Monday, March 20, 2017

ያገለገሉ የህክምና ቁሶች መልሰው ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ምን ይደረግ?


 
የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስቴር የደረቅ ቆሻሻ አያያዝ፣ አሰባሰብና አወጋገድ ስታንዳርድ (ደረጃ) አውጥቷል። በስታንዳርዱ የትግበራ ማንዋል ቁጥር 06/2007እንደተገለጸው ደግሞ ከህክምና ተቋማት የሚመነጩ አደገኛ ቆሻሻዎችን ለማከም ወይም ለማስወገድ አነስተኛ መጠን ያለው የቆሻሻ ማቃጠያ ፋሲሊቲ በየተቋማቱ መገንባት ታሳቢ መሆን አለበት። ይህም መልሰው ጥቅም ላይ ቢውሉ ችግር ሊያመጡ የሚችሉ የህክምና መገልገያዎች ዳግም ጥቅም ላይ እንዳይውሉ ይረዳል።
በትግበራ ማንዋሉ ላይ በጀርመን ዓለም አቀፍ ትብብር ድርጅት(ጂአይዜድ) በሚደገፍ ፕሮጀክት አማካኝነት በተመረጡ ሆስፒታሎች በተደረገ ፍተሻ ከጤና ተቋማት የሚመነጭ አደገኛ ቆሻሻ አያያዝ ወጥ እና ሥርዓት ያለው አወጋገድ እንደሌለ ነው የተጠቆመው። በመሆኑም አገልግሎት የሰጡ የህክምና መሳሪያዎች ዳግም ጥቅም ላይ ቢውሉ በምን ማረጋገጥ ይቻላል? የሚለው ጥያቄ አነጋጋሪ ሆኗል።
የቤተል ቲቺንግ ጄኔራል ሆስፒታል ማኔጂንግ ዳይሬክተር ዶክተር ይገረሙ አስፋው፤ «ሌሎች የህክምና ተቋማት መወገድ ያለባቸውን የህክምና ቁሶች መልሰው ጥቅም ላይ ስለማዋላቸው ማረጋገጫ የለኝም። ይሁንና በሆስፒታላችን በኩል ግን ለአንድ ጊዜ የሚውሉትን ዳግም አገልግሎት ላይ የማዋል ችግር እንደማይከሰት ማረጋገጥ እችላለሁ» ይላሉ። በህክምና ተቋማት ውስጥ የሚገኙ መሳሪያዎች ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም የሚሰጡ እና ወዲያው መወገድ ያለባቸው እንዲሁም በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ ውለው በየጊዜው ከተህዋሲያን እንዲጸዱ የሚታከሙ መሳሪያዎች መኖራቸውንም ይጠቁማሉ።
ለአንድ ጊዜ ጥቅም ላይ የሚውሉ እንደ መርፌ እና የህክምና ጓንት የመሳሰሉት አገልግሎት ከሰጡ በኋላ በሆስፒታሉ በተዘጋጀላቸው ቦታ ላይ እስከሚቀልጡ ድረስ በከፍተኛ ሙቀት እንደሚቃጠሉ ነው የሚያስረዱት። በመሆኑም ዳግም ጥቅም ላይ ለማዋል ሙያው የማይፈቅድ እና የሰዎች ጤና ላይ የሚያደርሰው ጉዳት የከፋ በመሆኑ ተቋሙ በራሱ የማቃጠያ ቦታ እንደሚያስወግዳቸው ነው የሚገልፁት። በዚህ ረገድ ውድ የሚባሉትን መሳሪያዎች ጭምር ህጉ በሚፈቅደው መንገድ እንደሚያስወግዱ ነው የጠቆሙት። ለአብነትም ኩላሊትን ተክቶ በሚሰራ ማሽን ላይ ለአንድ ሰው የሚያገለግል መሳሪያ ጥቅም ላይ ከዋለ በኋላ ወዲያውኑ እንደሚወደግ ያስረዳሉ።
«የተለያዩ የህክምና ተቋማት ወጥነት የሌለው የቆሻሻ አወጋገድ ባለመከተላቸው የተነሳ በርካታ ያገለገሉ የህክምና መሳሪያዎች በየጓሮው ተከማችተው ይገኛሉ» የሚሉት ደግሞ በየካቲት 12 ሜዲካል ኮሌጅ ረዳት ፕሮፌሰር ዳንኤል አበበ ናቸው። በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ እየተደረገ በሚገኘው እያንዳንዱ የህክምና ተቋም ጽዱ እና ምቹ ማድረግ አላማው ያደረገ ፕሮግራም ተዘርግቷል። በመሆኑም በየተቋማቱ የተከማቹት መርፌና ጓንትን ጨምሮ የተለያዩ የህክምና ቁሶች መወገድ እንደሚገባቸው ነው የሚናገሩት።
«የህክምና መርፌዎች ከተላላፊ በሽታዎች ጋር በተያያዘ መልሰው ጥቅም ላይ መዋል የለባቸውም» የሚለውን ሃሳብ የሚደግፉት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ ይልቁንም ባለሙያዎች መርፌውን ሲከፍቱ እንኳን መሬት ላይ ቢወድቅባቸው በቆሻሻ ማጠራቀሚያ ውስጥ መጨመር እንደሚገባ ነው የሚገልፁት። ይሁንና ፕላስቲክ እና ብረት ነክ የህክምና መሳሪያዎች ማቃጠል የማይገባ በመሆኑ መቅበር እንደሚያስፈልግ ነው የሚጠቁሙት። ይህንን ሁሉም የህክምና ተቋማት በአግባቡ ይተገብሩታል የሚለው ጉዳይ ላይ ግን እርግጠኛ እንደማይሆኑ ነው የሚናገሩት።
በቀድሞ ጊዜ የዘውዲቱ ሆስፒታል ኃላፊ በነበሩበት ወቅት ለአስር ዓመት የተከማቹ አገልግሎት የማይሰጡ የህክምና ቁሶች እና መድኃኒቶችን በኮሚቴ አማካኝነት በተመረጠ አካባቢ እንደተቃጠሉ ያስታውሳሉ። በየካቲት 12 ሆስፒታልም በተመሳሳይ የተከማቹ ቁሶች እንደሚገኙ ነው የሚያስረዱት። ይሁንና ይህ ማለት ግን መልሰው አገልግሎት ላይ እየዋሉ ነው ማለት እንዳልሆነም ነው የሚገልፁት። ሆስፒታሉም ጥቅም ላይ ውለው የሚከማቹትን ቁሶች በዘመናዊ ማሽን አማካኝነት ለማስወገድ ፍቃድ ለማውጣት በሂደት ላይ እንደሚገኝ ይጠቁማሉ። ይህንንም ተግባራዊ በማድረግ «የተጣሉ መሳሪያዎች ዳግም ጥቅም ላይ ሊውሉ ይችላሉ» የሚለውን ጥርጣሬ ሙሉ በሙሉ ማስቀረት እንደሚቻል ነው የሚጠቁሙት።
የኢትዮጵያ የምግብ፣ መድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን የመድኃኒት ተቋማት ኢንስፔክሽን ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ እንዳለ በበኩላቸው፤ ከበርካታ ዓመታት በፊት የህክምና መርፌዎች ከተቀቀሉ በኋላ ጥቅም ላይ ይውሉ እንደነበር ያስታውሳሉ። በአሁኑ ወቅት ግን የተላላፊ በሽታዎች ከመስፋታቸው የተነሳ ይህ ዓይነት አሰራር እንደማይፈቀድ ይናገራሉ። በመሆኑም ብረት ነክ የሆኑ የህክምና መሳሪያዎች አገልግሎት እንደማይሰጡ ከተረጋገጠ ለብረት አቅላጭ ተቋማት ማቅረብ እንደሚገባው ነው የሚናገሩት። ባለስልጣኑም በአወጋገዱ ላይ ለጤና ተቋማት አሰራር የመዘርጋት እንጂ ወደ እያንዳንዱ ተቋም ወርዶ ቁጥጥር ማድረግ እንደማይችል ነው ያሳሰቡት። ይሁንና እስካሁን መልሶ ጥቅም ላይ የሚያውል የጤና ተቋም ባይከሰትም ሲገኝ ግን አስፈላጊው ህጋዊ እርምጃ እንደሚወሰድበት ነው የሚያረጋግጡት።
በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር መስፍን ቸርነት፤ አገልግሎት የሰጡ የህክምና ቁሶች መልሰው ጥቅም ላይ ለማዋል የሚደረግ ቁጥጥር ባለመኖሩ ጉዳዩ እንደሚያሳስባቸው ይጠቁማሉ። «መወገድ ያለባቸው የህክምና መሳሪያዎች በአግባቡ ይወገዳሉ የሚለው ጥብቅ ቁጥጥር የለውም። በዚህም በህገወጥ መንገድ ለመክበር የሚፈልጉ አካላት መልሰው አገልግሎት ላይ ሊያውሉት አይችሉም ብሎ መከራከር አይቻልም» የሚል እምነት አላቸው።
እንደ አምባሳደር መስፍን ገለጻ፤ አደገኛ ኬሚካሎችን እና መድኃኒቶችን ጨምሮ ልዩ ክትትል የሚያስፈልገው ይህን ጉዳይ በተመለከተ ፓርላማው ባለፈው ዓመት ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጥያቄ አቅርቦ ነበር። በወቅቱም አንድ ኃይል ተቋቁሞ ችግሩ እልባት እንደሚያገኝ አቅጣጫ ተሰጥቷል። በመሆኑም የህክምና ቁሶች የገቡበት እና ጥቅም ላይ የዋሉበት ጊዜ በየተቋማቱ ተመዝግቦ የሚያዝ በመሆኑ የሚወገዱበት ወቅትም ማጣራት ይቻላል። እናም መልሰው ጥቅም ላይ ቢውሉ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት በማሰብ አወጋገዱን ስርዓት ማስያዝ ብሎም ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግ የግድ የሚያስፈልገው አገራዊ ጉዳይ መሆኑን ነው አምባሳደር መስፍን አፅንኦት ሰጥተው ያሳሰቡት።

የተማሪዎች ብቃትና የብሄራዊ ፈተና ተጣጥመው ይሆን?



