይገኛል። ይሁንና የትምህርት ጥራ ጉዳይ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ባለሙያዎች ይገለፃሉ። ሰሞኑንም በጅግጅጋ ዩኒቨርሲቲ አማካኝነት በተካሄደው ሰባተኛው ዓለም አቀፍ የትምህርት ጥራት ጉባኤ ላባለሙያዎች በጉዳዩ ዙሪያ የተለያዩ ሃሳብ አቅርበዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ጥራትና አግባብነት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ተስፋዬ ሙህዬ፣ የትምህርት ጥራት በሚጠበቀው ደረጃ አለመሆኑን የሚያሳዩ መረጃዎች እየተገኙ መሆኑን ይጠቁማሉ። ለዚህም ማሳያው በ2008.ም ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ከሶስት ነጥብ ሁለት በላይ አምጥተው የተመረቁ ተማሪዎች ላይ ፈተና መሰጠቱን ይጠቁማሉ። ለፈተና ከተቀመጡ ስድስት ሺ ተመራቂዎች መካከል 50 ነጥብ እና ከዚያ በላይ ማምጣት የቻሉት ግን 24 በመቶ ብቻ ናቸው። የተሻለ ነጥብ ያላቸው ተመራቂዎች አነስተኛ ውጤት ካሳዩ ቀሪዎቹ በዩኒቨርሲቲ ውጤታማነታቸው ደካማ የነበሩት ተማሪዎች በባሰ መልኩ አነስተኛ ውጤት እንደሚኖራቸው መገመት እንደሚቻል ያስረዳሉ።
እነደ ዶከተር ተሰፋዬ ገለጻ፤ የተሰጠው ፈተና በገለልተኛ አካላት የወጣ ቢሆንም አንዳንድ ነባር ዩኒቨርሲቲዎች አነስተኛ ተመራቂዎቻቸው ብቻ ማለፍ ችለዋል። ዪኒቨርሲቲዎቹ ለፈተናው ያቀረቡት ተማሪዎች ቁጥር የተለያየ ቢሆንም ፈተናውን ካለፉ ተመራቂዎች መካከል በመቶኛ ሲሰላ ከተቋቋሙ ጥቂት ጊዜ ያስቆጠሩ አንዳንድ ዩኒቨርሲቲዎች ከነባር ዩኒቨርሲቲዎች በላይ ውጤት ማስመዝገባቸው ታውቋል። ይህም አዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች በአግባቡ ከሰሩ ጥራት ያለው ተማሪ ማፍራት እንደሚችሉ ያሳየ አጋጣሚ ነበር። ይሁንና እንደ አጠቃላይ ፈተናውን ማለፍ የቻሉት ቁጥራቸው አነስተኛ መሆኑ ሲታይ የአገሪቷነ የጥምህርት ጥራት አደጋ ላይ መውደቁን የሚያሳይ ሆኗል። መንግስት ለ2009 .ም ለዩኒቨርሲቲዎች ከ36 ቢሊዮን ብር መድቧል። የተለያዩ መመሪያዎችን በማውጣት እና ተከታታይ ድጋፍ እያደረገ ቢሆንም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የትምህርት ጥራት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን መገንዘብ ይቻላል።
በመሆኑም በቀጣይ ጊዜያት የዩኒቨርሲቲ አመራሮች ቁርጠኝነት ያስፈልጋል የሚሉት ዳይሬክተሩ፤ በተለይም ቀጥተኛ የስራ አጀንዳዎችን በመያዝ ወደትግበራ መግባት እነደሚያስፈልገ ይጠቁማሉ። እነደ እርሳቸው በዋናነትም የመምህራንን የአዕምሮ ዝግጁነት ማዳበር ያስፈልጋል። መምህራኑ በዕውቀት እና በምግባር ከተማሪው ከፍ ብለው በመገኘት አርአያ ሆነው መቅረበ አለባቸው። በዚህም ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚገኙ መምህራን ለተማሪዎቻቸው የሞራል ውድቀት የሚያስተላልፉ እንዳይሆኑ ጥረት ማድረግ ይገባል። የስራ ፍቅር ያለው መምህር በሌለበት ተቋም የሚማሩ ወጣቶች የትምህርት ፍቅር ሊያድርባቸው አይችልም። በመሆኑም በመጀመሪያ መምህሪ ለስራው ፍላጎት እና ፍቅር እንዲኖረው ማድረግ የእያንዳንዱ ዩኒቨርሲቲ አመራር ቀጣይ ስራ ይሆናል። በተጨማሪም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የውስጥ ግንኙነት መጠናከር አለበት። በዚህም ከዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ጀምሮ እሰከ ትምህርት ክፍል ድረስ በመግባባት እና በጋራ የመስራት መንፈስ ሊዳብር ይገባል። በሌላ በኩል የሚኘውን ግብዓት እና የአካባቢውን ሃብት በማጣመር ተገቢው የሃብት አጠቃቀም መተግበር ጥራቱ የተጠበቀ ትምህርት ለመስጠት ዋነኛ አሰራር መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል።
ከስዊድኑ አፕሳላ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ፕሮፌሰር ተከስተ ነጋሽ በበኩላቸው፤ በቀድሞ ጊዜ ትምህርት ጥራት ቢኖረውም ተገቢነት ያለው ትምህርት እንዳልነበረ ያስታውሳሉ። በ1960ዎቹ ላይ በአገሪቷ የተመረቁ የኮሌጅ ተማሪዎች ስድስት ሺ ብቻ ነበሩ። በአሁኑ ወቅት ተገቢው እና ከአገሪቷ ሁኔታ ጋር የሚያያዝ ትምህርት እየተሰጠ ሲሆን በሚሊዮኖች ተመራቂ ተማሪዎች እንደሚገኙ ይገልፃሉ። ነገር ግን ትምህርት በኢትዮጵያ በብዛት ላይ እንጂ በጥራት ላይ ያልተመሰረተ ሆኗል ባይ ናቸው። በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚሰጠው ትምህርት በእንግሊዘኛ ቢሆንም በአብዛኛው የመግባቢያ ቋንቋው አማርኛ መሆኑን ማጥናታቸውን ያስረዳሉ።
«አማርኛ በትምህርት ተቋማት በጓዳ በር ገብቶ አገልግሎት እንዲሰጥ ከማድረግም በትክክለኛው መንገድ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማስተማሪያ ቋንቋ ተደርጎ ቢወሰድ ለትምህርት ጥራት መሻሻል አስተዋጽኦው ከፍተኛ ይሆናል»ይላሉ። 
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርትና ጥናት ምርምር ተቋም የትምህርት ዘርፍ አጥኚ የሆኑት ዶክተር ዋና ሌቃ በበኩላቸው እንደሚገልፁት፤ የትምህርት ጥራት መጓደል የተከሰተው የተማሪው ቁጥር እየጨመረ በመምጣቱ ነው። ለሶስት ሰው የተዘጋጀ ምግብ ለሃያ ሰው ቢቀርብ ጥራቱ የተጓደለ እንደሚሆን ሁሉ የትምህርት ዘርፉ ላይ ተማሪው ቁጥሩ ሲያድግ የማስተማሪያ ግብአቶች በዛው ልክ ማደግ ይኖርባቸዋል። በተመሳሳይ የአስተማሪዎች እና የመማሪያ ክፍሎች በመጣጣኝ ሁኔታ መቅረብ ይኖርበታል። ተጨማሪ ትምህርት ቤቶችን በየጊዜው በመስራት እና ብቁ መምህራንን በብዛት በማፍራት ጥራቱን ማስተካከል ይቻላል። በሌላ በኩል የተማሪውን ፍላጎት እና አስተዳደግ ከግምት ውስጥ ባስገገባ መልኩ ትምህርቱን በማስቀጠል የተማሪውን የመቀበል ችሎታ ማሳደግ ይቻላል። በዚህም ጥራቱን የተሻሻለ ትምህርት ለማቅረብ ይቻላል።

