Thursday, April 28, 2022

ጥብቅ ዕርምጃ የሚሻው - ከሐይማኖት ተቋምት እስከ መንግሥት ጓዳ የዘለቀውን ሙስና

 

ሙስና ለዕድገታቸው ጠንቅ ሆኖባቸዋል ከሚባሉ አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷና ዋነኛዋ አገር ናት። በየወረዳው፣ በፍርድቤቶችና፣ በትላልቅ ባለስልጣናት ጭምር ሙስና መቀበል ልክ ዕንደመብት የሚታይበት ጊዜ ላይ ነን። ደርሰናል።

Corruption Free India — A Far Cry | by Editor @ The Dialogue | The Dialogue  | Medium    

 

 

 

 

 

 

 

 

ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተሰኘው ዓለም አቀፍ ተቋም በሙስና መስፋፋት ረገድ ከዜጎችና ከባለሙያዎች በሚሰበሰብ መረጃና ግምታዊ አሰራር  በየዓመቱ በሚያወጣው ሪፖርት እ.አ.አ. በ2020 ለኢትዮጵያ ከ100 ነጥብ 39 ሰጥቷታል። ይህም  ኢትዮጵያን ሙስና ዕጅግ ተስፋፍቶባቸዋል ከሚባሉ አገራት ተርታ ያሰልፋታል። 

የማኀበራዊና ኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ጥናትና የማማከር አገልግሎት የሚሰጠው ፍሮንቲየርአይ ተቋም የኢትዮጵያ ኃላፊ የሆኑት ዶክተር በላይነህ ተቋማቸው እ.አ.አ. በ2021 ሙስና ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ጉዳት በተመለከተ ጥናት መስራቱን ገልጸው፤ በጥናቱ ውጤት መሰረት ሙስና ኢትዮጵያ ውስጥ የገነገነ አገራዊ ችግር ሆኖ መቀጠሉን ይገልጻሉ።

ሌብነትን መከላከል የሚገባቸው ተቋማት ጭምር የለየለት ዘረፋ ውስጥ መግባታቸውን መግባታቸውን በመጠቆም፤ በተለይም የሐይማኖት ተቋማት፣ የጉምሩክና ቀረጥ ተቀባይ ተቋማት፣ የመሬት አስተዳደር እንዲሁም ከፌዴራል አንስቶ እስከ ወረዳ ደረጃ ያሉ ፍርድ ቤቶች ላይ ሙስና በመስፋፋቱ ዜጎች ምሬት ውስጥ መሆናቸውን ይገልጻሉ።

ሙስና በድብቅ የሚከናወን በመሆኑ የሚጠፋውን ገንዘብ በትክክል ማወቅ ባይቻልም፤ የዓለም ባንክ በኢትዮጵያ በየዓመቱ በሙስና ከተገኘው ገንዘብ 30 ቢሊዮኑ ወደውጪ እንደሚወጣ  ይፋ አድርጓል። ይሁንና ቁጥሩ ከዚህም በላይ ሊወጣ የሚችልበትም ሁኔታ አለ ይላሉ።

ምክንያቱም ሙስና በየትኛውም ስፍራ እየተለመደ የመጣ በመሆኑ እንደአገር ከዚህም በላይ መጠን ያለው ገንዘብ ሊወጣ ይችላልና፤ ሕዝብ እየተበዘበዘ ስለመሆኑ ማወቅ አያዳግትም ሲሉ ሃሳባቸውን አጠናክረዋል።  

በጥቁር ገበያ የዶላር ምንዛሬ ጋር የተዛመዱ፣ ከአስመጪና ላኪነት ጋር በተያያዘ እንዲሁም በየመንግሥት ተቋማት ጉዳይ ለማስፈጸም በሚል የሚፈጸሙ የሙስና ወንጀሎች እንዳሉ መንግሥትም ሕዝብም ያውቃል። ዋናው ጉዳይ ግን ከወሬ በዘለለ ቁርጠኛ ዕርምጃ መውሰድ ነው። አስፈላጊውን የሕግ ቅጣት እየሰጡ አስተማሪ ውሳኔ መስጠት ይጠበቃል። ለዚህም የመንግሥት ቁርጠኝነት ወሳኝ ነው ይላሉ።