በኢትዮጵያ በ2008 .ም የተሰጠውን የ10ኛ እና 12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተናን ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች እንደወስዱ የሀገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና የፈተናዎች ኤጀንሲ መረጃ ያመለክታል። በየአመቱም በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተማሪዎች ብሔራዊ ፈተናውን እየወሰዱ ይገኛሉ። ይሁንና ብሔራዊ ፈተናዎች ተማሪዎች በፈተና ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርጉ እንደሚጋብዝ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ከፊንላንድ ጂቫስኪላ ዩኒቨርሲቲ የመጡት ፕሮፌሰር ጁውኒ ቫሊጃርቪ ሰሞኑን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ «የፊንላንድ የትምህርትና የፈጠራ ተሞክሮዎች» በሚል ርዕስ በተዘጋጀው ውይይት ላይ ተገኝተው የተናገሩት በፊንላንድ ብሔራዊ ፈተና እየተሰጠ አይደለም ሲሉ ነው። ብሔራዊ ፈተናዎች ሲደረግ ተማሪው ፈተና ላይ ብቻ ያተኩራል በሚል በምርምር እና ውጤታማነት ላይ ያተኮረ ምዘና ይካሄዳል። በአገሪቷም ለመምህራንና ትምህርት ተቋማት ሙሉ ሃላፊነት በመስጠት የተማሪዎች ዕውቀት እና ክህሎት እድገት ላይ የበኩላቸውን ጥረት እና ውሳኔ እንዲያስተላልፉ ይደረጋል። ከዚህ በተጨማሪ ብሔራዊ ፈተና በወጪ ረገድ ከፍተኛ ገንዘብ የሚጠይቅ በመሆኑ እየተሰራበት አይገኝም።
ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ ትምህርት ኮሌጅ ፕሮፌሰር ጥሩሰው ተፈራ እንደሚናገሩት ደግሞ፤ ብሔራዊ ፈተና የሚሰጥበት ዋነኛው ምክንያት የትምህርቱን ደረጃ መፈተሽ እንዲቻል ነው። ለአብነት በሁሉም ክልሎች እና ሁለቱ መስተዳደር ከተሞች ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት ስለማግኘታቸው ለማረጋገጥ አገር አቀፍ ፈተና ይካሄዳል። ይህም ከየአካባቢው የሚወጡ ተማሪዎች የሚመዘኑበት እና በእኩል ደረጃ ውጤታቸውን ለመገምገም የሚያስችል ነው። በተጨማሪም ሁሉንም በተመጣጠነ ሁኔታ ደረጃውን የጠበቀ ትምህርት መውሰዳቸውን ለማረጋገጥ የሚያስችል አሰራር ነው። በዚህም ተማሪው ብሔራዊ ፈተናውን ማለፉ ከተረጋገጠ በዕውቀትም ሆነ በክህሎት እንዲሁም በአመለካከት ረገድ ምን ደረጃ ላይ ደርሷል? የሚለውን ለመለካት ያግዛል። በመሆኑም የትምህርቱን ጥራት ለማስጠበቅ የሚካሄድ ፈተና አድርጎ መውሰድ ይቻላል።
እንደ ፕሮፌሰር ጥሩሰው ገለጻ፤ በኢትዮጵያም ውስጥ አንድ ተማሪ ቅድመ መደበኛ ትምህርት ሲያጠናቅቅ ማንበብ መፃፍ፣መግባባት፣ ስነምግባር እና ሁለንተናዊ ስብእና ያለው መሆኑ መረጋገጥ አለበት። በተለይም ከክፍል ክፍል ሲዘዋወሩ ማለፋቸውንና ብቁ መሆናቸውን የሚያረጋግጠው መምህሩ ነው። ይህም በመሆኑ አስተማሪም ብቁ ተማሪ እንዲኖረው ጥረት ያደርጋል። በቀጣይም ከመነሻው ጀምሮ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ ተጠብቆ መሄድ ያለበት አሰራር መሆን ይገባዋል። ተማሪው ትምህርቱን መማሩን ማረጋገጥ የሚቻለው በክፍል ውስጥ ነው። ይሁንና በርካታ ተማሪዎች ሳይማሩ በኩረጃ ብቻ ፈተናዎችን ያልፋሉ። በተለይ የግል ትምህርት ተቋማት ከብሔራዊ ፈተናዎች ጋር ተያይዞ ተማሪዎች ለፈተና ብቻ እንዲዘጋጁ ማድረጋቸው አግባብ አይደለም። ይህም ተማሪዎቹ ከፈተና በኋላ ዕውቀቱን እንዲረሱ የሚገፋፋ ይሆናል። በመሆኑም ውጤታማ የትምህርት አካሄድ የተከተለ ነው ለማለት እንደሚከብድ ይናገራሉ።
«በየትምህርት ቤቱ ያሉ መምህራን እና ርዕሰ መምህራን ሃላፊነታቸውን በሚገባ መወጣት ይኖርባቸዋል» የሚሉት ፕሮፌሰር ጥሩሰው፤ ብሔራዊ ፈተናን በኢትዮጵያ ማስቀረት የሚቻለው ሙሉ በሙሉ ሃላፊነቱን መሸከም የሚችል መምህርና ርዕሰ-መምህር ማዘጋጀት ሲቻል መሆኑን ነው የሚያስረዱት። እዚህ ላይ የመምህራን ብቻ ሳይሆን የወላጆችም ሃላፊነት መታከል እንዳለበት ይጠቁማሉ። ይህም ተማሪዎች በውስጣዊ የትምህርት ፍላጎት እንዲማሩ እንጂ ለፈተና ብቻ እንዳይዘጋጁ እንደሚረዳ ይናገራሉ። ይሁንና አሁን በአገሪቷ የሚታየው ተማሪዎችን ለፈተና ብቻ እንዲዘጋጁ የማድረግ አሰራር ሲሆን፤ በዚህ ጉዳይ ከፍተኛ የለውጥ እርምጃ የሚያስፈልገው የመምህራን ምልመላ እና ስልጠና ላይ መሆኑን ይገልፃሉ።
ዋነኛው የትምህርት አነቃናቂው ሞተር መምህራን በመሆናቸው ለአሰራሩ ዝግጁ እንዲሆኑ በቂ ዝግጅት ያስፈልጋል። በዚህም ትምህርት ቤቶች አስፈላጊውን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ያግዛል። በርካታ የግል ትምህርት ተቋማት ፈተና ላይ ያልተመረኮዘ የትምህርት አሰራርን እንዲከተሉ ማድረግ ይገባል። ይህ እስካልተከናወነ ድረስ ተማሪዎች ለዕውቀት እና ክህሎት ሳይሆን ብሔራዊ ፈተና ላይ ብቻ ያተኩራሉ የሚል ሃሳብ ይሰነዝራሉ።
የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ሽፈራው ተክለማርያም በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ «የኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓት የሚያተኩረው ዕውቀት እና ክህሎት የማሻሻል ተግባር ላይ ነው። በመሆኑም ፈተና ላይ ትኩረት አድርጎ ውጤት የሚለካው ተማሪዎችን መለየት ስለሚያስፈልግ ብቻ ነው። ስለዚህ 10ኛ እና 12ኛ ክፍሎች ላይ ብሔራዊ ፈተና እየተሰጠ የሚገኘው በዚሁ አሰራር መሰረት ነው። በመሆኑም በቀጣይ ብሔራዊ ፈተናዎችን ለማንሳት የሚያስችል ምንም አይነት ስራና አዲስ እቅድ አይኖርም። ሆኖም በትምህርት ዘርፉ ላይ ተማሪዎች አቅማቸውን ለማጎልበት እንዲችሉ የግል ጥረት እንዲያደርጉ ይጠበቃል። ይህም ብሔራዊ ፈተናን ብቻ ሳይሆን እውቀት እና ክህሎትን በበቂ ሁኔታ ይዘው አገራቸውን እንዲያገለግሉ ይረዳቸዋል» በማለት ነው ሃሳቡን ውድቅ ያደረጉት።

 

የኢትዮጵያ ሳተላይት የማምጠቅ እቅድ ይሳካ ይሆን?



እንደ ኢትዮጵያ ህዋ ሳይንስ ማህበር መረጃ ከሆነ በህዋ ላይ እየሰሩ የሚገኙ 1400 ሳተላይቶች አሉ። ከዚህ ውስጥ ከ500 በላይ የሚሆኑት የአሜሪካውያን ናቸው። ኢትዮጵያ እስከ አሁን የሌሎቸ አገራት ሳተላይቶችን በኪራይ እየተጠቀመች ትገኛለች። በዚህም የግል ተጠቃሚዎችን ጨምሮ በዓመት ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ለኪራይ ታወጣለች።
ይህን ችግር ለማቃለል ኢትዮጵያ ከሶስት እስከ አምስት አመታት ባሉት ጊዜያት ውስጥ ሳተላይት ለማምጠቅ አቅዳለች። በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የሚመራ የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ተቋቁሟል። የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲም ሰሞኑን በዘርፉ ከተሰማራው የፈረንሳዩ ኩባንያ ዩ ቴል ሳት ጋር የ13 ሚሊየን ዩሮ የማማከር ስምምነት ተፈራርሟል። የኢትዮጵያ ሳተላይት የማምጠቅ ፍላጎት እና ደረጃ ምን ላይ ይገኛል? የሚኖረው ፋይዳስ ከወጭው አንፃር እንዴት ይመዘናል?
የኢትዮጵያ በእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪና ምርምር ማዕከል የመሬት ምልከታ ምርምር ኃላፊ ዶክተር ቱሉ በሻ እንደሚገልፁት፤ የኢትዮጵያ አቅም በቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ሳተላይት ለማምጠቅ ያስችላል። የማምጠቂያ ወጪው እና ሳተላይቱ ከሚሰጠው ጥቅም ጋር ሲነጻጸርም የሚገኘው መረጃ አስፈላጊነት እጅጉን ልቆ ይገኛል። በኢትዮጵያ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ፣ የመገናኛ መሳሪያዎችን ጥራት እና ብዛት ከማሻሻል አኳያ እና ለተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች መረጃዎችን ከህዋ ለመሰብሰብ ሳተላይቱ ወሳኝ ድርሻ አለው። በተጨማሪ ኢትዮጵያ በማምጠቋ መረጃውን ከሌሎች አገራት ለማግኘት የምትከፍለውን ከማስቀረት ባሻገር ከሳተላይቱ የሚገኘውን መረጃ ለጎረቤት አገራት በመሸጥም ገቢዋን ለማሳደግ ይረዳታል።
«ለሳተላይቱ ማምጠቂያ የሚሆነውን መሰረተ ልማት የግድ ኢትዮጵያ ላይ መገንባት አያስፈልግም» የሚሉት ዶክተር ቱሉ፤ የመሰረተ ልማቱን ለመገምባት ቢታሰብ ከአገሪቷ አቅም በላይ እንደሚሆን ነው የሚናገሩት። በመሆኑም ከሌሎች አገራት ማስወንጨፊያ ተከራይቶ መላክ አዋጭ መሆኑን ያስረዳሉ። ይሁንና ማምጠቂያውን ገንብቶ ለመጠቀም እና ለማከራየት የረጅም ጊዜ እቅድ ሊያዝ እንደሚገባ ይጠቁማሉ።
የአስትሮ ፊዚክስ ምሁሩ ዶክተር ለገሰ ወትሮ፤ አሁን አይቻልም፤ ማስወንጨፊያውን መከራየት በሚለው ሃሳብም አይስማሙም። በአሁኑ ወቅት አንድ ሳተላይት ለማምጠቅ አንድ ቢሊዮን የአሜሪካን ዶላር እንደሚፈጅ ይገልፃሉ። «አገሪቷ ያላት የኢኮኖሚ ደረጃ ደግሞ ሳተላይት ማምጠቁም በድህነት ላይ ሌላ ወጪ መጨመር ነው። በቅርብ ዓመታት ውስጥ ይሳካል ብሎ መናገር አይቻልም» ይላሉ። በመሆኑም ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም የአገሪቷ ኢኮኖሚው የበለጠ ማደግ አለበት የሚል እምነት አላቸው። ይህም ጊዜ ወስዶ አስፈላጊውን ግብአት ለማሟላት እንደሚያግዝ ይናገራሉ።
«የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከዳበረ በኋላ የማምጠቂያ ቴክኖሎጂው ለመገንባት ዝግጅት ማድረግ ይገባል። አቅሙ ከተፈጠረና ማስወንጨፊያው ከተገነባ በኋላ የአገሪቷ በምድር ወገብ አካባቢ የሚገኝ በመሆኑ ከመሬት ሽክርክሪት ጋር ተያይዞ አመቺ የሳተላይት ማምጠቂያ አካባቢ ላይ ትገኛለች። በመሆኑም ይህን እድል መጠቀም ይገባል። አገሪቷ ከማስወንጨፊያ ኪራይ የሚያድናት ከመሆኑም በላይ ለሌሎች አገራትም በማከራየት ከፍተኛ ገቢ ታገኛለች። በመሆኑም ማስወንጨፊያውን ከመከራየት ይልቅ ማስወንጨፊያውን በአገር ውስጥ ስለመገንባት መታሰብ አለበት» የሚል አቋም አላቸው።
«ለዘርፉ ከኮሚዩኒኬሽን ጋር የተያያዘ በርካታ ስራ ቢያስፈልግም በኢትዮጵያ የተጠናከረ የቴክኖሎጂ አቅም ስለመኖሩ እርግጠኛ መሆን አይቻልም» የሚሉት ዶክተር ለገሰ፤ ለዚህም ደግሞ የአገር ውስጥ የተማሪዎችን እና ምሁራንን የቴክኖሎጂ አቅም ደረጃን ከፍ ማድረግ መቅደም አንደሚገባው ይናገራሉ። «በተለይም አሁን ያለው የህዋ ተመራማሪዎች የቴክኖሊጂ አቅም አገሪቱ በሙሉ እምነት ሳተላይት ለማምጠቅ የሚያስችል አይደለም። በዚህም ምክንያት የውጭ ባለሙያዎች ተቀጥረው እስካልተሳተፉ ድረስ ከሶስት እስከ አምስት ዓመታት ድረስ ሳተላይት ወደ ህዋ ለማምጠቅ አይቻልም። በመሆኑም በዩኒቨርሲቲዎች በኩል ዕውቀት እና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ይገባል» የሚል ጠንካራ አቋም ይዘዋል። በተጨማሪም ከሳተላይቱ የሚገኘውን መረጃ በሳይንሳዊ መንገድ በአግባቡ ስለመጠቀም ከወዲሁ ሊታሰብበት ይገባል። ይህ ካልሆነ ግን ከሳተላይት የሚገኘው መረጃ ከተለያዩ ሚዲያዎች ከሚገኘው ቁምነገር የተለየ ጥቅም ሊያገስገኝ እንደማይችል ነው የሚገልፁት።
የኢትዮጵያ ስፔስ ሳይንስ ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አብነት እዝራ በበኩላቸው፤ የተለያዩ የሳተላይት አይነቶች ቢኖሩም በአሁኑ ወቅት በአትዮጵያ ቅድሚያ የተሰጠው የመሬት ምልከታ/Earth Observation/ ሳተላይት ሲሆን ለመገናኛ መሳሪያነትም ያገለግላል። ይህም በህዋ ላይ እስከ 15 ዓመት የቆይታ እድሜ ይኖረዋል። አሁን ባለው እቅድ መሳሪያው በውጭ ሰዎች የሚዘጋጅ እና በአገር ውስጥ የሚገጣጠም በመሆኑ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎች በቂ የዕውቀት ሽግግር እንዲያገኙ ማድረግ ይገባል። በቀጣይ ሳተላይቱን ለመቆጣጠር እና ለማምጠቅ የቴክኖሎጂ ተላምዶ ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባ ነው የሚናገሩት። ናይጄሪያ የመጀመሪያውን ሳተላይቷን ስታመጥቅ የውጭ አገር ባለሙያዎችን ተጠቅማ ቢሆንም ከአራት ዓመታት በኋላ ስራውን ሙሉ በሙሉ በአገሯ ሰዎች መቆጣጠር ችላለችና ከዚህ ልምድ መውሰድ ይቻላል።
በመሆኑም አሁን ባለው የአገሪቷ ኢኮኖሚያዊ እና የዘርፉ ቴክኖሎጂ ደረጃ ሳተላይት ለማምጠቅ ረጅም ዓመታት ይፈጃል የሚለውን በዶክተር ለገሰ ሃሳብ አይስማሙም። በዋጋ ደረጃ አሁን አገሪቷ የሳተላይት አገልግሎት ለማግኘት በየዓመቱ የሚወጣው ወጪ ቢደመር ሳተላይት ለማምጠቅ በቂ መሆኑን ነው የሚናገሩት። የወጪው ጉዳይ እንደማያሳስብ ይገልፃሉ።
«ሳተላይት ስለተገኘ ብቻ ሁሉም አገራት ያስተኩሳሉ ማለት አይደለም» የሚሉት አቶ አብነት፤ 65 አገራት ሳተላይት ቢያመጥቁም በዓለም ላይ የእራሳቸው ማስወንጨፊያ ያላቸው 12 አገራት ብቻ መሆናቸውን ነው የሚጠቁሙት። በአፍሪካ ውስጥ ሳተላይት ተወንጭፎ እንደማያውቅ እና ኢትዮጵያም የሌሎች አገራት ማስወንጨፊያ መጠቀሟ ተገቢ መሆኑን ነው የጠቆሙት።
«ጉዳዩን ለማሳካት ቁርጠኛ በመሆን የዘርፉ ፖሊሲ እና ስትራቴጂ በፍጥነት መዘጋጀት አለበት» የሚሉት አቶ አብነት፤ ይህም ስራውን በትክክለኛው መንገድ ለመምራት እና ብቁ ባለሙያዎችን በብዛት ለማፍራት አይነተኛ ሚና ይኖረዋል። ይህ ከተሳካ የአሜሪካ የህዋና የጠፈር ምርምር ማዕከል (ናሳ) የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ባለሙያዎችን ጭምር በማስመጣት አገሪቷን በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ የእራሷ ሳተላይት ተጠቃሚ ማድረግ ይቻላል የሚል እምነት አላቸው።

