Thursday, July 5, 2018

ባጀት መዝጊያ እና የህዝብ ክንፍ

ቀልድና ቁምነገር...
ሰሞኑን የባጀት መዝጊያ ወቅት ነው። አለቃዬ ፋይናንስ ክፍል ውስጥ ሳይወራረዱ የቀሩ ገንዘቦች ካሉ በፍጥነት እንዳሰላ አዞኛል። እርሱ ደግሞ በአንድ ሳምንት ውስጥ ሶስት ስልጠናዎችን እና አንድ ስብሰባ አዘጋጅቷል። የመስሪያ ቤቱን ባጀት ሳይሰራበት ወደ መንግስት ካዝና ከሚገባ በስልጠናና በስብሰባ ምክንያት እምሽክ ላድርገው ብሎ የተነሳ ይመስላል።
ለባጀት መዝጊያ ታስበው ከተዘጋጁ መርሃ ግብሮች መካከል ደግሞ አንደኛው <<የሰራተኞች የፌስቡክ አጠቃቀምና የአዲስ አበባ የህዝብ ክንፍ አባላት ተሳትፎ>> የሚል ነበር። የስልጠና ቦታው ደግሞ አርባምንጭ ነው። ይሄኛው ልክ ባለፈው ጥር ወር ላይ አዳማ በሄድኩ ወቅት ከሰማሁት ታሪክ ጋር ይመሳሰላል። ጓደኛዬ እንደነገረኝ የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ስብሰባውን አዳማ ከተማ ላይ አድርጎ <<የክፍለ ከተማው የቆሻሻ አወጋገድ የመንግስት ተሳትፎ>> በሚል የህዝብ ክንፍ የተባሉ ሰዎችን ጠርቶ ሲያወያይ ነበር። በመጀመሪያ ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ስብሰባውን አዳማ ከተማ ላይ ማድረጉ ለምን እንዳስፈለገ ሲደንቀኝ ከህዝብ ክንፍ ጋር እየተወያዩ መሆኑ ደግሞ ሌላ ግርምት ጭሮብኛል።
በአዳራሹ አንድም ክንፍ ያለው ሰው ስላልታየ ጓደኛዬ አይኑን የአዳራሹ ጣሪያ ላይ ቢያንጋጥጥ ምንም አላገኘም። ኋላማ ሲሰማ ባለክንፎቹ ወንበር ላይ ኮታቸውን ለብሰው ቁጭ ብለዋል። ህዝብ ግን ክንፍ አለው እንዴ? እረ እኔንጃ የቂርቆስ ህዝብ ክንፍ የለውም እኮ፤ በመሆኑ የህዝብ አይንና ጆሮ ቢባሉ ሰዎቹ የተሻለ ስያሜ ይሆንላቸው ነበር። የሆነ ሆኖ የአዳማው የቂርቆሶቹ ስብሰባ አመሻሹ ላይ ሲጠናቀቅ ቆሻሻ ላይ ሊሰሩ ይገባል በሚል ባለአስር ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥቶ መበተኑን እኔም ሰምቻለሁ።
የእኛም ስልጠና አርባ ምንጭ በሚገኝ ም የመሰለ ሆቴል ውስጥ ለአንድ ቀን የሚካሄድ ነው። ለስልጠናው 80 ተሳታፊዎች እንዲገኙ ጥሪ ተደርጓል። ለዚህ ስልጠና ብቻ ለምግብና ለትራንስፖርት ተብሎ ምናለፋችሁ አንድ ሁለት ሚሉዮን ብር ይመደባል። ስልጠናው ደግሞ የህዝብ ክንፍ አባላቱ ንቁ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ቀደም ብሎ ሌላ ስልጠና ይሰጠን ሲሉ” ነበር። ሰዎቹን “የህዝብ ክንፍ” ያላቸው ሰው ግን የመብረር አላማ ያለው መሆን አለበት። እነርሱን የህዝብ ተወካይ ቢላቸው ኖሮ እንዲህም በየመስሪያ ቤቱ ባጀት መዝጊያ ሲደርስ በተጠሩ ቁጥር እየበረሩ አይሄዱም ነበር። ምን አለፋችሁ አንዳቸውም ይህ ርዕስ ምን ጥቅም አለው? ብለው አልጠየቁም። ምክንያቱም ባጀት መዝጊያ ነእነርሱም በክንፋቸው ይዘው የሚመለሱት ሲሳይ ይደርሳቸዋል። ደግሞም ርዕስ ይገኝ ብቻ እንጂ የትኛውም ቢሆን ተመራጭ ነው በዚህ ወቅት
