Thursday, July 5, 2018

ባጀት መዝጊያ እና የህዝብ ክንፍ

ቀልድና ቁምነገር...
ሰሞኑን የባጀት መዝጊያ ወቅት ነው። አለቃዬ ፋይናንስ ክፍል ውስጥ ሳይወራረዱ የቀሩ ገንዘቦች ካሉ በፍጥነት እንዳሰላ አዞኛል። እርሱ ደግሞ በአንድ ሳምንት ውስጥ ሶስት ስልጠናዎችን እና አንድ ስብሰባ አዘጋጅቷል። የመስሪያ ቤቱን ባጀት ሳይሰራበት ወደ መንግስት ካዝና ከሚገባ በስልጠናና በስብሰባ ምክንያት እምሽክ ላድርገው ብሎ የተነሳ ይመስላል።
ለባጀት መዝጊያ ታስበው ከተዘጋጁ መርሃ ግብሮች መካከል ደግሞ አንደኛው <<የሰራተኞች የፌስቡክ አጠቃቀምና የአዲስ አበባ የህዝብ ክንፍ አባላት ተሳትፎ>> የሚል ነበር። የስልጠና ቦታው ደግሞ አርባምንጭ ነው። ይሄኛው ልክ ባለፈው ጥር ወር ላይ አዳማ በሄድኩ ወቅት ከሰማሁት ታሪክ ጋር ይመሳሰላል። ጓደኛዬ እንደነገረኝ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ስብሰባውን አዳማ ከተማ ላይ አድርጎ <<የክፍለ ከተማው የቆሻሻ አወጋገድ የመንግስት ተሳትፎ>> በሚል የህዝብ ክንፍ የተባሉ ሰዎችን ጠርቶ ሲያወያይ ነበር። በመጀመሪያ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ስብሰባውን አዳማ ከተማ ላይ ማድረጉ ለምን እንዳስፈለገ ሲደንቀኝ ከህዝብ ክንፍ ጋር እየተወያዩ መሆኑ ደግሞ ሌላ ግርምት ጭሮብኛል።
በአዳራሹ አንድም ክንፍ ያለው ሰው ስላልታየ ጓደኛዬ አይኑን የአዳራሹ ጣሪያ ላይ ቢያንጋጥጥ ምንም አላገኘም። ኋላማ ሲሰማ ባለክንፎቹ ወንበር ላይ ኮታቸውን ለብሰው ቁጭ ብለዋል። ህዝብ ግን ክንፍ አለው እንዴ? እረ እኔንጃ የቂርቆስ ህዝብ ክንፍ የለውም እኮ፤ በመሆኑ የህዝብ አይንና ጆሮ ቢባሉ ሰዎቹ የተሻለ ስያሜ ይሆንላቸው ነበር። የሆነ ሆኖ የአዳማው የቂርቆሶቹ ስብሰባ አመሻሹ ላይ ሲጠናቀቅ ቆሻሻ ላይ ሊሰሩ ይገባል በሚል ባለአስር ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቶ መበተኑን እኔም ሰምቻለሁ።
የእኛም ስልጠና አርባ ምንጭ በሚገኝ ም የመሰለ ሆቴል ውስጥ ለአንድ ቀን የሚካሄድ ነው። ለስልጠናው 80 ተሳታፊዎች እንዲገኙ ጥሪ ተደርጓል። ለዚህ ስልጠና ብቻ ለምግብና ለትራንስፖርት ተብሎ ምናለፋችሁ አንድ ሁለት ሚሉዮን ብር ይመደባል። ስልጠናው ደግሞ የህዝብ ክንፍ አባላቱ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ቀደም ብሎ ሌላ ስልጠና ይሰጠን ሲሉ” ነበር። ሰዎቹን “የህዝብ ክንፍ” ያላቸው ሰው ግን የመብረር አላማ ያለው መሆን አለበት። እነርሱን የህዝብ ተወካይ ቢላቸው ኖሮ እንዲህም በየመስሪያ ቤቱ ባጀት መዝጊያ ሲደርስ በተጠሩ ቁጥር እየበረሩ አይሄዱም ነበር። ምን አለፋችሁ አንዳቸውም ይህ ርዕስ ምን ጥቅም አለው? ብለው አልጠየቁም። ምክንያቱም ባጀት መዝጊያ ነእነርሱም በክንፋቸው ይዘው የሚመለሱት ሲሳይ ይደርሳቸዋል። ደግሞም ርዕስ ይገኝ ብቻ እንጂ የትኛውም ቢሆን ተመራጭ ነው በዚህ ወቅት
ርዕሰ ጉዳዩ እንኳን ለሙሉ ቀን ስጠና ሊያበቃ ቀርቶ ሁሉም በሚሰራበት ቦታ ላይ አጠር ያለች መግለጫ ቢሰጠው ሊረዳው የሚችል ነበር። ነገር ግን ጠዋት ሶስት ሰዓት ተኩል የተጀመረው ስጠና ተብዬ ስድስት ሰዓት ላይ ለምሳ ተብሎ ሲበተን ሁሉም ለሶስ ቀን የተዘጋጀውን መመዝገቢያ ላይ ፊርማውን አስፍሮ ወደየማረፊያው እብስ ሲል እኔም አብሬ እብስ አልኩ። በኋላ እደሰማሁት ከሰዓት በኋላ የተወሰኑ ተሰብሳቢዎች የህዝብ ክንፎቹን ጨምሮ በአዳራ ተገናኝተው አስተየያየት ሲሰጡ እና ልምዳቸውን ሲያካፍሉ አልፎ አልፎም የቀረበው ጥናት ልክ አይደለም በዚህ መልክ ቢቀርብ ጥሩ ነበር” እያሉ ሲነታረኩ ዋሉ። የህዝብ ክንፍ ነን ያሉ ሰዎችም “ለህብረተሰቡ በፌስቡክ ጭምር አገልግሎት ሊቀርብለት ይገባል” እያሉ ተሳታፊውን ሲያስቁት አመሹ። አስራአንድ ሰዓት ገደማ ላይ ቢበቃን ይሻላል” በሚል የአለቃ ሃሳብ እና የመዝጊያ ዲስኩር ተደምድሞ ሁሉም ሲቋምጥለት ወደነበረው የአበል ክፍያ አመራ።
ሁሉም ተሳታፊ ለእያንዳንዱ የምሳ ወጪ እና የአበል ክፍያው በገንዘብ ተሰልቶ ተሰራለት። የህዝብ ክንፍ ነን ባዮች ግን “እኛ የወከልነው የከተማውን ህዝብ በመሆኑ ብሎም ደግሞ ባጀት መዝጊያ በመሆኑ ለምን አበላችን ያንሳል” በሚል ጉርምርምታ ውስጥ ገቡ። የዚህን ጊዜ አለቃዬ እንኳንም ዘንቦብሽ… ነውና “ባጀት ሲዘጋ ብር ተርፎ ወደመንግስት ካዝና መመለሱ ስለማይቀር ስትመለሱ አዲስ አበባ እንጨምርላችኋለን” ብሎ አረጋግቶ ሸኛቸው።
የእኛ መስሪያ ቤት የባጀት መዝጊያ ሁለተኛ ስልጠና ደግሞ ጉዳዩ ስለችግኝ ተከላ እና በዙሪያው ያሉ የአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው። ነገር ግን ለስልጠናው የተመረጠው ቦታ አፋር ነበር። አለቃዬ ከዚህ በፊት አፋርን አይቷት አያውቅም መሰለኝ አፋር እኮ ለችግኝ ተከላ ስልጠና አይሆንም ቢባል “አፋር ብያለሁ ለስልጠናው ጥሩ ቦታ ነው” ብሎ ሙጭጭ አለ። ሰልጣኞቹ ደግሞ የሶስት ክፍለ ከተማ የህዝብ ክንፍ አባላት ተብዬዎች ናቸው። በተጨማሪነት የሎተሪ አዟሪዎች እና የመስሪያ ቤታችን አስተዳደር ሃላፊዎች እንዲሳተፉ ተመርጠዋል። አለቃዬ የህዝብ ክንፍ ነን ያሉ ሰዎች ህዝብ እንዴት አይነት ችግኝ ተከላ ይወዳል? የሚለውን ሃሳብ ሊያቀርቡ እንደሚገባ መመሪያ ሰጥቷቸው ወደ ስልጠናው ይጓዛሉ።
ሶስተኛው ስልጠና ስለመስሪያ ቤቱ የህንጻ ደህንነት እና አደጋ መከላከል ላይ ያተኮረ ቢሆንም ቦታው ደግሞ የተመረጠው ሐዋሳ በሚገኘው የሐይሌ ሪዞርት ነበር። ለዚህ ስልጠና ከመስሪያ ቤቱ 150 ሰራተኞች መካከል 90ናው ተመልምለዋል። በዚህ አይነት ሰራተኛው ሲሄድ እና ሲመለስ እንግዲ ሳምንቱን ሙሉ ስራ ላይኖር ነው ማለት ነው። የማይቀሩት አስር የሚደርሱ የህዝብ ክንፎች ነን ያሉም አሉ።
ስለመስሪያ ቤታችን የህንጻ ደህንነት ስልጠና ለመውሰድ ሐዋሳ መኬዱ ያልጣማቸው አዛውንቱ አቶ አሸናፊ ለዚ ለዚ ምን አለፋቸው ስለአገሪቷ ህንጻዎች ደህንነት ነው የምናሰለጥናችሁ ብለው አገር አቀፍ ቢያደርጉን ይሻል ነበር ብለው አሸሞሩ። የህዝብ ክንፎችም ስላሉ ነው ሲባሉ ደግሞ እነሱማ መብረር ስለሚችሉ አደጋ ቢደርስም አይጎዱም ስልጠና አያስፈልጋቸውም ብለው አከሉበት። እውነታቸውን ነው ክንፍ ያለው ህጻ ቢደረመስ እንኳን በሰማይ ይበራል እንጂ ምን ይሆናል። አለቃዬ ደግሞ “ቸው ይሳተፉ ምን አለበት ባጀት መዝጊያ ነው እኮ አንድ ሚሊዮን ብር ተመድቧል አታስቡ እንጂ” እያለ አቅራራ።
የመጨረኛው የሳምንቱ የባጀት መዝጊያው ስብሰባ ደግሞ በአዳማ ከተማ የሚካሄድ ሲሆን ቅድመ ዝግጅቱም ሆነ የሆቴል መረጣው ቀድም ብሎ ተፈጻጽሟል። ኢንተርናሽናል ኮንፈረንስ የሚል ታርጋ የተለጠፈለት በመሆኑ የባጀት መጠኑም ሆነ የህዝብ ክንፍ ተብዬዎች ተሳታፊ ቁጥር አያሌ እንደሚሆን ይገመታል። እስከአሁን ድረስ ብቻ 500 ተሳታፊዎች እንዲገኙ በደብዳቤ ጥሪ እንዲደረግ ታዟል። የህዝብ ክንፎቹ ማን እንደመረጣቸው ባላውቅም እየተጠራሩ መጥተው የመግቢያ የጥሪ ወረቀቶችን አጽፈው ወሰዱ። አለቃዬ የመጡት ሁሉ ይውሰዱ የሚል መመሪያ አስተላልፎ ስለነበር 80 ሰዎች በክንፍነት ተመዝግበዋል። ይሄንጊዜ 'የአዲስ አበባ ህዝብ ክንፍ አለህ?' ተብሎ ቢጠየቅ 'እንኳን ክንፍ ሊኖረኝ በየቦታው የምሰለፍበት እግሬም እየተወላገደ ነው' ማለቱ አይቀርም መቼም ብዬ አሰብኩ። የስብሰባው ርዕስ ደግሞ <<አለም አቀፉ ያለፉት ጉባኤዎቻችችን ግምገማ>> የሚል ነው። ይሄን ስሰማ አለቃዬ ፊት ከት ብዬ ስቄያለሁ። ያለፉት ጉባኤዎች የትኞቹ ይሁኑ የት የተካሄዱት ተሰብሳቢዎቹም አያውቁም ብቻ ባጀት መዝጊያ በመሆኑ ለሶስት ቀናት መሰብሰባችን አይቀርም
ይሄ ባጀት ግን የህዝብ ክንፍ ተሳትፎም ተጨምሮበት ሊያልቅ አልቻለም። ታዲያ አስሩን በስልጠና እና በተለያዩ ጉዳዮች ስናወጣ ስናወርድ ካቃለልነው በኋላ አምስት ሚሊዮን ብሩ ተረፈ። ወዴት እናድርገው እባካኝሁ” እያለ አለቃዬ በየደቂቃው ቢሮዬ ይመጣል። አለቃዬን አስሩንም ክፍለ ከተሞች የህዝብ ክንፍ አባላት ሰብስበን እስካሁን የት የት ድረስ በራችኋል ብለን ስልጠና እንሰጣቸው እንዴ ብዬ ልቀልድበት አሰብኩና ይህችንም ደግሞ ስልጠና እንዳያደርጋት ሰግቼ ተውኩት። እባካችሁ እናንተዬ ይህችን አምስት ሚሊዮን ብር ወዴት እናድርጋት? እስቲ ሃሳብ አምጡ። መቼም አለቃዬ ብር ወደመንግስት ካዝና ከመመለስ መሞት ይመርጣል፤ ካልሆነ የሰፈሩን ሰው ጠርተን ክንፍ የሆናችሁ ደሞዝ እንከፍላለን እንበል እንዴ? ምክንያቱም ባጀት መዝጊያ ነዋ።





ሱሪው

አዛውንቱ እጃቸው ላይ ብር አጥሯቸዋል። በመሆኑም ሳምንቱን ሙሉ የት እንደሚያመሹ ግራ ገብቷቸዋል። እናም ካላቸው ሁለት ሱሪዎቸ መካከል የጓደኛቸው ልጅ ከውጭ አገረ ያመጣላቸውን ሱሪ አስቀርተው ሌላኛውን ሱሪ ለሰፈራቸው ልብስ በ70 ብር የሸጣሉ። በአስር በሩም የደንቡን ሶስት ብርሌ ጠጅ በላይ በላዩ ገልብጠው እያጋሱ ወደቤታቸው ይመለሳሉ። በእለተ ቅዳሜ 10 ሰዓት ገደማ የወጡት አቶ አበበ በጊዜ ወደቤታቸው አልተመለሱም። ምክንያቱም ድንገት በመንገድ ላይ እያሉ እጃቸውን ወደኪሳቸው ቢሰዱ 60 ባውንዳቸው የውሃ ሽታ ሆኖባቸዋል። ከጠጅ ቤቱ ወደቤታቸው እስኪጓዙ ድረስ ግማሽ መንገዳቸውን ቢያገባድዱም የረገጧትን መንገድ እየተመላለሱባት አቀርቅረው ብራቸው ሱፈልጉ አንድ ሰዓት ያህል ይፈጅባቸዋል። ጨለማው በመበርታቱም ብራቸውን እንደተበሉ አሰበው እየተበሳጩ እና እየተቆናጠሩ በእግራቸው ወደቤታቸው መኳተኑን ተያይዘውታል።

የሰፈራቸውን አስፓልት መንገድ ላይ ሲደርሱ ግራ ቀኝ አማትረው እንኳን መሻገሩን እረስተው አውራጎዳናው ላይ ዘው ቢሉ ግዜ ሁለት በተቃራኒ አቅጣጫ ይጓዙ የነበሩ ታክሲዎቸ በአንድነት የተጠንቀቁ ጥሩንባ ድምጻቸውን አምባረቁባቸው። አቶ አበበ ይህን ጊዜ ደንገጥ ብለው መኪናዎቹን ካሳለፉ በኋላ የሰፈራቸውን የኮብልስቶብ መንገድ ተያያዙት። በፍጥነት ቤታቸው እንደደረሱ በየስርቻው ብራቸውን መፈላለጉት ቀጥለዋል። ባለቤታቸው ወይዘሮ አሰገደች ግን ምን እንደሚፈለጉ በውል ባለማወቃቸው <<አቶ አበበ ምነው ዛሬ ቆዩ ጠፉ እኮ አሁን ምን እየፈለጉ ነው>> የሚል ቀጭን ድምፃቸውን አሰሙ። በዚህ ወቅት አቶ አበበ ንዴታቸውን ባለቤታቸው ላይ ለመወጣት <<እስቲ ዝም በይ፤ ገንዘብ ጠፍቶብኝ ነው፤ ከቤት ስወጣ ኪሴ ውስጥ ነበር ስመለስ ግን የለም>> አሉ። <<ታዲያ ሲሄዱ ከነበሩ እኪስዎ ውስጠ አሁን እቤት ውስጥ መፈለጉ ምን ያደርጋል መንገድ ላይ ጥለውት ነው የሚሆነው። ለመሆኑ ምን ያህል ብር ነው>> አሉ ወይዘሮ አሰገደች።

አቶ አበበ ግን ትናንትና ማታ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው የቡና መግዣ ሲጠይቋቸው ኪሴ ውስጥ ያለው 20 ብር ብቻ ነው ማለታቸው ትዝ ስላላቸው ስንት ብር እንደጠፋቸው ለመናገር አልቻሉም። የጠፋብኝ ብር 60 ነው ቢሉ እሰይ ማታ ስጠኝ ስልህ ታዲያ ምነው ተስቆነቆንክ እንደሚባሉ ያውቁታልና ዝም ማለትን ነበር የመረጡት። <<ብዙ ብር ነው እንዴ አሉ>> ወይዘሮ አሰገደች።

አባወራው የማታውን ቅጥፈታቸውን የሚሸፍን ምክንያት ያገኙ ይመስል <<አዎ ማታ ሰው ሰጥቶኝ ነበር የሰው ብር ጠፋብኝ 60 ብር ነው። አንድ አብሮኝ የሚሰራ ጓደኛዬ ከማጠፋው አንተ ጋር ይቀመጥልኝ ብሎ ቢሰጠን እኔው አጠፋሁት እስቲ አሁን አትጨቅጭቂኝ ብሩን ብቻ ፈልጊ>> ብለው ሶፋውን ያገለባብጡ ጀመር።

የቤቱ እመቤት ግን <<አይ እዚህ እንኳን የለም እኔ ቤቱን ጠርጌ ወልውዬዋለሁ የቤቱን መረገጫ ላስቲክ ውጪ ወይ ሌባ መንትፎት ይሆናል>> ብለው ወደጓዳቸው ገቡ። ነገሩ በዚሁ ታለፈና በሶስተኛው ቀን አቶ አበበ በቤታቸው ያለውን እንደእንቁ የሚያዩትን አንድ ሱሪያቸውን አውልቀው በቁምጣ ሆነው እንዲታጠብላቸው ለቤቱ ሰራተኛ ይሰጧታል። ታዲያ ይህች ሰራተኛ ልብሱን ከማጠቧ በፊት ኪሱን መፈታተሽ ነው የመጀመሪያ ስራዋ ሁሉምን ኪሱን ፈትሻ ስትጨርስ ምንም ነገር የለም ሱሪውንም አረፋ ወደደፈቀው የሳፋ ውሃ ውስጥ ጨምራ አንዴ አሸት እንዳደረገች ግን ከወደእግሩ አካባቢ ይቆረቁራታል። ሱሪውን አውጥታ በውስጥ በኩል ብታየው ገበሩ ነጭ ነበርና ብሩን ቁልጭ አድርጎ ያሳያታል። የሱሪው ኪስ በመቀደዱ ምክንያት እግሩ ጋር የደረሰው ብር ለማውጣት እጇን የሚያሳልፍ አልሆን ቢላት የሱሪውን ስፌት በሙሉ ተርትራ 60 ብሩን አወጣችው።

ጀብዱ እንደሰራ ሰው <<ጋሽዬ ጋሽዬ እያለች ሮጣ ሱሪዎ ውስጥ ብር ተገኝቷል>> ብላ የረጠበውን ብር ሰጠቻቸው። አቶ አበበ ወዲያው የጠፋባቸው ብር እንደሆነ ገብቷቸው ደስታውን አልቻሉትም ነበር። ወይዘሮ አሰገደች ግን ሰራተኛቸው ብሩን ስታገኝ ቅድሚያ ለእርሳቸው መስጠት እንደነበረባት እያሰቡ ውስጣቸው ቂም መቋጠር ጀምሯል። ቀስ ብለው ልጅቷ የምታጥበበት በረንዳ ላይ ሄደው <<ብሩን እንዳገኘሽ መጀመሪያ ለእኔ ለምን አልሰጠሽኝም ስንት የሚገዛዛ ነገር እያለ አንቺ ደነዝ>> ብለው ወረዱባት። ልጅት የጥፋተኝነት ስሜት እየተሰማት ይቅርታ ጠይቃ አጎንብሳ ማጠቧን ቀጠለች።

አቶ አበበ እና ባለቤታቸው ከብሩ መገኘት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት ተገናኝተው አይነ ለአይን እየተያዩ ነው። <<እሰይ አሰይ በሩ ተገኘ በሉ ለእኔም ሃምሳዋን ብር ይስጡኝና የሚገዛዛውን ለቤቱ ልግዛ>> አሉ ወየዘሮዋ።

አቶ አበበ << የሰው ብር ሲገኝ ይመለስ ይባላል እንጂ እናጥፋው እንዴ ደግሞ>> እያሉ ማጉረመረም ጀምረዋል። አይ እርስዎ ደግሞ እየተዋወቅን በሉ ይስጡኝና ምሳውም ይዘገጃጅ ብለው ወይዘሮዋ ወይ ፍንክች ያባቢላዋ ልጅ አልንቀቀሳቀስ አሉ። አቶ አበበ ነገሩን ለማረሳሳት ወደውጪ ወጥተው <<ጎሽ ጎሽ እንዲህነው ልጅ በይ ሁሌም ስታጥቢ ኮቶቹን ሙሉ ለሙሉ እየፈተሽ እንድታጥቢ>> ብለው ሰራተኛዋን ማሞጋገስ ቀጠሉ። ልጅት በተሰጣት ሙገሳ ተደስታ ፈገግ እያለች <<ደግሞ እኮ እጄን አላስገባ ቢለኝ ሱሪውን በአንድ ወገን ገንጥዬ እኮ ነው ብሩን ያወጣሁት>> ብላ ግማሽ ቀሚሽ ግማሽ ሱሪ ያደረገችውን ልብስ ከአረፋው ውስጥ መዝዛ አሳየቻቸው። አቶ አበበ የሚወዱት ብቸኛ ሱሪያቸው እንዲህ ተበላሽቶ ሲያዩት ደስታቸው ሁሉ በኖ ጠፋባቸው። ምነው ምነው አንድ ሱሪዬን እንዲህ እንደ እብድ ልብስ ቀዳደድሽው ብለው ሙሾ ማውረድ እስኪቀራቸው ድረስ አለቃቀሱ።

ሱሪውን በእርጠቡ እንዳለ ተቀብለው እያገላበጡ <<ምነው ብሩ ቢቀርብኝ እና አብሮ በታጠበ የጓደኛዬ ልጅ ካማሪካ ያመጣልኝ ውድሱሪ እኮ ነው>> እያሉ ማላዘኑን ቀጠሉ። ሁኔታውን በቅርበ ርቀት ሲከታተሉ የነበሩት ወይዘሮ አሰገደች ሳቅ እየተናነቃቸው <<ምንም አይደል አንድ ሺ ብር የሚያወጣ የአማሪካ ሱሪ ቢቀደድ ውስጡ 160 ብር ስለተገኘ በ15 ብር አሰፍተው እኔ እተኩስልዎታለሁ>> እያሉ የለበጣ ማስተዛዘኑን ተያያዙት። አቶ አበበ ይህን ጊዜ <<50 ሣንቲም ዶሮ የአንድ ብር ከሃምሳ ሣንቲም ገመድ ይዛ ጠፋች እንደተባለው ነው፤ በብሩ መገኘት ደስታዬን ሳልጨርስ የባሰ አመጣብኝ>> ብለው አማረሩ። ባለቤታቸውም ካረጋጉዋቸው በኋላ አግባብተው ብሩን እንዲሰጧቸው ቤት ያፈራውን ምሳ እየተመገቡ መጠየቅ ጀመሩ።