 

የዩኒቨርሲቲ ተማሪ እና የጥናት አማካሪዎች መገኛቸው አራምባ እና ቆቦ ሆኗል

 

አሁን አሁን የዩኒቨርሲቲ ትምህርት የማሟያ ጥናቶች የሚከናወኑት ከተማሪው ተሳትፎ ውጪ እየሆነ መጥቷል። በተለይም በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እና በአካባቢያቸው «የጥናት ጽሁፍ እናዘጋጃለን» የሚሉ ማስታወቂያዎችን መመልከት እንግዳ ነገር አይደለም። በዚህ ጉዳይ ላይ የዩኒቨርሲቲ መምህራን ሳይቀሩ እጃቸው እንዳለበት ተማሪዎች ይናገራሉ። ይሁንና ከህገወጡ ተግባር በተቃራኒው በትክክለኛው መንገድ ዕውቀታቸውን ከአማካሪ መምህራቸው ገንቢ አስተያየት ጋር አጣምረው ለአገር የሚጠቅም ጥናት የሚያቀርቡ እንዳሉም አይካድም። እዚህ ላይ «በተገቢው መንገድ ጥናት ለማቅረብ ብንጥርም አማካሪዎቻ ችንን በበቂ ሁኔታ ባለማግኘታችን ችግር ገጥሞናል» የሚል ቅሬታ የሚያነሱ ተማሪዎች ደግሞ እየተበራከቱ ነው።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጂኦግራፊ ትምህርት ክፍል የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪ ተሾመ ታደሰ እንደሚናገረው ከሆነ፤ ለዲግሪ ማሟያ ጥናት በሚያዘጋጅበት ወቅት አማካሪ መምህሩን በወቅቱ እና በአስፈላጊው ጊዜያት ባለማግኘቱ ምክንያት በ2008 .ም መጨረስ የነበረበትን ትምህርት አሁን ላይ እየተማረ ይገኛል። ባለፈው ዓመት ጥናቱን በሚያዘጋጅበት ወቅት አማካሪው በሥራ ምክንያት ከተማ ውስጥ ባለመገኘታቸው ጥናቱን በአግባቡ ማከናወን አላስቻለውም። ይህም ደግሞ አንድ ዓመት በትምህርት ጊዜው ላይ እንዲጨምር አስገድዶታል። ከጊዜ ብክነት በተጨማሪ ለተጨማሪ የገንዘብ ወጪም ዳርጎታል።
መምህራኑ በተገኙበት ወቅት ገንቢ አስተያየት ለተማሪዎች የሚሰጡ ቢሆንም አንዳንድ መምህራን የመገኘት እድላቸው አነስተኛ ነው የሚለው ተማሪ ተሾመ «ይህን ችግርም ለዩኒቨርሲቲው ለማሳወቅ ጥረት አላደረግንም ምክንያቱም እራሳቸው አማካሪዎቹ የትምህርት ክፍል ኃላፊዎች በመሆናቸው ችግሩን ለማን እናሳውቃለን በሚል ከተማሪዎች ጥያቄ አይቀርብም» ይላል። ቢቀርብም ጥያቄው ዞሮ ዞሮ ለእራሳቸው ለአማካሪዎቹ ይደርሳል። ይህም መፍትሄ ለማግኘት የሚደረገውን ጥረት እንዲቀንስ አድርጓል። በመሆኑም ችግሩ በኔ ይብቃ እና ቀጣይ በዩኒቨርሲቲው የሚማሩ ሁሉ የዚህ ችግር ሰለባ እንዳይሆኑ ማስተካከል ይገባል የሚል ምክር ሰጥቷል።
ተማሪ ታረቀኝ መኮንን በዩኒቨርሲቲው የሁለተኛ ዓመት የሶስተኛ ዲግሪ(ዶክትሬት) ተማሪ ነው። አማካሪ እና ጥናት የሚያቀርበው ተማሪ ያላቸው ግንኙነት ወሰን እንደሚያስፈልገው ነው የሚናገረው። አብዛኛውን ጊዜ ሁሉን ነገር አማካሪው እንዲሰጠው እና እንዲሰራው የሚጠብቅ ተማሪ አለ። በዚህም ምክንያት ብዙ ነገር ከአማካሪያቸው ጠብቀው ያላገኙ ተማሪዎች ለጥናቱ ያላቸው ፍላጎት በእጅጉ እየቀነሰ ይሄዳል። ይህም የተማሪዎች ክፍተት በመሆኑ ሊስተካከል እንደሚገባ ይመክራል። ይሁንና ዋነኛው ሥራ የሚያስፈልገው ከተማሪው በመሆኑ ለዲግሪም ሆነ ዶክትሬት ማሟያ ጥናት ጽሁፍ ከፍተኛውን መረጃ ለመሰብሰብ እና ለማጠናቀር ጥረት ማድረግ ተገቢ አካሄድ ነው። በዚህም የአንበሳውን ድርሻ ጥናት አቅራቢው ከያዘ በተጨማሪ የአማካሪው ሥራ የሚሆነው የተወሰነ ድጋፍ ማድረግ ብቻ ይሆናል። በመሆኑም ተመካሪ ያመጣውን መረጃ እና ጥናት አማካሪው አካል መንገድ የማስያዝ ሚና ብቻ እንዳለው መረዳት እንደሚገባ ያምናል።
«ይሁንና ሁሉም አማካሪዎች መልካም አገልግሎት ይሰጣሉ ማለት አይደለም። አንዳንድ አማካሪዎች ጋር ለጥናቱ ትኩረት ያለመስጠት እና የማማከር አገልግሎቱን እንደ ትርፍ ሥራ የመቁጠር ችግር አለ። ለአብነትም የተማሪውን የጥናት ንድፍ ወረቀት ለረጅም ጊዜ ይዞ የሚያቆይ የዩኒቨርሲቲ መምህር ይታያል። ይህም የሚከሰተው አንዳንድ መምህሮች ከተቋማቸው የሚሰጣቸውን የሥራ ጫና ለመከላከል 'እጄ ላይ ሥራ አለ' ለሚል ሰበብ ሊጠቀሙበት ሲፈልጉ ነው።ይሁንና ዩኒቨርሲቲው የሥራ ጫና እንዲቀንስ የተማሪውን ወረቀት ይዞ ማቆየት ተገቢ አይደለም » ይላል።
ከዚህ በተጨማሪም ኃላፊነት ላይ ያሉ አንዳንድ መምህራን ረጅም ጊዜያት ለሥራ ወደመስክ በመውጣታቸው ምክንያት ለአጥኚ ተማሪው የሚሆን ጊዜ ያጥራቸዋል። ይህም የተማሪውን የጥናት ጊዜ ያስተጓጉላል። በእነዚህ ምክንያቶች በሁለት እና ሶስት ዓመታት መጨረስ የነበረባቸውን የትምህርት ጊዜ እስከ አስር ዓመት ጊዜ የተራዘመባቸው የቀድሞ ተማሪዎች ይገኛሉ። በሌላ በኩል ዩኒቨርሲቲው አዳዲስ የትምህርት ዘርፎችን እያጠናከረ ቢገኝም ለዶክትሬት ተማሪዎች የሚያደርገው የግብዓት ድጋፍ ከክልል አቻ ተቋማት ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ መሆኑን ነው የሚናገረው። የተለያዩ የአገሪቷ ዩኒቨርሲቲዎች ለዶክትሬት ተማሪዎች ቢሮ እና ነፃ ላፕቶፕ እንዲሁም የኪስ ገንዘብ ያዘጋጃሉ። ይህ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኩል ያልተሟላ ከመሆኑም በላይ የኢንተርኔት አገልግሎቱ እንኳ ደካማ በመሆኑ የሚፈለገውን መረጃ ለማግኘት አስቸጋሪ ሆኗል። በዚህም ምክንያት የጥናት ሥራዎች ላይ ችግር ይፈጠራል። በመሆኑም በቀጣይ የተቋሙ ኃላፊዎች ሊያስተ ካክሉት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን ነው ያሳሰበው።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የድህረ ምረቃ መርሃ ግብር ዳይሬክተር ፕሮፌሰር በቀለ ጉተማ በበኩላቸው፤ በድህረ ምረቃ ትምህርት ከ16 ሺ በላይ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው እንደሚገኙ ይናገራሉ። ከረዳት ፕሮፌሰር ማዕረግ ጀምሮ ያሉ መምህራንም በድህረ ምረቃ ትምህርቶች ላይ አስተማሪ እና የጥናት አማካሪ ሆነው እየሰሩ መሆናቸውን አስታውሰው «በተማሪዎች ጥናት ማማከር ላይ መምህራን አይገኙም» የሚለው ወቀሳ ላይ ሁሉንም መምህራን ማጠቃለል እንደማይገባ ነው የሚጠቁሙት።
ምክንያቱን ሲያብራሩም «መምህራን ለምርምር ሥራ፣ በኮንፈረንሶች ላይ ለመካፈል እና ለተለያዩ ጉዳዮች ወደ ተለያዩ አገራት መሄዳቸው የተግባራቸው አንድ አካል ነው። መምህራንም ሥራቸውን የሚያውቁ እና ተገቢውን አገልግሎት ለመስጠት ኃላፊነት የሚሰማቸው ናቸው። ይሁንና ችግሩ ቢኖር የሚፈታበት መንገድ በዩኒቨርሲው የተቀመጠ በመሆኑ ተማሪዎች ከአማካሪ ጋር ተያይዞ የሚያነሱትን ጥያቄ ከትምህርት ክፍል ኃላፊ ጀምሮ ችግሩን መፍታት ይቻላል። ችግሩ ከዚህ ካለፈም እስከ ዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ድረስ ጥያቄ አቅርቦ ማስፈታት ይገባል።»
ይሁንና አማካሪ በአግባቡ ማግኘት አልቻልኩም እና ተያያዥ ችግሮች አጋጥሞኛል የሚል ቅሬታ ከማንኛውም ተማሪ መቅረቡን እንደማያስታውሱ ነው የሚጠቁሙት። ችግሩ መኖሩ ከተማሪው ካልመጣ በጋራ ለመፍታት እንደሚያስቸግር ነው የተናገሩት።
«ችግሩ አይኖርም ማለት አይቻልም። ነገር ግን ችግሩ ተማሪው ጋር ወይም መምህሩ ጋር ሊሆን ይችላል» የሚሉት ደግሞ በዩኒቨርሲቲው የስነ-ትምህርት ኮሌጁ መምህር ዶክተር አምቢሳ ቀነዓ ናቸው። በመሆኑም ችግሩን ሙሉ በሙሉ የአንድ ወገን አድርጎ መደምደም አይገባም። ተግባብተው የሚሰሩ ተማሪ እና መምህራን በመኖራቸው ጉዳዩ የሁሉም ችግር አድርጎ መውሰድ አይቻልም። ይሁንና በተማሪዎች በኩል ከአማካሪያቸው የጥናት አስተያየት ከተቀበሉ በኋላ ሁለት እና ሶስት ወራትን ቆይተው አማካሪያቸውን ለማግኘት ይዘጋጃሉ። የተለያዩ ተማሪዎች በአስተማሪነት እና በማማከር እንዲሁም በተለያዩ የሥራ መስኮች ላይ የተሰማሩ በመሆናቸውም ከአማካሪያቸው ጋር ለመገናኘት በቂ ጊዜ ያጥራቸዋል። በዚህም ምክንያት አማካሪው ቢገኝም አጥኚው አካል የማይገኝበት ሁኔታ ሊፈጠር እንደሚችል ያምናሉ።
ከዚህ በተጨማሪም ጥናቱን እንደጨረሰ አድርጎ ሪፖርት የሚያቀርብ ተማሪ በመኖሩ የአማካሪውን የመጨረሻ ሥራ እንደማያይ አድርጎ የመገመት ችግር ይከሰታል። አንድ ጥናት ሲከናወን የተለያዩ ደረጃዎች ያሉት ሲሆን፣ ከመነሻ ሃሳብ ጀምሮ እስከ መምደሚያ ሥራው ድረስ አማካሪውን ሊያሳትፍ ይገባል። በሌላ በኩል ለዶክትሬት ተማሪዎች በቂ ግብአት ማሟላት እንዳለበት ቢታመንም በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲው በተዘጋጁት ጥቂት የማረፊያ ክፍሎች ላይም ተማሪዎች አይገኙም። በመሆኑም ለጊዜውም ቢሆን የተዘጋጀውን ግብዓት በአግባቡ ተጠቅሞ ማሳየት እንደሚያስፈልግ ነው ዶክተር አምቢሳ የሚናገሩት።
«በአማካሪ በኩል ደግሞ አንዳንዱ ተማሪውን ጥናቱን ጨርሶ እንዲያመጣ የሚጠብቅ ይኖራል። ይህ ተገቢ አይደለም። በመሆኑም ወቅቱን ጠብቆ ገንቢ አስተያየት መስጠት አስፈላጊ ነው። በተጨማሪም አማካሪዎች ከመጀመሪያ ዲግሪ ጀምሮ እስከ ዶክትሬት ትምህርት ድረስ የሚገኙ ተማሪዎች በሚሰሩት ጥናት ላይ እንዲያማክሩ ይደረጋል። ይህ አስተማሪው ላይ የሥራ ጫና የሚፈጥር በመሆኑ ለተመካሪው በቂ ጊዜ እንዳይሰጥ ያደርገዋል። በዚህም ምክንያት የጥናት ሥራው ውጤታማነት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ያሳድራል። ይህ ወደፊት መታየት የሚያስፈልገው ጉዳይ ነው » በማለት ነው መፍትሄ ያሉትን የጠቆሙት።
ማንኛውም አካል ጋር ችግሩ ቢከሰት ተጠያቂው ማነው? የሚለውን ለመለየት የክትትል ሥራው መጠናከር አለበት። በመሆኑም የተጠያቂነት ስርዓቱ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ስለመኖሩ ማረጋገጥ ያስፈልጋል። በዚህም የየትኛው መምህር ተማሪዎች በጥናታዊ ሥራ ላይ አነስተኛ ውጤት አምጥተዋል ወይም ከፍተኛ ውጤት አስመዝግበዋል የሚለውን መፈተሽ ይገባል። ለዚህም አስፈላጊው የአሰራር ስርዓት መዘርጋት ለውጤታማነት ይረዳል። ከክትትሉ ጋር ተያይዞ ተማሪው በክፍል ውስጥ ሲገኝ ስለመገኘቱ እንደሚመዘነው ሁሉ ወደ ጥናት ሥራ ከገባ በኋላም ስለመገኘቱ ክትትል ያስፈልጋል። ይህንንም መምህሩ ሪፖርት የሚያደርግበት እና በቂ ቁጥጥር የሚደረግበት መንገድ መመቻቸት አለበት።