ጠንካራ ሰራተኛ ማህበራት አሉን?


ጠንካራ ሰራተኛ ማህበራት አሉን?


በርካታ ተቋማት የሰራተኛ ማህበር የላቸውም። ያላቸውም ቢሆኑ ስለሚያከናውኑት ስራ አንዳንድ ሰራተኞች ጥያቄ ያነሳሉ።
በርካታ የግል ተቋማት ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች ስለሚደርስባቸው ጫና እና የስራ ችግር የሚከላከልላቸው ማህበር የላቸውም። በተለይም በአንዳንድ ጨርቃጨርቅ ፋብሪካ ላይ የሚሰሩ ሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጾታዊ ጥቃት ለመከላከል ለማን አቤት እንደሚባል እንኳን አያውቁም። መብታቸውን እስከምን ደረጃ እንደሚያስጠብቁ መረጃ የላቸውም። በቦታው ያለው የሰራተኛ ማህበርም ለሰራተኞች ተደራድሮ ጥቅም የማስከበር ጉዳይ ላይ ደካማ ነው።
በአገሪቷ ውስጥ የሚገኙ የሰራተኛ ማህበርም ሆነ የማህበራቱ ኮንፌዴሬሽን ጠንካራ ናቸው ለማለት አያስደፍርም። ለዚህም ማሳያው ለሰራተኛው ችግር ከመቅረፍ አኳያ አርአያ ሆነው መቅረብ የቻሉ የሰራተኛ ማህበራት ማየት አለመቻሉ ነው።
ስንቱ ነው የሰራተኞች ቀንን /ሚያዚያ 23/ ዝግ የስራ ቀን ስለሆነ ብቻ የሚወደው። አብዛኛው ሰው እረፍት ስለሚኖር እንጂ ስለቀኑ ደንታ የሚሰጠው የለም።
ጠንካራ ሰራተኛ ማህበራት ባለመኖራቸው በተለያዩ ተቋማት ሰራተኛው መብት ላይ ለሚፈጸሙ በደሎች የሚከራከር እና ለውጥ የሚያመጣ አካል አይኖርም። በመሆኑም መብት ለማስከበር ከበላይ ሃላፊዎች ጋር የሚኖረውን ውጥረት በመፍራት እና ጥያቄ ካነሳሁ ያለአግባብ ከስራ ልባረር እችላለሁ ብሎ የሚሰጋ ተቀጣሪ በዝቷል። አንድ ሰራተኛ በግሉ ከአመራሮች ጋር የመብት ጥያቄ አንስቶ ቢከራከረ አመታት ሊወስድበት ይችላል። የቤተሰብ አስተዳዳሪ የሆነ ሰራተኛ ደግሞ ሶስት እና አራት አመታት ከስራ ውጭ ሆኖ የመከራከር ኢኮኖሚያዊ አቅም ስለማይኖረው መብቱን አጥቶ እንዲሰራ ይገደዳል። እንደዚህ አይነት ችግር ላለመግባት ደግሞ አብዛኛው ሰራተኞች ከማኔጅመንት አካላት ጋር እውነተኛ ያልሆነ ግንኙነት በመፍጠር እና እያጎበደዱ መሰራትን ምርጫቸው ያደርጋሉ። ይህም መንፈሱ የተሰበረ ትውልድ እንዲፈጠር እያደረገ ይገኛል።
አንዳንምድ አሰሪዎችም ጠንካራ ተከራካሪ እና ስለመብት ጠያቂ አካል ያለመኖሩን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሰራተኛው ላይ እንደፈለጉ ሲፈነጩ ይታያል። በተለይም የእራሳቸው እስር ቤት ያላቸው እና ሰራተኛን በእርግጫ እና በኩርኩመ የሚያቀዱ እንዳሉ መታዘብ ይቻላል።ይህ ጉዳይ በተለይ በውጭ አገራት ባለሃብቶች በሚተዳደሩ የጨርቃጨርቅ እና ማኑፋክቸሪንግ ፋብሪካዎች ላይ በብዛት የሚታይ ችግር ነው። ይህም በአብዛኛው ጊዜ ሰራተኛውን ተጎጂ ሲያደርገው ይስተዋላል። በመሆኑም በአግባቡ የሰራተኛውን መብት የሚያስከብር ማህበር ስለማቋቋም ሊታሰብ ይገባል። ከአሰሪዎች ጋር ስለደምዎዝዎ፣ የሥራ ሰዓት እና ሌሎች ማናቸውም የሥራ ቅጥር ግዴታዎችና ደንቦችን በተመለከተ በማህበር ተደራጅቶ የመደራደር አሰራር አልተለመደም። ጥያቄ ያለው ሰራተኛ ጉዳዩነ በግሉ ይዞ ያስፈጽማል።
የሰራተኛ ማህበራትን ጥቅም የሚረዳ ሰራተኛ ባለመኖሩ በተቋሙ ውስጥ ማህበሩን አደራጅቶ ለመሳተፍ ፍላጎት የሚያሳይ ሰራተኛ እምብዛም ነው። ሰራተኛ ማህበር ቢቋቋም ግን ጥቅሙ ለሰራተኛው ብቻ ሳይሆን ለአሰሪዎችም ጭምር ነው። ምክንያቱም በተደራጀ ሁኔታ በማህበር የሚነሱ የሰራተኛውን ጥያቄዎች ማስተናገድ እና መፍታት ከተቻለ የባንኩን እድገት ለማፋጠን ይረዳል። በግለሰብ ደረጃ የሚመጡ ጥያቄዎች እና ቅሬታዎች ማስተናገድ ግን ከጊዜም ሆነ ከወጪ አኳያ ተመራጭ አይደለም። በመሆኑም ሰራተኞች ብቻ ሳይሆን አሰሪዎችም የሰራተኛ ማህበር ለማቋቋም ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል።

Featured post

ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጠያቂነትን በማረጋገጥ፣ የሕግ በላይነትን በማስፈን፣ መንግሥትና የስራ አስፈጻሚ አካላቱ በመሉ ለሰብአዊ መብቶች መከበር፣ መጠበቅና መሟላት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያሳዩ ልዩ ትኩረትና ክትትል ይሻል

                    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየደረጃው ያሉ የመንግስት አስፈጻሚ አካላትና ኃላፊዎች ላይ የቅርብ ክትትል በማድረግ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር አስተዋጽኦ ሊያደር...