<<በቃ አሁን የሆነው ሆኗል 15ብሯን ይዘን ለልብሱ ማሰፊያ 30ዋን ለቡና መግዣ የተረፈችውን 15 ብር ደግሞ ለኪስዎ ቆሎእንኳን ቢደፉ ይዘው ወይም ደግሞ ጠጅዎትን ይጠጡባት መቼም የደንብ ነው አይቀርም ብዬ ነው>> ብለው አከፋፈለው ጨረሷት ብራን። የዚህን ጊዜ አቶ አበበ ካፈርኩ አይመልሰኝ በሚል ስሜት የሰው የተባለችውን ብር በሂሳቡ ስሌት መሰረት ባይስማሙም 15 ብር ለባለቤታቸው ሰጥተው <<ብትፈልጊ ቡና ባትፈልጊ ሻይቅጠል ገዝተሽ ጠጪበት>> ብለው ወርውረውላቸው ወጡ።

አቶ አበበ ከነቁምጣቸው ናቸው ሱሪያቸው ተቀዷል። በዚህ ላይ እየታጠበ ነበና በውሃ የተነከረውን ልብሳቸውንም እንዳንጠለጠሉ ወደ ሰፈሩ ልብስ ሰፊው ዘንድ ገሰገሱ። ልብሰፊው ደንግጠው ምን ሆንክ እርጥብ ሱሪ ይዘህ መጣህ ቢሏቸው ነገሩን ባጭሩ አስረዷቸው። እናስ አሉ ልብስ ሰፊው አቶ አበበ ግን ፈጠን ብለው ባለፈው በ70 ብር የሸጥኩልህን ሱሪ አምጣ እና ይሄን ሰፍተህ ልብስ እኔ እራቁቴን ስሄድ እብድ ከምባል አንተ የእጅ ሙያህን ተጠቅመህ ሰፍተህ መልበስ ትችላለህ ብታተርፍ እንጂ አትከስርም ከሱሪው አንፃር ብለው እርፍ።

ልብስ ሰፊው ደግሞ እንደአጋጣሚ የለበሱት በ70 ባውንደ ከአቶ አበበ ላይ የገዙትን ቡኒ ሱሪ ነበር። እናም መረር ያለነገር ከመምጣቱ በፊት ሱሪያቸውን አውልቀው ለአቶ አበበ ሰጥተው እርጥቡን ሱሪ እስኪሰፉ እርሳቸውውም በግልገል ሱሪያቸው መሃል ሰፈራቸው ላይ ከነመኪናቸው መቀመጥ ግድ ሆነባቸው። አለም የተገላቢጦሽ ናትና ከቤት በደህና ሱሩ የወጡት ልብስ ሰፊ አሁን ላይ ግማሽ እራቁታቸውን ሲቀመጡ ግማሽ እራቁታቸውን ከቤት የወጡት አቶ አበበ ደግሞ ደህና ሱሪያቸውን አድርገው መጭ አሉ።

የስንዱ ገብሩ አሻራ ያረፈበት የጥበብ አምባ

በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት የፓርላማ አባል እና የጦር አርበኛዋ ወይዘሮ ስንዱ ገብሩ አፄ ኃይለስላሴ ፊት ቀርበዋል። በልባቸው ያሰቡት እውን እንዲሆን ጃንሆይን እያነጋገሩ ነው። ወይዘሮዋ ለድሆች እና ለአካል ጉዳተኞች የሚሆን ቦታ እፈልጋለሁ እና ይፈቀድልኝ፤ ቦታው ላይም የእደጥበብ ውጤቶች ለማምረት የሚያስችል ስልጠና ልሰጥበት ስለሆነ ቦታ ተፈልጎ አዲስ አበባ ላይ ይሰጠኝ ብለው ይጠይቃሉ። ለቅዱሱ ዓላማ ንጉሱ ቦታውን ይፈቅዳሉ፤ የተፈቀደውም ቦታ አፍንጮበር አካባቢ የሚገኝ አንድ ግቢ ነበር።
ስንዱ ገብሩ እና አጼ ኃይለስላሴ ፊት ለፊት
 
የጎንደር ከንቲባ የነበሩት የአቶ ገብሩ ደስታ ልጅ በሁኔታው ተደስተው አፍንጮ በር ወደሚገኘውና አሁን ላይ መስማት የተሳናቸው ወጣቶችን መደበኛ ትምህርት ቤትነት ወደተቀየረው ስፍራ ያመራሉ። የአርበኛው መሸሻ ገብሩ እና የታዋቂዋ የሙዚቃ ቀማሪና የክላሲካል ፒያኖ ተጫዋች እማሆይ ጽጌ ማርያም ወይም የውብዳር ገብሩ እህት የሆኑት ወይዘሮ ስንዱ አስር የሚሆኑ ወጣቶችን በግቢው ሰብስበው በ1959 .ም ሀ ብለው ስራቸውን ጀመሩ። ከመደበኛ ስራቸው እና ከድርሰት ስራቸው ላይ እየቀነሱ በሚያገኟት ሰዓትም ከአካል ጉዳተኞች እና ድሃ ሆነው የአካል ጉዳት ከሌለባቸው አስር ወጣቶችን ስለዕደጥበብ ሙያዊ ስልጠና እንዲያገኙ ያደርጋሉ።
ይህ ወሬ እና የስልጠናው ጥቅም በመላ ከተማዋ በመዳረሱም የዕደጥበብ ስልጠናውን ፈላጊዎች ቁጥር ከአቅማቸው በላይ ሆነ። በመሆኑም ሰፊ ቦታ በማስፈለጉ የሚተባበር ሰው ይፈለጋል። በወቅቱም ሽሮሜዳ አካባቢ አንድ አዛውንት ልጃቸውን ሊድሩበት ያዘጋጁትን ግድግዳውም ጣሪያውም ቆርቆሮ የሆነ አዳራሽ ለዕደጥበብ ሰልጣኞች በመፍቀዳቸው 405 ሰዎች ለስልጠናው ዝግጁ ሆኑ። አፄ ኃይለስላሴ በይፋ የወይዘሮ ስንዱን መልካም ስራ ለመመረቅ በ1960 .ም ወደ ሽሮሜዳው አዳራሽ አመሩ።
በወቅቱም ንጉሱ የዕደጥበብ ውጤቶች እዚህም እዚያም ተሰርተው ተሰናድተው ሲያዩም በመደሰታቸው የዕደጥበብ ስልጠናው ቦታን «የችግራችን መርጃና ማቋቋሚያ» የሚል ስያሜ ሰጡት። ከግማሽ ምዕተ ዓመት በኋላ ደግሞ በወይዘሮ ስንዱ የተቋቋመው የስልጠና ማዕከል ወደ ሀገር ጥበብ ማደራጃ ድርጅትነት ተቀይሮ መገናኛ ከእስራኤል ኤምባሲ ፊት ለፊት በሚገኘው ቢሮው የእዮቤልዩ በዓሉን ሰሞኑን አክብሯል። ዛሬም ድረስ አካል ጉዳተኞች እና ገቢያቸው አነስተኛ የሆኑ አካል ጉዳተኛ ያልሆኑ ዜጎች ውብ ዕደጥበባትን ማምረታቸውን ቀጥለዋል።
አቶ አለማየሁ ምስጋናው አይነስውር ቢሆኑም አዕምሮዋቸው ጥበብን ቀስሟልና በዲዛይናቸው ያማሩ ስጋጃ ምንጣፎችን እያመረቱ በየቤቱ እና በየቤተመንግስቱ ደጃፍ ላይ የጥበብ አሻራቸውን እያሳረፉ ይገኛል። ለእርሳቸው ስጋጃ ማዘጋጀት የስራ ምድባቸው እና ገቢያቸው ብቻ ሳይሆን መስራት እንደሚችሉ ለዓለም ያሳዩበት የህይወት መንገድ ነው። በዲዛይናቸው ያማሩ ውብ ምንጣፎችን ሲመለከቱ አይደለም አይነስውር አይናማውም ቢሆን ሊሰራው ይከብዳልና እንዴት ጥልፎቹን አውቀው በስጋጃው ላይ ተጠበቡባቸው? ስል ጥያቄዬን አቀረብኩላቸው። ስጋጃውን ሊሰሩ ሲዘጋጁ በመስሪያ ቤቱ ውስጥ የዲዛይን መሪ የሆኑ አይናማ ሰዎች እንደሚያግዟቸው አጫወቱኝ። «ዶርማት» የሚባለውን የስጋጃ አይነት ማለትም ጎኑ 50 ሳንቲሜትር ቁመቱ ደግሞ 90 ሳንቲ ሜትር የሆነውን ምንጣፍ ግማሹን መስራት እንደሚችሉና በረዳቶቻቸው አማካኝነት በሚሰጣቸው የቁጥር ኮድ እየታገዙ ዲዛይኑን እንደሚያሳምሩት አስረዱኝ። ድር እየተከረረ በቁጥር አንድጊዜ ፣ ሁለት ጊዜ ና ሶስት ጊዜ እየተባለ፤ ከመንዝ በሚመጣው ጥሬ እቃ አማካኝነት እየተፈተለ በጥራት እንደሚሰራም አክለው አስረዱኝ።