ባዮሎጂካል ጥቃት እና የኢትዮጵያ ዝግጁነት

የባዮሎጂካል ጥቃት እና ኢትዮጵያ 
/Biological Attack/
... 1972 የባዮሎጂካል መሣሪያዎችን ማዘጋጀት እና መጠቀምን የሚያግድ ስምምነት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል አገራት መካከል ተፈርሟል። ኢትዮጵያም ተቀብላ አጽድ ቃዋለች። ይሁንና ስምምነቱን ያልፈረሙ 12 አገራት ሲኖሩ፤ ከዚህ ውስጥ ኤርትራ፣ ጅቡቲ እና ደቡብ ሱዳን ይገኙበታል። በሌላ በኩል ስምምነቱን ፈርመው ካላጸደቁት ስድስት አገራት መካከል ግብጽ እና ሶማሊያ ይጠቀሳሉ።

በሁለተኛው የዓለም ጦርነት አንዳንድ አገራት በምስጢር በእስረኞች ላይ የባዮሎጂካል መሣሪያ ተጠቅመው ሦስት ሺህ ሰዎች መግደላቸው በታሪክ ተመዝግቧል። እንደ አሜሪካው የደህንነት ቢሮ (FBI) መረጃ እ... 2001 «አንትራክስ» የተሰኘው ባክቴሪያ በጅምላ ጨራሽነት መልክ ተዘጋጅቶ በአሜሪካ አገር በፖስታ ይላክ ነበር። በዚህም የአምስት ሰዎች ሞት እና የ17 ሰዎች የከፋ ጉዳት መድረሱ አይዘነጋም።

አንድ ግራም ባዮሎጂካል መርዛማ ንጥረ ነገር እስከ አስር ሚሊዮን ያህል ሰዎችን የመግደል አቅም እንዳለው ባለሙያዎች ይናገራሉ። በመሆኑም የባዮሎጂካል ጥቃት በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ አሳሳቢነቱ እየጨመረ መጥቷል። በኢትዮጵያም ላይ በቀጣይ ሊፈጸም የማይችልበት ምክንያት ባለመኖሩ ስጋት እንዳለ ባለሙያዎች ይገልጻሉ።

የአፍሪካ የህክምና ላቦራቶሪ ሶሳይቲ የፕሮግራም ማናጀር እና የቀድሞው የኢትዮጵያ የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አምሃ ከበደ እንደሚናገሩት፤ ባዮሎጂካል ጦርነት ወይም ጥቃት ሕይወት ካላቸው ነገሮች የጦር መሣሪያ ማዘጋጀትን ያካትታል። በዚህም አማካኝነት ባክቴሪያዎች እና ቫይረሶችን በመጠቀም በመሣሪያ መልክ አዘጋጅቶ መርዛቸውን በመጠቀም ወይም እራሳቸው በዓይን የማይታዩ ጥቃቅን አካላት (ማይክሮ ኦርጋኒዝሞቹን) በመጠቀም ጅምላ ጨራሽ መሣሪያ የማድረግ ዘዴ ነው። ይህ ዘዴ ባልተፈለገ አካል ማለትም በአሸባሪዎች እጅ የሚገባ ከሆነ ችግሩን የከፋ ያደርገዋል የሚል ስጋት መኖሩን ይናገራሉ።

እንደ ዶክተር አምሃ ገለጻ፤ ይህን ለመከላከልም በቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አነሳሽነት የተጀመረ የዓለም የጤና ደህንነት አጀንዳ የተቋቋመ ሲሆን፤ የአደጋ ስጋቶችን ለመቀነስ የሚደረገው ጥረት አካል በመሆኑ የባዮሎጂካል ጥቃትን ለመከላከል ያግዛል። ኢትዮጵያም የዚሁ ጥረት አካል ነች። ይሁንና በኢትዮጵያ ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ አሸባሪዎች አደጋ እንዳይፈጥሩ በላቦራቶሪ አካባቢዎች የባዮሎጂ ምርምር ሲከናወን ጥንቃቄ ያስፈልጋል። በዚህም ማንኛውን አካል አውቆም ይሁን ሳያውቅ በሽታዎቹን እንዳይሰራጩ የቁጥጥር አቅምን ማጠናከር ይገባል። በመሆኑም ባዮሎጂካል ጅምላ ጨራሾቹን ለማዘጋጀት የሚረዱት ሥነሕይወታዊ ነገሮችን በላቦራቶሪ በአግባቡ ማስቀመጥ፤ ከቦታ ወደ ቦታ ሲንቀሳቀሱም ክትትል የሚደረግበትን አቅም ማጠናከር ያስፈልጋል። ይህ ካልተደገ ግን አሸባሪዎች ቴክኖሎጂውን በቀላሉ ተጠቅመው ጉዳት ሊያደርሱ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

በሌላ በኩል ከውጭ አገራት ሊመጡ የሚችሉ ጥቃቶችን ለመከላከልም ጥቃቱ በድብቅ የሚፈም እና ሕዝብ በተሰበሰበበት አካባቢ የሚፈጸም በመሆኑ ችግሩ ከመከሰቱ በፊት ክትባቶች በመጋዘን ውስጥ በአግባቡ እና በበቂ ሁኔታ ማስቀመጥ ይገባል። በተጨማሪም መርዙን የሚያረክሱ መድኃኒቶች በብዛት በአገር ውስጥ ማዘጋጀትም ይመከራል። ይህም ሊከሰት የሚችለውን የአደጋ ስጋት እንደሚቀንሰው ይናገራሉ።