ርዕሰ ጉዳዩ እንኳን ለሙሉ ቀን ስጠና ሊያበቃ ቀርቶ ሁሉም በሚሰራበት ቦታ ላይ አጠር ያለች መግለጫ ቢሰጠው ሊረዳው የሚችል ነበር። ነገር ግን ጠዋት ሶስት ሰዓት ተኩል የተጀመረው ስጠና ተብዬ ስድስት ሰዓት ላይ ለምሳ ተብሎ ሲበተን ሁሉም ለሶስ ቀን የተዘጋጀውን መመዝገቢያ ላይ ፊርማውን አስፍሮ ወደየማረፊያው እብስ ሲል እኔም አብሬ እብስ አልኩ። በኋላ እደሰማሁት ከሰዓት በኋላ የተወሰኑ ተሰብሳቢዎች የህዝብ ክንፎቹን ጨምሮ በአዳራ ተገናኝተው አስተየያየት ሲሰጡ እና ልምዳቸውን ሲያካፍሉ አልፎ አልፎም የቀረበው ጥናት ልክ አይደለም በዚህ መልክ ቢቀርብ ጥሩ ነበር” እያሉ ሲነታረኩ ዋሉ። የህዝብ ክንፍ ነን ያሉ ሰዎችም “ለህብረተሰቡ በፌስቡክ ጭምር አገልግሎት ሊቀርብለት ይገባል” እያሉ ተሳታፊውን ሲያስቁት አመሹ። አስራአንድ ሰዓት ገደማ ላይ ቢበቃን ይሻላል” በሚል የአለቃ ሃሳብ እና የመዝጊያ ዲስኩር ተደምድሞ ሁሉም ሲቋምጥለት ወደነበረው የአበል ክፍያ አመራ።
ሁሉም ተሳታፊ ለእያንዳንዱ የምሳ ወጪ እና የአበል ክፍያው በገንዘብ ተሰልቶ ተሰራለት። የህዝብ ክንፍ ነን ባዮች ግን “እኛ የወከልነው የከተማውን ህዝብ በመሆኑ ብሎም ደግሞ ባጀት መዝጊያ በመሆኑ ለምን አበላችን ያንሳል” በሚል ጉርምርምታ ውስጥ ገቡ። የዚህን ጊዜ አለቃዬ እንኳንም ዘንቦብሽ… ነውና “ባጀት ሲዘጋ ብር ተርፎ ወደመንግስት ካዝና መመለሱ ስለማይቀር ስትመለሱ አዲስ አበባ እንጨምርላችኋለን” ብሎ አረጋግቶ ሸኛቸው።
የእኛ መስሪያ ቤት የባጀት መዝጊያ ሁለተኛ ስልጠና ደግሞ ጉዳዩ ስለችግኝ ተከላ እና በዙሪያው ያሉ የአካባቢ ጥበቃ ጉዳዮች ላይ ያተኮረ ነው። ነገር ግን ለስልጠናው የተመረጠው ቦታ አፋር ነበር። አለቃዬ ከዚህ በፊት አፋርን አይቷት አያውቅም መሰለኝ አፋር እኮ ለችግኝ ተከላ ስልጠና አይሆንም ቢባል “አፋር ብያለሁ ለስልጠናው ጥሩ ቦታ ነው” ብሎ ሙጭጭ አለ። ሰልጣኞቹ ደግሞ የሶስት ክፍለ ከተማ የህዝብ ክንፍ አባላት ተብዬዎች ናቸው። በተጨማሪነት የሎተሪ አዟሪዎች እና የመስሪያ ቤታችን አስተዳደር ሃላፊዎች እንዲሳተፉ ተመርጠዋል። አለቃዬ የህዝብ ክንፍ ነን ያሉ ሰዎች ህዝብ እንዴት አይነት ችግኝ ተከላ ይወዳል? የሚለውን ሃሳብ ሊያቀርቡ እንደሚገባ መመሪያ ሰጥቷቸው ወደ ስልጠናው ይጓዛሉ።
ሶስተኛው ስልጠና ስለመስሪያ ቤቱ የህንጻ ደህንነት እና አደጋ መከላከል ላይ ያተኮረ ቢሆንም ቦታው ደግሞ የተመረጠው ሐዋሳ በሚገኘው የሐይሌ ሪዞርት ነበር። ለዚህ ስልጠና ከመስሪያ ቤቱ 150 ሰራተኞች መካከል 90ናው ተመልምለዋል። በዚህ አይነት ሰራተኛው ሲሄድ እና ሲመለስ እንግዲ ሳምንቱን ሙሉ ስራ ላይኖር ነው ማለት ነው። የማይቀሩት አስር የሚደርሱ የህዝብ ክንፎች ነን ያሉም አሉ።
ስለመስሪያ ቤታችን የህንጻ ደህንነት ስልጠና ለመውሰድ ሐዋሳ መኬዱ ያልጣማቸው አዛውንቱ አቶ አሸናፊ ለዚ ለዚ ምን አለፋቸው ስለአገሪቷ ህንጻዎች ደህንነት ነው የምናሰለጥናችሁ ብለው አገር አቀፍ ቢያደርጉን ይሻል ነበር ብለው አሸሞሩ። የህዝብ ክንፎችም ስላሉ ነው ሲባሉ ደግሞ እነሱማ መብረር ስለሚችሉ አደጋ ቢደርስም አይጎዱም ስልጠና አያስፈልጋቸውም ብለው አከሉበት። እውነታቸውን ነው ክንፍ ያለው ህጻ ቢደረመስ እንኳን በሰማይ ይበራል እንጂ ምን ይሆናል። አለቃዬ ደግሞ “ቸው ይሳተፉ ምን አለበት ባጀት መዝጊያ ነው እኮ አንድ ሚሊዮን ብር ተመድቧል አታስቡ እንጂ” እያለ አቅራራ።