የሐዲስ መስታወት


የኪነጥበብ ስራዎች ልክ እንደ መስታወት በዘመናቸው ያለውን ከሃድ ቁልጭ አድረግው ያሳያሉ መስታወቅ ጉድፍንም ውበትንም በግልጽ ፊት ለፊት እነደሚያቀርብልን የሥነጽሁፍ ስራዎችም እነዲሁ ናቸው። ደ ሐዲስ አለማየሁ ፍቅር እከመቃብ ያለው መጻህፍ ደግሞ በወቅቱ የነበረውን የንጉሳዊ ዘመን ኢትዮጵያ መስታወት ሆኖ አሳይቷል። ይህ መጻህፍ በርካታ ጊዜ ብዙ የተባለለት ቢሆንም በየጊዜው ምስጢሩ ቢነገር የማይሰለች ነውና ዛሬም የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት አቶ ምንዋጋው ተመስገን ስለፍቅር እስከመቃብር መስታወትነት ያነሱትን ጥናት መሰረት አድርጌ ሃሳቡን አቀብላችኋለሁ።
የባለቅኔውን ሕይወትና ሥራዎች የምንመረምረው ራሳችንን፣ አገራችንን፣ ባህላችንንና ማንነታችንን ለመመርመር ነው። ባለቅኔው ወደእውነታችን የሚያደርስ መንገድ እንጂ በራሱ የመጨረሻ ግብ አይደለም” በሚለው ሃሳብ አቶ ምንዋጋው ይስማማሉ። በድርሰት ስራዎች ላይ የደራሲውን ፖለቲካዊ አቋም እናይበታለን፤ ርእዮተ ዓለማዊ ድምጹን እናደምጥበታለን። የኪነጥበብ ስራዎች በተለይ ከታላቅ ተመስጦና አንጽሮት የሚወለዱ ሥነ ጽሑፋዊ ሥራዎች ትንቢታዊነት አያጣቸውም። ትናንትን ከመጥቀስ፣ ዛሬን ከመቅረጽ አልፈው ነገን በገሀድ ይተነብያሉ፤ ነገን በገሀድ ይገልጻሉ።ልቦለድም ይሁን ፍልስፍና የመሰሉ የሥነ ጽሑፍ ሥራዎች ሁሉ ከማኅበረሰቡ ታሪክ፣ ባህልና ሕይወት ተቀድተው በአዲስ መልክ ተፈጥረው መልሰው ያንኑ የሚያሳዩን መስታውቶች ናቸው።
እንደ አቶ ምንዋጋው ከሆነ፤ ፍቅር እስከመቃብር የተጻፈበት ጊዜም ሆነ የአሁኑ ዘመን ማሳያ ይሆናል። ድርሰቱ የሰዎች የተጨናነቀ ማኅበራዊ ዓለም ማሳያ ነው። ገጸ ባሕርያቱ ከተለያዩ የሕይወት አቅጣጫዎች የተሳሉ እንደመሆናቸው በሃያኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ ላይ የነበረውን ሰፊ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ይወክላል። ከበርካታ ገጸ ባሕርያቱ መካከል ባላባቶች (ፊታውራሪ መሸሻና ፊታውራሪ አሰጌ)፣ የቀሳውስት ቡድን (አባ ሞገሴና አለቃ ስርግው)፣ ገበሬዎች (ቦጋለ መብራቱና አበጀ በለው)፣ ባለቅኔዎችና መምህራን (በዛብህና አለቃ ክንፉ)፣ ባሮች (ሀብትሽና ልኩራ በሁሉ)፣ ንጉሠ ነገሥቱ (በስም ያልተጠቀሱ) ይገኙበታል።
ሐዲስ እንደሚነግሩን ለመማር ዓይነ ኅሊናን መክፈት ወሳኝ ነው። ብዙ ጊዜ አካላዊ ዐይኖች ሲዘጉ የማይታየው ይታያል፡፡ ለሰው ሁለት ዓይነት ዐይኖች አሉት። አንዱ ዓይነት አካላዊ ሁለተኛው ዐይነ ኅሊና ናቸው፡፡ ሁለቱ በአንድ ላይ አያዩም፤ ቢያዩም ደኅና አድርገው አያዩም። አካላዊ ዐይኖች ማየት የማይችሉትን ለማየት ዐይነ ኅሊናን መክፈት ያስፈልጋል። ከፍቅር እስከ መቃብርም እንዲሁ ምን እንማራለን? የሚል አጠይቆ አቅርበው ኅሊናችንን በመክፈት ስለ እያንዳንዱ ገጸባህሪ እና መልዕክቶቻቸው ያስረዱናል።
ላግባሽ አሰጌ” (ፊታውራሪ አሰጌ)
ደራሲው በፊውታራሪ አሰጌ አሳበው ለዚያን ጊዜዎቹም ሆነ ለወቅቱ ዋልጌ ባለሥልጣናት ሊነግሩን የፈለጉት ሥነ ምግባራዊ እሴት ትልቅ ዋጋ የሚሰጠው ነው። በመጻሕፉ በቅጽል ስማቸው “ላግባሽ አሰጌ” ስለተባሉት ፊታውራሪ አሰጌ ሲገልጹ እንዲህ ይሉናል።
ላግባሽ አሰጌ ከማናቸውም የበለጠ ሴትና ዘፈን አጥብቀው ይወዱ ነበር። ከጀግና ወይም ከሽማግሌ አዝማሪ የሚያከብሩ፣ ከንጉሥ ቀጠሮ ለሴት ቀጠሮ ቅድሚያ የሚሰጡ ነበሩ። ቆንጆ ሴት ከመጠን በላይ ከመውደዳቸው የተነሣ ቆንጆ ሴት ባዩ ጊዜ አእምሮ የሚሰውር በሽታ እንዳለባቸው ሰዎች ራሳቸውን መግዛት ያቅታቸው ነበር። ሴት ከመጠን ያለፈ መውደዳቸውን የሚያውቁ ሰዎቻቸው አንዳንድ ጥቅም ሲፈልጉ ሴት ይዘው በመቅረብ ወይም ሴት ለማቅረብ ተስፋ በመስጠት የእሳቸውን ክብርና ጥቅም የሚጎዳ ወይም ስለአስተዳደርና ስለፍርድ የነበራቸውን ኃላፊነት የሚጎዳ መሆኑን ለጊዜው ማየት አይችሉም ነበር።” ተብሎላቸዋል። ሐዲስ በዚህ በኩል የዘቀጠ ማንነት ለፍርድ ሰው እና ለአስተዳደርነት እንደማያበቃ በአግባቡ ነግረውናል።
መንግሥቱ ፊታውራሪ መሸሻ (የመንግሥታዊ ሥነ ምግባር ማሳያ)
ፊታውራሪ መሸሻን ህዝብ ያልወደደው ስራ ለማምም እንደማይጠቅም የታየበት ገጸ ባህሪ ሆኖ እናገኘዋለን። “በጎልማሳነትዎ በፈረስ፣ በጉግስ፣ በተኩስ ተወዳዳሪዎችዎን በማሸነፍዎ፣ በጦር ሜዳ ሄደው ጠላቶችዎን ድል መተው በመመለስዎ ሰዉ ሁሉ ሲያደንቅዎ፣ ሲያከብርዎ፣ ሲፈራዎ ጊዜ፣ ለምነው ሳይሆን ተለምነው፣ የጠየቁትን ብቻ ሳይሆን ያልጠየቁትን ጭምር ሲያገኙ ጊዜ እግዚአብሔር በሰፊ መሬቱ ከእርስዎ በቀር ሌላ ክብሩንና ጥቅሙን የሚወድ ሰው እንዳልፈጠረ፣ ሰዉ ሁሉ የእርስዎን ፈቃድ ለመፈጸም እንጂ የራሱ ፈቃድ የሌለው ሆኖ እንደተፈጠረ በሙሉ ልብዎ አምነው በዚሁ ልመራ ብለው ተነሡ። በዳኝነት መንበር ቢያስቀምጥዎ በሕግ ፈንታ ፈቃድዎን ሕግ አድርገው ልፍረድ አሉ። ሀገር ቢሰጥዎ በሕግ እንዲያስተዳድሩትና እንዲጠብቁት የተሾሙበትን ሕዝብ እንደቀማኛ ይዘርፉት ጀመር። እንዲያው በአጭሩ ሕዝብ የጠላው እግዚአብሔር የጠላው መሆኑን ማወቅ አቃተዎ። ስለዚህ ያደንቅዎ፣ ያከብርዎ የነበረው ሰው ሁሉ ይጠላዎ ጀመር። ሁሉም ሞትዎን ያለዚያም ሽረትዎን አጥብቆ ፈለገ።” በሚል ሐዲስ በመጻህፋቸው በገጽ 266 ላይ በአግባቡ አስተችተዋቸዋል።
የጉድ ማኅበር ምንነት
አብዛኛውን ጊዜ በርካቶች የተሳሳቱበት ነገር እንደ ትክክለኛ ነገር ይቆጠራል ይባላል። ጉዱ ካሳም ዕውነትን ይዞ ቢጓዝም በዙሪያው ከበውት የሚገኙ ሰዎች ጋር ለየቅል የሆነ አካሄድ ስላለው የእርሱ መንገድ የጥፋት ተደርጎ ተቆጠረ። ባለንበት ዘመንም አገርና ወገን የሚጠቅም ሃሳብ የሚያነሱ ሰዎች በአብዛኛው ህዝብ የተሳሳተ አስተሳሰብ ምክንያት እብድ ሊያስብላቸው ይችላል።
ጉዱ ካሣ እንደሚነግረን “ጉድ” የሚባለው መጠሪያ ለእርሱ የተሰጠ አላግባብ ሆኖ እንጂ ደገኛው ወይም ትክክለኛው ጉድስ የምንኖርበት ማኅበር ነው። በከበበው ዓለም ውስጥ የግሉን ዓለም ፈጥሮ በሰው መካከል ብቻውን ሆኖ ይኖር የነበረው ጉዱ ካሣ የሚኖርበትን (የምንኖርበትን) ማኅበር “ዐይን እያለው ፍሬውን ከገለባ ለይቶ ማየት የማይችል፣ አእምሮ እያለው የሚጠቅመውን ከሚጎዳው ለይቶ ማስተዋል የማይችል፣ እንደበግ መንጋ በፊቱ የሚሄደውን ተከትሎ የሚንጋጋ፣ እንደጭነት ከብት የጫኑትን ተሸክሞ የሚጎተት የጉድ ማኅበር” ይለው ነበር።
የንጉሥ ግብርንም ሲተች “ከሀብቱ ሀብት ከፍሎ እንደሚገብር ከሰውነቱ ከፍሎ ለንጉሥ የሚገብረው የመንፈስ ግብር ነው!” እያለም እምቢተኛነት መለመድ እንዳለበት ካሳ ያስተምራል። ነገር ግን ምንም ቢሆን በግዕዙ እንደሚባለው ‘ብዙኃን ይመውዑ’ ብዙኃን ያሸንፋል ነውና ብዙኃኑ አሸንፈው ጉዱ የሚለው ቅጥያ የካሣ ዳምጤ ስም ማዳመቂያ ሆነ።
ጉዱ ካሳም ይህንንኑ በእራሱ ላይ የደረሰውን ግፍ ያብራራል። የእኛስ ዘመን ማኅበራዊ ሥሪት በምን ይለያል? … ባሪያው እንዲሸጥ እንዲለወጥ፣ እጀ ሠሪው እንዲናቅ እንዲጎጠጥ፣ ደሀው በጌታ እንዲገዛ እንዲረገጥ ተመድቧል። የድሀ ሽማግሌ ‘አንተ’ እየተባለ እንዲሞት ተደንግጓል። ከንቱ አስቦ ከንቱ የሚናገር ‘ዘመናይ’ ተብሎ እየተደነቀ ገዥ እንዲሆን፣ ቁም ነገር አስቦ ቁም ነገር የሚሠራ የተናቀ ሆኖ ተገዥ እንዲሆን ተመድቧል፡፡ ይገርምሃል! ይህን የማይረባ ልማድ ይህን በግፍ ላይ የተመሠረተ ክፉ ልማድ ተመልክተህ ‘እንዲህ ያለ ልማድ ሊኖር የማይገባው የሚችልም አይደለምና ይልቅ አወዳደቁ እንዳይከፋ ቀስ ብሎ እንዲለወጥ ማድረግ ይሻላል’ ብለህ የተናገርህ እንደሆነ እንደከሀዲ ተቆጥረህ የምትሰቀልበት ገመድ ይሰናዳልሃል እያለ ያስረዳናል።
ዝም ብለህ እያዘንህ ተመልካች የሆንህ እንደሆነም እንዲህ እንደእኔ ‘እብድ፣ ጉድ’ እያሉ ሰላምህን አሳጥተው ከማኅበር አስወጥተው በዘመድ መሐል ባዳ ተወልደህ ባደግህበት ሀገር እንግዳ ሆነህ እንድትኖር ያደርጉሃል። ደግሞኮ ይህን ሁሉ የሚያደርጉብህ ‘የጌታ ዘር ነን’ የሚሉት ሁሉንም ረግጠው እላይ የተቀመጡት ብቻ ቢሆኑ ‘ጥቅማቸው እንዳይጎድልባቸው ነው’ ትላለህ፡፡ ነገር ግን ባሮቹ፣ እጀ ሠሪዎቹ፣ ድሆቹ ሁሉ፣ ግፍ የሚሠራባቸው ሁሉ ከግፍ ሠሪዎች ጋር አንድ ላይ ተባብረው ሲፈርዱብህ ምን ትላለህ? ‘ከልማድ ጋር የማይስማማ እውነት ሁልጊዜ ሀሰት ነው’ የሚባለውን የማይረባ ተረት አስበህ ዝም ማለት ብቻ ነው፡፡ እየውልህ! በጠቅላላው የዚህ ልማድ እስረኞች ነን፡፡” እያለ ዕውነት መገለባበጧን እያስረዳ ይቀጥላል።