«ጉዳዩ በኢትዮጵያ አሳሳቢ ባለመሆኑ በአሁኑ ወቅት እንደስጋት የሚቆጠር አይደለም» የሚሉት ደግሞ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባዮሎጂ ክፍል መምህሩ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ናቸው። በአስተኛ መጠን ያለው ባዮሎጂካል መርዝ ቢረጭ በአጭር ጊዜ ውስጥ በሰው አካል ውስጥ እየተራባ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን የማጥቃት አቅም እንዳለው ይገልፃሉ። ይሁንና አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ይህን ዓይነት ጥቃት የሚያደርስ ኃይል አለ ብሎ ለማሰብ አስቸጋሪ መሆኑን ይጠቁማሉ። ግብጽን ጨምሮ አቅሙ ያላቸው ጎረቤት አገራት ጥቃት ቢፈጽሙም የጅምላ ጨራሹን ምንጭ ማወቅ ስለሚቻል በዓለም አቀፍ ሕግ እንደሚጠየቁበት ያስረዳሉ። በመሆኑም በጣም የተቸገረ እና ተስፋ የቆረጠ አካል ሊፈጽመው የሚችል ቢሆንም የጎረቤት አገራት ሊሞክሩት እንደማይችሉ ይናገራሉ።

«ይሁንና በአንጻራዊነት የስጋቱ መጠን የጎላ አይሁን እንጂ ነፃ የሚባል ነገር የለም» የሚሉት ፕሮፌሰር በየነ፤ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ይስማማሉ። በመሆኑም ለችግሩ ተጋላጭ ሊሆኑ ይችላሉ የሚባሉ እንደ መከላከያ ሠራዊት እና ለጥቃቱ ተጋላጭ ሊሆኑ የሚችሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች ስለሳይንሱ እንዲያውቁ ሊደረግ እንደሚገባም ይገልጻሉ። በዚህም ጥቃቱ ቢፈጸም እንኳን ሰውነትን ለአየር ማጋለጥ እንደማይገባ እና የመተንፈሻ አካላት ጭንብል ማድረግ እንደሚያስፈልግ ማስተማር ይገባል።

በኢትዮጵያ ብዝሃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ስለ ባክቴሪያ የሚያጠኑት አቶ በፍቃዱ ተሾመ እንደሚናገሩት፤ ባዮሎጂካል መሣሪያ ሕይወት ያላቸውን ነገሮች ከሚያመነጩት መርዛማ ነገሮች በመጠቀም በሰው፣ በእንስሳት እና በእጽዋት ላይ ሞት ወይም ሌላ ጉዳት ለማድረስ ይውላል። ይህም በዓይን የማይታዩ ህዋሳትን እንዲሁም ከእጽዋት እና ከመርዛማ እንስሳት የሚገኙ ንጥረ-ነገሮች የመጠቀም ድርጊት ነው። ይህን መጠቀም በዓለም ላይ በሕግ የተከለከለ በመሆኑ በሕግ ያስጠይቃል። በመሆኑም ጅምላ ጨራሽ አዘጋጅቶ ማከማቸትም ሆነ ጥቅም ላይ ማዋል የሚገድብ ዓለም አቀፍ ስምምነት መኖሩን ይገልፃሉ።

ሁሉም ባለሙያዎች የተስማሙት አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ችግሩ ያን ያህል አሳሳቢ አለመሆኑን ነው። ይሁን እንጂ ሁሉም አገራት በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ ስጋቱን መቀነስ ይገባል። ይህም ችግሩ ከመፈጠሩ በፊት ለመከላከል ያግዛል። ከዚህ ስምምነት ውጪ ሆኖ ጥቃት የሚፈጽም ቢኖር የመጀመሪያው እርምጃ የህክምና ድጋፍ እና ማርከሻ መድኃኒቶችን በብዛት ማቅረብ ነው። በመሆኑም ይህን እና ተመሳሳይ አደጋዎች ቢከሰቱ ለመቆጣጠር የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል።

Thursday, March 2, 2017

What can you say About this picture

Ethiopian Traffic polices dealing and receiving something from foreigner
(pic from Facebook)

በኤጀንሲዎች የሠራተኛ ቅጥር ዘመናዊ ጉልበት ብዝበዛ ወይስ?

 
የኤጀንሲ ተቀጣሪ ጥበቃ ሰራተኞች በስልጠና ወቅት

ቅሬታ
«ለሥራዬ ተገቢውን ክፍያ አላገኝም። ሦስት ቤተሰብ የማስተዳድር ብሆንም ደመወዜ ከቤት ኪራይ ክፍያ እና ከቀለብ አታልፍም» በማለት ደመወዙን እዚህ ግባ የሚባል እንዳይደለ የነገረኝ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በጥበቃ ሠራተኛነት ተቀጥሮ የሚያገለግለው (ስሙን በሌላ የተካነው) ወጣት ሰለሞን አካሉ ነው። ላየን የጥበቃ አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በተሰኘው ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲ አማካኝነት በዩኒቨርሲቲው መቀጠሩን ነው የሚያስረዳው። ከስድስት ወር በፊት ሥራ በማግኘቱ ደስ ብሎት ቢቀጠርም በደመወዝ አከፋፈል ስርዓቱ ግን ደስተኛ አለመሆኑን ይናገራል። «ዘመናዊ ጉልበት ብዝበዛ ነው» ሲልም ይገልጻል።

ምን ችግር ገጠመህ የሚል ጥያቄ አቀረብኩለት? ፈራ ተባ እያለ ዙሪያ ገባውን ከገላመጠ በኋላ በለሆሳስ «ሥራውን ያስቀጠረኝ ኤጀንሲ ያለአግባብ የእኔን ጨምሮ የሌሎች ጓደኞቼን የጥበቃ ሠራተኞች ደመወዝ እኩል እየተካፈለ ነው። እንዳውም እኛ ታክስና ጡረታ ይቆረጥብናል» አለኝ።

አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለኤጀንሲው በአንድ ሠራተኛ 2400 ብር የሚከፍል ቢሆንም ኤጀንሲው ግማሹን በመጉመድ እንደሚያስቀር ነው የገለጸው። በወር የሚከፈለው ገንዘብ ከተቀጠረበት ዩኒቨርሲቲ የደመወዝ ስኬል እጅግ ዝቅተኛ መሆኑን እና ጡረታ እና ታክስ ተቆርጦ 1054 ብር ከ50 ሳንቲም እንደሚደርሰው ነው የሚጠቁመው። ይህም የተቀጣሪዎችን ሞራል የሚነካ፣ መብቱንም የሚጋፋ እና ያለአግባብ ለመበልጸግ የሚደረግ ሩጫ መሆኑን ይናገራል።

በመሆኑም ኤጀንሲው በየወሩ ከሠራተኞቹ ላይ ያለአግባብ የሚቀንሰውን ገንዘብ መጠን ዝቅ ሊያደርገው ይገባል። በተጨማሪም የህመም እና የተለያዩ ፍቃዶች በሚያስፈልጉበት ጊዜ ፈቃድ የሚጠየቀው ኤጀንሲው በመሆኑ ተገቢውን መፍትሔ እንደማይሰጥ ይናገራሉ። እንደ ዜጋም መብትና ጥቅማችን የሚከበርበት ህግና መመሪያ ሊኖር ይገባል የሚል እምነት አለው። «እኛ የኤጀንሲ ተቀጣሪዎች ብንሆንም የአገሪቱ ዜጎች በመሆናችን በአገሪቱ የአሠሪና ሠራተኛ አዋጅ መሰረት ተጠቃሚ መሆን ይገባናል። የሠራተኛ ማህበርም ኖሮን በመብትና ጥቅሞቻችን እንዲሁም ግዴታችን ዙሪያ መነጋገርና ማስከበርም ይኖርብናል። ሆኖም ግን እኛ የዚህ መብት ተቋዳሽ አይደለንም» ይላል።

በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የተለያዩ የመንግሥት እና የግል ተቋማት የጥበቃ እና ፅዳት ሠራተኞችን በኤጀንሲ አማካኝነት ቀጥረው የሚያሠሩ በመሆኑ ችግሩ የበርካቶችን በር እያንኳኳ እንደሚገኝ ይናገራል። ይሄ ዘመናዊ ጉልበት ብዝበዛ በመሆኑ ለዚህም ችግር የሚመለከታቸው ተቋማት አስፈላጊውን የመፍትሔ ሃሳብ ቢያዘጋጁ መልካም እንደሆነ ነው የሚጠቁመው።

ወይዘሮ ሰናይት አሸናፊ (ስማቸው በሌላ የተተካ) አጋር የጥበቃ አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር በተሰኘ ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ተቋም አማካኝነት በግል ባንክ በጥበቃ ሥራ ላይ ተሰማርተዋል። በአዲስ አበባ መቀመጫቸውን ያደረጉ የአገር ውስጥ ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ከቀጣሪ ድርጅቶች ጋር ውል በመዋዋል አብዛኛውን የአገሪቱን ጥበቃ ሠራተኞችን በኮንትራት እንደሚያሠሩ ነው የምታስረዳው። በዚህም አንድ ሠራተኛ ስለ ደመወዝ እና የተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች በመጀመሪያ የሚነጋገረው ከኤጀንሲው ጋር እንጂ ከቀጣሪው አካል ጋር አለመሆኑን ታስረዳለች። ይህም ኤጀንሲው በሠራተኞች መብት ላይ ሙሉ ኃላፊነት እንዲሰጠው እና የፈለገውን ያህል የደመወዝ መጠን እንዲተምን ዕድል እንደሰጠው ነው የምትገልጸው።

እንደ ወይዘሮ ሰናይት አገላለጽ ከሆነ፤ በተለያዩ ጊዜያት በባንኩ ውስጥ የሚቀጠሩ ጥበቃዎች በኤጀንሲው የአንድ ሺ ብር ደመወዝ ውል ይቀርብላቸዋል። ባንኩ የሚከፍለው ደመወዝ መጠን ከፍተኛ መሆኑን ሲረዱ ለሥራ ያላቸው ተነሳሽነት እጅግ ይቀንሳል። በመሆኑም ኤጀንሲዎች ከሠራተኛው ላይ የሚቀንሱት የኮሚሽን ክፍያ በህግ ላይ ተመስርቶ የተተመነ እና የሠራተኞችን ተጠቃሚነት የማይጎዳ መሆን ነበረበት። አብዛኛውን ጉልበት የሚያወጣው እና ሥራውን የሚያከናውነው ተቀጣሪው ሆኖ ሳለ ኤጀንሲዎች ተጠቃሚ የሆኑበት አሠራር መስተካከል ይገባዋል።
ከዚህ በተጨማሪ ኤጀንሲዎች በተለያዩ አነስተኛ ምክንያቶች በየወቅቱ ከሠራተኞች ደመወዝ ላይ በቅጣት መልክ ገንዘብ ይቆርጣሉ። ለአብነት በመኪና የሚዞሩ የኤጀንሲ ተቆጣጣሪዎች በምሽት ጥበቃ ሥራ ላይ ለተሰማራ ሰው የመኪና ጥሩንባ (ክላክስ) በማሰማት ሊጣሩ ይሞክራሉ። በዚህ ወቅት ሠራተኛው ካልወጣ እንደተኛ ተቆጥሮ ደመወዝ ይቀነስበታል። ይህንን አሠራር በተለይ መኪና በሚበዛባቸው እና የተለያዩ ድምፆች በሚሰሙባቸው አካባቢዎች ላይ ተግባራዊ ለማድረግ ያስቸግራል። ይህም የሠራተኞችን መብት የሚጋፋ እና ሊስተካከል የሚገባው ነው።
የኤጀንሲዎቹ ምላሽ
የአጋር የጥበቃ አገልግሎት ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር የሰው ሀብት ልማት አስተዳደር ኃላፊ የሆኑት ኮሎኔል ከበደ በጅሮ ከተቀጣሪ ዎቻቸው የሚነሳውን ቅሬታ አይቀበሉም። ማህበሩ ሠራተኞችን በመላ አገሪቱ ከሚገኙ የዲፕሎማቲክ አካላት፤ ባንኮች እና የግል ተቋማት ጋር በሚደረግ የውል ስምምነት አማካኝነት ከአምስት ሺ በላይ ሠራተኞችን እንደሚያቀርብ ይገልጻሉ። በዚህም ከተቋማቱ ለእያንዳንዱ ሠራተኛ ከሚከፈል ገንዘብ ለሠራተኛው 80 በመቶውን እንደሚከፍል ነው የሚናገሩት። ተቀናሽ የሚደረገውን ገንዘብ ማህበሩ የተለያዩ ወጪዎችን ሸፍኖ ለትርፍ እንደሚያውለው ያስረዳሉ። ይህም ከሠራተኞች ጋር በሚደረግ የውል ስምምነት መሆኑን ነው የሚናገሩት። በመሆኑም ሠራተኞች የሚያነሱት የደመወዝ አነሰኝ ቅሬታ ተገቢ ያልሆነና አሠራሩን ያልተከተለ ነው። ወደፊትም የደመወዝ ትመናውን ለማስተካከል እቅድ እንደሌለም ይናገራሉ።