በሙስና ሰዎችን ተጠያቁ ማድረግ ሲጀመርና አንዱን ሲነካ በጥቅም የተሳሰሩ ሰዎች ስላሉ ሌላውንም ሰው ሊነካ ይችላል ያሉት ዶክተር በላይነህ፤ ለዚህም አሰራሮችን ግልጽ ማድረግና ሌብነቱም ሲገኝ ሁሉንም ተጠያቂ በማድረግ ዘላቂ መፍትሄን ማምጣት እንደሚገባ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያ ውስጥ በሙስና የሚጠየቁ ሰዎች ከመንግሥት የፖለቲካ አካሄድ አፈንግጠዋል የሚባሉ ሰዎች ናቸው፤ ይሁንና ዘርፈውም ከመንግሥት ጋር የሆኑ ሰዎች በብዛት ተጠያቂ አይደረጉም የሚሉት ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊ መብቶች ጥናት ማዕከል መምህሩ ዶክተር አብዱለጢፍ ከድር ናቸው።

እንደ ዶክተር አብዱለጢፍ ገለጻ፤ ሙስና የሚገባውን ደረጃ ትኩረት ስላልተሰጠው፤ ዘርፈ ብዙ ውጥንቅጦችን በአገር ላይ እያስከተለ ነው። ከዚህ ቀደምም ያለው ሆነ የቀጠለው ፖለቲካዊ ስርዓት በሙስናና ጥቅም ትስስር ላይ የተመሰረተ ነው። አገርን አገለግላለሁ በሚል ዘለቅ ያለ ዓላማ ይዞ ሳይሆን እበላለሁ በሚል መንፈስ ነው ሰዎች ሹመቶችን የሚቀበሉት።

ስለሆነም ይህን ስር የሰደደ አስተሳሰብ እንዲወገድ ጥረት ማድረግ፤ እንዲሁም ችግር ሲገኝ አስተማሪ ዕርምጃ መውሰድ ከሕግ አስፈጻሚዎች አካላት ይጠበቃል። ይህ ሲባል ግን ሕግ አስፈጻሚውም በዕራሱ ሙሰኛ በመሆኑ ዕርምጃው መጀመር ያለበት ዕዚያው አስፈጻሚዎቹ ጋር ነው ብለዋል።

ምክንያቱም ሙስና የኢኮኖሚ ችግር ብቻ ሳይሆን የማኀበረስብም ሆነ የአገር አብሮ የመቀጠል ትልቁ ፈተና ነው። ስለዚህ ሙስናን ወይም ሌብነትን መቀነስ ካስፈለገ ከመንግሥት ጋር የተጠጉትንም ጭምር ተጠያቂ ማድረግ ያስፈልጋል ሲሉ ይሞግታሉ።

ስለዚህም ካንጀት ካለቀሱ ዕንባ አይገድም እንደሚባለው ሁሉም የሽግ አስፈጻሚዎች በሃቀኝነት ከሰሩ ውስብስብ የሆነውን የሙስና ወንጀል እንዲቀንስ ማድረግ ይችላሉ።   መረጃ ላይ መሰረት ያደረገ አሰራርን በመከተልና የፖለቲካ ወገንተኝነትን ባራቀ መንፈስ በመቆጣጠር ዋነኛ ሙሰኞችን ማደን እንደሚያስፈልግ ያስረዳሉ።

ዶክተር አብዱለጢፍ እንዳስታወቁት፤ አስተማሪ የሕግ እርምጃ በመውሰድ ከዚህ ችግር አገር እንድትድን  ማድረግ ያስፈልጋል። በዚህ ሂደት ህብረተሰቡም ሆነ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ሙስናን በማጋለጥ ረገድ ዋነኛ የመረጃ ምንጭ መሆን አለባቸው።

Tuesday, April 26, 2022

“በህዳሴው ግድብ ኢትዮጵያ ያለፈችባቸው ጫናዎች ለቀጣይ ስራዎች ብርታትን የሚያድሉ ናቸው”

 ረ/ፕሮፌሰር አደም ካሚል

የታሪክ ምሁር

 

ክፍል አንድ

 

የታሪክ ምሁሩ እና በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በዓረብኛ እና በተለያዩ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች መረጃዎችን በማሰራጨት የሚታወቁት ረዳት ፕሮፌሰር አደም ካሚል  የግድቡ ግንባታ ሂደት መለስ ብሎ ለሚያስብ ኢትዮጵያ ብዙ ውጣ ማለፏን ይታዘባል ይላሉ።

የየሃገራቱ ጫናው ከብድር እቀባ እስከ ግልፅ የጦርነት ማስፈራሪያ እና ሙከራዎች አልፋ ለመጀመሪያው ዙር ኤሌክትሪክ ማመንጨት የቻለችው ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ጽናቷን አሳይታለች።