ቄስ ምሕረቱ፣ ቄስ ሞገሴና አባ ተክለ ሃይማኖት

ቄስ ምሕረቱ በሐይማኖት ምግባራቸው ትክክለኛ ያልነበሩ አሳሳች ነበሩ። እንደ አቶ ምንዋጋው ከሆነ፤ “እናንተ የምድር ጨው ናችሁ፤ እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ” የተባሉ ካህናትና መነኮሳት ማጣፈጣቸው ቀርቶ ራሳቸው አልጫ ሲሆኑ፣ ብርሃንነታቸውን በጨለማነት ሲተኩ አያድርስ ነው።
ቄስ ምሕረቱ ከሰው ሕይወት ይልቅ የገንዘብ ፍቅር እንደሚበልጥባቸው የአቶ ቦጋለን መሞት ከእመት ውድነሽ ሲሰሙ የመለሱት መልስ ምስክር ይሆናል።
የአባ ምሕረቱን የሥነ ምግባር ደረጃ የአባ ቦጋለን ሬሳ እንዲያመጡ በሚልኳው ሰዎች በኩልም ማየት ይቻላል። ገብሬ የተባለ አገልጋያቸውን በተላላፊ በሽታ ነው የሞተ ወደተባለው የቦጋለ መብራቱ ሬሳ ወዳለበት ቤት ልላከው ወይስ ይቅር እያሉ ከተወዛገቡ በኋላ “ይሂድ ግዴለም፤ እግዚአብሔር ለእኔ ካለው ምንም አይሆንም፤ … መቼስ የሰው መፈረጃ ከመሆን የማይሻል የለም።” እያሉ ሰው ምን ይለኛል በሚል ስሜት ብቻ መወጠራቸውን ያሳያል። ይህም ሐዲስ በሐይማኖታዊ ግብራቸው ሳይሆን በጥቅም የሚመሩ ሰዎች መኖራቸውን ሲያሳዩን ነው።።
ቄስ ሞገሴ ደግሞ ዕውቀት አጠር ስለነበሩ ድጋፋቸውም ሆነ ተቃውሟቸው የእምነቱን ሕግጋት የተከተለ ሳይሆን የፊታውራሪና የቀራቢዎቻቸው ዓይንና ግንባር ብቻ ነበር። ለጉዱ ካሣ አንዱ ራስ ምታትም እነፊታውራሪን ገሥጸው ወደበጎ ከመመለስ ይልቅ ለግፉ ተግባራት ተባባሪ የሆኑ እነአባ ሞገሴ መሆናቸው ነው። ጉዱ ካሣ ስለዘመናችን አባ ሞገሴዎችም እንዲህ የሚለን ይመስላል፡- “አባ ሞገሴ እንደምታውቋቸው የራሳቸው ሐሳብ የሌላቸው፣ የሰውን ሐሳብ ብቻ ከዓይኑና ከግንባሩ አይተው ለመተርጎም ችሎታ ያላቸው፣ ሆዳቸውን የሞላና በፈለገው መንገድ የሚመራቸው፣ ተግባራቸውን ለሆዳቸው የሸጡ የለወጡ ናቸው፡፡” እያለ ይወርፋቸዋል።
ከጉሊትና ከናሞራ ባላገሮች ተልከው የመጡት ሽማግሌ ሲናገሩም አባ ሞገሴ ፊታውራሪ ሲቆጡ አይተው፣ “ዝም ይበሉ እርስዎ ምን ያሉ የሽማግሌ ባሕሪ የሌላቸው ናቸው እባካችሁ! እዚህ ጠብ ለመፍጠር የሰይጣን መላክተኛ ሆነው ነው የመጡት?” ማለታቸው የአባ ሞገሴን የወረደ ሥነምግባር ያሳያል። የሥነ ምግባር ትንተናችንን ሙሉ የሚያደርገው አባ ሞገሴንና መሰሎቻቸውን ከቤተ ክህነት አውጥተን ማየት ከቻልን ብቻ መሆኑን ደግሞ አጥኚው ያስረዳሉ።
አባ ሞገሴዎች የሌሉበት የማኅበረሰብ ክፍል ካለ ያ ማኅበረሰብ ከመለካውያን የጸዳ ስለሆነ ዕድለኛ ነው፡፡“መለካዊ” ማለት በሃይማኖት ስም የንጉሥን ፈቃድ ብቻ የሚፈጽም እግሩ ቤተ ክርስቲያን ልቡ ቤተ መንግሥት ያለ ጳጳስ ማለት ነው። እንደነዚህ አይነት ሰዎች “ድርጓቸውም ሹመታቸውም ከንጉሡ በመሆኑ ፣ ብዙ ጊዜም ከነገሥታቱ ጋር ስለሚውሉ ምንም ዓይነት ችግር ቢያዩ በዝምታ ከማሳለፍ በቀር የሚቃወሙበትና የሚገሥጹበት አጋጣሚ አልነበረም፡፡” ይላል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ለሐይማኖታዊ ግብራቸው በሀቀኝነት የሚቆሙ አይጠፉም። እንደዚህ አይነት ጊዜ ብዙ ጊዜ አለመግባባትና ችግር የሚፈጠረው ሹመትና ገንዘብን ንቀው በነበሩ አባቶች እና ለገንዘብ ሲሉ በመነኮሱትና ክህነት በተቀበሉት መካከል ነበር።
ስለ አባ ተክለ ሃይማኖት ደግሞ “እየውልህ! ቤተ እግዚአብሔር እንደዚህ ላሉት ሽፍቶች፣ እንደዚህ ላሉት ዘራፊዎች ዋሻ ሆነች! እየውልህ! ካህናታችን ከሐዋርያታችን የሚበዙት ከአለቆች ጀምሮ በመነኮሳቱ አልፎ እስከተራ ደብተሮች እስከዲያቆናቱ ድረስ አንዱ አስማት አድራጊ። አንዱ አስማት ፈቺ፣ ሌላው ጋኔን ስቦ አምጪ ሌላው አስወጪ፣ አንዱ መቅሰፍት አምጪ ሌላው ምሕረት አሰጪ ነን እያሉ ውሸታቸውን በየጥምጥማቸው በየቆባቸው በየደበሏቸው ሸሽገው ሊመሩት ሊያስተምሩት በተሰጣቸው መንጋ የሚጫወቱ ናቸው!። ታዲያ ከእነዚህ ጋር ማኅበርተኛ ሆኖ በአንድ ስመ እግዚአብሔርን መጥራት በተቀደሰ ስሙ ማፌዝ አይደለም?። እየውልህ! ይህ ነው ከምወዳት ቤተ እግዚአብሔር ያራቀኝ! ሰው የሚለው ሌላ ነው፡፡ ነገር ግን እውነቱ ይህ ነው፡፡” እያለ በመጻህፉ ገጽ 428 ላይ ያስቀምጣቸዋል።
ስለእኝህ አስመሳይ ሰው ወይም አባ ተክለ ሃይማኖት የቀረበው ምጸታዊ ገለጻ ቤተ እግዚአብሔርን ተጠግተው በሚያረክሱት የካህናት አባላት ላይ ያነጣጠረ ጠንካራ ሂስ ነው። ጉዱ ካሣ ስለብዙኀኑ ካህናት ምግባረ ብልሹነት ለበዛብህ ሲነግረው የነበረውን በተግባር የሚያሳይ ነው። ሰብለ የአባ ተክለ ሃይማኖትን የመነኩሴ ደበሎና ቆብ መግፈፍ በአንድ በኩል ትእምርታዊ ሆኖ እናገኘዋለን። አባ ተክለ ሃይማኖት የማይገባቸውን ሃይማኖታዊ ክብር በአስመሳይነት ስለተጎናጸፉ ያን በመግፈፍ እውነተኛ ማንነታቸውን የማጋለጥ ሚና ሲኖረው፣ ያ የተጨማለቁበት ትውኪያ ደግሞ የኃጢአታቸውን፣ የርኩሰታቸውን፣ የዝቅጠታቸውን መጠን ማሳያ ነው።
እንደ አቶ ምንዋጋው ከሆነ፤ ይህን የአባ ተክለ ሃይማኖትን “ቤተ እግዚአብሔርን ተጠግተው በሚያረክሱት የካህናት አባላት” ማሳያ ብቻ አድርጎ ማቆም አያስፈልግም። ይልቁንም እርሳቸውን “ቤተ መንግሥትን ተጠግተው” ያልተገባ ሥራ በሚሠሩ የካቢኔ አባላትም መመሰል ይቻላል። ይህ የዘመናችን መንፈስ መገለጫ ስለሆነ ደግሞ ዘረኝነት፣ ጉቦኝነት፣ ፣ ሴሰኝነትና ዕብሪት አድርገን ልንተረጉመው እንችላለን።