ላየን የጥበቃ አገልግሎት ማኔጂንግ ዳይሬክተር የሆኑት አቶ አቤል ወርቁ በበኩላቸው እንደሚናገሩት በአገሪቱ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ሥራ እና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች እንደየሁኔታው የተለያየ የደመወዝ አከፋፈል ይከተላሉ። ላየን ሠራተኞች ከሚያቀርብላቸው ድርጅቶች ውል ፈፅሞ ከሚቀበለው ገንዘብ ለሠራተኞች ከ60 እስከ 65 በመቶ ይከፍላል። (እርሳቸው ይህን ይበሉ እንጂ የኤጀንሲው ተቀጣሪዎች 50 በመቶ እንደሚከፈላቸው ነው የተናገሩት) በዚህም በድርጅታቸው አማካኝነት ከአራት ሺ በላይ ሠራተኞች በሥራ ላይ ተሰማርተው ይገኛሉ። ከሠራተኞች ደመወዝ ላይ የሚቀነሰው ገንዘብ ለኢንሹራንስ ክፍያ፣ ለቢሮ አስተዳደር ፣ ለደንብልብስ ወጪ እንዲሁም ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውል ሲሆን፤ ይህን ታሳቢ ሲደረግ ለሠራተኞች ጥሩ የሚባል ክፍያ ይሰጣል። በኤጀንሲው አማካኝነት ለሚቀጠሩ ሠራተኞች ትንሹ የደመወዝ ክፍያ 900 ብር ሲሆን እንደየደረጃው እያደገ ይሄዳል።

ሌሎች ኤጀንሲዎች በአንፃራዊነት የተሻለ ክፍያ ማለትም 80 በመቶ ለሠራተኛ የሚከፍሉ መኖራቸውን ላነሳንላቸው ጥያቄ እንደገለጹት ይህን ያህል ክፍያ የሚከፍል ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሠራተኛ የሚያስቀጥር ኤጀንሲዎች ይኖራሉ ተብሎ እንደማይገመት ይናገራሉ። «ቢኖርም እንኳን ያሉባቸውን ወጪዎች ሸፍነው ትርፋማ ለመሆን ስለሚከብዳቸው የተሟላ ቢሮ እና ለቀጣሪዎች ንብረት ዋስትና ሽፋን የሌላቸው እንዲሁም ለተቆጣጣሪዎች ክፍያ የማያወጡ ሊሆኑ ይችላሉ» ብለዋል።

እንደ አቶ አቤል አገላለጽ፤ ለሠራተኞች የሥራ ላይ ደህንነት እና ጤንነት የሚሰጠው ትኩረት ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ አስፈላጊው ስልጠና ይሰጣል። በተጨማሪም ተቆጣጣሪዎች የሠራተኛውን ንቃት ለመፈተሽ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ጥበቃዎች ለሥራ የሚመደቡበት አካባቢ በአብዛኛው ጸጥታ የሰፈነበት በመሆኑ ለሁለቱም አካላት የድምፅ እክል የሚፈጥር ችግር አያጋጥምም። በመሆኑን የንቃት ችግር የታየበት ጥበቃ ፣ የደንብ ልብስ አለባበስ ሥነ-ስርዓት ያልተከተለ ሠራተኛ ለቅጣት ይዳረጋል። ይህም የኤጀንሲው ደንበኛ የሆኑ ተቋማትን ደህንነት ለመጠበቅ እና የተገልጋዩን ፍላጎት ለማርካት ነው። በመሆኑም ሠራተኞች ያለአግባብ ቁጥጥር እንደሚደረግባቸው እና ደመወዝ እንደሚቆ ረጠባቸው የሚያነሱት ሃሳብ ትክክል አይደለም።
የባለድርሻ አካላት ምላሽ

የቀጣሪዎችንና የተቀጣሪዎችን ቅሬታና ምላሽ ይዘን ያመራነው ወደ ኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ነው። የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ በርካታ ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች በአገር ውስጥ እየተንቀሳቀሱ መገኘታቸው በመልካም ጎኑ የሚታይ ቢሆንም አገናኝ ድርጅቶቹ ከእያንዳንዱ ሠራተኛ ደመወዝ አከፋፈል ላይ ያላቸው አሠራር ህጋዊ አካሄድን የተከተለ አለመሆኑን ያምናሉ። አንድን ሠራተኛ ለተለያዩ ተቋማት ካቀረቡ በኋላ የሚቀበሉት ገንዘብ ከፍተኛ ከመሆኑ በተጨማሪ በየወሩ ከሠራተኛው ደመወዝ ላይ የሚቆርጡበት አግባብ ተገቢ አለመሆኑን ይጠቅሳሉ። «ይህም በሰው ጉልበት መነገድ ነው» ብለዋል። በየወሩ እየቆረጡ የሚያስቀሩት ገንዘብ ለሠራተኞች መከፈል የነበረበት ነው።

እንደ አቶ ካሳሁን ገለጻ፤ አገናኝ ድርጅቶቹ ሠራተኞችን ከአሠሪው ድርጅት ጋር በማገናኘ ታቸው ምክንያት ከሠራተኛው ወይም ከቀጣሪው ወገን አንድ ጊዜ የሚከፈል ኮሚሽን መቀበል ነበረባቸው። ይሁንና ዕድሜ ልክ ከሠራተኛው ደመወዝ ላይ እየቀነሱ የሚያስቀሩበት አሠራር ወደፊት በሚኖሩት ጊዜያት መቀየር አለበት። ይህንን ጥያቄ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽም እንዲስተካከል እና የሠራተኞቹ መብት እንዲከበር እየጠየቀ ነው። ይሁንና ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር «ችግሩ ላይ ተጨባጭ ማስረጃ ማግኘት ያስፈልጋል» በሚል ምክንያት ጉዳዩን እያድበሰበሰው ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል።

በተጨማሪም ስለአገናኝ ድርጅቶች የደመወዝ አከፋፈል የሚያስረዳ ተገቢ ህግ የለም በመሆኑም አገናኝ ድርጅቶች ደመወዝ ቀንሰው የመክፈል መብት አልተከለከሉም። በመሆኑም ጉዳዩን ለማስቆም አይቻልም የሚሉ ምክንያቶችን በማቅረብ ሚኒስቴሩ ተገቢውን ቁጥጥር ሊያደርግ አልቻለም። በመሆኑም ችግሩ የሠራተኞችን ገቢ የሚቀንስ በመሆኑ እና እስከ አሁን ድረስ መፍትሔ ያላገኘ በመሆኑ በቀጣይ ለከፍተኛ የመንግሥት አካላት ችግሩን ለማስረዳት ታቅዷል። በዚህም የሠራተኞችን መብት የሚያስከብር መፍትሔ እንደሚገኝ ይጠበቃል።

የአሠሪና ሠራተኛ ህጉ በጉዳዩ ላይ በስፋት የሚያነሳው ሃሳብ ባይኖርም የአገር ውስጥ ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ተቋማትን እና ተቀጣሪ ሠራተኞችን ግንኙነት የተመለከተ ረቂቅ አዋጅ እየተዘጋጀ እንደሚገኝ የጠቆሙት አቶ ካሳሁን፤ በረቂቁ ላይ የአገናኝ ድርጅቶቹን አሠራር የሚደግፍ ሃሳብ መኖሩ በመረጋገጡ አዋጅ ሆኖ ከመውጣቱ በፊት እንዲስተካከል መጠየቃቸውን ገልጸዋል። በቀጣይ በሠራተኞች የደመወዝ ክፍያ ላይ ተገቢው አሠራር እንዲመጣ የህግ ጉዳዩ ላይ ትኩረት ተሰጥቶ ክትትል እንደሚደረግ ነው የሚጠቁሙት።

ጉዳዩ ይመለከተዋል የተባለው የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአገር ውስጥ ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎችን ቁጥጥር እና ፍቃድ የሚሰጡት የክልል እና የከተማ አስተዳደር ቢሮዎች ናቸው በሚል ለጥያቄዎቻችን ምላሽ አልሰጡም።

በዚህም መሠረት ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የአገር ውስጥ ሥራ ስምሪት ንዑስ የሥራ ሂደት መሪ አቶ አህመድ ኢርጎ ነው። አቶ አህመድ እንደሚናገሩት፤ በከተማዋ ውስጥ 263 ፍቃድ አውጥተው የሚንቀሳቀሱ የአገር ውስጥ ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ይገኛሉ። እነዚህም በሥራቸውም 11 ሺ ሠራተኞችን በተለያዩ ተቋማት አሰማርተዋል። ኤጀንሲዎቹ ሁለት ዓይነት ሲሆኑ አንደኛው ሠራተኛ በመመልመል ከአሠሪዎች ጋር አገናኝተው ሥራቸውን በኮሚሽን የሚጨርሱ ኤጀንሲዎች ሲሆኑ፤ ሁለተኛዎቹ ደግሞ ከተለያዩ ተቋማት ጋር በመደራደር የጥበቃ፣ የፅዳት እና የመሳሰሉትን ሥራዎች በኮንትራት በመያዝ ሠራተኛ ቀጥረው የሚያሠሩ ናቸው።

ሁለተኛዎቹ ኤጀንሲዎች ቀጥታ የሥራ ውል ከአሠሪ ተቋማት ጋር በመፈጸም ክፍያ የሚቀበሉ ሲሆን፤ ለተሰጣቸው ሥራ በራሳቸው ሠራተኞችን በመቅጠር ያሠራሉ። በዚህ ጊዜ ሠራተኞቹን በቀጥታ የሚያዘው ኤጀንሲው የሚሆንበትን ዕድል ይፈጥራል። የደመወዝ አከፋፈሉም ሠራተኛው ከሥራ አገናኙ ድርጅት ጋር በተፈራረመው ውል መሠረት የሚፈጸም ሲሆን፤ የክፍያውን መጠን የሚወስን ህግ ባለመኖሩ ኤጀንሲዎቹ እና ሠራተኞቹ በተስማሙበት የገንዘብ መጠን መሠረት ደመወዝ ይከፈላል።

በተጨማሪም ኤጀንሲዎቹ ሥራ ለመሥራት ኮንትራት ከፈጸሙለት ተቋም ጋር ውላቸው እስኪቋረጥ ወይም በሥራቸው የቀጠሩት ሠራተኛ በስራ ላይ እስከሚገኝ ድረስ የደመወዝ ነክ ጉዳዮችን በፈጸሙት ውል መሠረት ሊፈጽሙ ይችላሉ። በዚህ መሠረት አገናኝ ድርጅቶች (ኤጀንሲዎች) የተለያየ የደመወዝ አከፋፈል ስርዓት የሚከተሉ ሲሆን፤ ቢሮው ኤጀንሲዎቹ የተተመነ አከፋፈል እንዲከተሉ ሊያስገድድ አይችልም። ይህም የነፃ ገበያ መርህን የተከተለ የውድድር አሠራር ነው።

