Thursday, July 5, 2018

ሱሪው

አዛውንቱ እጃቸው ላይ ብር አጥሯቸዋል። በመሆኑም ሳምንቱን ሙሉ የት እንደሚያመሹ ግራ ገብቷቸዋል። እናም ካላቸው ሁለት ሱሪዎቸ መካከል የጓደኛቸው ልጅ ከውጭ አገረ ያመጣላቸውን ሱሪ አስቀርተው ሌላኛውን ሱሪ ለሰፈራቸው ልብስ በ70 ብር የሸጣሉ። በአስር በሩም የደንቡን ሶስት ብርሌ ጠጅ በላይ በላዩ ገልብጠው እያጋሱ ወደቤታቸው ይመለሳሉ። በእለተ ቅዳሜ 10 ሰዓት ገደማ የወጡት አቶ አበበ በጊዜ ወደቤታቸው አልተመለሱም። ምክንያቱም ድንገት በመንገድ ላይ እያሉ እጃቸውን ወደኪሳቸው ቢሰዱ 60 ባውንዳቸው የውሃ ሽታ ሆኖባቸዋል። ከጠጅ ቤቱ ወደቤታቸው እስኪጓዙ ድረስ ግማሽ መንገዳቸውን ቢያገባድዱም የረገጧትን መንገድ እየተመላለሱባት አቀርቅረው ብራቸው ሱፈልጉ አንድ ሰዓት ያህል ይፈጅባቸዋል። ጨለማው በመበርታቱም ብራቸውን እንደተበሉ አሰበው እየተበሳጩ እና እየተቆናጠሩ በእግራቸው ወደቤታቸው መኳተኑን ተያይዘውታል።

የሰፈራቸውን አስፓልት መንገድ ላይ ሲደርሱ ግራ ቀኝ አማትረው እንኳን መሻገሩን እረስተው አውራጎዳናው ላይ ዘው ቢሉ ግዜ ሁለት በተቃራኒ አቅጣጫ ይጓዙ የነበሩ ታክሲዎቸ በአንድነት የተጠንቀቁ ጥሩንባ ድምጻቸውን አምባረቁባቸው። አቶ አበበ ይህን ጊዜ ደንገጥ ብለው መኪናዎቹን ካሳለፉ በኋላ የሰፈራቸውን የኮብልስቶብ መንገድ ተያያዙት። በፍጥነት ቤታቸው እንደደረሱ በየስርቻው ብራቸውን መፈላለጉት ቀጥለዋል። ባለቤታቸው ወይዘሮ አሰገደች ግን ምን እንደሚፈለጉ በውል ባለማወቃቸው <<አቶ አበበ ምነው ዛሬ ቆዩ ጠፉ እኮ አሁን ምን እየፈለጉ ነው>> የሚል ቀጭን ድምፃቸውን አሰሙ። በዚህ ወቅት አቶ አበበ ንዴታቸውን ባለቤታቸው ላይ ለመወጣት <<እስቲ ዝም በይ፤ ገንዘብ ጠፍቶብኝ ነው፤ ከቤት ስወጣ ኪሴ ውስጥ ነበር ስመለስ ግን የለም>> አሉ። <<ታዲያ ሲሄዱ ከነበሩ እኪስዎ ውስጠ አሁን እቤት ውስጥ መፈለጉ ምን ያደርጋል መንገድ ላይ ጥለውት ነው የሚሆነው። ለመሆኑ ምን ያህል ብር ነው>> አሉ ወይዘሮ አሰገደች።

አቶ አበበ ግን ትናንትና ማታ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው የቡና መግዣ ሲጠይቋቸው ኪሴ ውስጥ ያለው 20 ብር ብቻ ነው ማለታቸው ትዝ ስላላቸው ስንት ብር እንደጠፋቸው ለመናገር አልቻሉም። የጠፋብኝ ብር 60 ነው ቢሉ እሰይ ማታ ስጠኝ ስልህ ታዲያ ምነው ተስቆነቆንክ እንደሚባሉ ያውቁታልና ዝም ማለትን ነበር የመረጡት። <<ብዙ ብር ነው እንዴ አሉ>> ወይዘሮ አሰገደች።

አባወራው የማታውን ቅጥፈታቸውን የሚሸፍን ምክንያት ያገኙ ይመስል <<አዎ ማታ ሰው ሰጥቶኝ ነበር የሰው ብር ጠፋብኝ 60 ብር ነው። አንድ አብሮኝ የሚሰራ ጓደኛዬ ከማጠፋው አንተ ጋር ይቀመጥልኝ ብሎ ቢሰጠን እኔው አጠፋሁት እስቲ አሁን አትጨቅጭቂኝ ብሩን ብቻ ፈልጊ>> ብለው ሶፋውን ያገለባብጡ ጀመር።