አበጀ በለውና ነጋዴው ዓሊ ጅብሪ
አበጀ በለው በፊታውራሪና በሹማምንታቸው የሚፈጸመው ግፍ ሲበዛ ተመልክቶ ለብዙኀኑ መብት መጠበቅ ሲል የሸፈተ ገበሬ ነው። ሊዘርፉ የሄዱትን ፊታውራሪ ከማረካቸው በኋላ የሚናገራቸው ነገርም ይህን ዓላማውን ቁልጭ አድርጎ ያሳየናል። እርሳቸው ተማርከውም እንኳ ባልተረታ መንፈሳቸው አበጀ በለውን “ሕዝቡን ያሳመጽህ ሽፍታ ነህ” ቢሉትም አበጀ ግን ሲመልስላቸው ዕውነቱን ያግታቸው ነበር።
ሥልጣንን በዙሪያቸው አጥረው በሥልጣን ውስጥ ተሸሽገው ድሀ የሚዘርፉትን፣ ድሀ የሚቀሙትን፣ በራሳቸው ወንጀል ድሀ አስረው የሚገድሉትን ግፈኞች ሽፍቶች እቃወም ነበር እንጂ ሽፍታ አልነበርሁም። እቤቴ ተቀምጨ ባለሥልጣኖች የሚሠሩትን ግፍ በሕግ ለመቃወም ስላልቻልሁ ቤቴን ትቼ መሰደዴ ሽፍታ አያሰኘኝም። አብረውኝ ሰባት ዓመት በዱር በገደሉ የተንከራተቱት ብዙዎች ስለሆኑ አንዱን በአጋጣሚ አግኝተው ቢጠይቁት እንኳን የሰው የከብት ደም ሲፈስ ማየት የማልወድ መሆኔን ይነግርዎታል። ደም ሲፈስ ከማየቱም ደግሞ የድሀ ሕይወትና ንብረት እንዲጠበቅበት የተሠራው ሕግና የተሰጠው ሥልጣን ተጣሞና ተቆልምሞ ለድሀ ሕይወት ማጥፊያ፣ ለንብረት መዝረፊያ፣ ለአመጽ መፈጸሚያ ሲሆን ማየት ከሁሉ የበለጠ ያስጠላኛል፤ በጣም ያነገፈግፈኛል፡፡” እያለ የልቡን ይነግራቸዋል። ይህም በገሃዱ አለም የሚታዩ ለህዝብ ሲሉ የሚታገሉ ሰዎችን ያስታውሰናል።
ነጋዴው ዓሊ ጅብሪል በበኩሉ የንግድ ሥነ ምግባር የሌለውና ለህዝቡ ሲሉ በሚታገሉ ግለሰቦች ጋር አንድ አገር ላይ የሚኖር አስከፊ ሰው ነው። “የገበያ ሽብር ለሌባ ይበጃል” እንደሚባለው ሁሉ የንግድ ሥነ ምግባር ሲጠፋ ነጋዴዎች ሁሉ ሕጋውያን ቀማኞች ይሆናሉ። በዛብህ አዲስ አበባ ወደጉለሌ ሲሄድ ሁለት የጎጃም ነጋዴዎች ሲነጋገሩ ያደመጣቸውን እናንሳ “አሁንኮ ዐሊ ጅብሪ ቆዳችንን መዝንልንና ዋጋ እንነጋገር ብንለው አንድ ጊዜ ‘ሚዛኑ ተሰብሯል፤’ አንድ ጊዜ ‘መዛኙ ታሟል’ እያለ ዛሬ ነገ የሚለን ፋሲካ እስኪደርስለት ነው፡፡” አለ አንዱ ነጋዴ። “ፋሲካ ሚዛን ይሆናል ወይስ መዛኝ?” አለ ሁለተኛው፡፡ “የለም ‘ዛሬ ነገ እያልሁ ፋሲጋ እስኪለግት ካቆየኋቸው ለማጫረት ጊዜ ያጥራቸውና በርካሽ ዋጋ ጥለውልኝ ይሄዳሉ’ ብሎ ነው እንጂ።” እያሉ ስለ ዓሊ መጥፎ ስነምግባር አውርተዋል። ይህም ዝም ብሎ ከመጻህፉ ውስጥ የተገኘ አይደለም እነደውም የዘመናችንን የዘመናችንን የንግድ መንፈስ የሚወክል ይመስላል።
የቦጋለ መብራቱን ቻይነት
ቦጋለ ትዕግስተኛና ቻይ በመሆኑ ደግሞ ለትዳሩ መቆም አቅም ሰጠው። ችግር ሳይሸነፉለት ሲለምዱት ከእርሱ ጋር እየታገሉ እየወደቁ እየተነሡ ሲኖሩ ጥሩ ነው። ከችግር ጋር ሲታገል የኖረ ቆዳው ይወፍራል፤ ጅማቱ ይጠነክራል፤ ጡንቻው ይደነድናል፤ የተጣለበትን ሸክም ሁሉ መሸከም ይችላል፤ የገጠመውን ሁሉ ያሸንፋል። ስለዚህ እድሜ ላሳዳጊያቸው፣ እድሜ ለአስተማሪያቸው፣ እድሜ ለችግር፣ ቦጋለ መብራቱን ቆዳቸውን አወፍሮ፣ ጅማታቸውን አጠንክሮ ትግል እያስተማረ አደንድኗቸዋል። ስድብና ቁጣ፣ የንቀትና የግልምጫ ውሽንፍር እንዳይገባቸው አድርጎ ሁሉን እንዳመሉ እንዲችሉ አድርጎ ላነፃቸው ለቀረጻቸው እድሜ ለችግር አቶ ቦጋለ ሁሉንም ቻይ ነበሩ። ይህ የአቶ ቦጋለ መቻል ትዕግሥታቸውና መሸነፍን እንደውርደት አለመቁጠራቸው ከእመት ውድነሽ ይቅር ባይነት ጋር የተቆጡበትንና ምርር ብለው ያለቀሱበትን ቶሎ የሚረሱ ከመሆናቸው ጋር አንድ ላይ ሆኖ ጠቅሟቸዋል። ይህም ጊዜ ባለፈ መጠን ባልና ሚስት እንዲቻቻሉ፣ ባሕርይ ለባሕርይ እንዲተዋወቁ፣ ለፍሬ እንዲበቁ ‘ማን አለው? ማን አላት?’ እየተባባሉ እንዲተሳሰቡ አድርጎ ትዳራቸውን አጸናላቸው። በዚህ ገጸባህሪም ውስጥ በትዳር እና በማህበረሰብ ውስጥ የትዕግስትንና የጽናትን ተምሳሌትነት መማር እነደሚቻል አጥኚው ያስረዳሉ።
የቀኛዝማች አካሉ <<ጽርየት>> (ለሌሎች ክብር መኖር)
ቀኛዝማች አካሉ ፊታውራሪ መሸሻን በጣም ይወዷቸዋል። ትውልዳቸውም እኩል ነው። ፊታውራሪ መሸሻና የፊታውራሪ አሰጌ ግጭት በሆነ ጊዜ ደግሞ ቀኛዝማች የራሳቸውን ክብር ረስተው የፊታውራሪ አገልጋያቸው ለመሆን የቆረጡ ሰው መሆናቸው በሰው ሁሉ ዘንድ የታወቀ ባይሆን ኖሮ የመሰንበቻው ሁኔታቸው የፊታውራሪ አሰጌ ወገን አስመስሎ ባስጠረጠራቸው ነበር። በወሬው ሁሉ የፊታውራሪ መሸሻ ጀግንነትና የፊታውራሪ አሰጌ ፈሪነት ሲነሣ ጥርሳቸው ሌሎችን ለመምሰል ያክል ቢስቅም ግንባራቸው ሲቋጠር ወይም አንዳንድ ምክንያት ፈጥረው ከዘመድ መሐል ተነሥተው ሲወጡ ወይም ሌሎቹ የሚያደርጉትን ሁሉ በማድረግና ባለማድረግ መሐከል መቁረጥ አቅቷቸው ሲያመነቱ ይታዩ ነበር።
ምክንያቱ ሌሎቹ የማያውቁትን የፊታውራሪ አሰጌ ፈሪ አለመሆን እርሳቸው ያውቁ ስለነበረ ነው። ነገር ግን ተነስተው ዘራፍ አላሉም። ይህም ለሌሎች ክብር መኖር የመሰለ ህይወትን ያሳየናል። አቶ ምንዋጋው ሲያጠቃልሉም በአጠቃላይ ፍቅር እስከመቃብር ላይ ያሉ ገጸባህሪያትን ብንመለከት የአሁኑ ዘመንም የማህበረሰቡ ነጸብራቅ ሆነው እናገኛቸዋለን። የሐዲስን ማኅበራዊ ሂስ በታላላቆቹ ገጸባህሪያት ብቻ ሳይሆን በታናናሾቹም ላይ የሚያሳይ በመሆኑ ለዘመናት ቢነገርለት የማይሰለች ልብወለድ ነው። በመሆኑም ሐዲስ በስራቸው ለማህበረሰቡ መስታወት ሆነዋል።