ይሁንና ሠራተኛው ከተዋዋለው ውጪ ደመወዙን ቀንሰው የሚሰጡ ኤጀንሲዎች እንዳሉ ጥቆማ ሲደርስ ቢሮው በሥራና ሠራተኛ ማገናኘት አገልግሎትት አዋጅ ቁጥር 632/2001 በተሰጠው ስልጣን መሠረት በፍጥነት ዕርምጃ እንደሚወስድ ነው የሚጠቁሙት። ይሁን እንጂ በአሁኑ ወቅት በዚህ መንገድ ጥፋት ፈጽሞ የተቀጣ አገናኝ ድርጅት እንደሌለም ይገልጻሉ። ከኢትዮጵያ ሠራተኞች ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ስለቀረበው የአገናኝ ተቋማቱን አሠራር ስለሚመለከተው አዲስ ረቂቅ አዋጅ በተመለከተ ምንም መረጃ እንደሌላቸውና እንደማያውቁት ተናግረዋል።

እንደ አቶ አህመድ ገለጻ ከሆነ፤ በቀጣይ በሚኖሩ ጊዜያት የሠራተኞችን ጥቅም የበለጠ ለማስከበር እንዲቻል አንገናኝ ድርጅቶች በድርድር የደመወዝ አከፋፈል ስርዓታቸውን ከፍ እንዲያደርጉ ጥረት ይደረጋል። በመሆኑም የአመለካከት ችግር ያለባቸውን ተቋሟት በመለየት ጥሩ ክፍያ ይፈጽማሉ ከሚባሉ እና የሠራተኞችን ጥቅም ያስከብራሉ ከሚባሉ አገናኝ ድርጅቶች ትምህርት እንዲወስዱ ማድረግ ያስፈልጋል። በዚህም ኤጀንሲዎቹ የሚያገኙት ገቢ እና የሠራተኞቹ ደመወዝ ተመጣጣኝነት የለውም የሚለውን ቅሬታ መቀነስ ይቻላል ብለዋል።
የህግ አስተያየት

«በደመወዝ አከፋፈሉ እንዲሁም በሥራ ግንኙነቱ ላይ የሠራተኞቹ እና የአገናኝ ድርጅቶቹ ውል ስምምነት ወሳኝነት አለው» የሚሉት ደግሞ የህግ ባለሙያው አቶ ብርሃኑ አሰፋ ናቸው። እንደ እርሳቸው ገለጻ፤ አንዳንድ አገናኝ ኤጀንሲዎች ሠራተኛ ካገናኙ በኋላ ከቀጣሪው ተቋም ጋር ምንም ዓይነት ግዴታዎችን ሳይዋዋሉ አንድ ጊዜ ብቻ የኮሚሽን ክፍያቸውን ተቀብለው ይሰናበታሉ። ይሁንና አንዳንዶቹ ያገናኟቸው ሠራተኞች ሥራቸውን እስከሚያጠናቅቁበት ጊዜ ድረስ ለሚፈጽሙት ጥፋት እንዲሁም በቀጣሪያቸው ላይ ለሚያደርሱት ኪሳራ ዋስትና ይገባሉ።

በዚህ ወቅት ከሠራተኛው ደመወዝ ላይ በየወሩ ተቀናሽ በማድረግ ገንዘብ ሊቆርጡ የሚችሉበት አሠራር ይፈጠራል። በመሆኑም እያንዳንዱ ሠራተኛ ከአገናኙ ጋር ውል በሚፈጽምበት ወቅት ስምምነቱን መረዳት አለበት። ይሁንና ጉዳዩ በአገር ደረጃ በህግ የተደገፈ መመሪያ ወይም አዋጅ ቢዘጋጅለት የደመወዝ አከፋፈሉ እና ሌሎች የሥራ ግንኙነቶቹ ላይ ወጥ አሠራር ለመዘርጋት ያስችላል የሚል ሙያዊ አስተያየት አላቸው ።

በአጠቃላይ በአገር ውስጥ ሥራና ሠራተኛ አገናኝ ድርጅቶች፣ በሠራተኞች እንዲሁም የቀጣሪዎች ግንኙነት ዋነኛ ዓላማው ኢንዱስ ትሪያዊ ሰላምን በማምጣት ብቁ ሥራ ለመሥራት ነው። ይሁንና በሠራተኛ አገናኝ ድርጅቶች እና በአሠሪዎች መካከል ያለውን ግንኙነት ሙሉ በሙሉ ለሁለቱ ወገኖች ስምምነት ብቻ መተው ሠራተኛውን በአንጻራዊነት የኢኮኖሚ አቅሙ ጠንካራ ለሆኑ ድርጅቶች ጥቃት ሊያጋልጠው የሚችል ጉዳይ ሆኖ እናገኘዋለን።

በመሆኑም መንግሥት እንደ ሦስተኛ ወገን ሆኖ በግንኙነቱ ውስጥ እየገባ የሠራተኛውን መብትና ጥቅም ማስከበር ፤ ከአሠሪው የሚደርሱ ጥቃቶች ለመከላከልም ወጥ የሆነ ህግና መመሪያ እንዲኖር ማድረግ ይገባል። ይሄ ሲሆን ነው ዜጋው መብትና ጥቅሙ ተከብሮ ግዴታውን በአግባቡ መወጣት የሚችለው። በህግና ደንብ ያልተገዛ የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት አሁን እንደሚባለው «ከዘመናዊ ጉልበት ብዝበዛ » የተለየ አይሆንም።

ለወጣት ጥፋተኝነት መበራከት ተጠያቂው ማን ነው?



ወይዘሮ አመለወርቅ አበጋዝ በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖሩ የ13 እና የ15 ዓመት ልጆች አሏቸው። ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚያስተውሉት የልጆቻቸው ዕድገት ቢያስደስታቸውም አንድ ያስጨነቃቸው ጉዳይ ግን አለ። ይኸውም ለቤተሰብ አለመታዘዝ፣ ከማህበረሰቡ ሞራል ውጪ የሆኑ ድርጊቶችን ማከናወን እንዲሁም፣ ለጥፋት መጋበዝ አሳስቧቸዋል። ምክንያቱም በልጆቻቸው ባህሪ ላይ እንዳይከሰት ጥረት ቢያደርጉም የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው የሚያመላክተው ጉዳይ ግን ከዚህ የተለየ እየሆነባቸው ይገኛል።
በተለይም ከትምህርት ቤት ይልቅ አልባሌ ቦታ ውለው እንደሚመጡ ተገንዝበዋል። በዚህም በለጋ ዕድሜያቸው ጥፋት አጥፍተው እስር ቤት እንዳይገቡ የሚል ሃሳብ ገብቷቸዋል። በዋነኛነት ደግሞ ትልቁ ልጃቸው ከአንድም ሁለት ጊዜ በመኖሪያቸው አካባቢ በተነሳ መጠነኛ ጸብ ላይ ተሳታፊ መሆኑን በማረጋገጣቸው የልጆቹን ጸባይ የበለጠ ወደ ጥፋተኝነት እንዳይሄድ ምን ማድረግ አለብኝ? የሚለው የሚያሳስባቸው ጉዳይ ከሆነ ሰነባብቷል።
ለመሆኑ ልጆች በለጋ ዕድሜያቸው ወደ ጥፋት የሚከቱ ጉዳዮች እና ወጣት ጥፋተኝነትን ለመከላከል የሚያስችሉ ጉዳዮች ምንድን ናቸው? የፌዴራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የህጻናት ጉዳይ ዳኛ የሆኑት አቶ ልዑለስላሴ ሊበን እንደሚገልፁት፤ የኢትዮጵያ የወንጀል ህግ ከ18 ዓመት በታች ያሉ ህፃናትን ለወንጀል ፍትህ አስተዳደር ሂደት ሲባል ለሦስት ምድብ ይከፍላቸዋል፡፡ በመጀመሪያ ከ9 ዓመት ዕድሜ በታች ያሉ ህፃናትን የወንጀል ኃላፊነት የሌለባቸው በመሆኑ ቤተሰቦቻቸው ወይም ሌሎች የቅርብ አካላት ተገቢውን ጥንቃቄ ሊያደርጉላቸው እንደሚገባ ያትታል፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ከዘጠኝ እስከ 15 ዓመት የዕድሜ ክልል ያሉ ህፃናት በወንጀል ውስጥ ተካፋይ ሆነው በተገኙ ጊዜ እንደወጣት አጥፊ ተቆጥረው በወንጀል ተጠያቂ እንደሚሆኑም ተደንግጓል። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ከ15 እስከ 18 ዓመት የዕድሜ ክልል ያሉ የወንጀል ኃላፊነት ያለባቸው ሲሆኑ እንደ አዋቂ ተቆጥረው በመደበኛው ፍርድ ቤት ጉዳያቸው ይዳኛል።
ከዘጠኝ ዓመት እስከ 15 ዓመት ከሆናቸው ልጆች መካከል በልደታ፣ በቦሌ፣ በጨርቆስ እና በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተሞች ላይ በዓመት እስከ 450 የሚደርሱ የወጣት ጥፋተኝነት ጉዳዮች እንደሚታዩ የሚጠቁሙት አቶ ልዑለስላሴ፤ ጉዳዩ በአገር ደረጃ ሲታይ ከፍተኛ ቁጥር እንደሚይዝ ነው የሚያስረዱት። የወንጀል ሂደት ከአዋቂዎች በተለየ ሁኔታ ጥፋቱን ሳያውቁ ወንጀለኛ የሚሆኑበትን መንገድ በመገንዘብ እና በቀላሉ ከወንጀል ሊርቁ የሚችሉበት የዕድሜ እርከን ላይ የሚገኙ በመሆኑ ቀጪ ከመሆን ይልቅ ትምህርትንና ማረምን መሠረት ያደረገ መሆኑን ይጠቁማሉ።
እንደ ህግ ባለሙያው ማብራሪያ ወጣት ጥፋተኝነት የሚከሰተው ከኢኮኖሚ ችግር የተነሳ ገንዘብ በአቋራጭ ለማግኘት ከመፈለግ እንዲሁም በማህበራዊ ጉዳይ ላይ የቤተሰብ መፍረስ ሲያጋጥም እንዲሁም ከገጠር ወደ ከተማ በሚደረግ ፍልሰት ነው። በአጠቃላይ ምክንያቶቹ ሲታዩ ልጆች አሳዳጊ ወይም ተቆጣጣሪ አካል በሚያጡበት ወቅት ችግሩ ይከሰታል። በመሆኑም ልጆች በሚኖሩበት ማህበረሰብ ውስጥ ተገቢውን ክትትል እና ድጋፍ የሚሰጥ አሳዳጊ ያስፈልጋቸዋል። ወጣት ጥፋተኝነትን ለመከላከል ደግሞ ከህጉ ይልቅ የአገሪቷ ማህበራዊ ጉዳይ ጠንካራ ሊሆን ይገባል። በዚህም አሳዳጊዎች ወይም መንግሥት ለልጆች አስፈላጊው ትምህርት እና መሰረታዊ ፍላጎቶች እንዲሟሉ ክትትል የማድረግ ኃላፊነት አለባቸው። ይህ ካልሆነ ግን ጥሩ ሥነ ምግባር የላቸውም በሚባሉ ጓደኞቻቸው ጭምር እየተገፉ ጥፋት የሚፈጽሙ ወጣቶች ይበራከታሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህር ዶክተር ሰጣርገው ቀናው ደግሞ፤ እንደድሮው ዘመን የወጣቶችን ባህሪ መቅረጽ የሚችሉት ትምህርት ቤቶች እና ቤተሰብ ብቻ አለመሆናቸውን ይጠቁማሉ። ኢንተርኔት እና መገናኛ ብዙኃን በወጣቶች ባህሪ ላይ ተጽዕኖ ማሳደር የሚችሉበት ደረጃ ላይ እንደሚገኙ ነው የሚናገሩት። በተለይም ማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ የሚታዩ ከማህበረሰቡ ልማድ የወጡ ድርጊቶችን የያዙ መረጃዎች ሲቀረቡ ይስተዋላል። በተጨማሪም «በተለያዩ ኤፍ ኤም ሬዲዮ ጣቢያዎች ላይ በየዕለቱ በስፋት የሚተላለፉ ፕሮግራሞች የህብረተሰቡን ባህል እና የአኗኗር ዘይቤ ያላማከሉ በመሆናቸው ለወጣቶች ባህሪ መበላሸት ዋነኛ ምክንያት ናቸው» ይላሉ።
«መገናኛ ብዙሃን ለትውልድ የሚጠቅሙ መረጃዎችን በማስተላለፍ ለወጣቶች እንዲሁም ለአገሪቷ አጠቃላይ ህዝብ ከማይጠቅም ዘገባ መውጣት አለባቸው» የሚሉት ዶክተር ሰጣርገው፤ በዚህም ለ20 እና 30 ዓመታት በኋላ ለሚፈጠሩ ትውልዶች መሰረት የሚጥሉ አዝናኝ እና አስተማሪ መረጃዎችን በጥንቃቄ በማስተላለፍ ወጣት ጥፋተኝነትን መቀነስ ተገቢ መሆኑን ነው የሚያስረዱት። በሌላ በኩል «አንዳንድ ጥሩ ገቢ ያላቸው ቤተሰቦች ላይ ልጆች የቤተሰቡ አስተዳዳሪ እስኪመስሉ ድረስ ስልጣን ይሰጣቸዋል» ይላሉ።
ይህ አግባብ ካለመሆኑ የተነሳ ልቅ ነጻነት የተሰጣቸው ልጆች በአብዛኛው በወጣትነት ዕድሜያቸው ለጥፋት እንደሚጋበዙ ነው የሚናገሩት። በመሆኑም ወላጆች ለልጆቻቸው የሚያስፈልጋቸውን መምረጥ እንጂ ልጆች የጠየቁትን ሁሉ እንዲያደርጉ ልቅ ነፃነትን መስጠት የለባቸውም የሚል መከራከሪያ ያነሳሉ። ከዚህ ውስጥ ቤተሰብ ልጆች የሚጠቀሟቸውን የመገናኛ ብዙሃን ዝግጅቶች መምረጥ አንዱ ተግባር መሆኑንም ይጠቁማሉ።
የህግ ባለሙያውን እና የፍልስፍና መምህሩን ሃሳብ የሚጋሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ ልቦና መምህር ሆኑት ዶክተር ሙላት አስናቀ ናቸው፡፡ እንደ እርሳቸው ገለጻ የችግሩ መንስኤና መፍትሄዎች ላይ መመካከር ተገቢ እና በቀጣይ መፍትሄ ለማበጀት ይረዳል፡፡ በፍርድ ቤቶች የሚስተዋለው ህጻናት በፍርድ ሂደት የሥነልቦና ጫና እንዳይደርስባቸው የሚደረጉ ልዩ እንክብካቤዎች ማለትም ቤታቸው ያሉ እንዲመስላቸው የፍትህ መከታተያ ክፍሉ መዘጋጀቱ መልካም ከሚባሉ አሰራሮች ውስጥ ይመደባል፡፡ ነገር ግን ወጣት ጥፋተኞች መልሰው ወደ ወንጀል እንዳይገቡ መከላከል የሚቻልበት የእርምት አሰራሩ ጉድለት አለው፡፡ በተለይም በክልሎች ወጣት ጥፋተኞችን ከአዋቂ ጥፋተኞች ነጥሎ የእርምት ትምህርት ለመስጠት የሚረዱ ማዕከላት አልተገነቡም፡፡ በመሆኑም ጥፋተኞቹ በቀላሉ ከችግሩ እንዲወጡ ለመከላከል የማረሚያ ማዕከላቱ ግንባታ ጊዜ ሊሰጠው አይገባም፡፡
 የብር ምንዛሪ አቅምና ኢኮኖሚያዊ አንድምታ