ረዳት ፕሮፌሰር አደም እንደሚሉት የአባይ ወንዝና ኢትዮጵያ በልማት ተቆራኝተዋል፤ ይህ ደግሞ የማያስደስታቸው በርካታ ሀገራት ቢኖሩም የግድብ ግንባታ ዳር እስከሚደርስ የሚዘልቅ ጫናቸውን ማሳደራቸው አይቀርም።

ሶስተኛው ዙር ወደ ህዳሴው ግድብ ውሃ የማስገባት ስርዓት ዝግጅት ላይ ነው። ይህም በቀጣይ ዙር ተጨማሪ ኤሌክትሪክ ለማመንጨት የሚያስችል በመሆኑ ለኢትዮጵያውያን ትልቅ ደስታ እንደሚፈጥር አያጠያይቅም።

Ummah Network - ረ/ፕሮፌሰር አደም ካሚል እንኳን ደስ አለዎት! የ #ምርኩዝ ልዩ... | Facebook 

የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራትም የግድቡን ግንባታ እንደመጥፎ እድል የሚመለከቱት ግብጽና ሱዳን ነገር መቆስቆሳቸውን ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ተገማች ነው።

በመሰረቱ የግድቡ ግንባታ ለታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ጉዳት የሚያመጣ አለመሆኑን ቢያውቁትም የህዳሴን ግንባታ ግን ሲነቅፉ ነው የቆዩት። ግድቡን ልክ በዓለም ላይ እንደታየ አዲስ ክስተት ቢያዩትም፤ በምድራችን የመጀመሪያው ሀገር አቋራጭ ወንዝ ላይ የተሰራ ግድብ እንዳልሆነ ግን ይታወቃል ያሉት የታሪክ ምሁሩ ለአብነት የየሀገራቱም ተሞክሮ አንስትዋል።

አሜሪካ ከካናዳ እና ከሜክሲኮ በሚያዋስኗት ቦታዎች ላይ ግዙፍ ግድቦችን ገንብታለች። ቻይናም ቢሆን ከጃፓን እና ከደቡብ ኮሪያ ጋር የሚያዋስኗት ቦታዎች ላይ ግድቦች አሏት። ቱርክም ከኢራቅ ጋር በሚያዋስናት ቦታ ግድብ ገንብታለች።

በሌሎችም ሀገራት በሚገኙ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ላይ የላይኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ትናንሽም ይሁን ትላልቅ ግድቦችን ገንብተው እየተጠቀሙ ነው። ስለዚህ የህዳሴን ግድብ እንደአዲስ ጉዳይ አይቶ መቃወሙ ለግብጽም ሆነ ለሱዳን የማይበጅ ነገር ነው።

የእኛ ግድብ ሲሆን የሀገራት ጫናም ለምን ተበራከተ ተየሚለውን ማየት ቢቻል ጉዳዩ አነጋጋሪ ይሆናል ሲሉ ይጠይቃሉ።

ኢትዮጵያ ግድቡን ለመገንባት ስትነሳ በእቅድ እና በጥናት ላይ ተመስርታ ነው።  ግብጽና ሱዳን ህዳሴ ግድብ ኤሌክትሪክ የማያገኘውን 60 በመቶ ህዝብ የኢትዮጵያ ህዝብ መብራት እንዲያገኝ የተጀመረ ፕሮጀክት መሆኑ ቢገለጽላቸውም ሊዋጥላቸው አልቻለም።

ድህነትን ለመቅረፍ እና የኤሌክትሪክ ኃይል ለህዝቦች ለማዳረስ ታስቦ እንጂ እንሱ እንደሚሉት የውሃ ድርሻቸው ለመቀነስ ተቅዶ አይደለም ግንባታው የሚከናወነው። ይሁንና በቅኝ ገዥዎች የተቀመጠላቸው የውሃ ድርሻ መጠን ለማስጠበቅ ሲሉ ግብጽና ሱዳን አንድ ሆነዋል ይላሉ። 

ከአባይ ወንዝ ላይ አንዲትም ጠብታ ውሃ ሌላ ሀገር እንዲጠቀምበት ካለመፈለጋቸው የተነሳ ሁል ጊዜም በግድቡ ድርድር ላይ ሰበባሰበብ እያበዙ ክስ ማብዛታቸውን ቀጥለዋል። የግብጾች ጩከት መጀመሪያ አካባቢ አልነበረም።

ምክንያቱም ኢትዮጵያውያን ችለው ግድቡን በእራሳቸው ይገነቡታል ብለው አላሰቡም ነበር። ግንባታው 40 በመቶ ላይ ሲደርስ ግን ከየአቅጣጫው እንቅስቃሴ ማድረግ ጀመሩ። 