የመጨረኛው የሳምንቱ የባጀት መዝጊያው ስብሰባ ደግሞ በአዳማ ከተማ የሚካሄድ ሲሆን ቅድመ ዝግጅቱም ሆነ የሆቴል መረጣው ቀድም ብሎ ተፈጻጽሟል። ኢንተርናሽናል ኮንፈረንስ የሚል ታርጋ የተለጠፈለት በመሆኑ የባጀት መጠኑም ሆነ የህዝብ ክንፍ ተብዬዎች ተሳታፊ ቁጥር አያሌ እንደሚሆን ይገመታል። እስከአሁን ድረስ ብቻ 500 ተሳታፊዎች እንዲገኙ በደብዳቤ ጥሪ እንዲደረግ ታዟል። የህዝብ ክንፎቹ ማን እንደመረጣቸው ባላውቅም እየተጠራሩ መጥተው የመግቢያ የጥሪ ወረቀቶችን አጽፈው ወሰዱ። አለቃዬ የመጡት ሁሉ ይውሰዱ የሚል መመሪያ አስተላልፎ ስለነበር 80 ሰዎች በክንፍነት ተመዝግበዋል። ይሄንጊዜ 'የአዲስ አበባ ህዝብ ክንፍ አለህ?' ተብሎ ቢጠየቅ 'እንኳን ክንፍ ሊኖረኝ በየቦታው የምሰለፍበት እግሬም እየተወላገደ ነው' ማለቱ አይቀርም መቼም ብዬ አሰብኩ። የስብሰባው ርዕስ ደግሞ <<አለም አቀፉ ያለፉት ጉባኤዎቻችችን ግምገማ>> የሚል ነው። ይሄን ስሰማ አለቃዬ ፊት ከት ብዬ ስቄያለሁ። ያለፉት ጉባኤዎች የትኞቹ ይሁኑ የት የተካሄዱት ተሰብሳቢዎቹም አያውቁም ብቻ ባጀት መዝጊያ በመሆኑ ለሶስት ቀናት መሰብሰባችን አይቀርም
ይሄ ባጀት ግን የህዝብ ክንፍ ተሳትፎም ተጨምሮበት ሊያልቅ አልቻለም። ታዲያ አስሩን በስልጠና እና በተለያዩ ጉዳዮች ስናወጣ ስናወርድ ካቃለልነው በኋላ አምስት ሚሊዮን ብሩ ተረፈ። ወዴት እናድርገው እባካኝሁ” እያለ አለቃዬ በየደቂቃው ቢሮዬ ይመጣል። አለቃዬን አስሩንም ክፍለ ከተሞች የህዝብ ክንፍ አባላት ሰብስበን እስካሁን የት የት ድረስ በራችኋል ብለን ስልጠና እንሰጣቸው እንዴ ብዬ ልቀልድበት አሰብኩና ይህችንም ደግሞ ስልጠና እንዳያደርጋት ሰግቼ ተውኩት። እባካችሁ እናንተዬ ይህችን አምስት ሚሊዮን ብር ወዴት እናድርጋት? እስቲ ሃሳብ አምጡ። መቼም አለቃዬ ብር ወደመንግስት ካዝና ከመመለስ መሞት ይመርጣል፤ ካልሆነ የሰፈሩን ሰው ጠርተን ክንፍ የሆናችሁ ደሞዝ እንከፍላለን እንበል እንዴ? ምክንያቱም ባጀት መዝጊያ ነዋ።





No comments:

Post a Comment

Featured post

ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጠያቂነትን በማረጋገጥ፣ የሕግ በላይነትን በማስፈን፣ መንግሥትና የስራ አስፈጻሚ አካላቱ በመሉ ለሰብአዊ መብቶች መከበር፣ መጠበቅና መሟላት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያሳዩ ልዩ ትኩረትና ክትትል ይሻል

                    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየደረጃው ያሉ የመንግስት አስፈጻሚ አካላትና ኃላፊዎች ላይ የቅርብ ክትትል በማድረግ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር አስተዋጽኦ ሊያደር...