ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ አብዛኛዎቹ ሐይማኖታዊም ሆነ ባህላዊ ቅርሶች በሌላው ዓለም የማይገኙ ናቸው ያሉት አቶ መቆያ፤ ግጭት ሲፈጠር ስራዬ ብሎ እነዚህን ቅርሶች ፍለጋ የሚመጣም ዘራፊ እንደሚኖር አስረድተዋል።

ህወሃት ከፈጠረው ጦርነት በላይ ቅርሶቻችን ላይ ትኩረት በማድረግ አፍጥጠው የሚጠብቁ የውጭ ዜጎች በርካታ ናቸው ሲሉ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ መቆያ ማሞ አስታወቁ።
ስራ አስኪያጁ አቶ መቆያ ማሞ፤ በሰብአዊ እርዳታ ስምም ሆነ በተከለያየ መንገድ ወደኢትዮጵያ የገቡ የውጭ ዜጎች ሁሉ አላማቸው አንድ አይደለም ይላሉ።
ከፊሉ ህወሃት የጀመረውን ጦርነት ተገን አድርገው ውድ ቅርሶቻችንን ለማሸሽ የሚጥሩ በመሆናቸው ጥብቅ ክትትል ማድረግ እንደሚገባም ነው የሚያሳስቡት።
ግጭቱም ቅርሶቹን በተለያየየ መንገድ ለማውጣት ለሚጥሩ ሰዎች ይበልጥ ምቹ ሁኔታ ይፈጠርላቸዋልና በመውጫ መግቢያዎቻችን ሁሉ አስፈላጊውን የጥንቃቄ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል ብለዋል።
የውጭ ዜጎች የኢትዮጵያን ቅርሶች ካገኙ አያልፏቸውም፤ ያጓጓቸዋል ያሉት አቶ መቆያ፤ በዚህ ጦርነት ወቅት ቅርስን ማሸሽ ብቻ አላማው አድርጎ የሚንቀሳቀስም አካል ይኖራል። ከጦርነቱ በላይ ቅርሶቻችን ላይ ትኩረት አድርገው ሁኔታውን የሚጠባበቁ የውጭ ዜጎች በርካታ መሆናቸውን ተናግረዋል።
እንደ አቶ መቆያ ገለጻ፤ በሰብአዊ ድጋፍ ስም የገቡ የውጭ ዜጎች አንዳንዶቹ ከአላማቸውም ውጪ የሚንቀሳቀሱ ናቸው። ግጭቶችን ተጠቅመው በእርዳታ ስም የማንተካቸውን ቅርሶች ለማሸሽ መሞከራቸው አይቀርም።
በተግባርም እንደታየው ከሱቅ ነው የገዛሁት ነው፤ ከዚህ ቦታ ተረክቤ ነው በማለት ቅርሶችን ይዘው ሊወጡ ሲሉ በአየር መንገድ የተያዙ በርካታ ሰዎችም አሉ በማለት ያስረዳሉ።
ይሄን አጋጣሚ ተጠቅመው ንብረቶቻችንን ለመቀባበል ከፍተኛ ዝግጅት እንዳደረጉ ይገመታል። ከዚህ አደጋ ለመዳን ሁሉም ዜጋ የየትኛውም አካባቢ ቅርስ የእራሱ ንብረት እንደሆነ በመረዳት አጠራጣሪ ነገሮችን ሲያይ አስፈላጊውን የጥንቃቄ እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል ብለዋል።
እንደ አቶ መቆያ ከሆነ፤ በእርዳታ ስም እየመጡ የሐይማኖት ተቋማትንም ሆነ በየሙዚየሞቻችን የሚገኙ ቅርሶቻችችንን እንዳያሸሹ መውጫ መግቢያዎች ላይ አስፈላጊውን ቁጥጥር ማጠናከር እንደሚገባም አሳስበዋል።
በተለይ አየር መንገድ ፍተሻዎች ላይ ሐይማኖታዊ ቅርሶችን በበቂ ሁኔታ መለየት የሚችሉ መሳሪያዎች እና ባለሙያዎችን በመመደብ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ የሚጠይቅበት ጊዜ ላይ ነን ሲሉም ሃሳባቸውን አጠናክረዋል።
ለጥንቃቄ ስራው ያደጉ ሀገራት የሰለጠኑ ውሾችንና ዘመናዊ መሳሪያዎችን ይጠቀማሉ። እኛም ባለን አቅም ልምዳቸውን ልንተገብር ይገባል። በሐይማኖት አገልግሎት ያሳለፉ ወጣቶችና በዘርፉ ልምድ ያላቸውን ምሁራንን በበቂ ሁኔታ መጠቀም ይችላል ብለዋል።