ለግንባታው ብድር እንዳይገኝ ብቻ ሳይሆን ግንባታውን የሚያከናውነው ሳሊኒ ካምፓኒንም ጭምር ከስራው ለማስወጣት ያልፈነቀሉት ድንጋር አይነበረም።

ጣሊያን ድረስ ሄደው ሲወተውቱ የነበረውን መንግስቱ ፋብሪካውን ከኢትዮጵያ እንዲያስወጣው ነበር። ሁሉ ድካማቸው ግን እንዳልተሳካለቸው ረዳት ፕሮፌሰር አደም ይናገራሉ።

... 2015 ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ፤ የግብጹ አልሲሲ እና የሱዳን የወቅቱ ፕሬዚዳንት አልበሽር ተገናኝተው ከመከሩ በኋላ የተፈራረሙት ስምምነት የግድቡ ግንባታ መከናወን ላይ ብቻ ሳይሆን የውሃ ሙሌቱም እንደሚከናወን ጭምር ነው።

ይህ ሁሉ ስምምነት እና ፍትሃዊ የመልማት ጥያቄ ባለበት ግን የታችኞቹ ተፋሰስ ሀገራት ብግልጽም ሆነ በእጅ አዙር ኢትዮጵያ ላይ የሚያሳድሩትን ተጽእኖ አላቆሙም ሲሉ የታሪክ ምሁሩ ያስረዳሉ። 

እንደ ረዳት ፕሮፌሰር አደም ከሆነ፤ በህዳሴ ግድብ ላይ ግብጾች የሚያሳድሯቸው ተጽእኖዎች አንድም በመገናኛ ብዙሃኖቻቸው በኩል  በሌላ በኩል በቀጥታ በሚደረግ ማስፈራሪያ እና በአሜሪካ እና አውሮፓ ዓለም እንዲሁም በዓረብ ሊግ ጭምር የሚታገዝ እንደሆነ በተለያየ ጊዜ ታይቷል። 

ግብጾች በተለያዩ  ሚዲያዎች በግልጽ አላማችን ኢትዮጵያን ማፈራረስ ነው በሚል አዲስ ካርታ አዘጋጅተው እስከማቅረብ ደርሰዋል። በዓረብኛ በሚተላለፉ ስርጭቶቻቸው በየቀኑ ያለመታከት ስለአባይ ወንዝና ስለኢትዮጵያ ግድብ የተሳሳቱ መረጃዎችን ያሰራጫሉ። ሲፈልጉም ለግብጽ ብቻ የወገነ መረጃ በማስተላለፍ ዓረቡን ዓለም የእነሱ ደጋፊ ለማድረግ ሌት ተቀን ይሰራሉ።

በሌላ በኩል ግብጾች የውሃ መጠናቸው እንዳይነካ በመላው ዓለም በሚገኙ 80 ሺህ በሚሆኑ ምሁራኖቻቸው አማካኝነት ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለማሳደር እየጣሩም ነው።

ከፊሉ ለኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ብድርና ድጎማ እንዳይሰጥ ሲሟገት፤ ሌሎቹ የኢኮኖሚ እና ፖለቲካ ጫና ይባስ ብሎም ማዕቀብ ጭምር እንዲጣል የሚወተውቱ ናቸው። የዓለም ባንክ ጭምር በገንዘብ ጉዳይ ከኢትዮጵያ ጋር እንዳይተባበር ከፍተኛ ጫና የሚያደርጉ ግብጻውያን በርካታ ናቸው ሲሉ የታሪክ ምሁሩ ያስረዳሉ።

በዓረቡ ዓለም ላይ በሚነዙት የሃሰት መረጃዎች ደግሞ የዓረብ ሊግ ሀገራትም ግብጽን መደገፋቸውን ቀጥለዋል። ግብጾች በአባይ ግድብ ላይ ብቻ 1ሺህ 500 በላይ ጥናቶችን አዘጋጅተው በአረብኛ ቋንቋ አሰራጭተዋል።

በጽሁፎቻቸው ላይ ግን የሚወቅሱትና ውሃችንን ልትወስድ ነው የሚሉት ኢትዮጵያን ነው። በአረብኛ በሚያስተላልፉት መልዕክት የዓረቡን ዓለም ለመያዝ ይጠቀሙበታል።

የመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ከአባይ ወንዝ ጋር እራሳቸውን የሚያያይዛቸውን ፕሮጀክቶች በማለም ላይ በመሆናቸው ኢትዮጵያ ላይ ጫና ማድረጋቸውን አያስታጉሉም። ዓረቦቹ ለም መሬት እና ለግብርና የሚውል በቂ ውሃ ስለሌላቸው በግብጽና ሱዳን መሬቶች ላይ እርሻቸው እያከናወኑ የምግብ እጥረት ችግራቸውን ለመቅረፍ ይፈልጋሉ።