የቤቱ እመቤት ግን <<አይ እዚህ እንኳን የለም እኔ ቤቱን ጠርጌ ወልውዬዋለሁ የቤቱን መረገጫ ላስቲክ ውጪ ወይ ሌባ መንትፎት ይሆናል>> ብለው ወደጓዳቸው ገቡ። ነገሩ በዚሁ ታለፈና በሶስተኛው ቀን አቶ አበበ በቤታቸው ያለውን እንደእንቁ የሚያዩትን አንድ ሱሪያቸውን አውልቀው በቁምጣ ሆነው እንዲታጠብላቸው ለቤቱ ሰራተኛ ይሰጧታል። ታዲያ ይህች ሰራተኛ ልብሱን ከማጠቧ በፊት ኪሱን መፈታተሽ ነው የመጀመሪያ ስራዋ ሁሉምን ኪሱን ፈትሻ ስትጨርስ ምንም ነገር የለም ሱሪውንም አረፋ ወደደፈቀው የሳፋ ውሃ ውስጥ ጨምራ አንዴ አሸት እንዳደረገች ግን ከወደእግሩ አካባቢ ይቆረቁራታል። ሱሪውን አውጥታ በውስጥ በኩል ብታየው ገበሩ ነጭ ነበርና ብሩን ቁልጭ አድርጎ ያሳያታል። የሱሪው ኪስ በመቀደዱ ምክንያት እግሩ ጋር የደረሰው ብር ለማውጣት እጇን የሚያሳልፍ አልሆን ቢላት የሱሪውን ስፌት በሙሉ ተርትራ 60 ብሩን አወጣችው።

ጀብዱ እንደሰራ ሰው <<ጋሽዬ ጋሽዬ እያለች ሮጣ ሱሪዎ ውስጥ ብር ተገኝቷል>> ብላ የረጠበውን ብር ሰጠቻቸው። አቶ አበበ ወዲያው የጠፋባቸው ብር እንደሆነ ገብቷቸው ደስታውን አልቻሉትም ነበር። ወይዘሮ አሰገደች ግን ሰራተኛቸው ብሩን ስታገኝ ቅድሚያ ለእርሳቸው መስጠት እንደነበረባት እያሰቡ ውስጣቸው ቂም መቋጠር ጀምሯል። ቀስ ብለው ልጅቷ የምታጥበበት በረንዳ ላይ ሄደው <<ብሩን እንዳገኘሽ መጀመሪያ ለእኔ ለምን አልሰጠሽኝም ስንት የሚገዛዛ ነገር እያለ አንቺ ደነዝ>> ብለው ወረዱባት። ልጅት የጥፋተኝነት ስሜት እየተሰማት ይቅርታ ጠይቃ አጎንብሳ ማጠቧን ቀጠለች።

አቶ አበበ እና ባለቤታቸው ከብሩ መገኘት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ፊት ለፊት ተገናኝተው አይነ ለአይን እየተያዩ ነው። <<እሰይ አሰይ በሩ ተገኘ በሉ ለእኔም ሃምሳዋን ብር ይስጡኝና የሚገዛዛውን ለቤቱ ልግዛ>> አሉ ወየዘሮዋ።

አቶ አበበ << የሰው ብር ሲገኝ ይመለስ ይባላል እንጂ እናጥፋው እንዴ ደግሞ>> እያሉ ማጉረመረም ጀምረዋል። አይ እርስዎ ደግሞ እየተዋወቅን በሉ ይስጡኝና ምሳውም ይዘገጃጅ ብለው ወይዘሮዋ ወይ ፍንክች ያባቢላዋ ልጅ አልንቀቀሳቀስ አሉ። አቶ አበበ ነገሩን ለማረሳሳት ወደውጪ ወጥተው <<ጎሽ ጎሽ እንዲህነው ልጅ በይ ሁሌም ስታጥቢ ኮቶቹን ሙሉ ለሙሉ እየፈተሽ እንድታጥቢ>> ብለው ሰራተኛዋን ማሞጋገስ ቀጠሉ። ልጅት በተሰጣት ሙገሳ ተደስታ ፈገግ እያለች <<ደግሞ እኮ እጄን አላስገባ ቢለኝ ሱሪውን በአንድ ወገን ገንጥዬ እኮ ነው ብሩን ያወጣሁት>> ብላ ግማሽ ቀሚሽ ግማሽ ሱሪ ያደረገችውን ልብስ ከአረፋው ውስጥ መዝዛ አሳየቻቸው። አቶ አበበ የሚወዱት ብቸኛ ሱሪያቸው እንዲህ ተበላሽቶ ሲያዩት ደስታቸው ሁሉ በኖ ጠፋባቸው። ምነው ምነው አንድ ሱሪዬን እንዲህ እንደ እብድ ልብስ ቀዳደድሽው ብለው ሙሾ ማውረድ እስኪቀራቸው ድረስ አለቃቀሱ።