የመንዝ ምድር የእርቅ ማዕድ


እንኳን ሰው ይቅርና እግር እና እግር ይጋጫል እንደሚሉ አበው በሰው ልጅ የዕለት ተዕለት ህይወት አለመግባባት ሊከሰት ይችላል። ግጭት ካልበረደ ደግሞ አካላዊ፣ስነልቦናዊ እና ቁሳዊ ጉዳት ብቻ ሳይሆን ክቡር የሆነዉን የሰዉ ልጅም ለሞት፣ ለንግልትና ስደት የመዳረግ አቅም አለው። አሁን ባለንበት ዘመን ደግሞ በታዳጊ አገራት ላይ የሚነሱ የጎሳ ግጭቶች እና የግል ጸቦች እየሰፉ ሄደው ኑሮን ሲያቃውሱ ይስተዋላል። ይህ ቢሆንም ቅሉ በተቃራኒዉ ደግሞ እጅግ የጎለበቱ እና በማህበረሰቡ መልካም እሴቶች ላይ የተመሰረቱ እድሜ ጠገብ የግጭት አፈታት ተቋማትና ዘዴዎች በኢትዮጵያ ይገኛሉ።
ልክ በኦሮሚያ ጃርሱማ እና ገዳ ስርአት፣ በወሎ አባጋር እና ቅሬ፣ በትግራይ ዕርቂ እንደርታ እና ቃንጪ፣ በጉራጌ ኪቻ፣ በጋምቤላ አኝዋ ኦኩድሆ፣ በአፋር ሚዳ እንዲሁም በአማራ ሽምግልና፣ ደም አዳራቂ፣ ዘመድ ዳኛ፣ አዉጫጭኝ እና ወፋ የሚባሉ የእርቅ አይነቶች ለመዘናት ግጭቶችን በማድረቅ ለአርሶአደሩ እፎይታን ሲሰጡ የቆዩ ባለውለታ ናቸው። በአማራ ክልል መንዝ ቀያ ገብርኤል ወረዳ ያሉ የተለያዩ ባህላዊ ስርዓቶችም ግጭትን የሚከላከሉ፣ ከተከሰተ ብኋላ የሚፈቱ እና ከስሩ የሚያደርቁ በመሆናቸው ኢትዮጵያን ሀገር በቀል የግጭት አፈታት ስረዓቶች ባለቤት ካደረጓት ባህሎች መካከል ናቸው።
በወሎ ዩኒቨርሲቲ ፖለቲካል ሳይንስና አለምአቀፍ ግንኙነት ትምህርት ክፍል መምህሩ አቶ ጋሻዉ አይፈራም በተለይ በመንዝ የተለያዩ ቦታወች ማለትም በጃማን፣ በመርሀቤቴን፣ በጅሁር እና የላይኛዉም የመንዝ ክፍል የሚያገናኝ ታሪካዊ ቦታ በሆነው በዘረት የሀገር በቀል ግጭት አፈታት ላይ ጥናት አድርገዋል። ቅሬ ፣ የዘመድ ዳኛ፣ ወፋ፣ አውጫጭኝ ወይም አፍርሳታ የተባሉ የግጭት አፈታት ስረዓቶች በአካባቢው የተለመዱ መሆናቸው ይገልጻሉ። እያንዳንዳቸውንም የግጭት ማክሰሚያ ስርዓቶች በተናጠል ያስቃኙናል።
ቅሬ ዳኝነት
አቶ ጋሻው እንደሚያስረዱት፤ በአካባቢው የሚገኙ እያንዳንዱ አጥቢያዎች የየራሳቸው ቅሬ አላቸዉ። ቅሬ ማለት የየመንደሩ የፍትህ ሸንጎ እንደማለት ሲሆን በመንደሩ የተከበረ አንድ ሰው ዳኛ የደርጎ ይሰየማል። ቅሬዉ በሚሰበሰብበት ወር በገባ በ 12 በመሆኑ በደል የደረሰበት ሰዉ ጉዳዩን ዳኛው ፊት ቀርቦ ያስረዳል። የፍትህ ስርዓቱ ማህበረሰቡን አሳታፊ በመሆኑ ተከሳሽም የቅሬዉ ዳኛ ፊት ይቀርብና የተሰበሰበዉ ህዝብም ሀሳብ እንዲሰነዝር ይደረጋል። በመጨረሻም ዳኛው ግራ ቀኙን ካዳመጠ በኋላ በመንደሩ ህገደንብ መሰረት ብይኑን ያሳርፋል።
በዚህ መንገድ የሚፈቱ ችግሮች ጥቃቅን ሲሆኑ የሰው ህይወት የጠፋበት እና ከባድ ግጭቶት ያሉትን ለመፍታት አይችሉም። ተበዳይም ፍትሕ በማግኘቱ ተደስቶ እርሻ ስራውን ያለስጋት ይቀጥላል። ብዙ ጊዜ ቅጣቱም አንድ እንስራ ጠላ እና ድፎ ዳቦ ለቀጣዩ ወር ቅሬ ሲሰበሰብ በማምጣት ባለቅሬዉ እንዲቋደስና ማድረግ ነው። ይህም አነስተኛ ግጭቶች ወደከፋ ረብሻ እና የሰው ህይወት መጥፋት እንዳያመሩ ይከላከላል።
የሽምግልና ውሳኔዎችን ለማስፈጸም ደግሞ የዘመድ ዳኛ ይሰየማል። የዘመድ ዳኛ ሁለት አይነት ሲሆን አንደኛዉ የነገር አባት የሚባል ነዉ። የነገር አባት ማለት አንድ ግጭት ከተፈጠረ በኋላ በሽማግሌ የተወሰነን ዉሳኔ የሚይዝ እና ወደፊት እንዳይጣሉ የተጣለባቸዉን ገደብ እንዳይተላለፉ የሚቆጣጠር ነው። በግጭቱ ለተሳሰፉ ሁለቱም ወገኖች እንደ ቅርብ ዘመድ በመሆን የተጣለባቸውን ኃላፊነት ሁሉ ያስፈጽማል። ተከሳሽ የተወሰነበትን ቀላል ቅጣት አልቀበልም ካለ ግን ከቅሬዉ ብሎም ከአጥቢያዉ እስከ መዉጣት የሚያደርስ ዉሳኔ ይወሰንበታል።
የዘመድ ዳኛ
የመጀመሪያው የዘመድ ዳኛ የፍትህ አስፈጻሚ ቢሆንም ሁለተኛዉ ዘመድ ዳኛ በአይነቱ የተለየ ነው። የአንድ የዘር ግንድ አካል የሆኑ ዘመዳሞችን የሚዳኙበት ስርዓት ነዉ። የተቋቋመዉ ሰዉ በትምህርት እና በስራ ከቦታ ቦታ ሲዘዋወር አዉቆም ሆነ ሳያዉቅ ከዘመድ አዝማድ ጋር ጋብቻ እየመሰረተ በመሆኑ ይሄ ደግሞ ከታወቀ በኋላ ፍታ አትፍታ የሚል ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀዉስ ስለሚፈጥር ችግሩን ቀድሞ ለመከላከል የታሰበ ነዉ። በመሆኑ የዘረት፣ የሾላ፣ የጎየት፣የጎሽ፣የሻህ ዝርያ እየተባለ የዘመድ ዳኞች ተቋቁመው ተመሳሳይ ችግሮች ወደግጭት እንዳመሩ ይከላከላሉ። በየወሩ በቤተክርስቲያን ማርገጃ ተሰብስበዉ ልጅህ ልጅሽ የት ነዉ የት ናት በማለት ይመካከራሉ። ይህም በአካባቢዉ ያለዉል ለዝምድና የሚሰጠዉን ትኩረት ከትውልድ ወደ ትዉልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ ነዉ። ዝምድናን አፍርሶ ማግባት ግጭትን ብቻ ሳይሆን መገለልን፣ መረገምን፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ቀዉስ ስለሚፈጥር ይህ መቋቋሙ ግጭቱን ቀድሞ ለማኮላሸት ይጠቅማል።
ወፋ
ወፋ ሌላኛዉ የግጭት መፍቻ ስርዓት ነዉ። ወፋ ከጥንቆላ ጋር የተያያዘ ሲሆን በኢትዮጵያ በተለያዩ አካባቢዎች የተለያዩ ወፋዎች ሲኖሩ ለአብነት በዘረት እና አካባቢዉ ያሉ ወፋ ነገሰ ፣ ወፋ ዘነበ ክምር ድንጋይ እንዲሁም አንባት ይባላሉ። እነዚህ ወፋዎች በመንፈስ እንደሚፈርዱ ቅሬታ አቅራቢዎች ያምናሉ። ወፋ አጋፋሪ ሲኖረዉ አጋፋሪዉ ሰዎችን ሲመጡ መቀበል፣ መመዝገብ፣ የጉባኤ ቀንና ሰአቱን ማሳወቅ፣ ፍርድ የሚሹ ወደ ወፋዉ እንዲገቡ ማድረግ ሀላፊነቶቹ ናቸዉ። ለፍርድ የመጡ ደጅ ጠኚዎች ደግሞ የታዘዙትን በመፈጸም የፍርድ ሂደታቸዉን ይከታተላሉ።
ለወፋ የሚቀርቡት ሁሉንም አይነት የሲቪል እና ክሪሚናል ጉዳይ ያዩ ክሶች ሲሆን በተለይ ጭለማን ተገን ተደርጎ የተሰራ ድርጊት ማለትም ስርቆት፣ ነፍስ መግደል በብዛት ይቀርቡበታል። ለአብነት ያህል ያደራ ገንዘብ፣ የቤተሰብ ጉዳይ፣ ሽርክና፣የነጋዴ ጉዳይ ፣ የምርት ጉዳይ፣ ግድያ ፣ቅሚያ ወይም ዝርፊያ፣ የቤት እና ክምር ቃጠሎ ጉዳዮች በብዛት ወደ ወፋው ያመራሉ። የፍርድ ሂደቱም በጉባኤ የሚከወን ሲሆን የራሱ የተመደበለት ሰአትና ቦታ አለ። የተፈረደላቸዉም ሰዎች ሰዉ ጥሩ ከተባሉ መጥሪያ ይዘዉ ሄደዉ ይጠራሉ።
ሰዉየዉ ካልመጣ ጧፍ አስረዉ ይሄዳሉ። ጧፍ ሲታሰርም ተከሳሽ ላይ ችግረ ይመጣል ተብሎ ይታሰባለ። የጧፍ አሳሪዉ ቤተሰብ እርቅ እሰኪወርድ ከጠላቱ ቤተሰብ ጋር አብሮ መዋል፣ ማደር፣ መብላት አይችልምምክንያቱም ጧፍ ያሰረ ከተከሳሽ ጋር ከበላ መአት ይወርድበታል ተብሎ ይታሰባል። ነገር ግን ተከሰሰው ሰው ጧፉን ሄደህ አስፈታ ሲባል ወፋው ጋር ሄዶ ጥፋቱን ካመነ እርቅ ይወርዳል። በሌላ በኩል ሁለት ሰዎች ያልተግባቡበት ጉዳይ ካለ እና ወደ ግጭት እንዳያመራ ከታሰበ ወፋው ጋር ተያይዘው እንዲሄዱ ይደረጋል። በዚህ ወቅት ሁለቱን ሰዎች እንደ ቋረ አስተሳስረዉ ይልኳቸዋል። ወፋዉ ከፈረደላቸዉ ኋላ ከደጅ ተኚዎች ሽማግሌ መርጣችሁ ታዩ ካለ እንደተባለዉ በአጋፋሪዉ እገዛ ተሸማግለው ወደየቤታቸው ያመራሉ። የወፋ ጥንካራ ጎወጪ ቀናሽ መሆኑ ነው። ለወፋዉ የሚከፈለዉ ክፍያ አናሳ ሲሆን ባለ ጉዳዩ በእግር ወይም በትራንስፖርት ለሚመጣበት ብቻ ነዉ ገንዘብ የሚያወጣዉ
አውጫጭኝ ወይም አፍርሳታ
ተበዳይ ማን በደደል እንደፈጸመበት በውል በማያውቅበት ወቅት አንዱ ጎረቤቱ ላይ ያለአግባብ ጣቱን ሊቀስር ይችላል። ለአብነት አንድ አርሶአደር ከማሳው አምሽቶ ወደቤቱ በሚመጣበት ወቅት ለአይን ያዝ በሚያደርግ አካባቢ ሲደርስ ወንበዴዎች የያዘውን ንብረት ዘርፈውት ቢሰወሩ ማን እንዳጠቃው አያውቅም። በዚህም ምክንያት እገሌ ነው የዘረፈኝ ወይም ያዘረፈኝ እያለ ከብዙ ጎረቤቶቹ ጋር ግጭት ውስጥ ይገባል። በዚህ ጊዜ አውጫጭኝ ይጠራና የቀዬው ህዝብ በሙሉ አንድ ጥላማ ስፍራ ላይ እንዲሰበሰብ ደረጋል። አውጫጭኝ ወይም አፍርሳታ አሁን አሁን እየቀረ የመጣ የግጭት አፈታት መፍቻ ስርዓት ቢሆንም በመንዝ አንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል።
ለአፍርሳታ የተሰበሰበው ነዋሪ ማን ያውቃል ስለጉዳዩ? እያለ ሲወያይ ከቆየ በኋላ ወንጀሉ ሲፈጸም እማኝ የነበረ ወይም ዘራፊዎቹ እነማን እንደሆኑ መረጃው ያለው ሰው ተመርጦ በህዝብ ፊት እንዲቆም ይደረጋል። በወቅቱም ዳኝነት ሊሰጥ የሚችል ሰው ይሰየምና ጉዳዩን ከእማኞች እንዲሰማ ይደረጋል። የዳኛው ስራ ሽምግልና ሲሆን “ነገርን ከስሩ ውሃን ከጥሩ” እንዲሉ እዉነትን የመፈለጊያ ጥያቄ ከተሰብሳቢዎች ዘንድ ይቀበላሉ። ተበዳይም በጭለማ የተፈጸመበትን በደል በማስረዳት ወንጀለኞቹ እንዲጠየቁለት አቤቱታውን ያሰማል። እማኞኙም እነማን ዘረፋውን እንፈጸሙ በማጋለጥ ለዳኛው ያስረዳል። በዚህ ወቅት ተጠርጣሪዎቹ በቦታው ከተገኙ ተነስተው ስለጉዳዩ እንዲያስረዱ ይጠየቃሉ። ነገር ግን በቦታው ከሌሉ በሌላ ቀን እንዲመጡ ትዕዛዝ ተጥቶ ተሰብሳቢው ይበተናል። በድጋሚ በሚጠራ ጉባኤ ላይም ተጠርጣሪዎች ቀርበው የእውነት ውሸት ምስክራቸውን እንዲሰጡ ይደረጋል። ዳኛውም ጉዳዩን ካዳመጠ በኋላ ፍርድ በመስጠት ግጭቱ እንዲበርድ ያደርጋል። ካስፈለገም ሁለቱም ወገኖች እንዲስማሙ በዳይ ላይ የካሳ ክፍያ ይጣልና ቤተሰቡም እርቀ ሰላም እንዲያወርድ አብሮ ማዕድ የመቁረስበትን ቀነ ቀጠሮ ያደርጋል። ተበዳይ የሚፈልገዉ ነገር እዉነት ብቻ ነዉ ይህንንም አቆምኩት፣ ገተርኩት፣ ረታሁት አሳመንኩት በሚል ይገልጽበታል። የሚፈለገዉ የሞራል አሸናፊነት ብቻ ነዉ። ከዚህ በኋላ ከሳሽም ዘራፊዎችም እርቅ በመፈፀም ኑሯቸውን ይቀጥላሉ።
አቶ ጋሻው እንደሚሉት፤ ሀገር በቀሎቹ የግጭት አፈታት ዘዴዎች ግጭትን ከስሩ መፍታትና ከማድረቅ ባለፈ በየአካባቢው የሚከናወኑ በመሆኑ ለአርሶአደሩ ጊዜ፣ ገንዘብ እና ጉልበት ቆጣቢ ናቸው። በተፈረደበት ሰው ላይ ቀላል የሆነ ቅጣት ስለሚጣል ህብረተሰቡን ለኢኮኖሚ ቀዉስ አይዳረጉም። በግጭት አፈታቶቹ ላይ ዋናው የሚፈለገው የሞራል አሸናፊነት በመሆኑ ይቅር ባይነት እና አብሮነት እንደገና ከመገንባት አኳያ ከመደበኛዉ የፍትህ ስርአት ይሻላሉ። በመሆኑም ከመደበኛው የፍትህ ስርዓት ጋር እያጣጠሙ እንዲቀጥሉ ማድረግ ይገባል።