ለዚህ ሲባል በቀጣዮቹ ጊዜያት ህዝባቸውን ለመመገብ ከግብጽ እና ከሱዳን መሬት የሚገኘውን ምርት ለማስገባት እቅድ እያወጡ ነው።

ግብጾች ደግሞ እድሉን ተጠቅመው ኢትዮጵያ በህዳሴው ግድብ አማካኝነት የዓረቡ አለምንም በተዘዋዋሪ የሚጎዳና ስራ ታከናውናለች በዚህም ለእርሻ ስራ የሚሆነውን ውሃ የሚያስቀር ግንባታ እያከናወነች ነው በሚል ለቅስቀሳ ይጠቀሙበታል ሲሉ የታሪክ ምሁሩ ሁኔታውን ያስረዳሉ።

Thursday, April 14, 2022

የፖለቲካ ሰው የግል ሃሳብ የለውም፤የግል ሃሳቤ እያሉ ፌስቡክ ላይ የሚለጥፉትም ስህተት ነው

                                - መጋቤ ሃዲስ እሸቱ አለማየሁ

 

 

ፖለቲከኞች የመንግስት አሊያም የፓርቲያቸው ሃሳብ እንጂ የግሌ የሚሉት ሃሳብ ስለሌላቸው ፌስቡክ ላይ የግል ሃሳቤ እያሉ የሚጭኑት ነገር ማቆም አለባቸው ሲሉ መጋቤ ሃዲስ እሸቱ አለማየሁ ተናገሩ።

ፖለቲከኞች ፌስቡክ ላይ የግል ሃሳቤ እያሉ የሚጭኑት ሃሳባቸውን እንዳይኖራቸው እመክራለሁ ያሉት መጋቤ ሃዲስ የፖለቲካ አመራሮች እና የመንግስት ሹመኞች የግል ሃሳቤ ነው እያሉ ፌስቡክ ላይ የሚጽፉት ሃሳብ ህዝብን ለስህተት ይዳርጋል ብለዋል። 

ፖለቲከኞች እና አመራሮች የወከላቸውን ፓርቲና መንግስት ሃሳብ እንጂ የግል ሃሳባቸውን በአደባባይ ማራመድ የለባቸውም። 

HOME 1 – Absolute grid – Page 85 – Ethio Online

 

ለአብነት አንድ የከተማ መስተዳደር የግሌ የሚለው ሃሳብ ሳይሆን የወከለው መንግስትን ሃሳብ ስለሆነ የግል ሃሳቤ ነው እያለ ፌስቡክ ላይ መጻፍ አይኖርበትም ሲሉ ያስረዳሉ።

የግል ሃሳብ አለኝ የሚል የፖለቲካ አመራር ካለ ሃሳቡን ለባለቤቱ ወይም ለልጆቹ ይንገራቸው ያሉት መጋቤ ሃዲስ እሸቱ ፤ በግል ሃሳብ ሰበብ የፖለቲካ አስተሳሰብ መጫን ስሀተት መሆኑን ተናግረዋል። 

የግል ሃሳብ ካላቸውም ስራቸውን ወይም ፖለቲካ አባልነታቸውን ሲለቁ ማስተላለፍ አለባቸው የሚል ሃሳብ ያቀርባሉ። 

ካለበለዚያ ግን ፌስቡክ ላይ እየወጡ የግል ሃሳቤ እያሉ ህዝብን ማደናገራቸው ትርጉም የለውም፤ ለችግርም እየዳረገን ነው ሲሉ ተችተዋል። 

አሁን ላይ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ለሚታየው ልዩነትን የሚያሰፋ እና ግጭትን የሚቀሰቅስ አካሄድ ከአጠቃቀም ችግር የመጣ መሆኑን ሊታወቅ ይገባል ሲሉም መልዕክት አዘል መረጃቸውን አጋርተዋል።
     

Featured post

ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጠያቂነትን በማረጋገጥ፣ የሕግ በላይነትን በማስፈን፣ መንግሥትና የስራ አስፈጻሚ አካላቱ በመሉ ለሰብአዊ መብቶች መከበር፣ መጠበቅና መሟላት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያሳዩ ልዩ ትኩረትና ክትትል ይሻል

                    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየደረጃው ያሉ የመንግስት አስፈጻሚ አካላትና ኃላፊዎች ላይ የቅርብ ክትትል በማድረግ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር አስተዋጽኦ ሊያደር...