ሱሪውን በእርጠቡ እንዳለ ተቀብለው እያገላበጡ <<ምነው ብሩ ቢቀርብኝ እና አብሮ በታጠበ የጓደኛዬ ልጅ ካማሪካ ያመጣልኝ ውድሱሪ እኮ ነው>> እያሉ ማላዘኑን ቀጠሉ። ሁኔታውን በቅርበ ርቀት ሲከታተሉ የነበሩት ወይዘሮ አሰገደች ሳቅ እየተናነቃቸው <<ምንም አይደል አንድ ሺ ብር የሚያወጣ የአማሪካ ሱሪ ቢቀደድ ውስጡ 160 ብር ስለተገኘ በ15 ብር አሰፍተው እኔ እተኩስልዎታለሁ>> እያሉ የለበጣ ማስተዛዘኑን ተያያዙት። አቶ አበበ ይህን ጊዜ <<50 ሣንቲም ዶሮ የአንድ ብር ከሃምሳ ሣንቲም ገመድ ይዛ ጠፋች እንደተባለው ነው፤ በብሩ መገኘት ደስታዬን ሳልጨርስ የባሰ አመጣብኝ>> ብለው አማረሩ። ባለቤታቸውም ካረጋጉዋቸው በኋላ አግባብተው ብሩን እንዲሰጧቸው ቤት ያፈራውን ምሳ እየተመገቡ መጠየቅ ጀመሩ።

<<በቃ አሁን የሆነው ሆኗል 15ብሯን ይዘን ለልብሱ ማሰፊያ 30ዋን ለቡና መግዣ የተረፈችውን 15 ብር ደግሞ ለኪስዎ ቆሎእንኳን ቢደፉ ይዘው ወይም ደግሞ ጠጅዎትን ይጠጡባት መቼም የደንብ ነው አይቀርም ብዬ ነው>> ብለው አከፋፈለው ጨረሷት ብራን። የዚህን ጊዜ አቶ አበበ ካፈርኩ አይመልሰኝ በሚል ስሜት የሰው የተባለችውን ብር በሂሳቡ ስሌት መሰረት ባይስማሙም 15 ብር ለባለቤታቸው ሰጥተው <<ብትፈልጊ ቡና ባትፈልጊ ሻይቅጠል ገዝተሽ ጠጪበት>> ብለው ወርውረውላቸው ወጡ።

አቶ አበበ ከነቁምጣቸው ናቸው ሱሪያቸው ተቀዷል። በዚህ ላይ እየታጠበ ነበና በውሃ የተነከረውን ልብሳቸውንም እንዳንጠለጠሉ ወደ ሰፈሩ ልብስ ሰፊው ዘንድ ገሰገሱ። ልብሰፊው ደንግጠው ምን ሆንክ እርጥብ ሱሪ ይዘህ መጣህ ቢሏቸው ነገሩን ባጭሩ አስረዷቸው። እናስ አሉ ልብስ ሰፊው አቶ አበበ ግን ፈጠን ብለው ባለፈው በ70 ብር የሸጥኩልህን ሱሪ አምጣ እና ይሄን ሰፍተህ ልብስ እኔ እራቁቴን ስሄድ እብድ ከምባል አንተ የእጅ ሙያህን ተጠቅመህ ሰፍተህ መልበስ ትችላለህ ብታተርፍ እንጂ አትከስርም ከሱሪው አንፃር ብለው እርፍ።

ልብስ ሰፊው ደግሞ እንደአጋጣሚ የለበሱት በ70 ባውንደ ከአቶ አበበ ላይ የገዙትን ቡኒ ሱሪ ነበር። እናም መረር ያለነገር ከመምጣቱ በፊት ሱሪያቸውን አውልቀው ለአቶ አበበ ሰጥተው እርጥቡን ሱሪ እስኪሰፉ እርሳቸውውም በግልገል ሱሪያቸው መሃል ሰፈራቸው ላይ ከነመኪናቸው መቀመጥ ግድ ሆነባቸው። አለም የተገላቢጦሽ ናትና ከቤት በደህና ሱሩ የወጡት ልብስ ሰፊ አሁን ላይ ግማሽ እራቁታቸውን ሲቀመጡ ግማሽ እራቁታቸውን ከቤት የወጡት አቶ አበበ ደግሞ ደህና ሱሪያቸውን አድርገው መጭ አሉ።

No comments:

Post a Comment

Featured post

ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጠያቂነትን በማረጋገጥ፣ የሕግ በላይነትን በማስፈን፣ መንግሥትና የስራ አስፈጻሚ አካላቱ በመሉ ለሰብአዊ መብቶች መከበር፣ መጠበቅና መሟላት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያሳዩ ልዩ ትኩረትና ክትትል ይሻል

                    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየደረጃው ያሉ የመንግስት አስፈጻሚ አካላትና ኃላፊዎች ላይ የቅርብ ክትትል በማድረግ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር አስተዋጽኦ ሊያደር...