ለሒሳብ መጭበርበርን የማይዳርጉን የግዕዝ ቁጥሮች

ቀዳማዊ ኃይለስላሴ በ1917 .ም ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤትን ሲመርቁ እንዲህ ብለው ነበር የሀገሩን ትምህርት ጽህፈት ቋንቋ እንደሚገባው የማያውቅ የውጭውን እማራለሁ የሚል ምሳሌው ቀዛፊ እንደሌለው ታንኳ ነው። ከኢትዮጵያን የጽህፈት ቋንቋ ደግሞ አንዱ ግዕዝ ነው። የግዕዝ ቋንቋ በምስራቅ አፍሪካዎቹ አገራት ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ላይ ከአራት ሺ ዓመት በላይ አገልግሎት የቆየ እድሜ እንዳለው መዛግብት ያስረዳሉ። የጥንት አባቶች ደግሞ ቋንቋው ጽሁፍ ብቻ ሳይሆን ቁጥርም እንዲኖረው አድርገው ለዘመናት አቆይተውታል።
እንደ መሪጌታ ልሳነወርቅ ከሆነ "የኖኅ ልጆች የሆኑትን ሴም፣ ካምና ያፌት ኣብረን እያለን ሳንበታተን ስማችን የምናስጠራበትን እስከ ሰማይ የሚደርስ ግንብ እንገንባ ብለው በምድረ ሰናኦር ያገኙትን ሰፊ ቦታ ጡብ በእሳት እየጠበሱ ጡብም ድንግያ ስለ ሆነላቸው ዓስር ክንድ ቁመት፣ ሶስት ክንድ ወርድና ሶስት ክንድ ጎድንን ያለው ጡብ ሲሰሩ ነበር፡፡ እግዚኣብሔርም የልቦናቸው መጥፎ ክፋት ተገንዝቦ እያንዳንዳቸው እንዳይስማሙ ቋንቋቸው በታተነባቸው" የሚል የመጽሃፍ ቅዱስ ታሪክ ማስረጃ አለ። የግእዝ ቋንቋ የባቢሎን ግምብ/ጥቅመ ሰናኦር/ ሲፈርስ ከነበሩት 72 ቋንቋዎች አንዱ ነው፡፡ ከዚያም በየመን እና ቀይ ባህር አድርጎ ወደ ኢትዮጵያ መጥቷል። ቋንቋ ይወለዳል ያድጋል ይሞታል እንደሚባለው ግዕዙም በኢትዮጵያ እያደገ ከአራት ሺ አመታት በፊት ጥቅም ላይ ቢውልም አሁን ላይ ቋንቋውም ሆነ ቁጥሮቹ በአዲሱ ትውልድ የማይታወቁበት ደረጃ ላይ ደርሰዋል።
የታሪክ መምህሩ አቶ ደርብ አለሙ እንደሚሉት፤ አሁን ላይ የግዕዝ ቁጥሮች በዕለት ተዕለት የህይወት ክዋኔው ውስጥ የሚጠቀም ሰው አለ ለማለት ይከብዳል። አብዛኞቹ የዓለም አገራት ታሪካቸውን በጥልቀት ተረድተው ለመሰነድ ከቃላዊ ትውፊት ለመፃፍ በሚቸገሩበት ጊዜ ኢትዮጵያ ግን ከአራት ዘመናትን ያስቆጠረውን ጽሑፋዊ መረጃ ባለቤት ሁና ቆይታለች፡፡ ዘመናት ተሻግረው እኛጋር የደረሱትን የግእዝ ቁጥሮች ምን ያህል አጥንተን ጥቅም ላይ አውለናቸዋል የሚለው ደግሞ ሌላ ጥያቄ የሚያጭር ጉዳይ ነው። ነገር ግን እነዚህ ቁጥሮች የአሁኑ ትውልድ የሚሰጡትን ጠቀሜታዎች ባለመገንዘብ የራሱን እየተወ የሌላውን ቁጥር ሲገለገል ይታያል፡፡ ድሮ የተማሩትና የቤተ ክህነት እውቀት ያላቸው ሰዎች ካልሆኑት በስተቀር የግእዝ ቁጥሮች አገልግሎት እምብዛም ነው፡፡ በተለይም የአሁኑ ትውልድ ከግእዝ ቁጥሮች ተጠቅሞ ሒሳብ ማስላት እና መጠቀም ባለመቻሉ ከቁጥሮቹ ጋር ሆድና ጀርቧ ሆኗል።
በወልቂጤ ዩኒቨርሲቲ በተዘጋጀው አራተኛው አመታዊ የግዕዝ ጉባኤ ላይ ዲያቆን ካሕሳይ አብርሃ ያቀረቡት ጥናት ደግሞ ቁጥሮቹን እንዴት ለሒሳብ ደህንነት ማዋል እንደሚቻል ያሳየ ነበር። እንደ እርሳቸው፤ የአገሮችን ዕድገት እየጨመረ በሚሄድበት በትሪልዮን፣ ኳትሪልዮን የሚጀምር የብድርና የገንዘብ ዝውውር አለ። በተጻፈው የገንዘብ መጠን ልክ ደግሞ ከቁጥሮቹ በፊትና ኋላ ተጨማሪ ቁጥር በመጻፍ ለምዝበራ በር ከፋች በመሆኑ እያንዳንዱ የገንዘብ መጠን በአሃዝና በፊደል እንዲጻፍ አስገድዷል፡፡ በአሃዝና በፊደል ለመጻፍ የሚፈጀውን ጊዜ፣ ኃይልና ቦታ ደግሞ ትልቅ ነው፡፡ ነገር ግን የግእዝ ቁጥሮች ይህን ችግር የሚቀርፉ የቀደምት አበው ፍልስፍና ጥግ የሚያሳዩ ናቸው፡፡
ዓለም እየተራቀቀች በምትሄድበት ጊዜ በሌሎች ሰዎችን ላብ መኖር የለመዱትን ኣካላት ለስርቆት እየተራቀቁ በሚሄዱበት ጊዜ ለገንዘብ ዋስትና ሲባል አንድ ነገር ተፈለሰፈ፡፡ እሱም ከገንዘብ ጋር ንክኪ ያለቸው ነገሮች በአሃዝና በፊደል ካልተጻፈ ሕጋውነዊት የሌለው መሆኑ የሚገልጽ ነው፡፡ ስለ ሆነም የገንዘብ መጠን በአሃዝና በፊደል ካልተጻፈ የሚያስተናግድ የፋይናንስ ተቋም እንደሌለ የሚታወቅ ነው፡፡ ይህ የሆነበት ዋናው ምክንያት በተጻፉት ቁጥሮች በፊት ይሁን በኋላ ቁጥር ከመጨመር አልፎ ለተጻፉትን እያንዳንዱ ቁጥሮች በመቀየርም የማጭበርበር ስራ ስለ ሚሰራበት ነው፡፡ ለምሳሌ በቼኩ የተጻፈውን የገንዘብ መጠን 3000 ብር ከሆነ የግድ በፊደል ሶስት ሺህ ብር ተብሎ መጻፍ ኣለበት፡፡
የገንዘብ ነክ ጉዳዮች በዓረብ ቁጥሮች ያለው አደጋና በግእዝ ቁጥሮች ያለው ደኅንነት በንጽጽር ለማሳየት እላይ "ሶስት ሺህ ብር" የሚለውን የገንዘብ መጠን ለአብነት መመልከት ይቻላል፡፡ ይህ የገንዘብ መጠን በግእዝ ቁጥሮች ሲጻፍ ፴፻ ሲሆን በዓረብ ደግሞ 3000 ብር ተብሎ ይጻፋል። ነገር ግን በዓረብ ቁጥር3 የነበረው ወደ ሊቀየር ይችላል፡፡ በተለይም 0 የነበረው ወደ 68 እና 9 በቀላሉ ተቀይሮ ሊጻፍ ይችላል፡፡ አልፎ ተርፎም ብዙ ዜሮዎች እየተጨመሩበት ሲሄዱ መጠኑ እያደገ ስከሚሄድ የማጭበርበሪያ መንገዱ ከግዕዙ ቁጥር ጋር ሲነጻጸር ያደገ ነው።
በአረቡ የተጻፈውን 3000 ቁጥርን ወደ 8999 ለመቀየር ይቻላል። ነገርግን ሶስት ሺ በግእዝ ሲጻፍ ፴፻ ነው የሚሆነው፡፡ ከግእዝ ቁጥሩ ላይ ቅጥያ ቢጨመርም ሌላ ቁጥር የመምሰል እድሉ ስለማይኖረው የማጭበርበር ስራው ወዲያውኑ ይጋለጣል። በተመሳሳይ በዓረብ ቁጥር 4000 የነበረውን ዜሮ በመጨመር ወደ 40‚000 ሊያድግ ይችላል፡፡ በግእዝ ቁጥሮች ግን ዜሮ የሚጨመር የለም። እንዲሁም 3000 /፴፻/ የነበረውን የገንዘብ መጠን 3001 /፴፻፩/ ተደርጎ ከተጻፈ ከፊትም ይሁን ከኋላ ማንኛውንም ቁጥር ለመጨመር አይቻልም፡፡ የግእዝ ቁጥሮች ወደ ማንም በፈለገው መልኩ የማይቀየሩ ከመሆናቸው በተጨማሪ በቁጥሮቹ ፊት ይሁን ኋላ ሌላ ቁጥር የማይጨመርላቸው በዓለማችን ልዩ ከሆኑት ቁጥሮች ስለሚመደብ ለአጭበርባሪዎቸ የተመቻቸ አይደለም።
ሌላው የግዕዝ ቋንቋ ከአረቡ ጋር ሲነጻጻር በቁጥር አነስተኛ ናቸው። በዓረብ ቁጥሮች በስድስት አሃዝ የተፃፈ በግእዝ በሶስት አሃዝ ነው የሚገለጸው፡፡ በሌላ በኩል3000 የነበረውን የገንዘብ መጠን ከፊቱ 4 ቁጥር ከጨመርንለት 43000 ይሆናል፡፡ ይህ ቁጥር በግእዝ ሲጻፍ ግን ፴፻ የነበረውም ወደ ፬፼፴፻ ስለ ሚቀየር ለማጭበርበር እድል አይሰጥም፡፡ ይህ በመሆኑ በዓረብ ቁጥሮች የሚጻፉ በመላው ዓለም የሚገኙትን የፋይናንስ ተቋሞች በገንዘብ ይሁን በሰነዶች ላይ በህትመት ይሁን በእጅ ጽሑፍ ሲዘጋጁ ለከፍተኛ የማጭበርበር ኣደጋ የተጋለጡ ናቸው፡፡
ይህ በመሆኑ የፋይናንስ ተቋሞች ከአደጋ ለማምለጥ ሲሉ የገንዘቡ መጠኑን በአሃዝና በቁጥር ለማጻፍ ተገደዋል። የግእዝን ቁጥሮች ግን ከዚህ አይነቱ የፋይናንስ አደጋ ለማምለጥ አመቺ ሆነው የተዘጋጁ ናቸው። የግእዝ ቁጥሮች ወደ ተፈለገው ቁጥር መለወጥ የማይቻል በመሆናቸው በተለይ የገንዘብ ነክ ጉዳይ ሲያጋጥም በአሃዝና በፊደል ለመጻፍ ከሚባክን ጊዜና ጉልበት እንዲሁም ከመጭበርበር ይታደጋሉ። ምክንያቱም በዓለም ደረጃ የሚታዩትን ዘራፊዎች ምንም ቢሆን ቢራቀቁ በግእዝ ቁጥሮች ግን ሊያጭበረቡሩበት የሚችሉበት እድል ጠባብ ይሆናል። በመሆኑ የግዕዝ ቁጥር ከኢትዮጵያም አልፎ ለሌላም ዓለም የሚተርፍ ልዩ ሃብት ነው፡፡
የግእዝን ቁጥሮች በገንዘብ ደኅንነት ያላቸውን የላቀ ድርሻ ከግምት በማስገባት ለነዚህ ችግሮች የመፍትሔ አቅጣጫ በማስቀመጥ በጥቅም ላይ ለመዋል የሚያዳግት ጉዳይ አለመሆኑን አጥኚው ያስረዳሉ። እንደ እረሳቸው፣ የግእዝ ቁጥሮች በገንዘብ ደህንነት ያላቸውን ፋይዳ ከግምት በማስገባት በበለጠ ልንጠቀምባቸው ያስፈልጋል። የአስተሳሰብ ለውጥ ካለ የወላጆቻችን የግዕዙ ቁጥር ከቻይናውያን ፊደሎች በላይ አስቸጋሪ አለመሆኑንና በቁጥሮቻችን ለመጠቀም እንችላለን። የግዕዝ ቁጥሮች እስከሚለመዱ ድረስ አሁን በአሃዝና በፊደል እንደሚጻፈው ጎን ለጎን በዓረብና በግእዝ አሃዞች እየጻፉ መለማመድ ይገባል።
እንደ ዲያቆን ካሕሳይ አብርሃ ከሆነ፣ በአሁን ጊዜ ከቦንድ ሽያጭ ጀምሮ የተለያዩ ተቋማት ምርቶቻቸውን የሚያስተዋውቁበት የዘመን ኣቆጣጠር /ካላንደር/ አዘጋጅተው የኢትዮጵያን ኣቆጣጠር በግእዝ የፈረንጆቹን ደግሞ በዓረብ ቁጥሮች እየጻፉ የሚያቀርቡበት መንገድ ቁጥሮቹ እንዲለመዱ አስተዋጽኦው ቀላል አይደለም። እንደ አገር የእራሳችን ቁጥር እያለን በሌሎች አገራት ቁጥሮች መጠቀሙ ለራስ ዋጋ አለመስጠት ነውና ለጥንት አባቶቻችን ምርምር ክብር እንዲኖረን የግዕዝ ቁጥሮችን በስፋት መጠቀም ያስፈልጋል። በዋናነት ደግሞ የማንነታችን አሻራ የያዘውን የግእዝ ቁጥሮች በገንዘብ ነክ ጉዳዮችን ያለው ሁነኛ መፍትሔ ኅብረተሰቡን ተገንዝቦ እንዲጠቀምባቸው ህግ ማበጀት ያስፈልጋል፡፡

Featured post

ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጠያቂነትን በማረጋገጥ፣ የሕግ በላይነትን በማስፈን፣ መንግሥትና የስራ አስፈጻሚ አካላቱ በመሉ ለሰብአዊ መብቶች መከበር፣ መጠበቅና መሟላት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያሳዩ ልዩ ትኩረትና ክትትል ይሻል

                    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየደረጃው ያሉ የመንግስት አስፈጻሚ አካላትና ኃላፊዎች ላይ የቅርብ ክትትል በማድረግ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር አስተዋጽኦ ሊያደር...