የኢትዮጵያን ምጣኔ ሀብት ተወዳዳሪነት ለማጠናከር ይረዳል ያለውን ሃሳብ የዓለም ባንክ አቅርቧል። በዚህም የኢትዮጵያውያን መገበያያ ገንዘብ ብር የመግዛት አቅሙ መቀነስ እንዳለበትና ለዚህም ሥልጣን ያለው ብሔራዊ ባንክ ማስተካከያ ማድረግ እንደሚገ የፈረነጆቹ 2016 አመት ከመጠናቀቁ በፊት ማሳሰቡ የሚታወስ ነው። በዝርዝር ሲያስቀምጠውም በአሁኑ ወቅት ተግባራዊ እየተደረገ ያለውን የኢትዮጵያ ገንዘብ በዓለም ገበያ በከፍተኛ ብር መመንዘር እንደሚገባው ማለትም በአንድ የአሜሪካን ዶላር አሁን ካለበት(ለህትመት እስከገባንበት ድረስ) ካለው ከ22 ነጥብ 3 ብር በላይ መመንዘር እንደሚገባው ገልጿል። ይህም የአገሪቷን ኢኮኖሚ ለማሳደግ እንደሚረዳ ነው የዓለም ባንክ በሪፖርቱ ያስቀመጠው። የተለያዩ የኢኮኖሚ ባለሙያዎች በጉዳዩ ዙሪያ ምን ይላሉ? 
ባንኩ እ..አ በ2010 ላይ ተመሳሳይ ሃሳብ አቅርቦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም ምክረ ሃሳቡን ተቀብሎ ብር ከዶላር ጋር ያለው የመግዛት አቅም በ17 በመቶ እንዲቀንስ መደረጉ የሚታወስ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዢ አቶ ዮሐንስ አያሌው የምንዛሪ ማሻሻያ እንዲደረግ የቀረበው ሃሳብ ሊያመጣው ከሚችለው ጥቅም በላይ ጉዳቱ ሊከፋ እንደሚችል ይናገራሉ። የዓለም ባንክ ሪፖርቱን ባቀረበበት ወቅት ለጋዜጠኞች ገልጸው ነበር። ብሔራዊ ባንክ ከዓለም ባንኩ የቀረበው ሃሳብ ተቀባይነት እንደማይኖረው ያስረዱት ደግሞ ቀደም ባሉ ጊዜያት ተመሳሳይ ዕርምጃ በተወሰደበት ወቅት በአገሪቷ ላይ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት መከሰቱን በመጠቆም ነው።
የአፍሪካ አቅም ግንባታ ፋውንዴሽን ዋና ፀሐፊ የኢኮኖሚ ባለሙያው ፕሮፌሰር ኢማኑዌል ናዶዚዬ፣ «የአንድ አገር ገንዘብ የመግዛት አቅም እየቀነሰ መምጣት የአገሪቷ ኢኮኖሚ ችግር ውስጥ ስለመግባቱ ማሳያ አይደለም» ይላሉ። የበርካታ የአደጉ አገራት መገበያያ ገንዘብ ከአንድ የአሜሪካን ዶላር ጋር ሲነፃፀርም የመግዛት አቅሙ ዝቅተኛ መሆኑን ነው የሚያስረዱት። የኢትዮጵያ የብር አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ቢመጣም የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ዕድገት በአጥጋቢ ሁኔታ እያደገ እንደሚገኝ ይጠቁማሉ። ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ሲነጻጸርም አስተማማኝነቱን በሚያረጋግጥ መልኩ ለአስር ዓመታት የተረጋጋ ዕድገት መታየቱን ነው የጠቀሱት።
እንደ ፕሮፌሰር ኢማኑዌል ገለጻ፤ አገሪቷ የብር መግዛት አቅምን በመቀነሷ ምክንያት ሀብቷን ለውጭ ገበያ በቅናሽ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬን መሰብሰብ ያስችላታል የሚል እምነት አላቸው። ይሁንና «የብር አቅምን በመቀነሱ ምክንያት ተገቢ ጥቅም ማግኘት የሚቻለው ሠፊ ምርት ለዓለም ገበያ በማቅረብ ነው። ይህ ከተደረገ የብር ምንዛሬ መቀነሱ አሳሳቢ አይሆንም» በማለት ነው ሃሳባቸውን ያጠቃለሉት።
የደብረታቦር ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ መምህር አቶ ኃይሌ አደመ እንዳሉት የኢትዮጵያ መንግሥት ፖሊሲ የወጪ ንግድን የሚያበረታታ ነው። ልማትም የውጭ ምንዛሬን በሚያስገኙ ሥራዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባው ስለሚያምን የብር አቅም መቀነስ ወደ ውጭ በሚላኩ ምርቶች ላይ የሚገኘውን ገቢ በማሳደግ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ያስረዳሉ። የብር የመግዛት አቅም ሲቀንስ አገር ውስጥ ያሉ ምርቶች በዓለም ገበያ ላይ ዋጋቸው እንዲረክስ ያደርጋል። ይህ ደግሞ ላኪዎችን በዋጋ ደረጃ ተመራጭ ስለሚያደርጋቸው የወጪ ንግድን እንደሚያበረታታ ነው የሚጠቁሙት።
ይሁንና ባለፈው ዓመት ኢትዮጵያ ወደ ውጭ የላከችው እና የተገኘው የውጭ ምንዛሬ አነስተኛ በመሆኑ የብር የመግዛት አቅምን ሊቀንሰው እንደሚችል ነው የሚገልጹት። ከዚህ በተጨማሪ መንግሥት የብርን መግዛት አቅም በራሱ የሚቀንስ ከሆነ ቅነሳው ከፍተኛ ይሆናል። በሌላ በኩል በኢትዮጵያ ከወጪ ንግዱ በበለጠ የገቢ ንግድ እንደሆነ ይናገራሉ። በመሆኑም የብርን የመግዛት አቅም አሁን ካለበት በላይ መቀነስ ተገቢ እንደማይሆን ነው የሚጠቁሙት። የብር አቅም ከዚህ በላይ ከቀነሰም ያልተመጣጠነ የንግድ ስርዓት ስለሚፈጠር የአገሪቷን ኢኮኖሚ እንደሚያዳክመው ስጋታቸውን ያስቀምጣሉ።
የኢኮኖሚ ባለሙያው ዶክተር ተኪኤ አለሙ ደግሞ ፤ «የብር የመግዛት አቅም በአንድ ጊዜ እንዲጨምር ወይም እንዲቀንስ ከተደረገ በተለያዩ ዕቃዎች እና ምርቶች ላይ የተጋነነ የዋጋ ለውጥ ያስከትላል» ይላሉ። ይህም በተመሳሳይ ጊዜ አንዱን የንግድ ወገን ድሃ የሚያደርግ ሌላውን ደግሞ ሀብታም የሚያደርግ እንደሚሆንና ፍትሐዊውን የንግድ ስርዓትየሚያዛባ እንደሚሆን ነው የሚያስረዱት። የምርቶችን ዋጋ መልሶ ወደ ነበረበት ለማሸጋገርም እጅግ አዳጋች እንደሚሆን ነው የሚጠቁሙት።
መንግሥት የብር የመግዛት አቅምን በአንድ ጊዜ እንዲቀንስ ካደረገበት እ... 2010 ጀምሮ በየቀኑ የብር የመግዛት አቅም በአንድ ሳንቲም ደረጃ እየቀጠለ እንደሚገኝ ነው የጠቆሙት። «ይህም ጎልቶ የወጣ የዋጋ ግሽበት እንዳይከሰት ረድቷል» ይላሉ ዶክተር ተኪኤ። በመሆኑም እንደእስካሁኑ ብር በጊዜያቶች ሂደት የመግዛት አቅሙ እየቀነሰ ቢሄድ እንደሚሻል ነው የሚጠቁሙት። ይሁንና በቅጽበታዊ ሁኔታ የብር የመግዛት አቅም የሚቀነስ ከሆነ የተጋነነ የዋጋ ግሽበት እንደሚያመጣ ነው ስጋታቸውን የገለጹት።

Featured post

ለሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተጠያቂነትን በማረጋገጥ፣ የሕግ በላይነትን በማስፈን፣ መንግሥትና የስራ አስፈጻሚ አካላቱ በመሉ ለሰብአዊ መብቶች መከበር፣ መጠበቅና መሟላት ያላቸውን ቁርጠኝነት እንዲያሳዩ ልዩ ትኩረትና ክትትል ይሻል

                    የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በየደረጃው ያሉ የመንግስት አስፈጻሚ አካላትና ኃላፊዎች ላይ የቅርብ ክትትል በማድረግ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር አስተዋጽኦ ሊያደር...